የእንግሊዝና የአሜሪካ ዜጋ መሆን ቀርቶ ለምን የሲዖል ዜግነት አይኖርህም:

በትዕቢት የተወጠረ አመጸኛ ልቡ ተከትሎ ወደ ጥልቁ የተወረወረ ሰይጣን እኩል እንደ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ሰማያዊ ማንነትና ዜግነት የነበረው ፍጥረት መሆኑን በብዙሐን ዘንድ የተዘነጋ ሐቅ ነው። ሳጥናኤል አድርጎት ሳይሆን በልቡ አመጽን በማሰቡና በማሰላልሰሉ ብቻ ለደረሰበት ዘላለማዊ ውድቀት ስማያዊ ዜግነቱ አላተረፈውም። በእርግጥ በማነንቱ አሁንም ረቂቅ ፍጥረት ቢሆንም በዜግነቱ ግን የሲዖል ዜጋ/አጋፋሪ ነው። ቀድሞ በመላዕክት ህብረት ሳለ የነበረው ከፍ ያለ ሰማያዊ ክብርና መታወቂያ ተገፏል። በአሁን ሰዓት መታወቂያው ብርሃን መሆኑ ቀርቶ ጽልመት የተላበሰ ነፍሰ ገዳይ፡ የሐሰት አባት ለመሆኑ ማብራሪያ የማይሻው ሐቅ ነው።

የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር!

ኢየሱስ በአገልግሎቱ ከገጠሙት ትላልቅ ተግዳሮች መካከል እንደ ሽንፍላ በቀላሉ ታጥቦ የማይጠራ የአይሁድ የግብር ይውጣ ድርጊት/ምንነት አንዱ ነው። አይሁዳውያን እውነትም አዙሪት ናቸው። አይሁዳውያን በማስመሰል የተካኑ ዳሩ ግን ህይወት የረቀባቸው: በቁማቸው የደረቁ: ለክፋትና ለጥፋት የማይተኙ አመጸኞም ናቸው። ታድያ ከዕለታት አንድ ቀን አይሁድ – ያበጠ የሚያስተነፍስ፡ የደረቀ የሚያለመልም፡ ጎባጣ የሚያቀና፡ ከፍ ያለውን ዝቅ – ዝቅ ያለውን ከፍ የሚያደርግ፡ ተራራውን ደልዳላ ሜዳ የሚያደርግ: ጫካን የሚመነጥር  መድሃኒት መዋጥ ይገባቸው ነበርና ከኢየሱስ ጋር ተገናኙ። ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ እንዲህ አላቸው፡

“ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። እነርሱም መልሰው የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት። ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ። መልሰውም። አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም፦ የአብሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር። ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት። ኢየሱስም አላቸው። እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።” [የዮሐንስ ወንጌል 8፥ 31- 44]

“በቃሌ ብትኖሩ” የምትለዋን የኢየሱስ ቃል ባልተጠበቀ ሁኔታ በአይሁድ ዘንድ ቁጣ ቀሰቀሰችና ዘለው ‘ምን ይቀባጥራል ይሄ! እኛ ‘ኮ “የአብርሃም ዘር ነን!” በማለት ተመጻደቁበት። ይህ ማለት ምንም ማለት እንደሆነ ያውቁ ኖራል? ይህ ማለት ሰዎቹ (አይሁዳውያን ማለቴ ነው) ነን የሚሉት “የአብርሃም ዘር” በመሆናቸው ብቻ ከኢየሱስ ምንም ዓይነት ነገር የማይፈልጉ ራሳቸው ከሁሉ የበላይ አድርገው መቁጠራቸው፤ ”የአብርሃም ዘር” ተብለው በመጥራታቸው ብቻ “ማንም በፊታችን ቆሞ እኛን የመገሰጽ፡ የማስተማር፡ የመምራት፤ በእኛ በምርጦቹ ፊት ቃል የመተንፈስ፡ የመናገር፡ ሆነ የመሻገር መብትም ሞራልም የለውም።” ብለው ስለሚያምኑ ኢየሱስን ማቃለላቸው፡ መንፈጋቸውና ማጣጣላቸው ነበር።

እዚህ ላይ “የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ” እንዲል ኢየሱስ አይሁድ የአብርሃም ዘር ለመሆናቸው አልካደም። አይሁድ “የአብርሃም ዘር ነን” ሲሉ ላነሱስ መከራከሪያ ነጥብ ነገር መቀላቀላቸው ያስተዋለ ኢየስሱ ቁምነገሩ “የአብርሃም ዘር” ተብሎ መጠራቱ ላይ ሳይሆን የአብርሃም ዘር መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ሲነግራቸው እንመለከታለን። በነገራች ላይ “ነኝ” ማለት እና “ሆነህ መገኘት” ለየቅል ናቸው። የአይሁዳውያን አንዱ ትልቁ ችግራቸውም ይህ ነበር።

የልባቸው ትዕቢት አልበረደላቸውምና መልሰው እንዲህ ይሉታል – ‘ሰውዬ አብደሃል እንዴ!? “አባታችንስ አብርሃም ነው” ይላሉ። ኢየሱስም ‘ነው እንዴ!? ታድያ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ … ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም።” በማለት ሲመልስላቸውገና አሁን ነገሩ የገባቸው አይሁድ ጨርቃቸው ጣሉ። የሚይዙት የሚጨብጡት ከማጣታቸው የተነሳም በአሽሙር መሳደብ ጀመሩ።

አይሁድ ሳይቸግራቸው ራሳቸው ከጋለ ምጣድ ላይ አስቀምጧል። ኢየሱስም እንግዲያውስ ነገሩን ከጀመራችሁት አይቀር እንቅጭዋን ልንገራችሁ ሲል – ‘ትሰሙኛላችሁ ምንም እንኳ “የአብርሃም ዘር ነን!፡ አባታችን አብርሃም ነው!፡ የአብርሃም ልጆች ነን!” እያላችሁ ራሳችሁ ሰማይ ብትሰቅሉና ብትባርቁም ለማያውቃችሁ። ሐቁ እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ። የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ።” አክሎም የግብር አባታቸው ስለሆነ ስለ ዲያብሎስ ማንነን እና እኩይ ምግባር እንደሚከተለው ያብራራላቸዋል  “እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና”  እንዲል።

እና ምን ይጠበስልህ?

የሌላ አገር ዜጋ መሆን (ዜግነት መውሰድ) በራሱ ነውር አይደለም። እያንዳንዱ ግለሰብ ይህን የሚያደግበት ምክንያትም ይኖሮዋል። አገራቱ ባስቀመጡት መስፈርት መሰረት አንድ ሰው የሌላ አገር ዜግነት የመውሰድ (አሜሪካ/እንግሊዛዊ/ህንዳዊ/ቻይናዊ …) የመሆን ፍላጎት ኖሮት ሟሟላት የሚገባው አሟልቶ በህግ የሌላ አገር ዜጋ መሆን ሃጢአት አይደለም። የሰው አገር ዜግነት ከለላ በማድረግ ህገ ወጥ ድርጊት መሰማራት ግን በህግ የሚያስጠይቅ ከወንጅልም በላይ ወንጀል ነው።

እውነት ነው የሌላ አገር ዜግነት መውሰድ ወይም ዜጋ መሆን ማለት አገሪቱ በማንነታቸው የምድሪቱ ፍሬ ለሆኑት ለዜጎችዋ የምትሰጠው ጥቅማ ጥቅም በህግ ትሰጥህ እንደሆነ ነው እንጅ በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ውስጥ ተነክረህ ስታበቃ የእንግሊዝ ወይም የአሜሪካ ዜግነት በመያዝህ ብቻ በህግ ከመጠየቅ ታመልጣለህ ማለት አይደለም። የየትኛውም አገር ዜጋ ብትሆንም ደግ ደጉን ማሰብና መስራት ትተህ ራስህን በህገወጥና በአመጽ ጎዳና ካሰማራህ የያዝከው ዜግነት በህግ ከመጠየቅ አይገላግልህም።

ለምን ሰማያዊ ዜግነት አይኖርህም! (ሰማያዊ ዜግነት ያለው ሰው ከአመጽ ጋር ህብረት የለውም እንጅ) ሰው በሰራው/በሚሰራው ወንጀል በህግ ፊት መጠየቁ ግድ ነው። በአሜሪካ ምድር ተወልዶ ያደገ በማመልከቻ ሳይሆን በልደት አሜሪካዊ በትውልድ የመናዊ የሆነው አንዋር አል- አውላኪ ግሩም ምሳሌ ነው። ታድያ አሜሪካዊ ዜግነቱ በድሮን ተደብድቦና ተበጣጥሶ ከመሞት አላተረፍውም።

እኔምለው፡ አንድ ሰው የእንግሊዝ/የአሜሪካ የዜግነት ካባ በማጥለቁ ብቻ በሂደበት ሁሉ ቦንብና ፈንጅ ያፈነዳ ዘንድ መብት የሰጠው ማን ነው? ለመሆኑ የእንግሊዝ ሆነ የአሜሪካ ዜግነት መያዝ ማለት ከህግ በላይ መሆን ማለት የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው? አንድ ሰው ወንጀል ሰርቶ ሲያበቃ እንግሊዛዊ/አሜሪካዊ በመሆኑ ብቻ ግለሰቡ በሕግ አይጠየቅም/ከህግ በላይ ነው ያለ ማን ነው? ዳያስፖራው በሰው አገር ዜግነት መንግስተ ሰማያት ይገባ ይመስል ምን ነው ተቁነጠነጠሳ? የእንግሊዝ ሆነ የአሜሪካ ዜግነት መያዝ ማለት በምግብ ራስህን ትችል እንደሆነ ነው እንጅ ሌላ ምንም ማለት አይደለህም። ምንም ቢሆን ምን ደምህ ያው የቀድሞ ያገሬ ሰው አንተ ራስህ ነህ። 

“አሜሪካዊ ነኝ!” “እንግሊዛዊ ነኝ!” “ጀርመናዊ ነኝ!” “ስዊድናዊ ነኝ!” “ህንዳዊ ነኝ!” “ቻይናዊ ነኝ!” … እና ምን ይጠበስልህ? የሰው አገር ዜጋ መሆን ይህን ያህል ብርቅ የሆነበት ምስጢሩ ምንድ ነው? አንድ ‘ኦሪጅናል’ አሜሪካዊ/እንግሊዛዊ በማመልከቻ የእንግሊዝ ወይም የአሜሪካ ዜግነት ከወሰደ/ች ኢትዮጵያዊ ጋር ያነጻጸርን እንደሆነ ዋኖቹ ኦርጅናሎቹ ማለቴ ነው) ይህን ያህል በዜግነታቸው አይደነፋም። አንድ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካና የእንግሊዝ የዜግነት ካባ የደረበ/ች ዕለት (ዜግነት የያዘ/ች ዕለት) ግን እንደ ባለ አእምሮ ማሰብ አቁሞ: አየር ላይ የሚንሳፈፍበትና እንደ ተልባ የሚንጣጣበት ነገር ምንም ሊገባኝ አይችልም።

ለመሆኑ የትኛው እንግሊዛዊ ወይም አሜሪካዊ ነው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ራሱን ነክሮ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ከተሞች ለማሸበርና በቦንም ለማፈራረስ የተሰለፈ? አንድም ሰው አይገኘም። እንደውም “ኢትዮጵያ” ሆነ “ኤርትራ” የሚለው ስም የምግብ ስም ይሁን የዛፍ ስም የሚያውቀው ነገር የለም። እነዚህ አገራት ለመኖራቸውና የሚገኙበት አከባቢ የሚያውቅ ከሚልዮን አንድ ቢገኝ ነው።

ጎበዝ! አይደለም ደጅ ተጸንቶ ገንዘብህ ከፍለህ በማመልከቻ የምታገኘው ዜግነት ቀርቶ በእንግሊዝና በአሜሪካ ከተሞች እምብርት በመወለደህ የምትጎናጸፈው ዜግነትም ቢሆን (*ልዩነት አለው እያልኩ አይደለም) በሰው አገርና መንግስት ወንጀል ሰርተህ ስታበቃ የእንግሊዝ/አሜሪካ ዜግነት ከተጠያቀነት አያስመልጥህም።  

አንድ ግለሰብ የእንግሊዝ ወይም የአሜሪካ ዜግነት በመያዙ ብቻ ያሻውን ማድረግ የሚቻለው ቢሆን ኖሮ ከፓኪስታናውያን ወላጆች በሳውዲ ዓረቢያ የተወልዶ በኒው ዮርክ አሜሪካ ያደገ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነ ሳሚር ካሃን መስከረም 30 2011 ዜግነት በወሰደባት በአገሩ መንግስት በወጣትነት ዕድሜው (25) በድሮን ተደብድቦ ባልሞተ ነበር። ሳስበው ግን ዳያስፖራው የአንድ አገር ዜጋ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሳይቀላቀልበት አይቀርም።

እጹብ ድንቅ ነው!

የፊተኛውን ቀብረህ የኋለኛው በላይህ ላይ ሹመህ ስታበቃ ከህግ ከተቀመጠው ገደብ አልፈህ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣቶችህን ሰደህ ትፈተፍት ዘንድ የፈቀደልህ ማን ነው? እንዴት ነው ነገሩ፡ “እንግሊዛዊ ነኝ /አሜሪካዊ ነኝ” ማለት የሚቀናህ ከሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምን ያንቀለቅልሃል? ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውን ተዋት። መተው ነው እንጅ። አይመስሎትም? ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለው ፍቅር የሚገልጸው ተሸራርፎ፡ ተላልጦና የሞት ዋጋ ከፍሎ በማመልከቻ በሚያገኘው የአሜሪካና የእንግሊዝ ዜጋ በመሆን ከሆነ ደግሞ ነገሩ እጹብ ድንቅ ነው።  

የአገሬ ሰው ሲተርት “ድንጋይ ቢያስቀምጡት ሺህ ዓመት ይቀመጣል” እንዲል ሃያ ዓመት በተለወጠና በሰነጠነ አገር ተቀምጦ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ቀርቶበት እንዲሁ ከቆይታው ብዛት የተነሳ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ሳይማር የቀረ የሰው ዋልያ ታማኝ በየነ የጥላቻ፡ የመለያየትና የእርስ በርስ እልቂት ዘር ለመዝራት እስራኤል አገር የራሱን ወገን ሰብስቦ ባሰማው ቀረርቶ ይህን ነበር ያለው “የአሜሪካ ዜግነት ይዘህ እንዴት ትፈራለህ?!” ነበር ያለው ይህ ማፈሪያ አዝማሪ።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

July 11, 2014

Advertisements