ይድረስ ለኤልያስ ክፍሌ፥ … ስለ ምን ትመታኛለህ?

ኦሬንጅ ካውንቲ፡ ካሊፎርኒያ

March 20, 2013

ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየስስም መልሶ፦ እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ አለው። ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ። ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን? ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ፦ ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ስለ ምን ትመታኛለህ? አለው [የዮሐንስ ወንጌል  18፥ 19 – 23]። 

ወንድም ኤልያስ፥ ጽሑፎቼ በድረ ገጽህ እንዳይስተናገዱ የወሰንከው ውሳኔ በእርግጥ ጽሑፎቼ በሚገባ ተመልክተሃቸው ከሆነ ይህን ደብዳቤ በአማርኛ ጽፌልሃለሁ። 

ወንድም አለም ኤልያስ፥ የእኔ ጽሑፎች በድረ ገጽህ ላይ እንዳታስተናግድ በቀንም በሌሊትም የሚወተውቱህ፣ ሰላምህን የሚነሱና በተለያየ መልኩ ግፊትና ጫና የሚያደርጉብህ ግለሰቦች ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እኔ አንደ አንድ ግለሰብ ሞራላዊ መብቴን ተጠቅሜ የማምነው በጽሑፍ ለመግለጽ እንደቻልኩ ሁሉ ለንባብ በበቃ ጽሑፍ ላይ ተቃውሞ ያላቸው አካላት ደግሞ ተቃውሞአቸው በጽሑፍ መግለጽ አይችሉም ብለህ ታምናለህ? ምን የሚሉት ጥፋት ብታገኝብኝ ይሆን ሃሳቤን በነጻነት እንዳላካፍል እገዳ የጣልክብኝ? የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሮአዊ ነው። በዜጎች መካከል የሃሳብ ልዩነት ሲፈጠር ደግሞ ልዩነቶች በእኩልነት በማስተናገድና እኩል መድረክ በመስጠት በቀላሉ መፍታት የሚቻለው ችግር ሆኖ ሳለ እኔን ማፈን መፍትሔ ነው ብለህ ታምናለህ? በእውነቱ ነገር በምዕራቡ ዓለም እንደተማረ ሰው እኔን ከማገድ ይልቅ “የሙሉጌታ ጽሑፍ ስህተት ነው ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ ስህተቱን ነቅሳችሁ በማውጣት ‘እውነቱ ይህ ነው!’ ስትሉ ሃሳባችሁ በጽሑፍ ግለጹ” ማለት አይቀልህም ነበር? ለአእምሮ የሚመች፤ በታማኝነት አገርና ሕዝብ ማገልገል ይሉት ይህ ነውና።

ወዳጄ ኤልያስ! እኔስ ብሆን ከሰው ጋር የሚያላትም ጽሑፍ መጻፍ ወድጄ መስሎህ ይሆንን? የለም! ምን ሊበጀኝ?!  የምጽፈው ኑሮዬን ለመደጎም፣ ከመቃብር ለማያልፍ ስም – ወንዝ ለማያሻግር ዝና ሳይሆን ሕዝቤንና አገሬን በቅንነት፣ በእውነትና በጽድቅ የማገልገል ግዴታ አለብኝ ብዬ ስለማምን ነው። ታድያ እውነቱን እውነት ሐሰቱን ደግሞ ሐሰት ከማለት ውጭ ማንንም የማጥቃት ተልዕኮ የለኝም። መጻፌ ካልቀረ ደግሞ ህዝብን አርነት የሚያወጣ ተለዋጭ የሌለው አንድ እውነት ብቻ ነው የሚል ጽኑ እምነት ስላለኝና እውነቱን መናገሬና መጻፌ ነው እንጅ ሌላ ምክንያት ኖረኝ አይደለም። የምጽፈው ለራሴና ለህሊናዬ ነው። ሰውን አገለግል ወይም ደስ አሰኝ ዘንድ ብዕሬን ያነሳሁበት ዕለት የለኝም። ከጀርባዬ ስላለው አካል ማወቅ የፈለግ እንደሆነም ከጀርባዬ ያለ ሌላ ማንም ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ነው። ‘አለመታደል’ ሆኖ ግን ኢትዮጵያውያን ስንባል የሌላ ሰው ሃሳብና እምነት በልዩነት የመቀበል ባህል ‘ስላልፈጠረብን’ የሌላ ሰው እምነት ሳይጥመን የቀረ እንደሆነ በልዩነት ከማመን ይልቅ የምንሮጠው ስም ወደ መለጠፍና በጠላትነት ዓይን ማየት ስለሚቀናን ይሄው ለመታገድ በቃሁ። 

ወንድም ኤልያስ ሆይ! “ኢየሱስም መልሶ ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ስለ ምን ትመታኛለህ? አለው”  [ትመታኛለህ = ታግደኛለህ] ከሚለው ቃል ስተውህ በአክብሮት ነው።

አክባሪህ 

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Advertisements