“ኢትዮጵያዊነት” ማንነት ሳይሆን ዜጎች በህግ የሚጎናጸፉት ማሊያ ነው!

በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ የምትባል በህግ የታወቀች የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት የተረጋገጠባት ህብረ ብሔር አገር እስካለች ድረስ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በዜግነት “ኢትዮጵያዊ” አይደለሁም የሚል ግለሰብ ይኖራል ብዬ አላምንም። “ኢትዮጵያዊ” አይደለሁም የሚል የኢትዮጵያ ክልሎች ተወላጅ ግለሰብ ገጥሞኝ አያውቅም። [የብሔር ጥያቄ ያለው ዜጋ የለም አላልኩም] ይህ ከሆነ ዘንዳ ዜጎች ስለ ማንነታቸው በተናገሩና በጻፉ ቁጥር በጸረ “ኢትዮጵያዊነት” እና ጸረ “አንድነት” የመፈረጁ ጉዳይ ህጋዊ ሆነ ፖለቲካዊ ጭብጥ የሌለው ተራ ስም የማጥፋት ውንጀላ ከመሆኑ ያዘለለ እውነትነት የሌለው የተለመደ መሰረተ ቢስ ክስ መሆኑ አንባቢ ልብ ይለው ዘንድ እወዳለሁ። 

የአንበሳ ድርሻ ያላቸው ይመስል ስለ ማንነት በተነገረና በተጻፈ ቁጥር ጸጉራቸው የሚነጩ ዜጎች በተመለከተ ግለሰቦቹ ከተራ ስድብና የተካኑበት ስም የማጥፋት ዘመቻ ያለፈ ምክንያታቸው ከጭብጥ ጋር አስደግፈው ለመቅረብ ባይሞክሯትም በበኩሌ ስለ ማንነት መናገርና መጻፍ “ኢትዮጵያዊነት” ማቃለል ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት መተርጎም መሆኑን አስረግጬ ለመናገር እወዳለሁ። በተጨማሪ ስለ ማንነት መናገር ሆነ መጻፍ ከአገሩቱ ምስረታ ጀምሮ መልኩን እየለዋወጠ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የዘለቀው ችግር መፍትሔ ከመሆኑ አልፎ እንደ ችግር የሚታይበት ምክንያትም አይታየኝም። 

ኢትዮጵያዊነት Vs. ማንነት፡

ራሱ የቻለ፤ “እኔ” ማለት የሚችል፤ በራሱ የቆመ፤ ህልውና ያለው፤ ማንነቱ የሚገልጽበት የራሱ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሥልጣኔ፣ አስተሳሰብና ሥነ ልቦና ያለው “ኢትዮጵያዊ” የሚባል አንድ ሕዝብ ሆነ ማኅበረሰብ እንደሌለ ለሁላችን ግልጽ ነው። ይህ ከሆነ ዘንዳ አንባቢ  የቀረችው ጆከር “ኢትዮያዊነት” እንዲሁም “ማንነት” የሚሉ መሰረታዊ ሃሳቦች መካከል ያለው መጠነ ሰፊ ልዩነት የጠራ ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ ለጊዜው አምስት አንኳር ነጥቦች ላስቀምጥ። 

  • አንድ፡ “ኢትዮጵያዊነት” የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድምር ውጤት የሆነችው ሉዓላዊት አገር ኢትዮጵያ ሥር የተጠለሉ ሕዝቦች የጋራ ስምምነት ላይ የተመስረተ የሚለበስ ማሊያ ሲሆን ማንነት ደግሞ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተናጠል “እኔ” የሚሉበት መሉ መብትና ሥልጣን የሚያረጋግጥ ደም ነው። [በነገራችን ላይ “ደም” ሲባል የአንድ ሕዝብ/ብሔር ሁለመና ሥነ ልቦናዊ መገለጫ የሚያመላክት እንጅ ቀይ ቀለም የሰውነት ፈሳሽ ማለቴ እንዳይደለ ግለጽ ነው ብዬ አምናለሁ።] 
  • ሁለት፡ኢትዮጵያዊነት”፥ የህዝብ ውክልና ያለው፣ በህግ ከቆመው መንግሥት ሥር የሚተዳደረው የሀሪትዋ የግዛት ወሰን ውስጥ የሚኖረው ህዝብ በዜግነቱ የሚጎናጽፈው፤ አንድ ዜጋ በህግ ከለላ ሥር የሚያገኘው ጥቅማ ጥቅም ወይም ህጋዊ መብት የሚያረጋግጥ እንጅ ማንነትህ (ትግራወይነትህ፣ ኦሮሞነትህ፣ አማራነትህ … ወዘተ) ተፍቆ ወይም ጥለህና ሽጠህ አዲስ “ኢትዮጵያዊ” የሚባል ማኪያቶ ወይም “ቅይጥ ማንነት” መያዝ አልያም መላበስ ማለት አይደለም። ጥጉ፥ “ኢትዮጵያዊነት” ማንነት ሳይሆን ዜጎች በህግ የሚጎናጽፉት ማሊያ ነው። 
  • ሦስት፡ ማንነት ደብቀህ የምትደብቀው፤ ሲሞቅህ የምትጥለው – ሲበርድህ የምትደርበው፤ ገበያ አውርደህ የምትሸጠውና ምትለውጠው ማሊያ ሳይሆን ማንነት ደም ነው። ስለሆነም “ኢትዮጵያዊነት” ማሊያ ሲሆን ማንነት ደግሞ ደም ነው። ማሊያ ሲባል እንግዲህ የሚጠለቅ ልብስ እንጅ ጀርባ ላይ የሚሰፋ ላለመሆኑ ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ።
  • አራት፡ “ኢትዮጵያዊነት” የሕዝቦች በጎ ገቃድ (ምርጫ) ላይ የተመሰረተ ከ እስከ ተብሎ በጊዜ ገደብ ውስጥ የሚወሰን ሲሆን ማንነት ደግሞ ወደድክም ጠላህም እየከነከነህም ቢሆን እየቀረቆረህ አብሮህ የተወለደው እስከ መቃብር ድረስ አብሮህ የሚዘልቀው እሳት የማይበላው፣ ወንዝ የማያበሰብሰው የህልውናህ መገለጫ ነው።
  • አምስት፡ ማንነት ፍቀህ የማታጠፋው ቀጥቅጠህ የማትሰራው አንተነትህ ሲሆን “ኢትዮጵያዊነት” ደግሞ በጊዜ ውስጥ የምትደርበውና የምታወልቀው ካባ ነው። ላለፉት ሃያ ዓመታት ኤርትራዊ ብሎ ኢትዮጵያዊ የለም። ይህ ማለት ግን ኤርትራ የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት አልነበረችም ማለት አይደለም። ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት በነበረችው ጊዜ የኤርትራ ክፍለ ግዛት ተወላጅ በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ተብሎ ነበር የሚታወቀው እ.አ.አ ከ1993 ዓም ወዲህ ግን ኢትዮጵያዊነት ጀርባህ ላይ የሚሰፋ አይደለምናየኤርትራ ሕዝብ ባደረግ ድምጸ ውሳኔ [99.79%] ጉዳዩ “ነበር” ተብሎ የሚወራ ታሪክ ብቻ ሆኖ ቀርተዋል። ኤርትራ ከሃያ ዓመታት በፊት በምርጫዋ አውልቃው የሄደችው ካባ ኑሮ መሯት ወይም በርዷት የተመለሰች እንደሆነ ደግሞ እንደርብላታለን። 
  • ስድስት፡ “ኢትዮጵያዊት” የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች “በህብረት/በአንድነት” እስካሉ ደረስ የሚኖር ጊዜያዊ ሲሆን ማንነት ደግሞ ሕዝቦች የሄዱበት ድረስ የሚከተላቸው ከሌሎች ተለይተው የሚታወቁበት ልዩ መታወቂያቸው ነው። ኤርትራ ወደ ፊት ስትፈለቀቅ “ኢትዮጵያዊነት” እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ ከቀሩት ጋር ቀረ እንጅ ኤርትራን ተከትሎ አልሄደም፤ አልተከተላትም። 

ካርቦን ኮፒ ለመሆንህ አላፊው አግዳሚው ወጪ ወራጁ ይመሰክርብሃል፡

ከየትም ተወልድ ከየት የሚያሳፍር ሆነ የሚያኮራ ማንነት የለም። ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከደቡብ … ወዘተ በመወለዱ የሚቆረቁሮው፣ የሚያበሳጨውና እንቅልፍ የሚነሳው ሰው ካለ ራሱን ፈልጎ እስከያገኝ ድረስ ይህን መልዕክት አይመለከተውም። በተረፈ ግን ወድህም ተወለድ ተገደህ፤ በማንነትህ አንተ አንተ ነህ። በማንነትህ አንተ ራስህ ከመሆን አልፈ ሌላ ልትሆን አትችልም። አንተነትህ/ማንነትህ ትተህ ሌላውን ለመምሰል ትሞክር ይሆናል ታድያ አሁንም ቢሆን ግን አንተነትህ/ማንነትህ ደብቀህ የምትደብቀው እንዳይደለ ግልጽ ሊሆን ይገባል። 

ያገሬ ሰው ሲተርት “የደብተራ ሚስት አወቅሽ አወቅሽ ሲሉዋት መጽሃፍ አጠበች” እንዲል ማንነት – በአለባበስ፣ የሌላውን ማኅበረሰብ ቋንቋና ሥልጣኔ በመጋራትና በማነብነብ እንዲሁም ቅብ ቀባብተህና ሸላልመህ የምትሸውደው ዓይነት ነገር ሳይሆን ራስህን በመስተዋት የማየት ያክል ግልጽ ነው። ሥልጣኔ፣ ዕድገት፣ አሪፍነትና ሊቅነት መስሎህም የራስህ ትተህና ጥለህ ሌላውን ለመምሰል በምታደርገው ጥረት ገፋ ቢል ራስን ታታልል እንደሆነ ነው እንጅ የራስህ ያልኸነው ነገር ተሸክመህ ስትንገዳገድ፣ ጉራህን ስትቀድና ስትጃጃል ከሩቅ ትታወቃለህ። ካርቦን ኮፒ ለመሆንህ አላፊው አግዳሚው ወጪ ወራጁ ሁሉ ይመሰክርብሃል። 

በምሳሌ ላስረዳ፥ ሰዎች ዘመናዊ (አሪፍ) ለመምሰል ብዙ ሊጥሩ ይስተዋላሉ። ታድያ አሪፍ ለመምሰል በሚያደርጉት ጥረት ኩልል ብሎ የሚታየው ዘመናዊ (አሪፍ) መሆናቸው ሳይሆን ጥሬነታቸው ነው። ማንነትህ ጥለህ ሌላውን ለመምሰል በምታደርገው ጥረት ሁሉ የሆንክ ቢመስልህም ለመሆን የምታልመው አካል ግን ከራሱ ወገን እንዳይደልህ መንጥሮ ለማውጣት አጉሊ መነጽር ሆነ ዳኛ አያስፈልገውም። ጎበዝ! አስመሰልክና ነህ ማለት እኮ አይደለም። መሆንና መምሰል ለየቅል ናቸው። ስለ መሆን ስንነጋገር አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ሆነ ነገር ነው እየተነጋገርን ያለነው። ማንነት ማለት ይህ ነውና። ፍቀህ ስለማታጠፋው ቀጥቅጠህ ስለማትሰራው መገለጫ። 

የራስህ ያልሆነ ማንነት ገንዘብ ለማድረግ መቋመጥ በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ባይሆንም አሳፋሪ ድርጊት ለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም። በዚህ አጋጣሚ ማንነትህ መጣል፣ መዘንጋትና ማቃለል ዘመናዊነት፣ ዕድገት ወይም ሥልጣኔ ሳይሆን ዝቅጠት፣ ውርደትና ባርነት መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ። ያልሆንከውን ለመሆን ማስመሰል አይጠበቅብም፤ አይደለህም። ምን አለፋህ?! 

በመጨረሻ፥ ህዝብ ካልተመቸውና እንደ አንድ ራሱ የቻለ ህዝብና አገር ራሱን ችሎ ለመቆም ምክንያታዊ እስከ ሆነ ድረስ ህጋዊ መንገድ ተከትሎ እንደ ሀገር መቆም ይችላል። አንድ ግለሰብ “ማንነቴ ደበረኝ” ማለት ከደረሰ ግን ከድብርቱ ይላቀቅ ዘንድ አቋራጩ መንገድ ሁላችን የምስተው አይመስለኝ። ስለሆነም መጽሐፍ “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው” እንዲል በየትኛውም መመዘኛ የሚያሳፍር ሆነ የሚያኮራ ማንነት እንደሌለ ተገንዝበን በማንነታችን ሳንሸማቀቅ በሰላም እንድንኖር ይመከራል።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 29, 2013 

Advertisements