ዘንድሮ ሼባዎቹ ምን ነካቸው?

“ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቍጣ ነደደ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። ኤሊሁ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ከኢዮብ ጋር መናገርን ጠብቆ ነበር። ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ እንዲህም አለ። እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ። እንደዚህም አልሁ ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር። ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም። ስለዚህም ስሙኝ እኔ ደግሞ እውቀቴን እገልጥላችኋለሁ አልሁ። እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ፤ ብልሃታችሁን አዳመጥሁ እንዲሁም ልብ አደረግሁ እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥ ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም። እናንተም ጥበብን አግኝተናል እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ። እርሱ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልተናገረም እኔም በንግግራችሁ አልመልስለትም። እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም የሚናገሩትንም አጡ።” [መጽ. ኢዮብ  32፥ 1- 15]

ሌላ ጊዜ በሰፊው ስለምመለሰበት አሁን ግን ለጊዜው አጠር አጠር ባለ መልኩ አንኳር አንኳር ነጥቦች አንስቼ መጠነኛ ትምህርት ላካፍላችሁና በቀጥታ ወደ ርዕሳችን እንዘልቃለን።

ኤሊሁ ሌላ አራተኛ የኢዮብ ወዳጅ ሲሆን በዕድሜው ከሌሎች ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች እጅግ የሚያንስ ሰው ነው።  የኢዮብ ሦስቱ ወዳጆች በስም ኤልፋዝ፣ በልዳዶስ፣ ሶፋር ተብለው የሚታወቁ ሲሆኑ፤ 

ምንም እንኳር የመጡበት ዋና ምክንያት ወዳጃቸው ኢዮብ የደረሰበት መከራ ሰምተው ሊያስተዛዝኑትና ለያጽናኑት ቢሆንም ዳሩ ግን ምክራቸው ያለ እውቀት ነበርና ሲያደክሙትና ሲያለፉት ምዕራፍ ሦስት ላይ ተገልጠው ከምዕራፍ አራት ጀምሮ አፋቸው ያመጣላቸውን ሲናገሩ ኤሊሁ እስከተገለጠበት ምዕራፍ 32 ድረስ ዘልቀዋል። 

ኤሊሁ በኢዮብ የተቆጣበት ምክንያት ኢዮብ በተደጋጋሚ በደል የሌለበት ሰው መሆኑን በአጽንዖት ይናገር ስለነበር ኤሊሁ ደግሞ የኢዮብ አነጋገር እግዚአብሔር ተወቃሽ የሚደርግ ሆኖ ስለተሰማው ሲሆን ሦስቱ ሽማግሌዎች የተቆጣበት ምክንያት ግን ለየት ያለ ነበር። ኤሊሁ ሦስቱ ሽማግሌዎች የተቆጣበት ምክንያት ሽምግሌዎቹ ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ስም እየጠቀሱ መናገር ቢቻላቸውም በንግግራቸው ውስጥ ግን አንዳች እውነት ስላላገኘባቸውና ተሳላቂዎች ነበሩም ነው።

ፕሮፌሰሬ ተነኩ ሲል “ዘራፍ!” ለማለት ለሚቃጣው፥

በአጭሩ ከላይ ከፍ ሲል ካነበብነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምንማረው ቁም ነገር ቢኖር፥

  • አንደኛ፡ “ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ” እንዲል ሽማግሌ ነውና ያሻውን ይሁን ተብሎ የሚታለፍ ነገር እንደሌለ እንማራለን። አንድ ሰው በሆነ ባልሆነ ነገር ከመቀላቀልና ከመዘባረቅ የማይመለስ ከሆነ ሽማግሌም ቢሆን አደብ ይገዛ ዘንድ በቃ! ማለት እንደሚገባ። 
  • ሁለተኛ፡ “ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር”  እንዲል አንድ ሰው ገና ለገና የ70ና የ80 ዓመት የዕድሜ ባለ ጸጋ ስለሆነ ብቻ ሁል ጊዜ ቁምነገር አለው ማለት እንዳይደለ። ሽማግሌም ቢሆን ዝም ማለት በሚገባበት ሰዓትና ስፍራ ዝም ማለት የማያስችለው ከሆነ አፉን ሰብስቦ አርፎ ይቀመጥ ዘንድ አቁም! ማለት እንደሚገባ።
  • ሦስተኛ፡ “በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም።” እንዲል ኢትዮጵያ ውስጥ እርጅና ጨምሮ የዶክትሬትና የፕሮፌሰር ማዕረጎች ብዙ ተነግዶበታል። ቁም ነገሩ አያርፉበትም እንጅ አባ ጢሞቲዎስም ዶክተር ናቸው። ዛሬ ግን እንዲህ ያለ ትውልድ ገደይ አስተሳሰብ መቋጠሪያ እናበጅትለታለን።

የእርስዎ ባለሟል ሂትለርማ ዙምባቤ ነው ያለው!

ፕሮፌሰር መስፍን አልፎ አልፎ በሚንጸባርቁት አመለካከት የአቋም መዋዠቅ ጸባይ ማየት የተለመደ ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉ ጊዜ አሉታ ተኮር ጸሐፌ ናቸው ማለቴ አይደልም። ለዛሬው ዕለት ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ “ጎሠኛነትና ሽብርተኛነት” በሚል ርዕስ የካቲት 2006 በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ተዘጋጅቶ ቋጠሮ ድረ ገጽ ለንባብ የበቃ ጽሑፍ ሲሆን፤ ከፍ ስል ለመግለጽ እንደሞከርኩት የሚቀጥለውን ሰፊ ሐተታ ሲያነቡ ከመጽሐፈ ኢዮብ 32፥ 1- 15 ያጠኑትን ቃል በልብዎት እንደጠበቁ ያቀጥኑት ዘንድ ስጠይቅ በአክብሮት ነው። መልካም ንባብ!

ስለ ሂትለር ጥብቅና መቆም ቃጥቶኝ አይደለም። አልውለውምም። የፕሮፌሰር መስፍን ጽሑፍ ይነበበ ሰው እሳቸው ለምን ስለ ሂትለር አንስተው ለመናገር እንደ ፈለጉ ግልጽ የሆኖሎት ያህል የእኔም መልዕክት ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ። ሂትለር የራሱን ሕዝብ ከሌላው አስበልጦ “ንጹህ” ብሎ መጥራቱ ከልክ ያለፈ ትዕቢትና ልቅ የሆነ ትምክህተኝነት መገለጫ እንጅ በምን ሂሳብ ነው ይህ “ደንቆሮ” የሚያስብለው? አንባቢ ሆይ! ደንቆሮ ማለት ለእርስዎ ምን ማለት ነው? ደንቆሮ ማለት “ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ጽሑፎች ማጣፈጫ ቅመም” ነው ማለት ነው?  

ፕሮፌሰር መስፍን ሂትለርን “ደንቆሮ” ሲሉ የፈረጁበት መነጽር ስመለከት የተለመደ የፕሮፌሰሩ አቧራ የማስጨስ አጉል የጥንቆላ ጸባያቸው ነው ብዬ አልፌው ነበር። ዳሩ ግን ሰውዬው “ደንቆሮ” የሚለውን ቃል አለቦታው የሰነጠሩት በስህተት ሳይሆን የተለመደ ከመቃብር ይልቅ የከፋ የስድብ አፋቸው ያላቁቁበት ዘንድ የደሎቱበት ሰላማዊ ወገን ለመኖሩ/(እንዳለ) የገባኝ ሁለተኛው ገጽ የመጨረሻው አንቀጽ ያነበብኩ ቅጽበት ነበር። [ጽሑፉን ያነቡ ዘንድ እመክራለሁ።]

ጽሑፉ የተጻፈ በአማርኛ ነውና አማርኛ አንብቦ መረዳት የሚችል ሰው ሰውዬው ለማርጨት የፈለጉት መርዝ ይስተዋል የሚል እምነት የለኝም። ለመሆኑ ሂትለር ማን ነው? አይሁድስ ማን ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ በዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰስ የሚገባው አካል (ግለሰብ) አለ ብለው የሚያምኑ ከሆነ የእርስዎ ባለሟል ጓድ መንግሥቱ ሃይለማርያም ነው መከሰስ ያለበት። ምንድ ነው የሚያወሩብን? ገና ዛሬ ከሃያ ሁለት ዓመት በኋላ ከእንቅልፍዎ መባነንዎ ነው እንዴ? እንግዲያውስ፥ የእርስዎ ባለሟል ሂትለርማ አንድ ትውልድ ትግራዋይ ጨርሶ ዙምባቤ ነው ያለው። እዛው ሄደው ይፈልጉት። ቀልደኛ!

ደንቆሮው “ሂትለር” ወይስ ፕሮፌሰር መስፍን?

ሂትለር በአይሁዳውያን ላይ የፈጸመው ግፍ፣ አገሩ ጀርመን እሳት ውስጥ (2ኛ የዓለም ጦርነት) መጨመሩ ሳያንስሰው በጦርነቱ መሸነፉ … ወዘተ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በሌላ መልኩ ደግሞ ጀርመንን ከውድቀት ዜጎቹም ሥራ አጥነት ተከትሎ ሊከሰት ከሚችል የስነ ልቦናና ማህበራዊ ቀውስ (ስብራት) የታደገና ያተረፈ ሰው ነው። ሰው ከድርጊቱ የተነሳ “አውሬ” ተብሎ ለመግለጽ የሚቻል ከሆነ ሂትለር አረመኔ የማይገልጸው አውሬ ሰው እንደ ነበር ድፍን ዓለም የሚስማማበት እውነታ ነው። ታድያ አንድ ሦስተኛም ቢሆን ሂትለር በጀርመን ዕድገትና ሥልጣኔ ጎልቶ የሚታይ/የሚጠቀስ የራሱ ድርሻ አበርክቶ ያለፈ ሰው ነው። 

ስለ ታላላቅ ግለሰቦች ስንናገር አንደኛ ጎናቸው ብቻ እያነበብን “እገሌ ማለት ይህ ነው” የምንል ከሆነ ማን ንጹሕ ሊገኝ ነው? በ60 ዎቹ አከባቢ በአሜሪካ የጥቁሮች ሰብአዊ መብት ተሟጋች ቄስ ማርቲን ሉተር ኪንግ በምሳሌነት ላውሳ። ሉተር ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆን የባብቲስት (መጥምቃውያን) ቤተ ክርስቲያን ስመ ጥር አገልጋይም ነበር። ሉተር በትምህርት ብቃቱ አመኔታ የማይጣልበት፤ በተደጋጋሚ በፕላግሪስም (Plagiarism) ክፉኛ የሚከሰስና የሚወቀስ ሰውም ነበር። መች ይህ ብቻ ሉተር ለሚስቱም ለእግዚአብሔር (ለቃል ኪዳኑ) የማይታመን፤ ብቻ ቀሚስ ትልበስ እንጅ ውሻም ብትሆን የማይምር፣ ሽንቱን የመሽናት ያክል በእህቶች የማያስችለው ዕልል ያለ ስኬታማ አዳኝ ነበር። 

መልከ መልካሙ 35ኛ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ኬነዲም እንዲሁ በሄዱበት የአመሪካ ጠቅላይ ግዛቶች ሁሉ ቅምጦች ያበጃጁ ታላቅ መሪ ነበሩ። ትዳራቸውና ልጆቻቸው “በነጮች ቤተ መንግሥት” (White House) ጥለው ልጃ ገረዶችን ማማገጥ ያምርባቸው እንደ ነበርና ከዚህም አልፈው ከወዳጃቸው ከሉተር ጋር “ሞያተኞች አንስት” ሸምተው የፈንጠዝያ ምሽት እያዘጋጁ በግሩፕ ዓለማቸውን ይቀጩ እንደነበር የታሪክ መጻህፍት ያስነብባሉ። “ኪሊንግ ኬነዲ” (Killing Kennedy) አዲሱ የቢል ኦራይሊ መጽሐፍ ያነበቡ እንደሆነ ጉዳዩ በከፊል ኩልል ብሎ ያገኙታል። 

እናማ በታሪክ መዛግብት ስማቸው በወርቅ አስጽፈው ያለፉ ሰዎች (ሉተርና ኬነዲ) መነቀፍ በሚገባቸው በኩል መንቅፍ ትተን አንዱ ገጻቸው ብቻ እያነበብን በደፈናው “ደናቁርት” ብሎ ፍረጃ ምን ይሉት እውቀት ነው? አመንዝራውን “አመንዝራ” ማለትን ትተን አመንዝራን “ደንቆሮ” ብሎ ስያሜ መስጠት ማን ነው ደንቆሮው? እንደው ግን ለመሆኑ የቮልስዋገን ፈጠራ፣ የትላልቅ አውራ ጎዳናዎችና ቀለበት መንገድ ግንባታዎች፣ በህክምና ዘርፍ እንደሆነም ጀርመን ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው የላቀ ውጤትና ዕድገት የተሸጋገረችው በሂትለር አስተዳደር ዘመን ስር መሆኑን ያውቁ ኖሯል? እውነት ነው ሂትለር የለየለት አረመኔ ሰው ነበር። እዚህ ላይ ችግር/ጥያቄ ያለበት ሰው ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። 

ሂትለር  ጀርመናዊ ዜጋ ‹‹ንጹሕ›› ዜጋ ነው የሚል እምነቱ የሂትለር ትምክህተኝነት እንጅ ሂትለርን “ደንቆሮ” ማለት ሂትለርን አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ቋንቋዎ ልዋስና እርስዎ ኖት “ደንቆሮ” አይመስሎትም?። በኢትዮጵያ ታሪክ ሂትለር ማየት ካማሮት ደግሞ በቁጥር የሂትለር ያክል ነፍስ ባያጠፋም በጭካኔውና በአረመኔነቱ ከሂትለር የማይተናነስ ነፍሳት የጨረሰ የኢትዮጵያ መሪ ማን እንደሆነ ይዘጉታል የሚል እምነት የለኝም።
መሳደብ ካማሮት “መሳደብ አማረኝ” ብለው መሳደብ ይችላሉ። እስከ ዛሬ ድረስም እንዳበደ ውሻ ይህንንም ያንንም ሲቦጭቁ፣ ሲሰለቅጡ፣ ሲለክፉና ሲሳደቡ ነው የመጡት። ከዚህ ያለፈ ግን ሽምግልናዎንና የፕሮፌሰርነት ማዕረግዎን አስታከው መርዝን መርጨት ማንም አይፈቅድሎትም። እንዴት ነው ነገሩ? ሰው “ደንቆሮ” ላለመባል የፕሮፌሰር መስፍን ፌርማ ያረፈበት ወረቀት ማግኘት አለበት? 

ቁጭ ብለህ የባለ ሥልጣናት ዳህጸ ልሳን እየጠበቅህ የግለሰቦች መልካም ስምና ዝና ማጉደፍ፣ በእውቀትም በጥበብም ከእርስዎ እጅግ የሚልቁ ግለሰቦች መወረፍ፣ መዝለፍ፣ በተራ ቃላት ማቃለልና መሰደብ እንደ በጎ ነገር ካልተቆጠሮለት በስተቀር እርስዎ ለኢትዮጵያ ምን አደረጉላት? የእንጀራ ጉዳይ ቢሆንም አዲስ አባበ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ማገልገልዎን “ሰምቻለሁ”። ስለ አገልግሎትዎ ምስጋና ይገባዎታል። ከዚህ ያለፈ ግን በሰፈሩት መስፈሪያ ይሰፈርሎት ዘንድ ግድ ነው። 

አሁን አሁን የሰለቸኝ ነገር ቢኖር የእኝህ ሰው (የፕሮፌሰር መስፍን) ዝባዝኬና የሲዖል ፈላስፋው የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከንቱ ፍልስፍና ነው። ፕሮፌሰር መስፍን የት አገር ሂደው፤ ከማን አስተማሪ፤ ለብቻዎ ምን ዓይነት መጽሐፍ እንዳነበቡና ከሰው የተለየ ምን የሚሉት ትምህርት እንደ ተማሩ ባላውቅም የሰማዩ አባታችን (እግዚሃሩ) ራሱ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ዓይነት የዘቀጠ “ትምህርትና” “እውቀት” ሳያስፈልገው አይቀርም። 

“እውቀት” እንዲህ ከሆነ ግድ የሎትም በብርሃናት ውስጥ የሚኖር፣ የሌላውን እንዳለው የሚጠራ፣ በክንዱ ከፍ ያልውን ታላቅ ነገር የሚያደርግ፣ ለህልውናው ከ እስከ የሌለው፣ በምድር ክበብ ላይ የተቀመጠ፣ የጥበብ መንገድ የእውቀትም ቤትዋን የሚያውቅ፣ የብርሃናት አምላክ እግዚአብሔር ራሱ የእርስዎ ዓይነት እውቀት፣ የእርስዎ ትምህርትና እርዳታ በብርቱ ያስፈልገዋል። ዓለም እንዲሁ የታወከችበት፣ የተተረማመሰችበትና የተረባበሸችበት ዋና ምክንያት እርስዎ የመሰለ “አዋቂ” (ነገረኛ) እዚህ ምድር ተጎልቶ ሲያበቃ እግዚሃሩ አለ ቦታው መቀመጡ ነው። 

ሌላው የትግራይ ተወላጆች ሲጽፉና ሲናገሩ ፕሮፌሰር መስፍን የኢየሱስ ስም እንደ ተጠራበት ጋኔን ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚያስዘልሎትና የሚያንቀዥቅዥዎት ምንድ ነው? ሰው ከየትኛው አከባቢ ይወለድ እንደ ዜጋ/እንደ ግለሰብ ሥርዓት ባለው መልኩ፣ የሌላውን ወገን ክብር ሳይነካ የመሰለውን የመናገር ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት አለው።

ለመሆኑ ማን ነው እርስዎን ፖሊስ አድርጎ የሾሞት? ከሆነስ የእርስዎ ፖሊስነት በትግራይ ተወላጆች ብቻ ነውን? የትግራይ ተወላጅ እኩል እንደሌላው የመጻፍና የመናገር መብት የለውም? ሰው በጻፈና በተናገረ ቁጥር መልስ የመስጠት ግዴታ አለብኝ ብለው የሚያምኑ ከሆነ ደግሞ ደም ካሎት ለጀዋር መሐመድ መልስ መስጠት አይቀሎትም? ወይስ ደካማ አቅምዎ እየመዘኑ መርዝ መርጨትዎ ነው? ግልጹን በፍቅር ልንገርዎት፥ እርስዎ ውሸታም ኖት። በዚህ ዕድሜዎ ደግሞ ውሸት አያምርቦትም።

በትግርኛ ስለ ተጻፈ ብቻ የትግራይ ተወላጅ ይጻፈው የሻዕቢያ ሰላይ ማንነቱ በውል ለማይታወቅ ሰው መልስ መስጠት ከተቻልዎት ምን ነው ጃዋር መሐመድ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ታሪክ አይቀር ቅርስ እያነሳ ሲያፈርጠውና ሲፈጠፍጠው እርስዎ ዝምታን የመረጡ? ጀዋር “ለመወያየት አቅሙ አለኝ የሚል ግለሰብ ካለ በበኩሌ ዝግጁ ነኝ” በማለት ጥሪ ሲያቀርብ በፌስ ቡክ ተደብቆ አልነበረም። ፊትዎ ላይ ወጥቶ ነበር እርስዎና የእርስዎ ዓይነት አጀበኞች በሽፋን የሚነግዱበት “ኢትዮጵያዊነት” የበጣጠሰው። ያን ጊዜ የት ነበሩ? እውነት “ኢትዮጵያዊነት” የሚቆረቁርዎት ከሆነ http://www.gadaa.com/ ይጎብኙና በአማርኛ የሚጻፉ ጽሑፎች አንብበው መልስ ለስጠት ይሞክሯት።

ፕሮፌሰር መስፍን፥

  • ለመሆኑ አንድ ጽሑፍ ሲጽፉ ምን አተርፋለሁ ብለው ነው የሚጽፉ? – ሕዝቦች ለማናቆር?
  • እንደ ፓኪስታን ባቡር የተበጣጠሰ ሃሳብ ቢሆንም ቢያንስ ቢያንስ ግን የጽሑፍዎ ዓላማ ምንድ ነው? – ጸብና ሁከት ለመዝራት? ለማቃቃር? ህውከትና ትርምስን ለመፍጠር? 
  • በጾም በጸሎት ተወስነው መኖር በሚገባዎት በዚህ ዕድሜዎ ሰው ከእርስዎ እንዲህ ያለ ነፍስን የሚያቆሽሽ እድፋም መልዕክት ለማንበብ መገደዱስ ምን ይሉታል? 
  • ጽሑፉን ሲያዘጋጅ አንባቢ ከጽሑፌ ምን ይማር ብለው ነው ጽሑፉን የሚያዘጋጁት? – ክፋት? ምቀኝነት? ስድብ? ልቅነት? ሥርዓት አልበኝነት፣ ጋጠ ወጠነት? አሽሙርን ይማር ዘንድ?
እንደው ግን እንደ መዥገር በትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተለጠፉበት ምክንያት ምንድ ነው? ይህ ህዝብ ምን ያደረገ ህዝብ ነው? ምን ቢበድልዎት ነው የአንድ ቅሌታም ሽማግሌ መቀለጃ የሆነው? እውን ሌላ የሚጻፍ ርዕስ ታጥቶ ነው? ገንቢና አስተማሪ ጽሑፍ የመጻፍ አቅምና እውቀት ካሎት፤ ፖለቲካ ለመተንተን የሚያስችል በቂ ትምህርት ካሎት ለምን ዜጎችን የሚያቀራርብ፣ የሚያፋቅርና የሚያዋድ ጽሑፍ አይጽፉም? እስከ መቼ ነው እንክርዳድ እንደ ዘሩ የሚኖሩ? ዘንድሮ ሼባዎቹ ምን ነካቸው? መቃብር አፋፍ ላይ ሆነው ጸብ ጸብ የሚላቸውና ደም ደም የሚሸታቸው እንዴት ነው ነገሩ?

 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 23, 2014

Advertisements