“ኢትዮጵያዊነት” እና “አንድነት” ከሚለው ዘፈን ጀርባ ያለው ጸረ እኩልነት የነፍጥ ፖለቲካ ሲፈታ፡

 የጽሑፉ ዓላማ፥

“ኢትዮጵያዊነት” እና አንድነት” የሚሉ የማታለያ፣ መደለያና የማጭበርበሪያ ቋንቋዎች ጀርባ ያለው የትምክህተኞችና ግብዞች ጸረ እኩልነት አጀንዳ ለማራቆት ተጻፈ።

ሐተታ፥

ጻፎችና ፈሪሳውያን ማለት በአንደኛ ክፍለ ዘመን በግብዝነታቸው ተለይተው የሚታወቁ ጽንፈኛ የአይሁድ ክፍል ሲሆኑ ተራ ሰው በቀላሉ የማይደርስበት ነውራም ልምምድ ነበራቸው። ጻፎችና ፈሪሳውያን ውስጣቸው በክፋት የተሞሉ ደንቃራዎች ሆነው ሳሉ በውጭ ለሚያያቸው ሰው ግን እንደ እነርሱ ያለ ጻድቅና እውነተኛ ሰው የለም። መች ይሄ ብቻ ከአንደበታቸው የሚወጣ ቃልና ከመጋረጃ በስትጀርባ የሚሰሩት እኩይ ስራ ምንም የማይገናኝ አስመሳዮችም ናቸው። 

ጻፎችና ፈሪሳውያን መስጠት ሲያሻቸው መለከት ነፍተው የማስነፋት ልማድም ነበራቸው። ለምን? ይሉኝ ይሆናል። ጻፎችና ፈሪሳውያን ከተረፋቸው ለድሆች ሲወረውሩ፥ 

  • “ህይወት ማለት ያለህን ተካፍለህ መኖር ነው” የሚል ወንጌላዊ አመለካከት ስላላቸው፤
  • የሌለውን መርዳት ስለሚወዱ፤ 
  • ችግርና መከራ ለሚፈራረቅባት ነፍስ ማዘን ስላለባቸው፤ 
  • ለድሃ ስለሚቆረቆሩ፤
  • ድሃን የመርዳት መንፈሳዊ ግዴታ አለብን ብለው ስለሚያምኑ፤ 
  • በአጠቃላይ ስለ ድሆች ግድ ብሎአቸው ሳይሆን ሃይማኖታዊ ትምክህተኝነት ክፉኛ የተጸናወታቸው ተመጻዳቂዎች ስለነበሩ ምጽዋት ለመስጠት ጥሩምብ (መለከት) ያስነፉ ነው።

ከፍ ስል እንደገለጽኩት ጻፎችና ፈሪሳውያን መስጠት ሲያሻቸው መለከት ነፍተው የማስነፋት ልማድ ነበራቸው። ለምን? የሚለው ጥያቄ ላብራራ። ጻፎችና ፈሪሳውያን መስጠት ሲያሻቸው ለምን መለከት ነፍተው እንደሚያስነፉ ለሚጠይቃቸው አካል፡ “ነው እንዴ! እንዲህ ከሆነማ መለከት መንፋት ምን ችግር አለበት!” የሚያስብል ዓይናማ የሚያሳውር (የዋኁን ማህበረሰብ በቀላሉ የሚያሳምን) እውነት የሚመስል ዳሩ ግን ማደናጋሪያ መልስ አላቸው። ይኸውም፥ “የሚነፋው መለከት” ይላሉ “ድሆች የመለከት ድምጽ ሰምተው ይሰበሰቡ ዘንድ ነው” የሚል መልስ ይሰጣሉ። ሐቁ ግን ይህ ሳይሆን ጸሐፍት ፈሪሳውያን መስጠት ሲያሻቸው መለከት ነፍተው የሚያስነፉበት ምሥጢር ሌላ ነው።

የጻፎችና ፈሪሳውያን መንፈሳዊ ህይወታቸው በተመለከተ እጅግ ሃይማኖተኞች፣ ጽንፈኛና ግብዝነት የተሞላበት የታይታ ህይወት ነው ብለንናል። መንፈሳውያን ተብለው በሰዎች አንደበት ዘንድ ይወደሱና የሰው ትኩረት ለመሳብ ያደርጓቸው ከነበሩ እንቅስቃሴዎች መካከል በጥቂቱ ያየን እንደሆነ ሲጸልዩ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን፤ ሲጾሙም እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፉና ያጠወልጉ ነበር። ሲመጸውቱ ነፍተው የሚያስነፍዋት መለከትም ድሃ ይሰበሰብ ዘንድ አስበው ሳይሆን ውስጠ ወይራው መስጠታቸው ሰው ያይላቸው ዘንድ ነበር“እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” እንዲል [ማቴ. 6፥ 2]።

ታድያ ይህ ምሥጢር ኢየሱስ ዓይንዎን ካልከፈተሎት/ካልገለጠሎት በስተቀር ሁለት ዓይን ስላሎት፤ ወይም እንደ “ማኅበረ ቅዱሳን” የኮሌጅ ዲግሪ ስለጫኑ ብቻ እንዲሁ በቀላሉ የሚያዩት አይደለም። የጻፎችና ፈሪሳውያን ምንነት ለማወቅና ለመረዳት መንፈሳዊ ዓይን፣ ሰማያዊ መገለጥና መንፈሳዊ ብስለት ያስፈልጋል፤ ይጠይቃልም። ይህ “መንፈሳዊ” የሚመስል ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ፊት እጅግ የተናቀና የተዋረዳ የጻፎችና ፈሪሳውያን አሳፊሪ ልምምድና ግብዝነት የተሞላበት ርካሽ ህይወት ሁሉም በቀላሉ በግልጽ የሚያየው ድርጊት እንዳይደለ ሁሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ “በኢትዮጵያዊነት” እና “በአንድነት” ስም የሚደለቀው ከበሮና የሚመታው ዳንኬራ ጀርባ የብሔር ብሔረቦችና የሕዝቦች መብት በመጨፍለቅ የአንድ ብሔር የበላይነት መልሶ የመገንባት አጀንዳ “ተራ” ዜጎች (ብዙሐኑ ለማለት ተፈልጎ ነው) በቀላሉ ሊያዩትና ሊገነዘቡት የሚችሉት አይደለም። 

“ኢትዮጵያዊነት!”፣ “አንድነት!” … ከሚሉ መፈክሮች ጀርባ ያለው “እንቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው” የነፍጠኞች ጸረ እኩልነትና ጨፍላቂ የደም ፖለቲካ ለማወቅ በዋናነት ከስሜት የጸዳበእውቀት የታጠቀምክንያታዊበማንነት ቀውስ ያልተጠቃበራስ መተማመን ብሎም ቆራጥ ስብእና ይጠይቃል። 

“ኢትዮጵያዊነት”፣ “አንድነት” … የሚሉ ቋንቋዎች “ፎልስ ፍላግ” ናቸው!

ፎልስ ፍላግ፥ መርፌ የሌላት (ያልተገኘባት) አገር “ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ አላት” ብሎ ዓለምን በፕሮፖጋንዳ ብዛት ማደናገር፣ ማሳመንና ቀጥሎም የሰው አገር አውድመህ የምትፈልገውን መግበስበስ ነው። ጎበዝ! ኢትዮጵያዊነት የተቃወመ፤ አንድነትንም የሚጠላ ዜጋ የለም። ቢከፋንም ቢለማንም፣ ቢመቸንም ባይመቸንም፣ ብናምንበትም ባናምንበትም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩነት ተጠቃሚ የሚሆኑባት ኢትዮጵያ እንደ አገር እስካለች ድረስ ሁላችን ኢትዮጵያውያን ነን። አይደለም ዛሬ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሙሉ መብትና ስልጣን ኖሯቸው ባህላቸው መግለጽ፣ በቋንቋቸው መማርና ማስተማር፣ ብሎም ራሳቸውን የማስተዳደር ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ትናንት በደርግና በጃንሆይ ጊዜ አባቶቻችን የልጆቻቸው ሬሳ መንገድ ለመንገድ እየተጎተተና ማኸል አደባባይ እንደ ብቅል ተዘርግቶ እያዩም ኢትዮጵያዊነትን አልተቃወሙም። ኢትዮጵያዊነት የተቃወመ ማንም የለም። በውኑ ጋንጩር ካልሆነ በስተቀርስ አንድነት የሚቃወም ሰው ማን ነው? 

ስለ ኢትዮጵያዊነት ስጽፍና ስናገር ኢትዮጵያዊነት አልያም አንድነትን እየተቃወምኩ ሳይሆን “በኢትዮጵያዊነት” “በአንድነት” ስም ተደበቀው የውሸት ባንዴራ እያውለበለቡ ንግዳቸው እያጧጧፉ ያሉ የአገርና የትውልድ ነቀርሳዎች መግለጤ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይል ዘንድ ይገባል። 

  • ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያን “ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ” ሲል እንደገለጻቸው፥ ሐቁ የኢትዮጵያ ባንዴራ አሰፍተህ ስለ ለበስክ፤ “ኢትዮጵያ ሀገሬ! ኢትዮጵያ መቃብሬ! … አንድነት! ምናምን ” እያልክ እንባ እየተናነቀህ ሰለዘፈንክና ስለአቀነቀንክ አይደለም። በአይሁድ ባህል ሰውን አቅፈህ መሳም የፍቅር ምልክት ነው። ይሁዳ ኢየሱስን አቅፎ ሲስመው ግን ፍቅሩን መግለጹ ሳይሆን ሊይዙት ለመጡት ሰዎች መጠቆሙ ነበር። 

ኢትዮጵያዊነት/አንድነት አይደለም ችግሩ። ችግሩ “ኢትዮጵያዊነት/አንድነት” ከሚል ጩኸትና ዘፈን ጀርባ የተደበቁ ግብዞችና አስመሳዮች፤ የሰው ደም ጠጥቶው ያልጠገቡ/ያልረኩ፤ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ሥልጣን ገፈው የአንድ ብሔር የበላይነት የማንገስ ክፉ በሽታ የተጸናወታቸው ጸረ እኩልነት አጀንዳ ያነገቱ ሊሂቃን እንደሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። 

ታድያ እነዚህ ሊሂቃን የሚፈልጉት ለማግኘት ዓይናቸው አፍጥጠው ጥርሳቸው አግጥጠው አይመጡም። ጻፎችና ፈሪሳውያን ምን ይመስሉ እንደ ነበሩ ኢየሱስን ቢጠይቁት “በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮች” ይመስላሉ የሚል ቅልብጭ ያለች መልስ ያገኛሉ። የእኛዎቹም በተመሳሳይ ብዙሐኑ በቀላሉ ለመደለል ያስችላቸው ዘንድ “ኢትዮጵያዊነት!” “አንድነት!” … ወዘተ በሚሉ ማለፊያ መፈክሮች ራሳቸውን ደብቁ እንጅ ውስጣቸው ጸረ አንድነትና እኩልነት ጨፍላቂ መንግሥት ለማቆም ያደቡ መራራዎችና የጥፋት ኃይሎች ናቸው። ወጣም ወረደ “ኢትዮጵያዊነት”፣ “አንድነት” … ወዘተ የሚሉ ቋንቋዎች ‘ፎልስ ፍላግ’ ለመሆናቸው ለአፍታ የሚጠራጠር ዜጋ ሊኖር አይገባም።

  • ጡት ያልተወ ህጻን ልጅህ አቡ ወለድ ቡስኩት ወይም ደስታ ከረሜላ ሰጥተህ ታባብለው፣ ታታልለውና ታስተኛው ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ግን “በኢትዮጵያዊነት” እና “በአንድነት” ስም የምታማልለው፣ የምትደልለው ብሎም የምታደማው፣ የምትልጠውና የምትግጠው ዜጋ የለም፤ አይኖርምም። ተነቃቅተናል። “ኢትዮጵያዊነትና አንድነት” እኔንና የአባቴን ቤት የሚያጠፋ፣ የሚያፈርስና የሚያወድም ከሆነ እኔና ወገኔ በህይወት የምንኖርበት፣ የአባቴ ቤት ታሪክና የአባቶቻችን አጥንት ያረፈበትን መሬት በክብር የምንጠብቅበት ሌላ መንገድ እንጠርጋለን።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com 

April 4, 2014 

Advertisements