ሰባኪው እውነት ተናግሯል – ኢሳት ቅዠት ውስጥ ነው!

ያገሬ ሰው ሲተርት “ሞኝ አንድ ጊዜ ንገረው ሺህ ጊዜ ራሱን እየሰደበ ይኖሯል” እንዲል። ሰባኪው ስለ ኢሳት ተናገረው የተባለ ቃል ኢሳት ራሱ “ሰባኪው እንዲህ አለኝ” (ESAT Efeta Feb 25 2015) ሲል እየተንቀለቀለ ባቀረበው ዝግጅቱ ነው እኔ ለራሴ የሰማሁት። ኢሳት እግዚአብሔር ፊቱን ፀፍቶ ሲያስለፈልፈው ነው እንጅ የተባለው ነገር ፕሮግራም ሰርቶ ባያቀርበው ኖሮ የሰባኪው ቃል እዛው የተነገረበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ተነግሮ ተዳፍኖ ይቀር ነበር። እውነት ግን ሁል ጊዜ እውነት ናትና የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ይህን እንሰማ ዘንድ ስለረዳን የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተባረከ ይሁን። ይህን ፅሑፍ ለሚያነብ ሁሉም ሰላም ይሁን።

መንደርደሪያ፥

ሙሉ ይዘቱ ወደሃላ በደንብ አመሳጥረዋለሁ ለመንደርደሪ ያክል ግን አላፊ አግዳሚ ወጪ ወራጅ ከሚመስል የኢሳት ቅጥረኛ የተናገረው ልጀምር እንዲህም ይላል “ፖለቲካን ወይም የአገር ጉዳይ መከታተል ልክ ከእግዚሄር እንደ መጣላት ተደርጎ ሲሰበክ እንሰማለንና እዛ ላይ ኢሳትም ይነሳል …” እያለ ይቀጥላል። እውነት ሰባኪው በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ “ፖለቲካን ወይም የአገር ጉዳይ መከታተል ከእግዚአብሔር ያጣልል” ሲል ሰብከዋልን? ኢሳት ሰባኪው የተናገረው/ያስተላለፈው ቁምነገር በማዳፈን እንደውም በአንፃሩ ሰባኪው ያላለውና ያልሰበከው ለማስተጋባት ለምን ፈለገ?

እርግጥ ነው የመፅሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች/አዋቂዎች በአገራችን በኢትዮጵያ ከቤተ ልሔም እስከ ቤተ መቅደስ ይህ ማለት ከቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ ውጭ ስፍራ የማይሰጣቸው ከተራም የተራ ተራ ሰዎች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ስራ ፈት የማየት ጎደሎ ባህል ነው ያለን። በሀገራችን ባህል መንፈሳዊ ሰው በፖለቲካ መድረክ ጨርሶ የማይታሰብ ነው። ቁምነገር ይገኝበታል ብሎ የሚያስብ ፍጥረትም የለም። ይህ ደግሞ ከእነዚህ ሰዎች ማለትም ከመንፈሳውያን ብቻ ማግኘት የምንችለው ሁሉን የሚያስማማና የሚያግባባ የላቀ ምክር እንዳናገኝ አደረገን እንጅ ደካማ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን ምን ያህል ቁልቁል እንደሰደደን ምስክር መጥራት አይሻኝም (በነገራችን ላይ ይህን ስል የፖለቲካ ሰዎች መጠቀሚያ ስለሆኑ የሚናገሩትን እንኳን ስለማያውቁ አንዳንድ ካባ ለባሾች አይመለከትም።)

ሐቁ ይህ ነው። የእግዚአብሔር ባሪያ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ብሩህ አእምሮ ያለውና የአስተሳሰቡ ጥልቀና ምጥቀትም በማንም የማመዘን/የማይመረመር ምስጉን ሰው ነው። “ደግሞ ቄስ ምን ያውቃል … ” ብሎ መሳለቅና መሰልቀጥ መብትህ ነው። ከየትም ልታገኘው የማትችል – የምትፈልገው ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልግህ ጭምር የሚሰጥህ ግን ይህ ሰው ነው። ፕሮፌሰርና ዶክተር የማይሰጥህ ይህ ሰው እንደሚሰጥህ የማመንና የአለማመን ጉዳይ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው። በብዙ ነገር ደቀህ ሳለ ከንቀት የተነሳ ይህን ሰው አልፈህ ዓይኖችህ ሌላ ቦታ ያሰማራህ እንደሆነ እምነት የጣልክበት “ምሁር” ደርቆ ሲያደርቁህ ዓይኖችህ ያያሉ።

ወዳጄ! ዶክተር እንደሆነ የተሰበረ “አጥንት” ከመጠገን ያለፈ በቁምህ ሳለ የሞተ መንፈስህ ላይ ነፍስ ስልጣን የለውም። አልተሰጠውማ። በየት አልፎ? እንዲህ ያለ ኬላ ደጃች ውቤ ጠጅ ቤት አይደለም ኪስህ ተማምነህ ዘው ብለህ የምትገባ። እንደው የዘንድሮ ዶክተርና ፕሮፌሰርማ የተሰበረ ሊጠግን ቀርቶ ጤናማ የሚሰብር ነው። የመንፈሳዊ ሰው ስልጣን ሊገባዎት ይገባል። የአማኝ ክብደት ሊረዝንብን/ሊሰማን ይገባል። የአንድ አማኝ ክብደት የሺህ ሰው ግምት ነውና።

ሐተታ፥

ሰባኪውም አለ “እኔ የፈለጋችሁ የፖለቲካ ግሩፕ ደግፉ መብታችሁ ነው። ግን እኛ ቁጭ ብለን ፖለቲካ እንሰራለን!? ያውም ደግሞ ኢሳትን እያደመጥን? ሰዎቹ በቅዥት ላይ ናቸው። ልንገራችሁ ቅዠት ውስጥ ናቸው። ማንም አይናገራቸውም ከዚህ መድረክ ግን ይሰማሉ። ቅዠት ውስጥ ናቸው። ልንገራችሁ ሰዎቹ ቃዠተው ሊያስቃዣችሁ ነው። እስቲ ፖለቲካ ሰምቶ በሰላም የሚያድር ማን ነው? ማን ነው ንገሩኝ እስቲ? በሰላም የተኛ አለ? ስትቃዡ ታድራላችሁ። አዎ! አንድ ጊዜ ሸለቆ ውስጥ ሲውስዳችሁ፣ አንድ ጊዜ ተራራ ላይ እየውሰዳችሁ፣ አንድ ጊዜ ሲያስተኩሳችሁ ..”

ኢሳት የሰባኪው መልዕክት ቆረጠው እንጅ “ግን ብንፀልይ እኮ ሰማይ ተከፍተዋል። ኤርምያስ …” ብሎ የጀመረው መፅሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ኢሳት ያደምጡት ዘንድ ስላልፈለገ ቆጥጦታል። ኢሳት የተያያዘው ሰሚ የማደናገርና የማምታታት ስራ ነው ሰባኪው በዋናነት በንፅፅር ለማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት በሙላት በደንብ ይገባዎት ነበር። ያም ሆነ ይህ የሰባኪው መልዕክት ኢሳት ነገሩ አጣምሞ እንዳቀረበው ሳይሆን የሰባኪው መንፈሳዊ አስተምህሮ፣ ፖለቲካዊ አመለካከቱ ሆነ የአስተሳሰቡ አድማስ እንዲሁም ሊያስተላልፈው የፈለገው መልዕክት በማያሻማ መልኩ እንደሚከተለው ኩልል ቁልጭ ባለ አነጋገር ግልፅ አድርጓል። “እኔ” ይላል ሰባኪው “እኔ የፈለጋችሁ የፖለቲካ ግሩፕ ደግፉ መብታችሁ ነው” እንዲል።

ሰባኪው “እኔ የፈለጋችሁ የፖለቲካ ግሩፕ ደግፉ መብታችሁ ነው” ሲል በጅብርሽኛ አልነበረም። ሰባኪው ይህን ያለው ኢሳት በሚናገርበት የአማርኛ ቋንቋ ነው። ይህ ደግሞ “ካድሬ” የሚያስብ ከሆነ ሰባኪው አላለም እንጅ አንፃራዊ መልዕክት ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ምን ሊባል ነው? ለመሆኑ የሰባኪው ቃል እንዲህ በድምፅ ሰምቶ ሳለ የኢሳት ሰንካላ ሐተታ የሚጋራ አድማጭ ማን ነው? ቅንነት የጎደለበት፣ አእምሮው የተወሰደበትና በጥላቻ የሰከረ የሲሳይ ዓይነቱ ሰላቢ ግለሰብ ካልሆነ በስተቀር። አይመስሎትም?

ሰባኪው ቀደም ሲል “የእግዚአብሔር ሰው” ብሎ ስለ ተናገረው ቃል ሰባኪው እውነት ብሏል። ዛሬም ድረስ በአሮጌ ማንነቱ የሚመላለስ፣ ያልተፈወሰ አእምሮ ያለው የኢሳት ቅጥረኞች ዓይነቱ የሰው አገልጋይ/ትልቱላ ካልሆነ በስተቀር፦

 • የእግዚአብሔር ሰው በአጠቃላይ አማኝ፦ “አባው ምን ተባለ? … በለው አልሰማህም እንዴ? … በቃ የለህማ። አንዳፍታው የከተማ ባህታዊ ሁኛለሁ አትልም .. እንዴ! ድፍን ከተማው ተናውጦ አንተ ደግሞ ይህን አልሰማሁም ትላለህ? .. ” እያለ እንደ አውራ ደሮ ከሰፈር ሰፈር እየተክለፈለፈ ለፈለጣ አይሰማራም።
 • በኢየሱስ ደም የነፃችና በመንፈሱም የተቀደች ነፍስ ፅድቅን ታደርጋለች እንጅ ክፉ ወሬ አታሳድድም።
 • ይሄ ‘የማህበረ ቅዱሳን’ ዓይነቱ በዝሙት የተጨማለቀ ነጭ ለባሽ ተመፃዳቂ ሳይሆን እውነተኛ የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር ክፉ ወሬን እንደ ዱላ ቅብብል ‘አሉ’ እያለ ያልተጨበጠ አሉባልታ ይዞ ለማሰራጨት አይንቀለቀልም።
 • ሰባኪው -የእግዚአብሔር ሰው እንደ መበለት ፊቱ እንኳን ሳይታጠብ በማለዳ ተነስቶ በሬ ወለደ ወሬ ማሳደድ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሰው ከእግዚአብሔር መስማት ይገባዋል ነው እያለ ያለው።
 • የሰባኪው መልዕክት ለወሬ አትንገብገብ። ክፉ ወሬ ለአማኝ የሚበጅ ሳይሆን ነፍስን የሚያጠፋ የዲያብሎስ መሳሪያ ነው! ነው እያለ ያለው። ይህ ደግሞ አምላካዊ መፅሐፍ ቅዱሳዊም ነው። አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ ስለ ሰዎች ከእግዚአብሔር ይሰማል እንጅ ከሰው ለሰው ብሎ ፀጋም ሆነ ስጦታ የለምና። ወሬ ለማን በጀ? ወሬ ቤት ሲያፈርስ እንጅ ክፉ ወሬ የማን ቤት ገነባ?

ጠቢቡ በመጽሐፈ ምሳሌ 6፥ 16 -19 ባለው ቃል እንዲህ ያላል “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች” ይልና ዝርዝሩንም እንደሚከተለው ያስነብበናል “(1) ትዕቢተኛ ዓይን፥ (2) ሐሰተኛ ምላስ፥ (3) ንጹሕን ደም የምታፈስ እጅ፥ (4) ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥ (5) ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥ (6) በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር (7)በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ” እንዲል። ሰባኪው ስለ ኢሳት ሲናገር ከራሱ ሳይሆን እግዚአብሔር ነፍሱ አጥብቃ የተፀየፈችው የአማኞች ህይወት የሚያቀጭጭና የሚያዝግ ልምምድ ነው እየተፀየፈ ያለው። ሰባኪው እውነት ተናግራል። የኢሳት ዓይነቱ የደም ፖለቲካ ከእግዚአብሔር የሚለይ የጥፋት መንገድ ብቻ ሳይሆን የሐሰት አባት ከዲያብሎስ ጋር የሚስተላፅቅ ርኩሰትም ነው።

ሰባኪው “ያውም ደግሞ ኢሳትን እያደመጥን?” እንዲል ይህን በሚሰማ ጭምት ሰው አእምሮ ቀድሞ የሚነሳ ጥያቄ “ኢሳት ደግሞ ማን ነው?” የሚል ነው። ኢሳት ማለት ደግሞ ሁላችን በተጨባጭ እንደምናውቀው –

 • ኢሳት – ኢትዮጵያ ለመበታተንና ኢትዮጵያውያን ለማተረማመስ የተከፈተ የጠላት አንደበት መሆኑን ነው፤
 • ኢሳት – በቀንም በለሊትም ዘወትር ፍትህ!፣ ዲሞክራሲ!፣ ነፃነት! … ቢልም ዳሩ ግን የሚለው ሁሉ ውሸትና ጦርነት አብሳሪ የጠላት ማጉልያ መሆኑን ነው፤
 • ኢሳት – ለበጎ ስራ ሁሉ የማይበቃ አእምሮአቸውና ህሊናቸው በሐሰት የረከሰና የደነዘዘ ግለሰቦች ስብስብ ማፈንጫ ማፀዳጃ መሆኑን ነው፤
 • ኢሳት – በስህተትም ቢሆን ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን መልካም ነገር ተናግሮ የማያውቅ ነፍስን የሚያጠፋ ክፉ መርዝ፤ ዜጎች አክ ብለው የተፉት … መሆኑን ነው የሚታወቀው።
 • ለመሆኑ ኢሳት ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገር ተናግሮ ያውቃል እንዴ? ኢሳት መቼና የት ቦታ ነው ለኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ? ኢሳት ከመቼ ወዲህ ነው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪ የሆነው? ቀላል የቅርብ ምሳሌ ላንሳ – ይኸውም የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በአደባባይ ኢትዮጵያን ሲገሸልጥዋትና የኢትዮጵያ ሕዝብም ባለቤት እንደሌለው … በቁሙ ሲሸልቱት ኢሳት የት ነበር? ኢሳት ምን አለ? ይልቁንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከሚያውቀው ድረስ ኢሳት ኢትዮጵያን የሚያራክሱና የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም መኖር የእግር እሳት የሆነባቸው የሞት ጥላ ያረፈባቸው ምዋርተኞች መናገሻ መሆኑን ነው የሚያውቀው። ታድያ ሰባኪው “ኢሳት ቅጀት ውስጥ ነው!” ቢል ምኑ ላይ ነው ስህተቱ? የሰባኪው ምስክርነት እውነት።

ሰባኪውም አለ “ሰዎቹ በቅዥት ላይ ናቸው። ልንገራችሁ ቅዠት ውስጥ ናቸው! ማንም አይናገራቸውም ከዚህ መድረክ ግን ይሰማሉ። ቅዠት ውስጥ ናቸው። ልንገራችሁ ሰዎቹ ቃዠተው ሊያስቃዣችሁ” እንዲል።

 • የእግዚአብሔር ሰው ሲናገር እንዲህ ነው። ማንም የማይደፍራት እውነት ይናገራል።
 • የእግዚአብሔር ባሪያ ሲናገር ሃይል ያለው ሃይል የሚያወድር ቃል ነውና ሲናገር እንዲህ ነገሮች ይገለባብጣል።
 • የጌታው ድምፅ የሚሰማ አገልጋይ ሲናገር የፅድቅ ቃል ይናገራልና ከአፉ የሚወጣ ቃል በክፍዎች መካክል እንዲህ ነውጥን ይፈጥራል።
 • እግዚአብሔር ተናገር ያለውን ለመናገር የማያመነታ ታማኝ ባሪያ ሲናገር ህፀፅ የለበትም። ሲናግር እውነትና ፅድቅን ይናገራል። መልእክቱ እንዲህ ስራ ይሰራል።
 • ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ መልዕክት ሲነገር እንዲህ አጥንት ውስጥ የሚገባ መልዕክት ነው።
 • ሰው ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ቃል ሲናገር ንግግሩ እንዲሁ በከንቱ ተነግሮ አይቀርም። የሚሰራው ስራ አለው።
 • የተቀባ ሰው ሲናገር እንዲህ ቁጭ ብድግ ያደርጋል።
 • ፅድቅ የታጠቀ የእግዚአብሔር ሰው ሲናገር ከአፉ የሚወጣ ቃል እንዲህ የሰው ዓይነ ልቡና ያበራል።
 • ሰው ለእግዚአብሔር ሲያድር አንደበቱ በሰው ነፍስ ላይ ህይወትን ይዘራል።

ጎበዝ! ይሄኔ’ኮ ይህ ሰባኪ መልዕክቱ ያስተላለፈው በጣት ለሚቆጠሩ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባላት ይሆናል። ደግሞም ነው። ታድያ ክንደ ብርቱ እግዚአብሔር ነገሩ ለሕዝቡ የሚያደርስበት መንገድ ያውቅበታልና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የተነገረች ቃል የማስታወቂያ ክፍያ መፈፀም ሳያስፈልገው በራሱ በኢሳት አንደበት በመላ ዓለም ያሉ የቋንቋው ተናጋሪዎች ለምስክርነት ይህን ለመስማት በቅተናል። መፅሐፍ ቅዱስ የደም ሰው ሐማ መርደክዮስ ለመስቀል ባዘጋጀው መስቀል ራሱ ተንጠለጠለበት ሲል ተረት አይደለም። ይሄው ኢሳት ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ እርስ በርሱ ለማጨፋጨፍና ለማጨራረስ በከፈተው አንደበቱ በራሱ አንደበት እንዲህ አመድ ሲለብስ ድንገታዊ አይደለም። ሰው በአንደበቱ የሚሸነግለው ሳይሆን በልቡ የሚያስበውን የሚያውቅ እግዚአብሔር አዋቂ ነው። የሰባኪው ቃል ቀርፆ ለኢሳት የላከ ግለሰብም እንደሆነ ውለታው ከእግዚአብሔር ነው። ምን አተርፋለሁ ብሎ አስልቶ ይህን እንዳደረገ የሚያውቅ ግለሰቡ ራሱ እና መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነውና።

ሰባኪውም አለ “እስቲ ፖለቲካ ሰምቶ በሰላም የሚያድር ማን ነው? እስቲ ንገሩኝ ስትቃዡ ታድራላችሁ። አንድ ጊዜ ሸለቆ ውስጥ ሲውስዳችሁ፣ አንድ ጊዜ ተራራ ላይ እየውሰዳችሁ፣ አንድ ጊዜ ሲያስተኩሳችሁ .. ” እንዲል።

ሰባኪው በአጠቃላይ ለአማኞች እያለ ያለው – ከተራባችሁ አይቀር የእግዚአብሔር ቃል ተራቡ የሚበጃችሁ ይህ ነውና። ክፉ ወሬ ያጠፋችሁ እንደሆነ ነው እንጅ አይበጃችሁም። በፀሎት ትጉ! ክፉ ቀን የሚያሻግራችሁ ይህ ነውና የእግዚአብሔር ፊት እሹ ነው የሰባኪው መልዕክት። የቅዠታም ቅዠት ወንዝ አያሻግርህም ነው እያለ ያለው። ቅዠታም ቃዠቶ ሲያስቃዠህ መገኛህ ቅዠታም የገባበት ጉድጓድ ይሆናል ነው እያለ ያለው። ሰባኪው ይህን ማለቱ ታድያ ምኑ ላይ ችግሩ? በመሰረቱ ሰባኪው “ዜና አትስሙ” ያለው የት ቦታ ነው? ሰባኪው አንድም ቦታ ላይ “ዜና አትስሙ/አታዳምጡ” አላለም። ይህ ነገር በመፍተልና በማጣመም የሰለጠነ የኢሳት ፈጠራ ነው።

ሰባኪው “ግን ብንፀልይ እኮ ሰማይ ተከፍተዋል። ኤርምያስ …” ማለቱ “ዜና አትስሙ አለ!” ብሎ መተጎም ዝቅተት ነው። ኢሳት – “ድምፁ ነኝ” ለሚለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ “የኢትዮጵያ ህዝቦች ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ ተፋቀሩም። ዕድገትም ሆነ ብልፅግና ያለው ልዩነቶቻችሁ አጥብባችሁ በአንድነት ለመቆም ስትበቁ ነውና” ብሎ ዜናም ሆነ ሐታታ የማይሰራ ያህል (ባህሪው አይፈቅድለትም። ኢሳት የተመሰረተው ሰላም ሊያወርድ ሳይሆን የሕዝቦች ሰላም ለማወክ ነው። የኢሳት ጥቅም በሕዝቦች መካከል በሚያነደው እሳት ነው።) ሰባኪው ደግሞ አድማጮቹን “ደቀ መዛሙርት ሆይ! ፀሎት? ሂዱና በሬ ወለደ ወሬ እያነፈነፋችሁ ስጋችሁን አደልቡ፤ ክፉ ወሬ እየተቀባበላችሁም እርስ በራሳችሁ ተቦጫጨቁ፤ በዚህም እግዚአብሔር ደስ አሰኙ” ብሎ ይሰብክ ዘንድ መጠበቆ ነው ትንግርት የሆነብኝ። ሰባኪው ኢየሱስ ያላስተማረውን አላስተማረም። ኢየሱስም አለ “እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ” ሰው በሚሰማው ነገር መወሰዱ አይቀርምና። የሰባኪው መልዕክትም ግልፅና ቀጥተኛ ነው። 

 • የሌለ ነገር እየዘባረቀ በሕዝቦች መካከል ፀብን የሚዘራ፤
 • አፉ በከፈተ ቁጥር ሰላምና ዕረፍት የሚያርቅ፤
 • ወሬው ሁሉ በፍቅርና በስኒት ፈንታ ሁከትና ብጥብጥን የሚያነግስ፤
 • ለነፍስም ለስጋም የማይበጅ ተራጋሚ የኢሳት አንደበት ነው ሰዎች ልብ ይሉ ዘንድ እየተናገረ ያለው።
 • ሰባኪው – ቆሻሻ፣ ለሀገርና ለሕዝብ የማይጠቅም ከፋፋይ፣ አጥፊና አውዳሚ የኢሳት ቀበሌ ተኮር ርካሽ ፖለቲካ ነው እየተቃወመ ያለው።
 • ሰባኪው – አማኞች ፊታቸው ወደ እውነት ይመልሱ ዘንድ ነው ግሳፄው።
 • ሰባኪው – ኢሳት በሕዝቦች በመካከል የሚዘራው መጥፎ ዘር ነው እየተፀየፈ ያለው። ኢሳት የሚጠቅም ነገር ቢኖረው ኖሮ ሰባኪው ይህን አይናገርም። ሰባኪው ኢየሱስ ያላስተማረው አላስተማረም። ሰባኪው እውነት ተናግሯል – ኢሳት ቅጀት ውስጥ ነው!

ርዕሰ ጉዳያችን መቋጫ ስናበጅለት – የሰባኪው መልክዕት ከተጋችሁ አይቀር ለመልካም ነገር፣ ለሚረባችሁና ለሚበጃችሁ፣ ለነፍስ ለስጋም ለሚጠቅማችሁ ለበጎ ነገር ትጉ። እጆጃችሁ ካበረታችሁ አይቀር ለስራ አበርቱ። እግሮችሁ ካፈጠናችሁ አይቀርም ለመልካም ነገር አፍጥኑ። በእግዚአብሔር ይሁንባችሁ! በሚመስል ዳሩ ግን ወደ ሞት በሚነዳችሁ መንገድ አትጠመዱ ነው የሰባኪው መልዕክት። ጠማማ ምን ጊዜ ጠማማ ነውና ሲሳይ ከመንገድ ጎትተው ያመጡት ከሚመስል የጋዜጠኝነት መንፈስ ያላለፈበት አሽከሩ ጋር በመሆን ይህን የመሰለ ነፍስ የሚያለመልም ጣፋጭ መልዕክት ለማጣመም መትጋቱ ምንም አልደነቀኝም። ቀለብ የሚሰፈርለት የስራ ድርሻው መወጣቱ ነውና። 

Dn. Mulugeta Weldegebrial

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 2, 2015

Advertisements