የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ተጠንቀቅ

ህልውናው እስኪመናመን፣ እስኪጠፋና እስኪፈልስ ድረስ እንደ ስንዴ የተበጠረ ህዝብ (ትግራይዋይ) ሊሞሸር አልነበረም እባብና ጊንጥ የሚርመሰመሱበት ወደ ደደቢት በርሃ የወረደው። እንደ ቀበሮ ቤት ሳያውቅ ጉድግድ ውስጥ፤ በረሃብ ላለመሸነፍ ሽንቱን ጠጥቶ ቅጠል ምሶ፤ ነፍስና ጅማት የሚለያይ ድንጋይ ላይ ተንተርሶ፤ ከጨለማና ከበላተኛ አውሬ እየተጋፋ ለ17 ዓመታት ከሞት ጋር ተናንቆ የመከራ ጽዋ ይጎነጭ ዘንድ የተገደደው ከማንነቱ የተነሳ ብቻ ከደረሰው በደልና ጭቆና የተነሳ ነበር። ጨርቄ ማቄ ሳይል ቤት ንብረቱን ጥሎ ከአራዊት ጋር በርሃ ለመስፈር የተገደደው ለማንነቱ ያለው ክብር ግድ ብሎት ነበር።

“ፌስ- ቡክ” ላይ ተዘርተህ ለበቀልከው ትውልድ[1]

 • ዛሬን ለማየት የበቃኸው በስለት አይደለም።
 • የምትተነፍሰው ንጹህ አየር ከጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ደገነትና ቸርነት የተነሳም አይደለም።
 • እንደ ሰው (እንደ ሕዝብ) ከሌላው ብሔር ጋር እኩል ለመታየትና ለመቆጠር የበቃኸው ይገባዋል ተብለህ/ሎም አይደለም።
 • ጥጉ እንደ ፖስታ በአድራሻህ ታሽጎ የተላከልህ ነፃነት የለም። አባቶችህ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለውበታል። ማንነትህ ዋጋው ውድ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች አጥንት ተዘርቶበታል።
 • ትግራዋይ ማንነትህ የሞት ዋጋ ተከፍሎበታል። ይህ የተከፈለው የህይወት መስዋዕትነት የቀለለህ እንደሆነ ግን ታሪክ ለመድገም ትገደዳለህ። ያለፈው የጨለማ፣ የልቅሶና የዋይታ ዘመን ለመድገም ትገደዳለህ።
 • ትውልድ ሆይ! የተከፈለው የህይወት መስዋዕትነትና የፈሰሰው ደም በጊዜውና አለጊዜው ትግራይዋይ ማንነትህ እንደያዝክ ፀንተህ እንድትቆም እንጅ ዘመናዊት በሚሉት ፈሊጥና አጉል ስልጣኔ ስም ትግራይዋትነትህ ለውጠህና ጥለህ ከነፈሰ ጋር እንድትነፍስ፣ እንድትቀል፣ የማንነት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቀህ ዳግም የባርነት ቀንበር ስር ወድቀህ እንድትማቅቅና ራስህን እንድታጣ አይደለም።
 • ማንነትና ዘመናዊነት ተቀላቅለውብህ ክቡር ትግራዋይ ማንነትህ መርሳትና መዘንጋት አንተነትህ ማቃለል ብቻ ሳይሆን ከእሳት ጋር እንደመጫወትም ነው። አንተነትህ ማቃለል ራስህን ለባርነት አሳልፈህ መስጠት ነው። ባሪያ ማለት ደግሞ ነፍሱ ጭምር “ይህ የእኔ ነው” የሚለው የሌለው “ነፍስ” ያለው ተንቀሳቃሽ ዕቃ ለመሆኑ በዝርዝር መፃፍ፣ ማተትና መተንተን ጊዜ ማባከን ብቻ ነው የሚሆነው። ቁጥሩም ከእንስሳትና ከቤት ቁሳቁስ ማለትም ማንኪያ፣ ሹካ፣ ካራ፣ ሲኒ፣ ጀበና፣ ማጥሊያ … ወዘተ ተርታ ውስጥ ለመሆኑ ለማስረዳት መሞከር ቀባሪን ማርዳት ነው። እንግዲያውስ ባርነትን የሚመርጥ ማን ነው? ጎበዝ፥
 • ማንነት የፖለቲካ የሃስብ ወይም የአመለካከት ልዩነት አይደለም።
 • ማንነት የሚሸቀጥ የሚለወጥ ጨርቅ አይደለም።
 • ማንነት በድርድር ሰጥተህ የምትቀበለው ፖለቲካዊ ጥቅምም አይደለም።
 • ማንነት “ምን ችግር አለበት” ተብሎ የሚጣል፣ የሚደለዝና የሚሰረዝ አይደለም።
 • ማንነት “ምን ታካብዳለህ” ብለህ የምታቃልለው የገብስ ገለባም አይደለም። ታድያ፥

“ፎተኻ ፀላእኻ አነ እየ አዴካ በለት ባሪያ”- እንዲል

 • በሰዎች ፊት ልብህን ሞልተህ በራስህ ቋንቋህ (በትግርኛ) መናገር፣ ሃሳብህን መግለፅና ማዋራት አንገት የሚያስደፋ ብሎም ሃላ ቀርነት ሆኖ ከተሰማህ፤
 • በማንነት ከሚመስሉህ ወንዶችና ሴቶች የትግራይ ተወላጆች በአደባባይ መታየትና ህብረት መፍጠር የሚያሸማቅቅህ ከሆነ፤
 • “ማነህ?” ስትባል የተጠየቅከው ጥያቄ ትተህ ያልተጠየቅከውን ነገር የምትቀላቅልና የምትዘላብድ፤ በአጠቃላይ  ትግራይዋይነትህ የሚያስፍርህ ከሆነ – ምን አለፋህ ውድቀትህ በደጅህ ነው።
 • ገና “የአንድ ትውልድ ዕድሜ”[2] ያልሞላው በደም የተዋጀ መስተንክራዊ ታሪክ ረስተህ የማንነት ቀውስ ውስጥ የገባህ ዕለት፤
 • ማንነትና ዘመናዊነት ተቀላቅለውብህ በብርና በወርቅ የማይገመት የህይወት መስዋዕነት የተከፈለበት ትግራዋይ ማንነትህ ጥለህ ያልሆንከውን ለመሆንና ለመምሰል እንቅልፍ ያጣህ ዕለት፤
 • ትግራዋይ ማንነትህ ዕዳ ሆኖ የተሰማህና የከደበህ ዕለት – ያን ጊዜ ወዮ ላንተና ለልጆችህ። እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልፅ ለማድረግ እወዳለሁ። ይኸውም- ኢትዮጵያ የምትባል የብዙሐን (የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች) አገር እስካለች ድረስ ኢትዮጵያዊነህ ማንም አይወስድብህም። ኢትዮጵያ የጋራ አገርህ ናት። በዜግነትህም ኢትዮጵያዊ ነህ።

በተረፈ፥

 • የራስህ የሆነውን ትተት የሌላውን መቃመት አዋቂነት ሳይሆን ድንቁርና ነው።
 • የራስህን ጥለክ የሌላውን ማነፍነፍ ክብር ሳይሆን ውርደት ነው።
 • አንተነትህን ጥለክ ሌላውን ለመምሰል መራወጥ ዘመናዊነት ሳይሆን ዝቅጠት ነው። በማለት ሃሳቤን ሳካፍሎት በታላቅ አክብሮት ነው።

[1] “ፌስ- ቡክ” ላይ ተዘርተህ ለበቀልከው ትውልድ” – የሚለው አገላለፅ ሌላ ለማለት ሳይሆን እኔ ራሴን ጨምሮ “አዲሱ ትውልድ” ለማለት ተፈልጎ ነው።

[2] በመጽሐፍ ቅዱሰ ሊቃውንት ዘንድ  40 ዓመት የአንድ ትውልድ ዕድሜ ተብሎ ይታወቃል

Advertisements