ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ከማን ጋር ነው ሥልጣን የሚጋራው?

“እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩን እንደ ሰራሁ ከፍራሹም አንዳች እንዳቀረበት ሰንበላጥና ጦቢያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ። ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮች ውስጥ ሳንቃዎቹን አለቆምሁም ነበር። ሰንበላጥና ጌሳም መጥተህ በኦና ቄላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናን ብለው ላኩብን ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ያስቡ ነበር እኔም ትልቅ ስራ እሰራለሁ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም። ስራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ስለ ምን ስራውን ይታጎላል? ብዬ መልዕክተኞችን ላክሁባቸው። ሰንብላጥም እንደ ፊተኛው ጊዜ ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ። እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር የሚል ክፍት ደብዳቤ ነበረ።” (መጽሐፈ ነህምያ 6፥ 1- 6)

የፅሑፉ ይዘትና መልዕክት በዚህ መልኩ (መንፈስ) ያንብቡት፥

በመጀመሪያ ደረጃ ጽሑፉ የአንድ ፓርቲ የበላይነት በመደገፍ መድብለ ፓርቲ በመቃወም የተፃፈ ጽሑፍ አይደለም። ጽሑፉ ከተጠቀሱት ሁለቱ ዓበይት ርዕሰ ጉዳዮች ምንም የሚያገናኝ የለውም። ዜጎች የተለያየ ፖለቲካዊ አስተሳሰብና አመለካከት የመያዝ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። የተለያየ አመለካከት መያዝ፣ ማራመድና ማንፀባረቅ ማለትም በራሱ ነውር ወይም ወንጀል አይደለም። ፀሐፊው የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከትና አስተሳሰብ መያዝ፣ ማራመድና ማንፀባረቅ የበለጠ፣ የተሻለ፣ ፍትሐዊና ሚዛናዊ ህዝባዊ የአስተዳደር ስርዓት በመፍጠርና መገንባት ረገድ የራሱ የሆነ ጉልህ ሚና የሚጫወት የሚበረታታ ለውጥ አብሳሪ የብስለት ምልክት ነው የሚል ፅኑ አቋም አላቸው። ታድያ የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከትና አስተሳሰብና ኖሮን ሲያበቃ ድምፃችን ከፍ አድርገን “አገሬ” የምንላት አገር (ልዩነቶቻችን እንደተጠበቀ) ህልውናዋና ሉዓላዊነትዋ አንድ ካላደረገን ግን ችግር አለ ማለት ነው። ችግሩም የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ ልዩነት የፈጠረው ክፍተት መሆኑ ይቀርና ሌላ ራሱ የቻለ መዘዝ ያለው ታሪካዊ አጀንዳ መሆኑ ነው። “ኢትዮጵያ” ማን ናት? የሚለው ጥያቄ ሳይመለስ ኢትዮጵያ እንደ አገር መምራትና ማስተዳደር አንድ ሊያደርገን አይችልም። ምን ነው? ቢሉ ሥልጣን አንድ አያደግምና። ስለሆነም ጸሐፊው የጽሑፉ ይዘትና የጸሐፊው ዋና መልዕክት በዚህ መንፈስ ያነቡት ዘንድ ሲጠይቅ በአክብሮት ነው።

ንገረኝ፥ .... ከማን ጋር ነው ስልጣን እንዲጋራ የምትፈልገውና የምትመክረው?    

 • ራዕይ ቀርቶባቸው የፖለቲካ ፕሮግራም ከሌላቸው?
 • ዜግነትና ማንነት፣ ብሔርና አገር በቅጡ ከማይለዩ? ሌላውን ማህበረሰብ ማስረዳት ቀርቶ ለራሳቸው በቂ መረዳትና ግንዛቤ ከሌላቸው?
 • በፓርቲ ታቅፈው ሲያበቁ “እኔ” እንጅ “እኛ” ማለት ካልተማሩ የሥልጣን ጥመኞች?
 • “በዚህ ጉዳይ የፓርቲያችሁ አቋም ምንድ ነው?” ተብለው ሲጠየቁ “ስልጣን ላይ ከወጣን በኃላ እናስብበታለን” ከሚሉ?
 • “ሥልጣን ላይ ካልተቀመጥኩ በዚህ ሁኔታ የሚታየኝ ነገር የለም” በማለት ቡክርናቸው ለሥልጣን ከሸጡ?
 • ሥልጣን ላይ ቢወጡ እንኳ ነገ ምን ማድረግና መስራት እንደሚፈልጉ ጭላንጭሉ ከሌላቸው መሰረት አልባዎች?
 • “ለምን ተነካሁ”፣ “ለምን ተገመገምኩ”፣ በማለት “ዘራፍ!” ማለት ከሚቀናቸው?
 • ከስህተታቸው በመማር ፈንታ አሻፈረኝ በማለት ከሚታወቁ?
 • የያዙትን ሳይጨርሱ አዲስ ውጥን ከሚሸላልሙ አፍላዎች?
 • መረጋጋት ብሎ የህይወት ፍልስፍና ካልፈጠረባቸው ልበ ስሶች?
 • በራሳቸውና በስራዎቸው ከመታመን ይልቅ የውጭ ሃይሎች ትክሻ መንጠላጠል ምርጫውቸው ካደረጉ ካርቦን ኮፒዎች?
 • 2007 ላይ ሆነው የጃንሆይ አጀንዳና የደርግ መፎክር ከሚናፍቃቸው መናኛዎች?
 • “ኢትዮጵያ!” የሚለው የሕዝቦች አገር መጠሪያ እንደ ጆከር እየመዘዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው ተሸማቀው፣ ማንነታቸው አጥተው በበታችነት ስሜት ጨፍለቅ ለመግዛት ከሚቋምጡ ጆቢራዎች?

አንባቢ ሆይ! ንገረኝ- ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ከማን ጋር ነው ሥልጣን እንዲጋራ የምትፈልገውና የምትመክረው? በባዶ ሜዳ እንዲሁ “ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ሥልጣን ማጋራት አለበት/ይገባዋል!” ብሎ መጮህ ሥልጣኔ አይደለም። ዘመናዊነት አይደለም። እውቀትም አይደለም። እንደውም ያለ እውቀት የሚጮህ ጩኸት ሁሉ የዝቅጠት ምልክት ነው። ጎበዝ! ሥልጣን መጋራት ማለት አንባሻ ቆርሰህ አብረህ መብላት ማለት አይደለም። ሥልጣን መጋራት ማለት አንባሻ ቆርሰህ አላፊ አግዳሚው ወጩ ወራጁ “ጀባ በል! ተፈደል!” እያልክ አብረህ መብላት ማለት ከመሰሎት በእውነቱ ነገር እጅግ ተሳስተዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የኬንያ ፖለቲካ አይደለም

ወገን! የኢትዮጵያ ፖለቲካ የኬንያ ፖለቲካ አይደለም። የአገሬ ሰው ሲተርት “የማያውቁት አገር ይናፍቃል” እንዲል አንዳንድ የኢትዮጵያ ስመ ፖለቲካውያን – ዜጎች በባይተዋርነት የሚኖሩባት አገር ኬንያ በምስሌነት እያነሱ የኢትዮጵያ ባለ ሥልጣናት ሲወቅሱና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲያቃልሉ “በራሴ” አፍራለሁ። የኬንያ ፖለቲከኞች ችግር ከ ኮፊ አናን [Kofi Annan UN Secretary-General 1997 – 2006] አያልፍም። አልፎም አያውቅም። ችግር ቢፈጠር እንኳ ኮፊ አናን  “አንተ እዚህ ላይ ተቀምጠህ ዝረፍ፤ አንተ ደግሞ በዚህ በኩል መዝብር …” በማለት “ኩኩዩ”[1] በፕሬዝዳንትነት “ጀሎ” በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሌሎችም በየደረጃው አስቀምጦ በሚሰጣቸው ቡራኬ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ትርምሱ ይበርዳል። የኬንያ ፖለቲከኞች ችግር የጥቅም (“የፔሳ”)[2] ችግር ነውና። ሚኒስትሮችዋ ያለቅጥ የሰበሰቡት ሃብት ለመጠበቅና አገሪቱ በቱሪስት እንዲሁም በምድሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ህልውናቸው የሚታወቅ የምዕራባውያን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚገኝ ብቸኛ የአገሪቱ የገቢ ምንጭ (የሚፈሰው ዶላር) ለመዝረፍ የሚፈጠረው ትርምስ ከኢትዮጵያ የእኔነት ብሔር ፖለቲካ ጋር ምንም የሚያገናኝ ነገር የለውም።  አንድ የኬንያ ባለ ሥልጣን ብሔሩ ትዝ የሚለው ሲዘርፍ ከተያዘ በሃላ በጠራራ ፀሐይ ላይ ከፈፀመው ወንጀል ለማምለጥ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ገንዘብ እስካገኘለት ድረስ ሚስቱንም ያጋረዎታል።

አሜሪካውያን “ዲሞክራቶችና” “ሪፐብሊካኖች” እንደፈለጉ ቢቧቀሱና ቢናቆሩ የአሜሪካ “ፌደራላዊ” ስርዓት በተመለከተ ግን በግልም ሆነ በፓርቲ ደረጃ በውናቸው ቀርቶ በህልማቸውም ጥያቄ ያላቸውም። በአገራቸው የፖለቲካ የማዕዘን ድንጋይ ጉዳይ ሁሉም አሜሪካውያን ናቸው። ውድ አንባቢ! የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሒቃን ችግር “ፖለቲካዊ አስተሳሰብና አመለካከት” የፈጠረው/የወለደው  ልዩነት ነው የሚል እምነት ካሎት ሲበዛ የዋህ ኖት። አንድም ፖለቲካዊ የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነት ምን ማለት እንደሆነ የጠራ ግንዛቤ የሎትም (የግንዛቤ እጥረት አለቦት) ማለት ነው። “ፖለቲካዊ አስተሳሰብና አመለካከት” የሚለው ምክንያት ከአእምሮዎ ሊወጣ ይገባል። እንዲህ በግልፅ መነጋገር ኢትዮጵያዊ ባህላችን ባይሆንም እውነት እውነቱ ተነጋግረን ብንፈወስ ነው የሚሻለው። አይመስሎትም?

የኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ ቀውስ ምንጭ ሁለት ፅንፍ ላይ የተቀመጡ ማለትም ወደ ፊት የሚሄድና ወደሃላ የመመለስ አጀንዳ ባላቸው ባለ ራዕዮችና ዛሬም ድረስ ከህልማቸው ባልነቁ ትምክህተኞች መካከል የሚደረገው የምድሪቱ ታሪክ የወለደው ፍልሚያ ነው። “ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነፃነት … ” ፍለጋ በሚመስል ውስጣዊ አጀንዳቸው በሚምምሩ ቃላቶች ቢሸፋፈንም የእነዚህ የፖለቲካ ልሒቃን ችግር አንድና አንድ ነው። ይኸውም የስልጣን ጥያቄ ነው። ችግሩ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የህይወት መስዋዕትነት ምዕራፉ የተዘጋ የአንድ ብሔር የበላይነት የመመልስ አባዜ ነው። በሽታው ሌላ ሳይሆን ትውልድና አገር ሲያጠወልግ፣ ሲያጠፋ፣ ሲገድልና ሲያደቅ የኖረ ዘመናት ያስቆጠረ “የእኔነት” ክፉ በሽታ ነው።

....ሥልጣን ማጋራት ቀርቶ አንድ መዓድ ላይ መቀመጥ የለበትም

ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ይህችን አገር የመለወጥ፤ ሲወርድ ሲ-ዋ-ረ-ድ የመጣው የበሰበሰ እምነት የመቅጨት፤ የመበጣጠስ፤ ትውልድ የመፈወስና የማሳረፍ አጀንዳ አለኝ ብሎ የሚያምን ከሆነ (ካለው) ከመገደኞች ጋር ውህደት፣ ህብረትና ጥምረት ቀርቶ አንድ መዓድ ላይ መቀመጥም የለበትም። ምን ሊበጀው? “በአንድነት” ስም የበሰበሰ ፖለቲካ ከሚራምዱ ርዝራዞች ሥልጣን መጋራት ቀርቶ ለድርድር መቀመጥ በራሱ ጊዜ ማባከን ነው። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ድምር ውጤት መሆንዋን ከማይቀበል ማንኛውም ወገን የሚደረገው ድርድር አይደለም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ራሱ አይበጅም።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ማንነት ሙሉ ሥልጣንና መብት ማጎናፀፍ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፖለቲካ ምሰሶ (ልዩ መታወቂያ) እስከሆነ ድረስ የአፍሪካ መንግስታት መልክ የማጥፋት፤ ስራዎቻቸውም በጀምላ ዋጋ የማሳጣትና የማጠልሸት፤ መሰረተ አልባ ውንጀላዎችና የሐስት ክሶች በመንዛት ላይ የተሰማሩ እንደነ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሁማን ራይትስ ዎችና ስቴት ዲፓርትመን … ወዘተ ፈርቶ ከፖለቲካ ድርጀት ያለፈ አገራዊና ሕዝባዊ አጀንዳውን ይቀለብሳል የሚል እምነት የለኝም። ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የዓለም ባንክ ብድር ላለማጣት የዋለው እንደሆነ ግን ታሪካዊ ስህተት መፈፀሙ አይቀርም። የኢትዮጵያ ህዝብ የመምራትና የማስተዳደር ሃላፊነት የኢትዮጵያ መንግስት ግዴታ እንጅ የምዕራባያን መንግስታት ስራ አይደለም።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት መብትና ሥልጣን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረታዊ አጀንዳ እስከሆነ ድረስ ምላሳቸው እስኪደማ ድረስ “አንድነት! አንድነት!” ከሚሉ ማናቸውም አካላት ለመደራደር በር መክፈት ሆነ መለሳለስ ዕብደት ነው። “አገሬ! ኢትዮጵያ! እናቴ! አጎቴ …” ያለ ሁሉ አገር ወዳድ አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠለለው ሰይጣን እግዚአብሔር ለማምለክ አይደለም። ታዲያ እግዚአብሔር የሚያመልኩትን እየመለመለ ወደ ዓለም ወርውሮ ለመጣልና አማኞች እሳት ውስጥ ለመቀቀል ያደባ መልዓከ ሞት ነው። “አብረን እንስራ!” ያለ ሁሉ መልካም አሳቢ፣ ታታሪ ሠራተኛ፣ ለውጥ ፈላጊ፣ መንገድ አዳሽ ነው ማለት አይደለም እያልኩ ነው። “አብረን እንስራ!” ከሚል ሁሉ አብረህ አይሰራም። እርስዎስ ቢሆኑ ቤትዎ ለማፍረስና ቤተሰብዎን ለመበተን ጨለማ ተገን አድርጎ ዕድሜዎን ለማሳጠር ከሚሸነግሎት ግለሰብ ይወዳጃሉ ወይ? በእውነቱ ነገር የዋሉት እንደሆነ “ሞኝ ኖት” ለማለት ባልደፍርም በእርስዎ ዕይታ “የአንድነት/የወዳጅነት/የውህደት/የህብረትና የጥምረት” ትርጓሜ ለተቀረው ዓለም ያስረዱ ዘንድ ብቻ ነው የምጠይቆት።

ገብተህ ለመረሳት ምን ያጣድፈሃል?

ፖለቲካ ከህያዋን (ህዝብ መኸል በንቃት ከሚመላለሱ) እንጅ ከሙውታን (ከህዝብ እስትፋስ ከራቁ – በእስር ሊሆን ይችላል ከአገር ውጭ መኖሪያቸው ያደላደሉ ሊሆን ይችላል) ጋር ምንም ውል የለውም። “ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አለ” ብለህ የምታምን ከሆነ ግርግር በመፈጠር የሚፈታ ችግር እንደሌለ ደግሞ ልታምን ይገበሃል። “የካው ቦይ”[3] ፖለቲካ ማንን በጀ ነውና? በተረፈ “ግርግር በመፍጠር ሥልጣን እጋራለሁ” የሚል ስሌት የነገሰብህ እንደሆነ ተመዝነህ ስታበቃ መቅለልህ አይቀርምና መጨረሻህ ማበላሸት ብቻ ነው የሚሆነው። ይህ ዓይነቱ ፍፃሜ ደግሞ አገር ቀርቶ አንተ ራስህ ተጠቃሚ እንደማያደግህ አስረጅ አይሻህም። ገብተህ ለመረሳት ምን ያጣድፈሃል?

የታሪክ ልዩነትም ቢሆን ይፈታል

ይህ ትውልድ የማይፈታው ችግር አይኖርም። ይህ ትውልድ አዲስ ታሪክ መፃፍ ሳያስፈልገው ያለፈውን የአባቶቹ ግድፈት እንዳለፈ ወንዝ የመርሳትና ተቻችሎ የመኖር አቅም ያለው ትውልድ ነው። ይህ አዲስ ትውልድ ፍትሐዊነትንና ነፃነትን አጥብቆ የሚሻ ትውልድ የመሆኑ ያክልም የባርነት ቀንበር የሚሸከም ትክሻ የሌለው ትውልድ ነው። ታድያ ይህ ሁሉ የዚህ አዲስ ትውልድ ውስጣዊ መገለጫ እውን ሊሆን የሚችልበት መንገድ አንድና አንድ ነው። ይኸውም፤ ሲወርድ ሲ- ዋ- ረ- ድ የመጣው አገር በታኝ፣ ትውልድ ገዳይ “የእኔነት” ክፉ በሽታ ራሱን ሲጠብቅ ነው። ለማንም የማይበጅ ያረጀ እምነት የተፀናወታቸው በጃንሆይ ዘፈን የደነቆሩ ለአረጋውያን ፓለቲካ የለም! ማለት ሲችል ነው።

ኢትዮጵያውያን ሁለመናችን ልዩ ልዩ ሳለን በዜግነታችን እንደ አንድ ሰው መቆም የምንችለው ኢትዮጵያ እንደ አገር የመምራት ሆነ የማስተዳደር ሥልጣንና መብት “ለእኛ ብቻ የተሰጠ ሰማያዊ ስጦታ ነው” ብለው ለሚያምኑ ልሒቃኖቹ “አይደለም! ኢትዮጵያ እንደ አገር የመምራት ሆነ የማስተዳደር ሥልጣንና መብት የትግራይና የኦሮሞ ጨምሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ መብት ነው!” ብሎ ማስርዳት ሲችልና በዚህ አቋም ጸንቶ ሲቆም ብቻ ነው። “እኔ” ማለት ያልተውክ እንደሆነ ግን “እኛ” ማለት አይቻለንም። በተረፈ የተቀረው የአገሪቱ ችግር ይህን መሰረታዊ የምድሪቱ ቋጠሮ ሲፈታ የሚፈታ ድጥ ላይ ያለ መሰረት የሌለው ችግር ነው።

ለክፉም ለደጉም ጸሐፊው ለመገናኘት yetdgnayalehe@gmail.com ይመይሉ።

[1] ኩኩዩ፣ ጀሎ .. ማለት በኬንያ ፖለቲካ የጎላ ድርሻ ካለቸው በኬንያ ከሚገኙ ወደ አርባ የሚጠጉ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ናቸው።

[2] “ፔሳ” የኬንያ ቋንቋ ሲዋህሊኛ ሲሆን ወደ አማርኛ የመለስነው እንደሆነ ገንዘብ ማለት ነው።

[3] የካው ቦይ ፖለቲካ – የግርግር፣ የኮርፊያ፣ የአመፅ ፖለቲካ እንደ ማለት ነው።

Advertisements