የመገንጠል ጥያቄ ያለው ሕዝብ – ይቀንጠስ!

ትርጓሜ፥

መገንጠል፥ የራስህ የሆነ ነገር በራስህ ማስተዳደርና ቀዳሚ ባለቤትነትን የሚያመላክት ቃል እንጅ መገንጠል ሲባል “የአገር አንድነት ማፈራረስ ነው” ተብሎ የሚተረጎመው መሰረተ ቢስ አንድምታ የሚያገናኝ ነገር የለውም። 

መቀንጠስ፥ በዋናነት ምርጫን የሚያመላክት ሆኖ የቃሉ ክብደት የሚያርፈው የራስህ በሆነ ነገር፤ በእጅህ ባለው ነገር ላይ፤ የራስክን ከያዝ በኋላ በራስህ ሜዳ ላይ እንደወደድክ መሆንን፤ ብትፈልግ “እሾህ ዝራበት” በሚል እሳቤ ይነበቡ ዘንድ ሳሳስብ በአክብሮት ነው።

የመገንጠል ጥያቄ ያለው ሕዝብ – ይቀንጠስ! Salsaywoyane

መሪ ጥቅስ፥

“እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ።” (ገላትያ 5፥ 1- 12)

ሐተታ፥

ገላትያ ወደምትገኘው የቅዱሳን ህብረት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፈቸው ሌሎች አሥራ ሦስት መልዕክቶች ይልቅ በይዘቱ ጥንካሬና ክብደት የገላትያ መልዕክት ቀዳሚ ስፍራ ይይዛል። ገላትያ ቱርክ በማለት የሚታወቀው ማዕከላይ ምስራቅ አከባቢ የምትገኝ አውራጃ ስትሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ጳውሎስ ራሱ ከመሰረታቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ናት። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጳውሎስ ወደ ሶርያ በተመለሰ ጊዜ “የለም! መገረዝ አለባችሁ … ካልተገረዛችሁና የሙሴም ሕግ ካልጠበቃችሁ በክርስቶስ ማመን ብቻ በቂ አይደለም!” የሚል የክህደት ትምህርት የሚያሰራጩ  አይሁዳውያን ሰርገው በመግባታቸውና ምእመናኑንም ክፉኛ በማወካቸው ብዙዎችም በዚህ እንግዳ ትምህርት መወሰዳቸው ሲሰማ ጳውሎስ ይህን መልዕክት ይጽፍ ዘንድ ግድ ብሎታል። ጠቅለል ባለ መልኩ የገላትያ መልዕክት ቅዱስ ጳውሎስ ግልጽ በሆነ ቋንቋም ስለ ጸጋ፣ ስለ ሕግ ስለ፣ ስለ እመነትና ስለ ሥራ፣ ስለ ነጻነትና ስለ ግዝረት ለተግሳጽና ለትምህርት የጻፈው መልዕክት ነበር።

ቅዱስ ጳውሎስ ያን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ የተመሰረታት ቤተ ክርስቲያን ዘወር ካለ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የቤተ ክስቲያኒቱ አባላት (አማኞች) በእንግዳ ትምህርት ተጠልፈው ወደሚናቅ ርካሽ ወደ ሆነው ወደ ሕግ ትምህርት ፊታቸው መመለሳቸውና መማረካቸው ሲሰማ ሊሰማው የሚችለው ሐዘንና የልብ ስብራት ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም። ቢሆንም ጳውሎስ የሚያመናታ ዓይነት ሰው አልነበረምና በጉዳዩ ላይ (ግዝረት በተመለከተ) ከምንባቡ ለመረዳት እንደሚቻለው የጳውሎስ አቋም ግልጽ ከግልጽም በላይ ለድርድር ብሎ ቋንቋ ዕድል ፈንታ የማይሰጥ ቀጥተኛ ትምህርት ያዘለ መልዕክት ነበር የላከላቸው። 

ግዝረት ወይም መገረዝ ማለት ሸለፈትን ማስወገድ ማለት እንደሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ። በብሉይ ኪዳን ትምህርትም እግዚአብሔርና በአብርሃም መካከል በተደረገው ቃል ኪዳን መሰረት ግዝረት የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ እንዲሁም የአይሁዳዊነት መታወቂያ ምልክት ሲሆን አገልግሎቱ በክርስቶስ ኢየሱስ መወለድ፣ ስቅለት፣ ሞትና ትንሳኤ ተጠናቋል። በሃዲስ ኪዳን ትምህርት መሰረት በሮሜ 2፥ 28 እና 29 እውነተኛ መገረዝ ማለት በመንፈስ የልብ መገረዝ መሆኑን በግልጽ ሰፍሮ የምናገኘው ትምህርት ሲሆን የገላትያ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ግን ይህን ሁሉ እያወቁ በአይሁዳውያን ዲቃላ ትምህርት በቀላሉ ተማርከው “ካልተገረዝኩ ሙቼ እገኛለሁ!” እስከ ማለት ደረሱ። 

በሌላ አነጋገር ለማብራራት ያክል ቅዱስ ጳውሎስ “የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ” ሲል/ያለበት ዋና ምክንያት “እገረዛለሁ … ካልተገረዝኩ ሙቼ እገኛለሁ!” የሚል ማንም ቢኖር አይደለም ሸለፈቱ ከፈለገም ዕቃውን ሙሉ በሙሉ ቆርጦ ይጣለው! ጀንደረባ መሆን ያማረው ካለ ይተልተል! ሲል ከበድ ባለ አገላልጽ ሲጽፍላቸው ድርጊታቸውን ምን ያህል እንዳሳዘነው የሚያሳይ፤ ተቃውሞውን ከበድ ባለ አገላለጽ ሲያሰማ የምናገኘው። እዚህ ላይ በድጋሜ ግልጽ ለማድረግ የምፈልገው ነጥብ ቢኖር ይህ ድምዳሜ የጳውሎስ ትምህርት ሳይሆን የእንቢተኞች ምርጫ መሆኑን ልብ ይባል ዘንድ እጠይቃለሁ። 

የመገንጠል ጥያቄ ያለው ሕዝብ – ይቀንጠስ!

በጥቂቱ መወሰን የላቀ ጥቅም ቢኖረው አሜሪካውያን አንዷ አሜሪካ 51ና ከዚያም በላይ ቦታ ላይ በጣጥሰውና ተበጣጥሳ በማሳየት መልካም ምሳሌ በሆኑን ነበር። ዳሩ ግን ይህ ሲሆን አላየንም። ይልቁንስ አፍሪካ እርስ በርሷ ተባልታ እንድትበታተንና እንድንበጣጠስ እያደረጉ ያስጨፍሩናል። በፍትህ፣ በሰብአዊ መብት ስም፣ በእርዳታ ስም … ግባቸው አንድ ሆኖ ሳለ ልዩ ልዩ መልክና መዋቅር ያላቸው በሚመስሉ አፍራሽ ተቋሞች እኛን እርስ በርስ ሲያናቁሩንና ደም ሲያቃቡን እነሱ ግን ብዙ ሳሉ በሰላም ለመኖር ተችሎአቸውል። ይህ ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? ለማለት እንኳን አልቻልንም።

  • ወጣም ወረደ ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መጻኢ ዕድል በተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል በዋናነት ሊኖር የሚችለው መግባቢያ ቋንቋ “ኢትዮጵያ” ማለት የአንድ ሕዝብ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣  አስተሳሰብ፣ ሥልጣኔና ስነ ልቦና ያለው የአንድ ሕዝብ አገር ሳትሆን ኢትዮጵያ ማለት ሕዝቦች በተናጠል የእኔ የሚሉት የማንነታቸው መገለጫ የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሥልጣኔና ሥነ ልቡና ያላቸው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድምር ውጤት አገር መሆንዋን፤ 
  • በተጨማሪም “ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊነት” ብሎ ደም ሆነ አንድ ወጥ ማንነት እንደሌለ፤ ይልቁንስ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተስማምተው በሚመሰርትዋት ወይም በሚኖሩባት አገር በዜግነታቸው ህጋዊ ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙበት የዜግነት መግለጫ እንዲሁም ህጋዊ እውቅና ያለው መንግሥትነትን የሚያመላክት እንደሆነ  የጋራ ስምምነት ላይ የደረሰ ማዕከል ያደረገ/መሰረት ያለው እንደሆነ ብቻ ነው አንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ላይ ተቀምጠን ስለ ኢትዮጵያ መነጋገር የሚቻለው። 
  • ተወደደም ተጠላ ከእንግዲህ ወዲህ ከማኸል አገር ተነስተህ ትግራይ፤ ከትግራይ ተነስተህ ኦሮሚያ ግዛት ማስፋፋትና ግብር መሰብሰብ ህልም ነው። ዜጎች ከስፍራ ስፍራ እየተንቃሳቀሱ መኖርና መስራት አይችሉም አላልኩም።
  • የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጨፍልቆ የመግዛት ህልም ያለው ግለሰብ ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ያለ እንደሆነም ነገሩ እንደ እናቱ ጡት ሊረሳው እንደሚገባ። 
  • በደም የመሰረተች ኢትዮጵያ እንደ አንዲት ሉዓላዊት አገርና መንግሥት እንድትቀጥል ከተፈለገም  ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይሁንታ ያረረፈበት እንደሆነ ብቻ ለመሆኑ ምንም ሊያጠያይቀን አይገባም ባይ ነኝ።

የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በዓለም ታሪክ በጾታ፣ በዕድሜ፣ በትምህርት ደረጃ … የተደራጀት አገር ለመኖርዋ አልሰማሁም፣ አልተማርኩም አላነበብኩምም እንጂ ኢትዮጵያ የህጻናት ክልል፣ የወጣቶች ክልል፣ የጎልማሶች ክልል፣ የሽማግሌዎና የአሮጊቶች እንዲሁም የሙውታን ክልል በሚል መዋቅር ከፋፍለን በሰላም ለመኖር ቢቻለን የሁላችን ደስታ ነው። በሃይማኖት፣ በጾታ ከተባለም እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ የወንዶች ክልል፣ የሴቶች ክልል – የክርስቲያን ክልል፣ የእስላም ክልል፣ ምንም ውስጥ የሌሉ ክልል … ወዘተ ተብሎ ተደራጅተን በአንድነት ለመኖር የሚስችል ተጫባጭ የፖለቲካ መዋቅር ቢኖር ኖሮ ደስ እያለን ተግባራዊ የማናደርግበት ምክንያት የለም። ዳሩ ግን በታሪክ በዚህ መልኩ ተዋቅራ የቀናች አገር ከቶ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም/አይታወቅም። እንዲህ ያለ ነገር  ጥምር ጭንቀት የወለደው ቅዠት ብቻ ለመሆኑ ግን አስምሬበት ለማለፍ እወዳለሁ።  

ሃሳቤን ለመሰብሰብ ያክል ኢትዮጵያውያን በሰላም፣ እርስ በርስ ተቀራርበን በመነጋገር፣ በመወያየትና በመመካከር፣ ልዩነቶቻችንን አቻችለን ችግሮቻችንም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት እንደ አንድ መንግሥት ለመቆምና አገር ለማቅናት በመትጋት ፈንታ መነታረክን ከመረጥን ጊዜ ሳናጠፋ ደምም ሳይፋሰስ በሰላም ተመራርቀን የመሸናኘቱ ጉዳይ የሁሉም ሕዝቦች ህገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በድጋሜ ለማስታወስ እወዳለሁ።

  • ቅዱስ ጳውሎስ “ካልተገረዝኩ ሙቼ እገኛለሁ!” ሲሉ ህውከት ለፈጠሩ የገላትያ ሰዎች “የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ” እንዲል “እኔ ሥልጣን ላይ ካልወጣሁ …!” ብሎ የስልጣን፣ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ሽፋን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የመገንጠል ጥያቄ ያለው ሕዝብ ይቀንጠስ! ባይ ነኝ። ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች ለወሰዱት እርምጃ ተቃዋሚ እንጅ መገረዝን የሚያበረታታ ሰው እንዳልነረ ግልጽ ነው። በግሌ መገንጠልን የማበረታታ ሰው አይደለሁም።
  • የመገንጠል ጥያቄ ያለው፤ የሚበጀን መገንጠልን ነው! ብሎ የሚያምን ሕዝብ ግን ጥያቄው “ምኞች አይከለከልም!” ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን የመገንጠል ጥያቄ ያለው ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ጭምር መሆኑን ልናውቅ ይገባል ባይ ነኝ። “ይቀንጠስ!” የሚል ኃይለ ቃል ለመጠቀም የተገደድኩበት ዋና ምክንያትም በጽሑፌ መግቢያ ያሰፈርኩት የቃሉ ትርጓሜ  እንደተጠበቀ ሆኖ በኃይል የሚሆን ነገር የለም ብዬ ስለማምን ነው። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

May 10, 2012 

Advertisements