ለምን አድዋን ቆርጣችሁ ወደ ኤርትራ አትቀጥልዋትም!?

“አንባቢ ሆይ ይህን በፊትህ ላይ የተዘረጋውን ጽሑፍ* (ዋናው “መጽሐፍ” ነው የሚለው)  አንብበኽ ለመረዳት ከፈለግኽ ከሥር እስከ ጫፍ አንብበኽው ነው እንጅ አንዱን መስመር ወይም አንዱን አንቀጽ* (ዋናው “ምዕራፍ” ነው የሚለው) አንብበኽ አትፍረድ። አስከ መጨረሻው ዝለቀው ከዚያ በኋላ ፍርድ እስከ መጨረሻው ለማንበብ ፈቃድኽ ካልሆነ ግን ነገሩ ምንም እንደ ሆነ አትረዳውምና ጊዜኽን በከንቱ ይባክንብኸል ስለዚህ ባትጀምረው ይሻልኋል።” መቅድም ገጽ 12 [ነጋ ድረስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፡ መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፡ ንግድ ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ 1953 ዓም]

የጽሑፉ ዓላማ፥ 

የጽሑፉ ዓላማ ግልጽና አጭር ሲሆን ይኸውም፥ የትግራይ ሕዝብ ለሚደርስበት ታሪካዊ ውድቀትና ኪሳራ በተለመዶ “ህወሐት” ተብሎ የሚታወቀው የህ.ወ.ባ.ት [የህዝባዊ ወያኔ ባርነት ትግራይ] አባላት ግለሰቦች ተጠያቂዎች ናቸው! ሲል ለግንዛቤ ተጻፈ።

የጽሑፉ ውሱንነት 

ይህ ጽሑፍ በትግራይ ጠቅላይ ግዛት ያለውንና የተሰራፋውን ችግር የማይገልጸው ሥር የሰደደ ችግር ዙሪያ የሚያጠነጥን አጭር ጽሑፍ ነው። ጽሑፉ በይዘቱ ከክልሉ አልፎ የተረፈ የችግሩ ማዕከል አንድ ክፍል ያነጣጠረ ጽሑፍ እንጅ ሌሎች ተደራራቢ ችግሮችን አያነሳም። 

ሐተታ፥

ሁላችን እንደምናውቀው የታሪክ መዛጋብትም እንደሚያስረዱት የትግራይ ሕዝብ በከፋ መልኩ ለ17 ዓመታት በሞት ጥላ ሥር የነበረ፤ ከፍትህ ዕጦት የተነሳም የህልውናው መገለጫ ማንነቱ ተገፎ ሌላ እንዲመስል የተገደደና ረሀብ ተጨምሮበት ህልውናው ደብዝዞ የነበረ ሕዝብ ነው። ይህ በእንዲህ ሆኖ ሳለ ግን ጭብጥ የማይቀርብበት ደረቅ የኢሳት ፕሮፖጋንዳ ታክሎበት በአንዳንድ ጨለምተኛ አስተሳሰብ የነገሰባቸውና በጥላቻ የተጠመቁ አትራፊ ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች “ትግራይ ውስጥ ከሌሎች ክልሎች ይልቅ የተሻለ መሰረተ ልማት አለ” ተብሎ የሚወራው በሬ ወለደ ወሬ መስማትና ማንበብ የተለመደ ነው። ዳሩ ግን የሚነዛው ወሬ አማርኛ ተናጋሪ የሻዕቢያ ቡችላ ወይም ኢሳት እየደጋገመ የሚያስተጋባው ተራ ፕሮፖጋንዳ ከመሆን አልፎ “ትግራይ ውስጥ ከሌሎች ክልሎች ይልቅ የተሻለ መሰረተ ልማት አለ!” የሚል ግለሰብ ሆነ እንደ ግንቦት 7 ያለ ነውረኛ ድርጅት ለሚነዙት ያልተጨበጠ ወሬ በማስረጃ አስደግፈው ሲያቀርቡ ታይተውም ተሰምተውም አያውቁም። 

ለነገሩ ለእንዲህ ዓይነት ነጭ ቅጥፈት በሚከተለው ንጽጽራዊ ምሳሌ ቅጩን ላስረዳና ፋይሉን ዘግተን ወደሚቀጥለው እናዝግም። ሁለት የተለያዩ የአሜሪካ ጠቅላይ ግዛቶች ወስደን ያነጸጸርን እንደሆነ ለምሳሌ ያኽል የካሊፎርኒያ ጠቅላይ ግዛት ከኦክሎሃማ እንዲሁም  የኔቫዳ ጠቅላይ ግዛት ከቴክሳስ … ወዘተ በተናጠል በስቴት ደረጃ ያላቸውን ዕድገትና የምጣኔ ሀብት አንዱ ከሌላውን ያወዳደርን እንደሆነ በምሳሌነት የተጠቀሱ የአሜሪካ ጠቅላይ ግዞት እኩል ገጽታ የላቸውም። የፋብሪካ ዕቃም አይደሉምና እኩል ይሆኑ ዘንድ የሚጠብቅ ባለ አእምሮ አለ ብዬ አላምንም። 

ጣት ከጣት እንደሚበልጥ ሁሉ በብዙ ዓይነት ምክንያት አንዱ ከሌላው የሚለይበት መልክና ገጽታ ይኖረው ዘንድ ግድ ነው። “አይ የለም! ፌደራል መንግሥቱ (ስለ አሜሪካ ነው እየተናገርኩ ያለኹተይ) የለም! የለም! በዘር ተደራጀ የአንድ ብሔር አድላአዊ ሥርዓት ነው!” ለማለት የሚቃጣን ከሆነ ግን እውነትም ታመናል። በተረፈ “የትግራይ ሕዝብ በዘመነ ኢ.ህ.ዲ.ግ በልዩ መልኩ የተጠቀመ ሕዝብ ነው” ማለት የትግራይ ሕዝብ ጠጋ ብሎ አለማወቅ ነው። በተረፈ ይህ ኩልል ያለውን ሐቅ ማለትም ሕዝብና ሥርዓት በተናጠል ማየት ስንችልና ሲገባን ብቻ ነው ለድል የሚያበቃ ትግል ለመታገል የሚያችል አቅምም ሆነ የሞራል ብቃት ሊኖረን የሚችለው ለማለት እወዳለሁ።

የትግራይ ሕዝብ ለሚደርስበት ታሪካዊ ውድቀትና ኪሳራ ህ.ወ.ባ.ት ተጠያቂ ነው!

በተለያዩ ምክንያቶች በተሰበሰብክ ቁጥር በልተህና ጠጥተኽ “ከጓይላ”/ከጭፈራ ብዛትም የተነሳ ራስህን አድክመህ መበተን ደርግን ለመጣል እንደወጣ የቀረው ስፍር ቁጥር የሌለው ትግራዋይ ዓላማ ነበር ብዬ ነበር አላምንም። የምትሰባሰበው በዓላማ እስከሆነ ድረስ በመሰባሰብህ መልዕክት ማስተላለፍ፣ ሕዝብ የሚገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በማንሳት   ተገቢ የሆነ መጠየቅና የሕዝብህን ቅሬታ ማሰማት ይጠበቅበሃል። አንተም እንደ ሌላው የሳበር ታጋይ እንዳትሆን ብቻ ሳይሆን ስጋቴ ውለህ ስታድር ሊጥ እንዳትሆን ነው የምፈራው ።

ትግራይ ውስጥ የት ቦታ ከማን እንደተወለዱ እንኳን ማስረጃ የማያቀርቡ፤ በትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተቀመጡ፤ በትግራይ ሕዝብ ስም ሥልጣናቸውን አለ አግባብ በመጠቀም ሕዝብና አገር እየበደሉ ያሉ፤ የተጨማለቀና የዘቀጠ አስተዳደር ሰለባ የሆነው ሕዝብ ድምጽ ልትሆነው አይገባም ወይ? መሳሪያውን አስረክቦ ቁም ስቁልን እያየ ባለው ሕዝብ ፈንታ አቤት ማለት ይሳንህ ዘንድ አዚም ያደረገብህ ማን ነው? በውኑ የፈሰሰው ደምና የተከፈለው የህይወት መስዋዕትነት ተሰባስበህ ለመዝለል ነበርን? “እስክትሽም” ማለትን እየተቃወምኩ አይደለም። 

ለዓላማ በርሃ ላይ ወድቀው የቀሩት ሰማዕታት ሰውነት የሚከብረው ወንዶችና ሴቶች የትግራይ ልጆች ሳይሳሱ ነፍሳቸው የገበሩነት ዓላማ በመጠብቅ እንጅ በገዛ ሕዝባችን በደልና ግፍ፣ ብልሽውነትና ዝቅጠት ሥር ሰደው ሕዝብ ሲታወክ አይተህ እንዳለየህ ሰምተህም እንዳልሰማህ መሆንን ነው እየተቃወምኩ ያለኹተይ። የአንዲት ቀበሌ ልጆች፤ በደም የሚዛመዱ የአንድ ቤተ ሰብ አባላት፤ በእከክልኝ ልከክልህ የተሰባሰቡ ወረበሎች፤ ከዚህም አልፎ ባልና ሚስት የሰለጠኑባት ትግራይ ይዘህ ዝላይ፣ ጭፈራና ዳንኬራ ማብዛት መጨረሻው ያሳምረው ከማለት ውጭ ብዙ ማለቱ ትርፉ ድካም ብቻ ነው የሚሆነው። 

  • የትግራይ ሕዝብ በህዝባዊ ወያኔ ባርነት ትግራይ የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች እየታለለ ራሱን አጥቶ ከሌላውም ተቆራርጦ ሰላምና መረጋጋት በሌለባት ከተማ ተከቦ የተቀረው ዘመኑ በስጋት የሚገፋበት ምክንያት የለውም። 
  • የትግራይ ህዝብ በተለዋጭ ትግርኛ ተናጋሪ እጅ ዳግም የሚወድቅበት የሚረገጥበትና በድህነት አዘቅት ውስጥ ተዘፍቆ በረሃብ የሚቆላበት፣ በችግር የሚማቅቅበትና ከፍትህ እጦት የተነሳም ልበ ጠማሞች እጅ ላይ ወድቆ  ዳግም ህልውናውን በሚፈታተን መልኩ የሚንገዳገድበት አንዳች ምክንያት የለውም። ቀን የቆረጠለት ዕለት ይቆርጥለታል።
  • የትግራይ ሕዝብ ጉልበት እየበላ ያለው ‘የአድዋ’ ትምክህት መሰበር አለበት። ከስሩ መነቀል አለበት። ይህ የበላይነት፣ የጌትነትና በትዕቢት የተወጠረ ስብእና እርም መቆረጥ አለበት። በትግራይ ሕዝብ ሰማይ ላይ የተዘረጋ ‘የአድዋ’ ጥቁር መጋረጃ መቀደድ አለበት። 
  • ይህ ጠባብነት አይደለም – መሬት ላይ ያለው እውነት ነው። ይህ መከፋፈል ወይም ብሶትም አይደልም በትግራይ ክልል ውስጥ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ጠንቅ የሆነው የአንጃው በልሽውና መጠቆም ነው። ከፈለጉ አድዋን ቆርጠው ወደ ኤርትራ ይቀጥልዋት። ተነቅለው ይሂዱልን! ይህ ሕዝብ ግን [የትግራይ ሕዝብ ማለት ነው] ማንም ራርቶለት በቸርነት የሰተጠው ሳይሆን በዱር በገደል አልፎ፣ ጤዛ ልሶ፣ ድንጋይ ተንተርሶ፣  አዎ! አስራ ሰባት መርፌ ያለፈበት ቁምጣ ለብሶ፣ ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ የወደቀውን ወድቆ፣ የቆሰለውን ቆስሎ የደም ዋጋ ከፍሎ ያመጣውን ሰላምና የተጎናጸፈውን ነጻነት  እፎይ ብሎ ማጣጣም ይፈልጋል።
  • አበው “ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል ሲካፈል ይጣላል” እንዲሉ ዛሬ በውጭ ዓለም ተዘሎ ተቀምጦ ወያኔ ይውደም! ወያኔ አሸባሪ ነው! ወያኔ አንባገነን ነው! ዲሞክራሲ!፣ ነጻነት!፣ ፍትህ! ምንትሴ ቅብርጥሴ … በአጠቃላይ ባለ አጀንዳ የሚያስተጋባው ተራ ጩኸት ሳይቀንስ ሳይጨምር እሪ በማለቱና አፉን በመክፈቱ ብቻ ከፍትህ የሚያመልጥ የሚመስለው ትናንት ውስጡ ውስጡ ለአድዋና ለኤርትራ የበላይነት ስያቀነቅን የነበረ ቀልደኛ የአድዋ ተወላጅ እኩል ተጠያቂ ነው። ሲካፈል ሳይስማማ ቀርቶ የኮበለለ ኮብልሎ በምዕራቡ ዓለም እስከ ከተመበት ዕለት ደረስ ተስማምቶ ገድሎ በቀበራቸው የትግራይ ልጆች ነፍስ በወንጀል ከተጠያቂነት አያመልጥም። 

ታድያ ይህን ሁሉ የምለው በሌላኛው ክንፍ የተሰለፈ የሥልጣንና የአንድ ብሔር የበላይነት ጥያቄ ያለው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አውራ ጠላት የደርግ ቅሪት ሳይዘነጋ ነው። 

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 7, 2014

Advertisements