ነጻ ፕሬስ?!?

Eritrea #giant prison
 
መሪ ጥቅስ፥
“ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። 
ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ።
ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” [የማቴዎስ ወንጌል  25፥ 14 -30]
“ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ ፕሬስ የለም!፣ ሃሳብህን በነጻነት የመግለጽ አይቻልም!” ብለህ የምታምን ከሆነ አስመራ ሂደህ ሃሳብህን በነጻነት ለመግለጽ ሞክራት። ያህን ጊዜ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከወረቀት ያለፈ አንጻራዊ አማናዊ ትርጓሜው ይገባሃል።
ህግደፍ እንዲህ ብሎ ቀልድ አያውቅም። የተሰጠህን ከማነብነብ አልፈህ ሰው የሚያየውና የሚሰማው መጻፍና መናገር ቀርቶ “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት” በሃሳብ ደረጃ ያሰላሰልከው እንደሆነ ህግደፍ ጉድጓድ ቆፍሮ አይቀብርህም። አስቆፍሮ በቆፈርከው ጉድጓድ ይጨምርሃል እንጅ።

እንግዲያውስ ትግል ማለት ያለህን ቀብረህ ለወሬ፣ ለሀሜት፣ እና ለአሉባልታ መሰማራት እንዲሁም ማጉረምረም ሳይሆን በእጅህ ያለህን ይዘህ ለትርፍ መዝመት ነው። በነገራችን ላይ ይህን ለማድረግ ራሱ ሙያው የሚጠይቀው በቂ ትምህርት፣ እውቀትና ብቃት ግድ መሆኑን ሳይዘነጋ ነው። በተረፈ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር የምንፈለገው ዓይነት ሥርዓት ህጸጽ የሌለበት ሰማያዊ ስርዓት ካልሆነ በስተቀር በዚች ምድር የሰው ልጅ በታሪክ ከተጠያቂነት ነጻ የሆነበት ዘመን የለም።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 5, 2012

Advertisements