አንዳርጋቸው ጽጌ፥ ከባህር የወጣ ሙት አሳ!

መሪ ጥቅስ፡

“ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ። እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ። ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር። አጋንንቱም ታወጣንስ እንደሆንህ፥ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት ሂዱ አላቸው። [ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው የማርቆስ ወንጌል 5፥ 10፤ ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው ለመኑት የሉቃስ ወንጌል 8፥ 31] እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም፥ የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ። እረኞችም ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም በአደሩባቸው የሆነውን አወሩ። እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት። [የማቴዎስ ወንጌል 8፥ 28- 34]

ይህን መልእክት ሲያነቡ አጋንቱ ከከተማ ውጭ እንዳይሰዳቸው ወደ ጥልቁም እንዳያባርራቸው ደጋግመው ኢየሱስን ሲማጸኑ፤ እንደውም ወደ እሪያዎቹ መንጋ ይሰዳቸው ዘንድ ሲለምኑት በአጋንቱ አእምሮ ያለውን ክፉ ሐሳብና መሰሪ ተንኮል ለማየት ካልቻሉ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ (ድራማው) በቀላሉ እንደማይገባዎት ነው የማምነው።

ማሳሰቢያ፡ ጽሑፉ በይዘቱ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን መንግስት በኩል ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ ተሰጥታል አልተሰጠም የሚል ሙግት አያንጸባርቅም።

እገታ ካለ ጥቆማ አለ!  

ኢሳት “የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ሰር መዋላቸው ተገለጸ” ንቅናቄው የመን ታሳሪው እንድትለቅ ከመጠየቁ ባሽገር “አሳልፋ እንዳትሰጥም አሳስባል” ይላል።

የየመን መንግስት እንደሆነ የሰው አገር ሰው ከመሬት ተነስቶ በቁጥጥር ስር አያውልም። ይነስም ይብዛ ለጊዜውም ቢሆን ግለሰቡን “በተጠርጣሪነት” በቁጥጥር ስር ማዋል የሚችለው በቂ ምክንያት ይኖሮዋል። ደግሞም “አለው።” ግለሰቡ በቆይታው በህገ ወጥ ድርጊት ተሰማርቶ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር የዋለ ባለ አመል እንደሆነስ ማን ያውቃል? እነዚህ እውነታዎች በመቅበር ጉዳዩ በቀጣታ ለዛውም ያለአንዳች ተጨባጭ መርጃ ተፈጸመ ከተባለው ጉዳይ በምድርም ሆነ በሰማይ ምንም አይነት ግኑኝነት የሌለው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ማያያዝስ ምን አመጣው? “የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ ስለሆነ ነው” የሚለው ተራ ደመ ነፍሳዊ ሙግት ወደ አእምሮዎ እንዳያልፍ።

የየመን የጸጥታ ሃይሎች አንድን የሌላ አገር ዜጋ በተጠንቀቅ ጠብቀው በቁጥጥር ስር የሚያውሉበት ምክንያት እንዲሁ በድንገት/በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። እገታ ካለ ጥቆማ አለ። ጥያቄው እገታው ያቀናጀ ማን ነው? ለምንስ የመን ተመረጠች? ነው። የሚደንቀው ደግሞ ፕሮፖጋንዳው በማራገብ ረገድ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉ የራሱ የግንቦት 7 ልሳኖች መሆኖቸው ነው። አሁንስ ምን እየሆነ እንዳለ አልነቁም?

ጎበዝ! እንዲህ ያለ ወዝ የሌለው ድራማ በመተወን የዋሁን ማህበረሰብ ማደናገር ገንዘብ መሰብሰና የሌላቸው ስብእና መገንባት ለግንቦት 7 ግለሰቦች እንግዳ አይደለም። የቀድሞ የኢሳት ቅጥረኛ አቶ አበበ ገላው ስማቸው ለመገንባት አስልተው ይረዳኛል ያሉትን ሁሉ ባልዋለበት አስቀድሞ የተፈረደበት የተከሳሹ ግለሰብ ሙሉ ስምና አድራሻ ሳይቀር አስቀድመው አቤቱታ አሰምተው/ጥቆማ ሰጥተው ሲያበቁ “የትግራይ ተወላጅ ሊገድለኝ ሲያሴርብኝ እግዚሃር ይስጣቸው “FBI” ደረሱልኝ” ሲሉ ከዚህ ቀደም የሰርዋት ሞቅ ያለች ቤተኛ ድራማ ባለ አእምሮ የሚዘነጋው አይደለም። ታድያ ቀድሞ ከሆነ ነገር ቁም ነገር ተምረው ካላለፉ እየሆነ ያለው እንዴት ሊገመግሙ ይችላሉ? በነጋራችን ላይ አቶ አበበ ገላው በድጋሜ መጮሃቸው የሰማሁት ገና አሁን። ታድያ በዙሪው የምለው ስለሚኖረኝ ሰሙኑ እመለስበታለሁ።

*  *  *  *

ኢሳት “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን ውስጥ የተያዙት ወደ ሌላ አገር ለመሻገር የመንን የአየር መተላለፊያ ማድረጋቸውን እንደሆነ አስታውቀዋል” ይላል።

የግለሰቡ የጉዞ የጊዜ ሰሌዳ በተመለከተ በቀዳሚነት መረጃ ሊኖረው የሚችል አካል ቢኖር፡ አንደኛ ግለሰቡ ራሱ ከዚህ ያለፈ ደግሞ ህልውና ይኑሮው አይኑሮው በውል የማይታወቅ ምላሰ ረጅም ድርጅታቸውና በእርግጥ ቀለብ የሚሰፍርላቸው የኤርትራ መንግስት ብቻ ናቸው።

እዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ጭምር (የግለሰቡ የጉዞ የጊዜ ሰሌዳ) መረጃ አለው ወይም ነበረው ብሎ ለመሞገት የሚቃጣው ዜጋ ካለ እውነትም አንዳርጋቸው ጽጌ አስመራ ውስጥ የፖለቲካ ስራ ሳይሆን እየሰራ ያለው ግለሰቡ “ሐሸውየ” እየተጫወተ ለመሆኑ ማለፊያ ማሳያ ነው።

ኢሳት “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ ይሰጣሉ የሚል ስጋት እንዳደረበት የገለጸ ሲሆን የመን ይህንን እርምጃ ከወሰደች በሁለቱ አገራት ዘላቂ ግኑንነት ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም አሳስባል … አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ ቢሰጥና በአካላቸው፡ በመንፈሳቸው እንዲሁም በህይወታቸው ላይ ለሚከተለው ጉዳት የኢትዮጵያ መንግስት ባለ ስልጣናትን ዋጋ የሚያስከፍል የበቀል እርምጃ እንደሚወስድም ንቅናቄው አስጠንቀዋል” ይላል።

ሰው ያላሰበውን ማሰሰብ ይሉት ይሄውሎታ። ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ መንግስት  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ያለውን አመለካከት በቃላት ማስቀመጥ ካስፈለገ አንዳርጋቸው ጽጌ ማለት ለኢህአዴግ ከባህር የወጣ ሙት ኣሳ ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ በአመት አንድ ጊዜ ከአስመራ ዋሽንግተን ድረስ እየመጣ ስለ ጌቶቹ “ደግነትና” “ጽድቅ” ከመደስኮር ያለፈ አንዳች የሚፈጥረው ተአምር የሌለው: አቅመ ቢስ: ለሆዱ ያደረ – ባንዳ ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከማናችን በተሻለ መልኩ የጠራ ምስልና በቂ ግንዛቤ አለው።

ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮኸለች!

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አንዴ – “የግድያ ሙከራ ተደረገብኝ” ሲፈልግ “ኮምፒተሬ ተጠለፈብኝ” ሞቅ ሲለው ደግሞ  “ከአሁን በሃላ የምንገናኘው አዲስ አበባ ነው” አሁን ደግሞ “የየመን መንግስት ወደ ኢትዮጵያ አሳልፎ ሊሰጠኝ ነው ኡ! ኡ! ኡ!” እያለ በሚሰራቸው ድራማዎች ሳያነብ በመፈረምና ሳያይ መርዝን በመጨለት የሰለጠነ ዳያስፖራ ከማወናበድ፡ ከማታለልና ከማደናገር ያለፈ አንዳርጋቸው ጽጌ ለሌላ ለማንም ራስ ምታት ሊሆን አይችልም።

ሐቁ ይህ ነው! አቶ አንዳርጋቸው ለራሱ ሳይማርና ሳይሰለጥን ወታደሮች አሰልጥኜና አስተምሬ መንግስትነት በእጄ አስገባለሁ ሲል የጀመረው ቅጀች ሲያቅተው የመን ድረስ ሂዶ በመታሰር በእስር ወደ ኢትዮጵያ ከመግባት ውጭ ሌላ ምንም አይነት አማራጭ የለውም። እውነት ነው ግለሰቡ (አቶ አንዳርጋቸው ማለቴ ነው) ወደ ፖለቲካ አለም መመለስ ከፈለገ የሲኦል ፈላስፋው ኢሳይያስ አፈወርቂ በመቱት  መላ መሰረትታስሮ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባት ውጭ ሌላ ምንምአማራጭ የለውም።

በነጋራችን ላይ አቶ አንዳርጋቸው ስጋው አፈር አልበሰብ እንጅ አስመራ ገብቶ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ራሱን ካሰናበተ አመታት አልፈዋል። ልጅ የናቱን ጡት የተወ ያህልም በውስጥም በውጭም ተረስተዋል። አንዳርጋቸው ጽጌ ሲል/ብሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ስመ ዝክሩ የሚስታውሰው ሆነ የሚዘክረው ዜጋ የለም።

እስቲ በሞቴ ይህ ሰው “ታሰረ/ታሰርኩ”ብሎ ጩሆ ካላስጨኸ በስተቀር በአሁኑ ሰአት አቶ አንዳርጋቸው በምኑ ይታወስ? ተረስቶ የነበረ ግለሰብ “Free Andargachew …” በሚል ሞፈክር ከወዲሁ ላሜቦራ መካነ ድሮች አጨናንቀዋል። ኢሳት እንዲህ ርእስ እያስጮኸ የሰውዬው ህልውና ካላስታወሰን በቀርስ በምን እናስታውሰው? ያልደከመበትን መሰብሰብ የለመደ ግንቦት 7 እንደሆነስ በሬ ወለደ ድራማ ስያልቅበት መሪውን አሳልፎ በመስጠት ገንዘብ መሰብሰብ ካልቻለ እንዴት ይዝለቀው? ዶክተር ብርሃኑ ከውዲሁ እዚም እዛም መገኘት ጀምራል። ኢሳትም ደርተዋል። ድሮም እኮ የተፈለገው/የሚፈለገው ይሄ ነው። የአዞ እንባ እያነባህ አገር እያፈረስክ ቤትህን መገንባት።

የግንቦት 7 እውነተኛ ስጋት …

ታየኝ እኮ የኢትዮጵያ  መንግስት የመን ድረስ ሂዶ አንዳርጋቸው ጽጌ የአውሮፕላን ቲኬት ከፍሎ ወደ ኢትዮጵያ ሲመልሰው። ምንሊበጀው? ታስሮም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በብርቱ የሚሻ ሌላ ምንም ሳይሆን ካርታው የጠፋበት የሳይበር ታጋይ ራሱ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ብቻ ነው። የግንቦት 7 እውነተኛ ስጋትም ይህ ነው: አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱ ላይ ሳይሆን ወደ አስመራ መመለሱ ላይ ነው ትልቁ የግንቦት 7 ስጋት። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ኤርትራ ተመልሶ የአስመራ ፋታ እየበላ ከህያዋን በታች ከሙታን በላይ ሆኖ የቀድሞ የብቸኝነት: የተስፋ መቁረጥ: የኪሳራና የጨለማ ኑሮ የተመለሰ እንደሆነ ነው ትልቁ የግንቦት 7 ስጋት።

ጥጉ: ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ በጻፉት አጭር ልብ ወለድ ድርሰት የኢትዮጵያ መንግስት ማዶ ተቀምጦ “ወፌ ቆመች!” እያለ ክት ብሎ ከመሳቅ ያለፈ ኢህአዴግ በህግደፍ/ግንቦት 7 ወጥመድ ይገባል ብሎ መጠበቅ ቀልድ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ግለሰቡንም ቢሆን ከነአካቴው አይፈልገውም። [በሕግ አይፈለግም አላልኩም።]

“ጠልፎ ነው የወሰደው የሚለው” አመለካከት ከአእምሮአችን ሊወጣ ይገባል። በመሰረቱ ኢህአዴግ የሚፈልገው ሰው በዚህ መልኩ አይደለም እጁ ላይ ማስገባት የሚፈልገው። በሚያውቀው መንገድ ባለበት ነው የሚያመክነው እንጅ ኢህአዴግ ሜዳውን ትቶ ስራ ሲፈታና ሲራራጥ አናገኘውም። ኢህአዴግ ስራ ለመስራት ተነስቶ ግርግር ሲፈጥር ሆነ አባራ ሲያስጨስ ከዚህ ቀደም አይተንም ሰምተንም አናውቅም። ለባህሪውም አይስማማውም። ታድያ አንድን ሕዝብ ነጥሎ ለማጥቃትና ዘሩንም ለማጥፋት ራሱን ያደራጀ፡ በጥላቻ የሰከረ፡ በህግ የሚፈለግ የደም ሰው ደጃፉ ድረስ ሲመጣለት “አይ! አልፈገውም” ብሎ በሰላም ያሰናብተዋል ብሎ ማሰብም ሞኝነት ነው።

ወረደም ወጣ የኢሳት ቅጥረኞች “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ ይሰጣሉ” ሲሉ ምላሳቸው እስኪደማ ድረስ ያለመሰላቸት የሚያማርቱት ምዋርት ተደናብሮ የኢትዮጵያ መንግስት አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፎ እንዲሰጥ በማድረግ የሻእቢያና የግንቦት ሰባት ሊሂቃን እንጀት ያርሳል ብሎ መጠበቅ ሲበዛ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግን በሚገባ አለማወቅም ነው። አንጀታቸውን ለመበጣጠስ ግን አያደርገውም አይባልም። ያደረገውም እንደሆነ ኢህአዴግ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ከነተረቱም ”በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንደሚባለው የዋጠዉን ውጦ ማዶ ለሰፈሩት ብዙም ከክንዱ ያልራቁ ለኤርትራ መንግስት ሆነ ለግንቦት 7 ሊሂቃን ሌላ የቤት ስራ እንደሚሰጣቸው ለማየት ያብቃን ነው የሚባለው።

የአጋንንቱ ሃሳብ:

የአጋንንቱ ሃሳብ ሰዎቹ ለቀው መውጣታቸው ያልቀረ ኢየሱስን ከከተማ ሕዝብ ማጣላት ነው። ይህን ሴራቸው እውን የሚደርጉበት መንገድ ደግሞ መጣል ወደሚገባቸው ወደ ጥልቁ እንዲሁም ከከተማ ውጭ አርቆ እንዳይጥላቸው በመማጸን እንደምንም ብለው ወደ እሪያዎቹ የሚሄዱበት መንገድ በመፍጠር እሪያዎቹን በመግደል ኢየሱስ ከባለሀብቶቹ ማጣላት ነበር።

ኢየሱስ አጋንንቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀብሎ በማስተናገድ የፈቃዳቸው ማድረጉ ለጊዜው ባይገባኝም ኢየሱስ የለመኑትን ሰጣቸው። ይህን ተከትሎም የከተማዋ ሕዝብ ኢየሱስ አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድላቸው ጠየቁት። አጋንንቱ የሚፈልጉት ይህን ነበርና እውነትም አንደኛ ውጥናቸው ተሳካላቸው።

በእርግጥ ኢየሱስ ተሸውደዋል የሚል እምነት የለኝም። ኢህአዴግ በህግደፍ ድራማ እንደማይዘናጋ ግን እርግጠኛ ነኝ። “ልጅ እናትዋ ምጥ አስተማረች” አለች ያገሬ ሰው። ታየኝ እኮ ኢህአዴግ ሻእቢያ/ግንቦት 7 በሸረቡት ወጥመድ ተጠላልፎ ሲወድቅ። እንግዲያውስ እውነት የኮሶ መድሃኒት ያህል ብትመርና ብትከነክንም ሐቁ ኢህአዴግ ራሱን ጠልፎ ካልጣለ በስተቀር በዚህ አያያዛችሁ የዛሬ አርባ አመትም አትደርሱበትም።  እንግዲያውስ አሜን!” ባትልም ሐቁ ይህ ነው።

ዶክተር፤ ፕሮፌሰር … ተብለህ ስለተጠራህ አይደለም። ወደድክም ጠላህም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ እጅ ቁጥጥር ስር ነው። ሲፈልግ ጨርቅህን ጥለህ እስክታብድ ድረስ ያስጮኃል፤ ሲሻው ደግሞ በላይህ ላይ ትኩስ የመቃብር አፈር የተነሰነሰብህ ያህል አዚም ያደርግብሃል። “ከብት!” ብለህ ብትጠራውም ቅዠት የሆነብህ፡ ያቃተህ ፖለቲካ ግን ሰልጥኖበታል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመንድረስ በመሄድ በምድሪቱ ሕግ ሊያስጠይቀው የሚችል ድርጊት በመፈጸም ሆነ በአለም አቀፍ ስምምነት መሰረት በሁለትዮሽ አገራት በሚደረጉ ስምምነቶች አንድ ወንጀለኛ ወደ አገሩ መንግስት ተላልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ በመፍጠር  በእስር ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ዳግም በኢትዮጵያ ፖለቲካ “የፖለቲካ እስረኛ ተብሎ/እየተባለ” ስሙ ይነሳ፡ ይዘከርና ይወደስ ዘንድ ሃሳቡን ያመነጨ አምስት ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር ቢያቅተውም በአንጻሩ አገር ቁልቁል ለመድፋትና ሕዝብን ለመበተን ግን የሚስተካከለው የሌለው የሲኦል ፈላስፋ ኢሳይያስ አፈወርቂ ምክር እንደሆነስ ማን ያውቃል? ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ እንደሆኑስ ፍሬ አልባ በለስ ግለሰብ ቁጭ አድርገው የሚቀልቡ እስክመቼ ነው? በዚህ መልኩ ስራህ ያውጣህ ብሎው ይሽኙት እንጅ።

ያም ሆነ ይህ አንዳርጋቸው ጽጌ በየትኛውም መንገድ ማለትም የኤርትራ መንግስት ባሰላው ስሌት ይሁን ግንቦት 7 ይቀቅለው ሳያስበውም ቢሆን በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት እጅ መውደቁ የግለሰቡ ያበቃ ታሪክ ማረጋገጫ ማህተም ነው። የሚገላግለውም የለም። ግመሉ ይሔዳል ውሻው ይጮሃል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

July 5, 2014

Advertisements