ወዳጄ ሆይ! የሚሾመውና የሚከብረው ሌላ ሆኖ ሳለ አንተ ለምን ትሞታለህ?

ማሳሰቢያ/ትርጓሜ፥ “ድሃ” የሚለውን ቃል የጽሑፉ መንፈስና ዓውደ ንባቡን ጠብቆ ይነበብ ዘንድ ስጠይቅ በእክብሮት ነው። 

 • ድሃ! መዘዝህ ብዙ ነው። ድህነትህና የሃብታም መጠቀሚያ መሆንህ ሳያንስህ የገዛ ራስህ ሰውነት ጭምር ጠላት መሆንህ ሳስበው ማስታወሻ እጽፍልህ ዘንድ ግድ አለኝ።
 • ድሃ! መዘዝህ ብዙ ነው። ሙሉ ሰው የሚበላውን የመብል ዓይነት፣ ሰው የሚለብሰውን መልበስና መመገብ ባይሆንልህና ባትታደልም፤ ሰው የሚያየውን ማየት፣ ሰው የሚያስበውን ማሰብ አቅቶህ የሰው ባሪያ፣ የጥቂቶች መጫወቻና መቀለጃ ሁነህ ሳይህ ልቤ ያዝናል።
 • ድሃ! መዘዝህ ብዙ ነው። የአገሬ ሰው “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንዲል ድግስ ሁሉ ሰርግ ይመስልህና ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ በግ ጠቦት እግሮችህ ለሞት ስታፈጥን አይቼ አጅግ አዘንኩልህ። 
 • ድሃ! መዘዝህ ብዙ ነው። ሰው በታሪኩ ሲባል ከመስማት ያላለፈ በህይወቱ ያላያቸውና ያላጣጣማቸው ቃላቶች አሸክመው ጎዳና ላይ ያወጡሃል። አንተ ደግሞ እውነት መስሎህ በባዶ ሆድህ፤ አንዱ ጫማህ አንዱ እጅህ ላይ ይዘህ፤ ጉሮሮህ እስኪደርቅ ድረስ “ነጻነት!፣ ፍትሕ!፣ ዲሞክራሲ! …” እያልክ ተጮኸለህ በዚህ ማኸል በሚፈጠረው ግርግር አንተ ትሞታለህ፤ ከቀናህ ደግሞ አካልህ ጎድሎ የሰው ቤት ልብስ አጥባ፣ እንጀራ ጋግራ፣ ውሃ ተሸክማ፣ እንጨት ለቅማ፣ እህል ፈጭታ … ያሳደገችህ እናትህ ተመልሰ ሌላ ሸክም ትሆናለህ። 

ወዳጄ ልብ በል! ለአንተ ነው የምናገረው፥ በአንተ ሞት ከአባትህ ቤት የሚሾም አንድም ሰው የለም። በአንተ ደምና አጥንት የቀረው የአባትህ ቤት ይመዘብር ዘንድ አቧራ ያልነካው ለሹመት የተዘጋጀ ሰው ከማዶ አለ። አንተን ወደ ሞት ቀጠና አሰማርቶ ሲያበቃ መብልና መጠጥ ተርፎ ከሚደፋበት ከተማ የተሰማራ፣ ስለ አንተ ግድ የማይለው፣ ያይህ ዘንድ እጅግ የሚጸየፍህ፣ በአንተ ሞት የአባትህ ቤት ሰማይ ሲደፋ መብልንና መጥጥ አዘጋጅቶ ወዳጆቹም ጠርቶ ዓለሙን የሚቀጭ ለሹመትና ለክብር የታጨ ጆቢራ አለ። ወዳጄ ሆይ! የሚሾመውና የሚከብረው ሌላ ሆኖ ሳለ አንተ ለምን ትሞታለህ?

ድሃ መዘዝህ ብዙ ነው 

 • ግርግር ቢፈጠር በግርግሩ የምትሞተው አንተ፤ 
 • የቱንም ያህል ኑሮ ቢወደድ በኑሮ ውድነት የሚትታመሰውና የሚትቸገረው አንተ፤  
 • ረሃብ ቢከሰት ከምግብ ዕጦት የተነሳ በርሃብ የሚታልቀው አንተ፤ 
 • አገር በጠላት ተደፈረች ተብሎ መለከት ሲነፋ ቀድሞ የምትሰለፈው አንተ በጥድፍያ የምትቀበረው አንተ፤ 
 • ጦርነት ቢቀሰቀስ በርሃ ላይ ወድቆ የሚቀረው አንተ፤ 
 • ችግር አለ ቢባል የሚቸገረው አንተ፤   
 • ፍትህ ተጓደለ ቢባል በፍትህ እጦት የሚሰቃቀይ አንተ፤ 

ወዳጄ ሆይ! የሚሾመው፣ የሚከብረው፣ የሚጠቀምና የሚደላው ሌላ ሆኖ ሳለ አንተ ለምን ተብሎ ትሞታለህ? ኧረ ምን በወጣህ ወዳጄ!?! ለምን ትሞታለህ?

 • የአንተ ሞት ለአንተ የሚፈይደው ላይኖሮው፤
 • በአንተ ደም የሚለውጥ የአባትህ ቤት ኑሮ ላይኖር፤
 • በሞትህ አዲስ ነገር ላይፈጠር አንተ ለምን ትሞታለህ? 
 • ወዳጄ ሆይ! ከንቱ ሞት ለመሞት ምን ይጣድፋሃል? ድሃ የሆንክበት ምክንያት በመጠኑም ቢሆን ባይገባኝም ከንቱ ሞት ለመሞት – ለሞት ያለህ ፍቅር ግን ጨርሶ  አይገባኝም። 

ድሃ! መዘዝህ ብዙ ነው። የአንተ ሞት ለጥቂቶች ሹመት፤ ዘጠኝ ወር በማኅጸንዋ ተሸክማ፣ ጡት አጥብታ፣ ተጨንቃና አምጣ ወልዳህ ስታበቃም ለሁለት ዓመት ሙሉ በጀርባዋ አዝላ፣ በችግር ውስጥ ሆናም ሰው ትሆን ዘንድ ትምህርት ቤት ለላከችህ ለእናትህ ደግሞ የሞት ሞት መሆኑን ሳታውቅ ቀርተህ ይሆንን? ወዳጄ እውነቱ ልንገርህ፥ የድሃ ሞት የሚጨምረው ነገር ቢኖር ለእናቱ ሀዘን ብቻ ነው።

እንግዲያውስ ግልጹ ልንገርህና ልለየህ፥ በአንተ ጉድለት የሚወቀስ አምላክ ሆነ ሰው የለም። ሌላው ቢቀር የምትሆነውና የምታደርገውን ከመሆንህና ከማድረግህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብ ትችለለህ። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 14, 2012

Advertisements