የየመን ባንዴራ ማቃጠል ምን ዋጋ አለው? ካቃጠሉ አይቀር የእንግሊዝ ነው እንጅ!

መንደርደሪያ፡  

ኢትዮጽያና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለማፈራረስ፡ ለማተረማመስና ለማውደም፤ ብሎም ኢትዮጵያ ካልፈራረሰችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርስ በርስ ደም ካልተቃቡ በስተቀር ሳትወለድ የተጨናገፈች፡ ሳታብብ የጠወለገች ሓዳሽ ኤርትራ ሲንጋፖር ማድረግ ሆነ ሆና ማየት የማይታሰብ ነው! ብሎ ከሚያምን ቅዥት ያበላሸው የኤርትራ መንግስት ጋር ግንባር በመፍጥርና ተላላኪ በመሆን ሽር ብጥስ ሲል በነበረው የደም ሰው የየመን መንግስት ቀደም ሲል አሸባሪዎችን በመያዝና በመለዋወጥ ረገድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነትና በተፈራረመው ሰንድ መሰረት የጥፋት መልእክተኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፎ መስጠቱ የሚታወቅ ነው። british-flag- Salsay woyane

“ጭር ሲል አልወድም!” ባዩ ይህ የአመጽ ሰው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን መንግስት በኩል ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱ ተከትሎ የቀድሞ ባለደረባ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የተባሉ ሁለተኛ የጥፋት መልዕክተኛ ግለሰብ በምዕራቡ ዓለም መሽገው ሲያበቁ  “እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ!” ሲሉ ሰሙኑ በበተኑት የምጸት በራሪ መጣጥፋቸው እንግሊዝን ለይስሙላ አሻሽቶ ሲያልፍ ”ድሮን” ያልታጠቀ የየመን ሕዝብና መንግስት ደግሞ ኢላማ አድርገው መነሳታቸው ለማንበብ ችለናል።  

በነገራችን ላይ ግንቦት 7 “የየመን መንግሥት የዓለም ዓቀፍ ህግም ሆነ የየመን የራሷን ህግ በመተላለፍ መሪያችንን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶብናል።” ሲል ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ/ም በለቀቀው ማደናገሪያ ዲስኩር የየመን መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፎ በመስጠቱ እውነትም የየመን መንግስት በህግ የሚያስጠይቀው ጉዳይ ከሆነ ግንቦት 7 ጉዳዮን በህግ መልክ እንድይዝ በማድረግ ሂሳቡን ማወራረድ ሲችልና ሲገባው ቀላሉና ውጤት ሊያስገኝ የሚችል መንገድ በመተው እንደ ሰፈር ድሩዬ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ያበዛበት ዋና ምክንያት ድርጅቱ (ግንቦት 7) ከመጋረጃ በስተጀርባ የሰራው ወንጀል ለመደበቅ ከመሆኑ በተጨማሪ “ነኝ” እንደሚለው መሬት ላይ የረገጠ የፖለቲካ ስራ መስራት የሚያስችል የፖለቲካ ሰውነት፡ አቅም ሆነ እውቀት እንዲሁም ሞራል የሌለው ትልቱላ ለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን የሚጠራጠር ዜጋ ሊኖር አይገባም።  

የጽሑፉ ይዘት፡

ግንቦት 7 የቀድሞ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ነበር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ “ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን!” ሲል በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ/ም የበተነው ጽሑፍ  የመንን በተመለከተ ያስተዋወቀው የሽብር ድርጊት ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ አተኩሮ አጠር ባለ መልኩ የሚያትት ጽሑፍ ነው። መልካም ንባብ!

    • አንድ፡ “ለየመን ፕሬዚዳንት አዲስ መረር ያለ ደብዳቤ ተጽፎ በፋክስና በኢሜል በየመን መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች አድራሻዎች መላክ። በመልዕክት መጨናነቅ” ይላል። እኔምለው ይህ ኢትዮጵያ የምታክል አገር ለመምራት የሚውተረተረው ግንቦት 7 የሚባለው ድርጅት አንድ አርቆ ማየት የሚችል፡ ከስሜት የጸዳ፡ ምራቁ የዋጠ፡ ራሱን የሚገዛ፡ በነገሮች የማይቸኩልና ቁጡብ ሰው፡ ሕዝብ ለመምራት የሚያስችል በቂ ትምህርትና ስልጠና የወሰደ፡ በፖለቲካ አመለካከቱ የበሰለ፡ ጭምትና አስተዋይ ሰው እንዴት ይታጥበት? “አዲስ … መረር ያለ … በመልዕክት መጨናነቅ!” በቃ ይሄ ነው ግንቦት 7 ማለት? የሰው ያለህ!
    • ሁለት፡ “የየመን ኤምባሲዎችን ሥራ ማወክ በሚችሉ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ማጨናነቅ።” ቀጥሎም “የፕሬዚዳንቱን ፎቶና የአገሪቱን ባንዲራ ማቃጠል” ይላል። “የፕሬዚዳንቱን ፎቶና የአገሪቱን ባንዲራ ማቃጠል” ወደው አይስቁ! ይላል ያገሬ ሰው ሲተርት። እነ ሃማስ፡ ታሊባን … ባንዴራ ሲያቃጥሉ ደካማን እየመረጡ ሳይሆን የእንግሊዝና (የአሜሪካ) ባንዴራ ሲያቃጥሉ ነው የናውቀው። ለመሆኑ ስንት ባንዴራ በማቃጠል ይሆን አቶ አንዳርጋቸው ከአንበሳ ምንጋጋ ማላቀቅ የሚቻለው? “ባንዴራ አቃጥሉ” ብቻ ሳይሆን አቶ አንዳርጋቸው ለማስለቀቅ ስንት ባንዴራ ማቃጠል እንዳለበትና እንደሚገባ ቁጥሩንም ጭምር አብሮ ማሳወቅ ይገባ ነበር ባይ ነኝ። ደግሞስ የየመን ባንዴራ ማቃጠል ምን ዋጋ አለው? ካቃጠሉ አይቀር የእንግሊዝ ነው እንጅ! ግንቦት 7 የሰው አገር መሪና ባንዴራ ማቃጠል የሚያመጣው ለውጥ አለ ብሎ የሚያምን ከሆነ “ዜጋዋ ተላልፎ መሰጠቱ እያወቀች ምንም እንዳልሰማችና እንዳላየች በመሆን ምንም አላደረገችም” አሁን ደግሞ “የአንድዬን የጎዞ ሰሌዳ በተመለከተ ለኢትዮጵያ መንግስት መረጃ ያቀበለ የብሪታኒያ የስለላ ድርጅት ነው” በማለት ፈራ ተባ እያለ የሚከሳት የታላቅዋ ብሪታኒያ ንግስትና ባንዴራ ነበር ተከታዮቹ ያቃጥሉ ዘንድ ማዘዝ የነበረበት። ሥራ ማወክ በሚችሉ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ማጨናነቅም እንግሊዝ ኤምባሲን ነበር። ታድያ ብርሃኑ ነጋ ይህን የዋለው ዕለት የእንግሊዝ መንግስትና ሕዝብ እንደ የመስቀል በዓል ደመራ (ችቦ) እዛው አብሮ እንደሚያነው/እንደሚያቃጥለው ጠንቅቆ ያውቃል። ቀልደኛ! 
    • ሦስት፡ “በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዳወጁ የምንቆጥረው መሆኑን” ይህን ምኞታዊ ልበ ወለድ ያረቀቀ ግለሰብ ጽሑፉን የጻፈው በእንቅልፍ ልቡ መሆን አለበት። ለመሆኑ ይህ ግንቦት 7 ተብሎ የሚታወቅ ምላሰ ረጅም ድርጅት በቢሮክራሲ የተዋቀረ የሰው ሃይል ሊኖረው ቀርቶ እውን መልክ ያለው ወንበርና ጠረጰዛ አለውን? የመን ስራዋን ሰርታ ጨርሳለች ሰውዬውም (አቶ አንዳርጋቸው) ከወደ አገራችን ኑዛዜአቸውን አሰምተውናል። አሁንም ድርስ ያልገባኝ ነገር ቢኖር ግን የግንቦት 7 “በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዳወጁ የምንቆጥረው መሆኑን” የሚለው ቀረርቶ ነው። ደግሞስ የመን ምን ብላ ነው ጦርነት የምታውጀው? የየመን መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ሳይውሉ ሳያድሩ ወደ አገራቸው መሸኘትዋን ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አልሰሙ ይሆን እንዴ? ዶክተሩ ባይሰሙ ነው እንጅ በጠራራ ጸሐይ ላይ እንዲህ ነገር ባልቀላቀሉ ነበር። አይመስሎትም ውድ አንባቢ?

 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

July 12, 2014

Advertisements