የሒሳብ አያያዝ ባለሞያ የለም ወይ ባገሩ? (በለንደን ለምትገኝ ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አባላት)

ልደቴም ዕድገቴም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በቤተ ክርስትያን ነው። በሀገሬ ሳለሁ በልጅነት ጊዜ በክህነት አገለግልባት የነበርኩት ቤተ ክርስትያን ራሱ “ማኅበረ ቅዱሳን” ብሎ የሚጠራ የጥቁር ራስ ስብስብ ሰለፊያ ሰርጎ ገብነት (በምዕራቡ ዓለም እንደምንሰማውና እንደምናየው ባይሆንም) በመጠኑም ቢሆን “በማኅበረ ቅዱሳን” አብያተ ክርስትያናት የማተረማመስ መሰሪ አጀንዳ ይታመሱ ከነበሩ አብያተ ክርስትያናት መካከል አንዷ ነበረች። 

አንድ ዘወትር የማልረሳውና ትዝ የሚለኝ ነገር ቢኖር እሁድ በመጣ ቁጥር ከቅዳሴ በኋላ ዓውደ ምህረት ላይ የሚደረገው አጠቃላይ የካህናትና የምእመናን ስብሰባ ነው። አንደኛው ችግር ፈጣሪ በዕድሜአቸው የገፉ (ከ50ና ከ60 በላይ የሆናቸው) ግለሰቦች ነበሩ። እስከማውቀው ድረስ እነዚህ ሰዎች ሁሉም ማለት ይቻላል የደርግና የጃንሆይ ጡረተኞች ወይም ሹሞች ሲሆኑ ገሚሰቹ ደግሞ የናጠጡ ከበርቴዎች ነበሩ። እነዚህ ግለሰቦች ሰበብ አስባብ እየፈለጉ ይፈጥሩት የነበረው  ነውጥ፣ ሁከትና ግርግር እንደ ምክንያት ያቀርቡት የነበረው “የአስተዳደር ችግር አለ” በሚል ሽፋን ነበር። በነገራችን ላይ በካህናቶቹ በኩል ይህ ነው የሚባል የጎላ ችግር ኖሮ ሳይሆን ግለሰቦቹ ግን ነገር የማራገብ ክፉ አመል ነበራቸው። የእነዚህ ግለሰቦች “የአስተዳደር ችግር አለ” በሚል ሽፋን ይፈጥሩት የነበረው ችግር ምስጢሩ፥ 

  • አንደኛ፡ እነዚህ ግለሰቦች በጡረታ ከመገለላቸው በፊት ረጅም ዘመናቸው ያሳለፉት ከስራቸው የሚገኝ ሰው ማዘዝና በከፍተኛ የውትድርና የሥልጣን እርከን የነበሩ ከመሆናቸው የተነሳ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡም ካህናቶቹ ሳይቀሩ እጥፍ ዝርግት ብለው ይሰግዱላቸው ዘንድ የሚወዱ፤
  • ሁለተኛ፡ ከላይ ከፍ ሲል በተመለከትነው ነጥብ በተያያዘ እነዚህ ችግር ፈጣሪ ግለሰቦች በምዕመናን መካከል የክብር ስፍራ ይሰጣቸውና ልዩ እንክብካቤ ይደረግላቸው ዘንድ የሚባዝኑ፤ 
  • ሦስተኛ፡ በሰበካ ጉባኤ ተመራጭ ሆነው ቤተ ክርስትያን በወታደራዊ አሰራር ለመዘወርና የግላቸው ለማድረግ የሚቃጣቸው፤
  • አራተኛ፡ እነሱ ያልተካፈሉበት ማንኛውም ዓይነት የቤተ ክርስትያኒቱ አገልግሎትና ስራዎች ስለማይዋጥላቸው፤ 
  • አምስተኛ፡ ምእመኑ እነሱን ሲያይ በመንቀጥቀጥ ጎንበስ ብሎ እጅ በመንሳት እንዲያሳልፋቸው መፈለጋቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ከሁሉ የከፋው ግን እግዚአብሔር ለማምለክ የሚመጣ ህዝብ እነዚህ ግለሰቦች “የእገሌ የልጅ ልጅ!”፤ በተጨማሪም የቀድሞ ማዕረጋቸውና ስልጣናቸው እያስታወሰና እያሰበ ተጨማሪ አምልኮ ያቀርብላቸው ዘንድ የሚቋምጡ ግለሰቦች ስለ ቤተ ክርስትያንና ስለ ምእመናን “መጨነቃቸው” በሚመስል አቀራረብ “የአስተዳደር ችግር አለ” በሚል ሽፋን አቧራ ያስነሱ እንደ ነበር በሚገባ አስታውሳለሁ። 

ሌላኛው ችግር ፈጣሪ ቡድን ደግሞ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በክህነት አገልግሎት ተሰማርተው በእግዚአብሔር ሕዝብ ፊት መሻገር ባለመቻላቸው የማጉረምረም ህይወት የሚመሩ “ማኅበረ ቅዱሳን” መክሮ፣ በክፋትና በትንኮል አጥምቆና አመጻን አስታጥቆ ያሰማራቸው የነበሩ ማይክራፎን ናፋቂዎች የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ናቸው። አመራሩ የተቆጣጠሩት በአብላጫ የመንግሥት ሰራተኞች ሲሆኑ ሁሉም “የማኅበረ ቅዱሳን” አባላት የነበሩ ናቸው። 

እንግዲህ ይደረጉ በነበሩ ስብሰባዎች እነዚህ ግለሰቦች እንወክለዋለን የሚሉት ሰንበት ትምህርት ቤት ወክለው ይናገሩ ዘንድ በሚሰጣቸው ዕድል ተጠቅመው ካህናትን ማሯሯጥ፣ ከአለቃ ጋር መሟገት፣ በአጠቃላይ ብዙ ህዝብ በተገኘበት በቤተ ክርስትያን ዓወደ ምህረት ማይክራፎን ይዘው “ዘራፍ!” ማለት ያምርባቸው ነበር ብቻ ሳይሆን ይፈጥርላቸው የነበረ ደስታ ራሱ መጨረሻ አልነበረውምና በሃሜት ጎዳና ተሰማርተው ነገርን ማቀጣጠል የዕለት ዕለት ስራቸው ነበር። እውነት ለመናገር ለሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ከዚህ በላይ አገልግሎት፤ ከዚህ በላይ ደስታ አልነበረምና በተሰበሰበው ህዝብ ፊት ካህናትን መዘንጠልና መወረፍ ጀብድነት ነበር። የልብ ልብ እየተሰማቸው ይህን ሲያደርጉም በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅን የማስቆጠር/ያስቆጠሩ ያህል እጅግ ይደሰቱ ነበር።

ታድያ በቀኝ ጡረተኞችና የመኳንንት የልጅ ልጆች – በግራ በኩል “የማኅበረ ቅዱሳን” ታጣቂዎች ተሰልፈው በቤተ ክርስቲያኒቱና በካህናቶችዋ ላይ የከፈቱት ዘመቻ ብዙሐኑ ምእመን የወጠጤዎቹ ኩርፍያና መንጣጠት፤ የእነ መቶ አለቃና የእነ ሻለቃ እንዲሁም የእነ ደጃ ዝማች የልጅ ልጅ ጭብጥ አልባ ክስና ተራ ውንጀላ ውስጠ ሚስጢሩ ጠንቅቆ ያውቅ ስለ ነበር የጥቂቶቹ ጩኸት የቁራ ጩኸት ከመሆኑ አልፎ ይህ ነው የሚባል አደጋ ሳያደርስ መክሸፉን አስታውሳለሁ።

ማን መጥቶ ይዳኛችሁ ዘንድ ነው የምትፈልጉ?

በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን እየሆነ ያለው ሁከትና መበጣበጥ ያልሰማና የማያውቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ተከታይ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። ሰዎቹ ገንዘባቸውም ህንጻቸውም ፍሪዝ ካደረገ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው። ችግሮቻቸውም የፖለቲካ ችግር እንጅ የቤተ ክርስትያን አስተዳደር ሆነ መንፈሳዊ ችግር እንዳይደለ ከዓመታት በኋላ አሁን በግልጽ በአደባባይ በሚወጡ ጽሑፎች እያነበብን ነው። ነገሩ እንዲህ ከሆነ “ሰዎቹ ማን መጥቶ እንዲዳኛቸው ነው የሚጠብቁ?” አላሉም ውድ አንባቢ።

ማን መጥቶ እንዲዳኛችሁ ነው የምትፈልጉ? ማን በማሃከላችሁ እንዲገኝ ነው የምትሹ? ቤተ ክርስትያን እንዳይባል ዳኛም ሆነ ራስ የላችሁ? መንፈሳውያን በማሃከላችሁ ተንኝተው “ችግራችሁ ምንድ ነው?” ብለው እንዳያደምጥኋችሁ ችግራችን ፖለቲካ ነው አላችሁ። ለነገሩ ቀድሞውኑ ለመንፈሳዊ ስልጣን ስትገዙ አይደል። ኧረ ማንን ነው የምትጠብቁ? ክርስቶስ ሳምራ? እግዚአብሔርማ እንዲያ ያለ ቀልድ መች ይገባዋል። መላዕክቶቹን ስራ አስፈትቶ ከእናንተ ጋር የሚጨቃጨቅበት ምክንያት የለው፤ በቅድሳት መጻህፍት አልተጻፈማ። ችግር በተነሳ ቁጥር የለመዳችሁት ፌርማ ማሰባሰብ አይደል? ‘ፔተሽን’ አዘጋጁና ክርስቶስ ሳምራ ትዳናችሁ ዘንድ ስምታችሁ ግጥም አድርጋችሁ ጽፋችሁ በኢሳት በኩል ላኩላት። እስከ አሁን ድረስ ይህን ሳታደርጉ የዘገያችሁበት ምክንያት ራሱ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው። 

ልታፍሩ ይገባችኋል። ሰው ሰርቶ መኖር በሚችልበት አገር ተቀምጣችሁ በእግዚአብሔር ስም የሚሰበሰብ ገንዘብ ለመብላት ከሆነ እንዲህ የሚያተረማምሳችሁ በእውነቱ ነገር ምን ያደርግላችኋል? በእግዚአብሔር ስም ወደሚሰበሰብ ገንዘብ ካዝና እጃችሁ በሰደዳችሁ ቁጥር ወደ ሆስፒታል እግር ነው የምታበዙ። ለመሆኑ ምን የሚሉት ፖለቲካ ነው የሚያጣላችሁ? ቤተ ክርስትያን የጸሎት ቤት እንጅ የደም አይደለች። “ልፋ ያለው መጫኛ ይጎትታል” ነው የሚባለው እንደው ለነገሩ ነው እንጅ ከእናንተ በላይ “አዋቂ” ማን ቢኖር ነው? ይህን ሁሉ የምለው። ቃሉ በተነገረ ቁጥር “ዘራፍ እኔ የጃንሆይ ዘመድ! ዘራፍ የደርግ ጄነራል! ዘራፍ! ዘራፍ!” እንደሚያስብላችሁ እያወቅኩ ለእናንተ መልዕክት ማካፈሌ እኔ እብሳለሁ። የእግዚአብሔር ቃል ምን ያድርግላችኋል? የሰማችሁት ቃል ለህይወት ካልሆናችሁ ምን ይበጃችኋል? በእሾህ መካከል እንደ መዝራት ነው። 

አንድ ነገር በፍቅር ልማጸናችሁ፥ የእግዚአብሔር ስም በእናንተ የግብር ይውጣ ስራ ከሚሰደብ እግዚአብሔር በእናንተ ገንዘብ የሚድረው ወንድ ልጅ ሆነ የሚሞሽራት ሴት ልጅ የለውምና ህንጻውን ሽጣችሁ ገንዘባችሁን ተካፍላችሁ በሰላም ወደ የቤታችሁ ሂዱ። ገንዘባችሁ ለጠበቃ በትናችሁ በዜሮ ከምትባዙ በጊዜ ገንዘባችሁ ተካፍላችሁ ብትለያዩ ነው የሚሻላችሁ።

ካለቀስክ ለራስህ አልቅስ!

ቤተ ክርስትያን ተዘጋች እየተባለ የሚፈሰው የአዞ እንባ፣ የሚሰማው ለቅሶና ዋይታ እግዚአብሔር ዘንበል አያደርገውም። ለመዘጋትዋ ምክንያት ማን ቢሆን ነውና? ለመዘጋትዋ ምክንያት የሆንከው እኮ አንተ እንጅ ሌላ ማንም አይደለም። የሰማይ መላዕክት አልያም የአገሪቱ መንግሥት አልዘጉባችሁ። ወይስ በለንደን የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን መዘጋት በሰማያት እግዚአብሔር የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጠን የተከትሎ የሚከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ (የዋጋ ግሽበት) ይገጥመዋል ብለህ ለእግዚአብሔር ተጨንቀህ ነው? ተው ባክህ! ቤተ ክርስትያን ብትከፈት በናስ ብረት ብትቆለፍ የምትጎዳው አንተ የምትጠቀመውም አንተ ብቻ ነህ።  

እውነቱን በፍቅር ልንገርህ፥ ስለ እግዚአብሔር አትጨነቅ። “ደብረ ጽዮን ተዘጋች … ወይኔ እግዚአብሔር ምን ሊሆን ይሆን? ምን ይደርስበት ይሆን?” ብለህ አትጨነቅ፤ ሃሳብ አይግህ። እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ ስታመልከውና ስትከተልው የኖርክ አምላክ የምትጨነቅለት አምላክ ከነበረ እሱ የክርስትና አምላክ አይደለም። ቀድሞውኑ አድራሻ ተሳስተህ የተሳሳተ ፌርማታ ወርደህ ነው በራህ ጊዜ ባያያዝከው እሳት ስትጠበስ፣ ስትለበለብና ስትቃጠል የከረምከው። ወዳጄ! ከተጨነቅክ ስለ ራስህ ተጨነቅ። ማን ሞተብህ ነው እንዲህ በእንባ የምትራጨው? በቁምህ የሞተከው አንተ። ካለቀስክ ለራስህ አልቅስ። እግዚአብሔር የምታለቅስለትና የምታዝንለት አምላክ አይደልም። እጅግ የሚያሳዝነኝ ነገር ምን እንደሆነ ያውቃሉ? ሰው ራሱንና ባለ እንጀራውን ማታለል ስለ ቻለ እግዚአብሔር ጭምር ማደናገር እንደሚችል ማሰቡ ነው።  

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ትገኝ ለነበረችው ቤተ ክርስትያን ምእመናን አባላት እንዲህ ብሎ መልዕክት ጻፈላቸው “አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?” ሲል [1ኛ ቆሮ. 6፥ 5] በቆሮንቶስ ቤተ ክርስትያን ምእመናን መካከል ምን እንደተፈጠረ ያውቃሉ? በአማኞች መካከል ጨርሶ ይሆናል ብለው የማይስቡትን የክፋት (የኃጢአት) ዓይነት በዝርዝር ያስፍሩ። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስትያን ምእመናን መካከል የሆነው በዝርዝር ያሰፈሩት በአማኝ አእምሮ የማይታሰብ የኃጢአት ዓይነት ነበር። ለበለጠ መረጃ [1ኛ ቆሮ ከምዕራፍ 1- 6 ያለውን ቃል ያንብቡ] ታድያ ጳውሎስ ይህ ለሰሚ ጆሮ የሚሰቀጥጥ ትርምስ በሰማ ጊዜ በሰማው ነገር ከመደናገጡ የተነሳ ማለት የቻለው ከፍ ሲል ያነበብነውን ቃል ይጠቀሳል። 

የሒሳብ አያያዝ ባለሞያ ፈልጉና ሂሳብህን ይዘህ ተቀየስ:

  • በለንደን የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን አባላት! እግዚአብሔር የደብር አለቆች የቤተ ክርስትያን መዝገብ አምጡልኝ ብሎ በማዘዝ መዝገብ እያገለባበጠ በስም ጥሪ ወደ መንግስተ ሰማያት የምትገባ ነፍስ የለችም። ይህ ከሆነ ዘንዳ በእናንተ ዘንድ የሚታየውና የሚሰማው ነውር ለእግዚአብሔር ክብር ከሆነ ያደረጋችሁት (እያደረጋችሁ ያላችሁተይ)፤ በእውነቱ ነገር ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ይህ ከሆነ – በእግዚአብሔር ዘንድ ደስታ፣ መስዋዕታችሁም ፍጹም ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር አንድ ውለታ ትውሉለት ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ይህን ደግሜ እጠይቃችኋለሁ። በእግዚአብሔር ስም እየተሰባሰባችሁ ከምትናቆሩና እርስ በርስ ከምትናከሱ የሂሳብ ባለሞያ ፈልጉና የሚከተለውን መመሪያ በመከተል በሰላም ወደ የቤታችሁ ተሰናበቱ። 

አንደኛ፡ በቤተ ክርስትያኒቱ የይገባኛል ጥያቄ ያለው ምእመን እንዲሰበሰብ ቀደም ብሎ በአዋጅ አሳውቁ። (ኢሳት የተለመደ ትብብሩ እንደማይነፍጋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ)

ሁለት፡ ሁለቱ ባላንጣዎች በተገኙበት ከሁለቱም አካላት የተውጣጣ የሂሳብ አያያዝ ባለሙያ የሚገኝበት አምስት ወይም ሰባት አባላት ያሉት አድማ በታኝ ኮሚቴ አቋቁሙ።

ሦስት፡ የተቋቋመው ኮሚቴ የመጀመሪያ ስራው በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ከተቋቋመችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ተዘጋችበት ባለው ጊዜ ውስጥ ጥሬ ገንዘብ ጨምሮ አጠቃላይ የቤተ ክርስትያን ሀብት ይመዘግባል፤

አራት፡ አድማ በታኝ ኮሚቴው ቀን ቀጥሮ አጠቃላይ ስብሰባ ይጠራል፤ የደረሰበት ያሳውቃል፤ ቀጣይ የኮሚቴው እርምጃም ለተሰበሰበው ህዝብ ግልጽ ያደርጋል። ይኸውም፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ህንጻ ጨምሮ ተሽጦ ዋጋ የሚያወጣ ማንኛውም የቤተ ክርስትያኒቱ ቀዋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ገምቶ በግልጽ ጨረታ ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ያሳውቃል፤ 

አምስት፡ ኮሚቴው ለሦስተኛ ጊዜ በሚጠራው አጠቃላይ ስብሰባ በቤተ ክርስትያኒቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥር የተቀመጠው ገንዘብ ጨምሮ ለሽያጭ ከቀረቡ ንብረቶች የተገኘ ጥሬ ገንዘብ አንድ በአንድ ለተሰብሳቢው አጠቃላይ ድምር ያሳውቃል። በመቀጠል ለሽያጭ የማይቀርቡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት በከተማው ለሚገኘው የቅርሳ ቅርስ ስፍራ (ለአንዱ ሙዝየም) በስጦታ መልክ ማበርከቱን ለህዝብ ይገልጻል።  

ስድስት፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከማናቸውም ዓይነት ዕዳ ነጻ መሆንዋን ከተረጋገጠ በኋላ አድማ በታኝ ኮሚቴው ለ4ኛ ጊዜ በሚጠራው ጉባኤ ምእመናኑ ከገቢ ወጪ የቀረውን ሂሳብ ተካፍሎ የድርሻውን ይወስድ ዘንድ በለንደን ቅድስት ማርያም ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስትያን በአባልነት ተመዝግበው የሰበካ ጉባኤ ክፍያቸው በአግባቡ ሲከፍሉ የነበሩት ምእመናን ኮሚቴው በሚያቀርበው የጊዜ ገደብ የከፈሉበት ደረሰኝ ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪ ያደርጋል። መዝገብ ካለ መዝገቡን እየታየም ሳንቲም ሳትቀር የድርሻቸውን በመስጠት ኮሚቴው አድመኛውን ይበትናል። በመንፈሳዊ ቋንቋ አነጋገር በሰላም ያሰናብታል። [ይህ በጥቂቱ ነው]

ከዚያ በኋላማ “የኢየሱስ ተከታይ ነኝ” ለማለት የሚቃጣው ደፋር አይገኝ እንጅ ሰዉ ቢፈልግ ኮማንደር፤ ቢፈልግ ሻለቃ፤ ከፈለገም መኖክሴ፤ ቄስ ይሻለኛል የሚል ቄስ፤ የለም! ጋዜጠኛ ይሻለኛል የሚል ጋዜጠኛ በአለቅነት ሹሞ የወደደውን ማድረግ ይችላል። በነገራችን ላይ “ክርስትያን ነኝ” የሚል ሁሉ የክርስቶስ ተከታይ እንዳይደለ አይዝነጉትም። ክርስትና ፍሬ ነውና 

ወገኖቼ! ለወደፊቱ የግል ህይወታችሁም እንደሆነ ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊት “ምሕረትና እውነት ተገናኙ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ።” [መዝ. ዳዊት 85፥ 10] እንዲል ሰላም ስለተመኛችኋት በስለት የምትገኝ ሳትሆን የጽድቅ ህይወት በመኖር የምትገኝ ፍሬ ናትና የጽድቅ ህይወት የሌለው ሰው ሰላምን አገኛለሁ ብሎ በሃሳብ ደረጃ ራሱ ያስበው ዘንድ አይገባም። 

በማታውቁት እሳት ሰላማችሁ ላጣችሁ ወገኖች በሙሉ!

ምንም በማታውቁት ፖለቲካ እየታመሳችሁና እየታወካችሁ ለምትገኙ አግብረተ እግዚአብሔር ካህናት፤ ወንዶችና ሴቶች የእግዚአብሔር ልጆች፥ ብርሃናተ ዓለም ሐዋ. ቅ. ጳውሎስ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤”[ፊል. 4፥ 8] እንዲል የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ትመላለሱ ዘንድ ጸሎቴ ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 25, 2014

Advertisements