ሰላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ ተነበበ እንጅ አልተተረጎመም!

ሰላማዊ ትግል፥ በአመዛኙ ከማናቸውም የአመጽ ተግባራት በመራቅ፤ ራስህን ከህግ በታች አስገዝተህ/በማስገዛት ጥቅምህንና መብትህን ማስከበር የሚል ትርጓሜ እጅግ ቀረቤታ አለው። ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ወደኋላ መለስ ብለን ታሪክን የቃኘን እንደሆነ የሰላማዊ ትግል መሪዎች ከሌሎች የተለየ የፖለቲካ መርህና አቋም የሚያራምዱ የፖለቲካ መሪዎች ተለይተው የሚታወቁበት ልዩ ሰብእና የተላበሱ ግለሰቦች ሆነው ነው የምናገኛቸው። ከብዙ በጥቂቱ የተመለከትን እንደሆነ 

የሰላማዊ ትግል መሪዎች ገጽታ (በታሪክ)

 • በዋናነት አዳዲስ ሰላማዊ ሃሳቦች በማፍለቅ የሚታወቁ፤ 
 • ብዙሐኑ (ሕዝብ ያላየው) የማየት አቅም ያላቸው፤
 • በመልካም ሥነ ምግባራቸው  የተመሰከረላቸው፤
 • ከመንፈሳዊ/አእምሮአዊ እስራት ነጻ የወጡ/የተፈቱ፤
 • አርቆ አሳቢዎች፤
 • ከአድልዎ የጸዱ፤
 • አመጽን እጅግ አድርገው የሚጸየፉና የሚቃወሙ፤
 • በቃላት አጠቃቀማቸው ጭምቶች፤  
 • ቂም በቀል ብሎ ቋንቋ በህይወት መዝገባቸው ተፈልጎ የማይገኝባቸው፤ 
 • ለሕዝባቸው የተሰጠ ልብ ያላቸው፤ 
 • የሚሰሩትን የሚያውቁ፤
 • በስራቸው ግልጽነትና ቅንነት የሚያስቀድሙ፤ 
 • በተሰለፉበት መስክ በእውቀት የማይታሙ/የተፈተኑ ግለሰቦች ሆነው ነው የምናገኛቸው። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስመ “ሰለማዊ” ትግል እንቅስቃሴ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ አጠቃላይ ገጽታው በጥንቃቄ የመረመርን እንደሆነ በእውነቱ ነገር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰዎች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ገና የመቶ ዓመታት ጊዜ ሊያስፈልግ ነው። ይህ ደግሞ እርግማን ሳይሆን በመሪነት ሥፍራ ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች አሌ የማይባል ጉልህ ድክመት ነው።

በአገራችን የፖለቲካ ባህል ጠማማውን ጠማማ፣ ሰባራውን ደግሞ ሰበራ ከማለት ይልቅ እውነቱን እያድበሰበስን የራሱ ያልሆነውን በመስጠት መጥራት ነው የሚያሸልመው። ይህ ኋላቀር መገለጫ ማንነታችን – አባቶቻችን ምንም ዓይነት የቴክኖሎጂ ዕርዳታ ባልነበረበት ዘመን ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተሰራ ሃወልት ሲያቆሙና ቤት ሲገነቡ እኛ ደግሞ የሰው ልጅ መሬት ላይ ኑሮ መናኛ ሁኖበት ጨረቃ ለመርገጥ ወረፋ በያዘበት ዘመን ተንቀሳቃሽ “ድንጋይ”/በለዘበ አነጋገር ተመጭዋች ፍጥረቶች ሆነን እንድንቀር ተገደናል።

“ሰለማዊ” ሰልፍ ምን ለመሆን?

ትግል ሁለት አፍ ባለው ስለታም ሰይፍ ይመሰላል። ምን ነው? ቢሉ ትግል በጠላትነት የፈረጅከው (የምትፈርጀው) አካል ለመፋለም መሰለፍ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ትግል ከራስህ ጋር የምታደርገው ወይም የሚደረግ ትግልም ያቅፋል። በትግል ዓለም ውስጥ የዕለተ ዕለት እንቅስቃሴዎችህን መፈተሽ፣ ራስህን መመርመርና ሥራዎችህን መገምገም … ወዘተ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህ ሳይሆን የቀረ እንደሆነ ደግሞ ተፋልመህ ጠላትህን መጣል ይቅርና ውድቀትህን ማመቻቸት፣ የገዛ ራስህን ዕድሜ ማሳጠርና፣  ዕለተ ሞትህን ማፋጠን ብቻ ነው የሚሆነው። 

በነገር ሁሉ እንደ አህያ ከሁለት ሜትር በላይ አርቆ ለማየት ያልታደለ ታማኝ በየነ “ዋልድባ!፣ መጅሊስ!፣ ሳውዲ!፣ ጀማይካ! ታኒካ! … ወዘተ” እያለ ቢጮህና ቢንቀለቀል ግለሰቡ ኑሮውን የሚደጉምበት ሥራው/እንጀራው ነው። ታማኝ በየነ እየሆነው/እያደረገው ካለ የቅሌት ድርጊት ያለፈ ሌላ መሆን የማይችል “የማክሰኞ ፍጥረት” ነው። ለማሰብ ያልታደለ ጥሬ/ምስኪን እንደመሆኑም መጠን ከዚህ በላይ ምንም የሚፈጥረው ተአምር የለም። የማይገባኝ ነገር ቢኖር ግን በአገር ውስጥ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ህጋዊ ፈቃድና እውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ “የፖለቲካ” ድርጅቶች ነፋስ የሚፈጥራቸው ሁኔታዎች እያነፈነፉ “ሰልፍ” ብሎ ቋንቋ ነው ፈጽሞ ሊገባኝ ያልቻለ። 

ሰላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ ተነበበ እንጅ አልተተረጎመም!

ሁን ባለው ነባራዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ (አቅም በማጣት የተገደበ እንቅስቃሴ) “ሰላማዊ” ትግል ተብሎ የሚጠራ ከሆነ ታሪክ ሰርቶ ያለፈ ታሪክ የማይረሳው የጋንዲ እንቅስቃሴስ ምን ተብሎ ሊጠራ ይሆን? ጎበዝ! ሰላማዊ ትግል አጭር፣ ግልጽና ሁሉም በቀላሉ የሚገባው ግብና ዓላማ ያለው የትግል መስመር ለመሆኑ ማናችንም አንስተውም። ሰላማዊ ትግል፥

 • ጠላትህ ለይተህ ማወቅና ጠላትህን መትተህ የምትጥልበት መሳሪያ ማወቅ ነው።
 • ሰላማዊ ትግል ከሁከትና ከብጥብጥ ምንም ዓይነት ክፍል የሌለው የትግል መስመር ነው።
 • ሰላማዊ ትግል አእምሮ የሚጠይቅ የአእምሮ ስራ እንጅ ዜጎች በስሜታዊነት በመኮርኮር ለሁከትና ለግርግር ማሰለፍ አይደለም።
 • ሰላማዊ ትግል በየትኛውም መልኩ ከገዢዎችህ ተሽለህ መገኘት ነው።
 • ሰላማዊ ትግል ከግለ ጥቅምና ስልጣን ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለው ለሕዝብ ጥቅም የቆመ የህዝብ ትግል ነው።
 • ሰላምዊ ትግል ሀገራዊና ሕዝባዊ ትግል እንጅ ራስህን በሀገርና በሕዝብ ስም ደብቀህ የግል ጥቅምህን የምታሳድድበት መሳሪያም አይደለም።
 • ሰላማዊ ትግል በባዶ ጭኸት እየተንደረደርክ ከመንግሥት ጋር መላተም ማለት አይደለም።
 • ሰላማዊ ትግል ጫፍ ተይዞ መንጣጣት፣ ዘራፍ ማለትና አላስፈላጊ ዋጋ ለመክፈል መንቀልቀል አይደለም።
 • ሰላማዊ ትግል አጋጣሚ የሚፈጥራቸው ቀዳዳዎች ይዘህ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለትም አይደለም።
 • ሰላማዊ ትግል ያልተጣራ/ያልተጨበጠ ወሬ ይዘህ እንደ አውራ ዶሮ ከሰፈር ሰፈር መክለፍለፍም አይደለም። ጥጉ፥ ሰላማዊ ትግል፡ ሰፊው ሕዝብ ከጨቋኑ አካል ጋር ያለው ሸካራ ግኑኝነት መሰረት ሥርዓቱን የሚቃወምበት ዋና ምክንያት በተቀናጀና ወጥነት ባለው መልኩ ማስተማር፣ ማንቃት፣ ማሳወቅና መጎዳቱን ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ጠንቅቆ ያወቀ/የሚያውቅ ዜጋ ማስተባበር ነው። ይህን የማድረግ ሃላፊነት ደግሞ የመሪዎች ድርሻ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በ“ሰለማዊ” ትግል ስም የሚደረጉ አንዳንድ ሰልፎች ምን ዓይነት መልክና ይዘት እንዳላቸው በተጨማሪም “በሰላማዊ ትግል” ስም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች/ሰልፎች ምን ያህል ከሰለማዊ ትግል መርህ ጋር እንደሚርቁና እንደሚጋጩ በቀላሉ ላሳዮት። በአንድ ወቅት በከፍተኛ የሆነ ግርግር ፈጥሮ የነበረ ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ “ምኒሊክ ጨፍጫፊ፣ ገዳይ፣ … ነው!” በማለት ቃሉን በሰጠበት ሰሞን አከባቢ መሆኑ ነው በባህርዳር በተጠራ ሰልፍ የተሰማው መፎክር “አማራ ጨዋ እንጅ ፈሪ አይደለም!” የሚል ነበር። “በሰላማዊ” ስም ተሳቦ የተጠራው ሰልፍ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት እንግዲህ ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ። 

እኔ የምለው፥ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥ ለማምጣት ነው የሚፈለገው? ሕዝብን በዘፈን ስሜቱን በመቀስቀስ ነው  የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈለገው? ተራ ሁከትና መበጣበጥ በመፍጠር የሚመጣ ዓይነት ለውጥ ምን ዓይነት ለውጥ ነው? በግርግር ማኸል ተጠቃሚ የሚሆነውስ ማን ነው? በእውነቱ ነገር ሕዝብ ሰብስበህ የባለ ሥልጣናት ነውር በማውራት ምኒልክ ቤተ መንግሥት መግባት ይቻላል ብሎ ማሰብስ የጤና ነው? 
ሕዝብን ማደራጀት/ማንቃት ማለት አማራጮችህን ይዘህ በመቅረብ ፖሊስዎችን ማስተዋወቅ፣ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ትምህርት መስጠት፣ የሃስብ ብልጫ በማሳየትም የዜጎች ልብ መግዛት መሆኑ ቀርቶ በረባ ባልረባ ዜጎች ፀሐይ ማስመታት፤ ማለቂያ የሌላቸው መፎክሮች እያሸከምክ ጩኸህ ማስጮህ፤ በመንታርቦ የሕዝብ ጆሮ እስኪበሳ ድረስ መፎክር ማሰማት ምን ለመፍጠር ነው? በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነቱ ዓይነ መርፌው የጠፋበት እንቅስቃሴ “ሰላማዊ” ትግል ሳይሆን ተብሎ መጠራት ያለበት “የከተማ ውስጥ ሽብር” ተብሎ ነው መታወቅ የሚገባው። 

ሰልፍ በተጠራ ቁጥር መንገድ ለመንገድ እየተንቀዋለለ ጉሮሮውን እስኪደርቅ ድረስ ከሚጮኸው ዜጋ ማኸል ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚቃወምበት ምክንያት የሚያውቅ ስንቱ ነው? ተራውን ዜጋ ይቅርና በከፍተኛ ተቋማት ያለፉ፤ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመማር ያሉና የሚገኙ ዜጎች ምን ያክል ቁጥር ነው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ያነበበ? ማንበቡ ቀርቶ የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ውጫዊ የመጽሐፉ ሽፋኑ ቀለም የሚያውቅ ስንቱ ነው?

እንግዲያውስ የሰላማዊ ትግል መሪዎች ቀዳሚ ድርሻ በሕዝቦች መካከል ጸብን መዝራት፣ ሁከትንና ብጥብጥን ማበረታት፣ ለድንጋይ ውርወራ፣ ለተራ ስድብና ዝማሬ ማስተባበር ሳይሆን ሕዝብ መብቱንና ግዴታውን ያውቅ ዘንድ በእውቀት ማስታጠቅ፣ ማስተማርና መመገብ ነው። ለነገሩ ሰላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ ተነበበ እንጅ አልተተረጎመም! በማለት ሃሳቤን ብቋጭ ብዙ ከመድከም ይገላግለኛል።

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

March 4, 2013

Advertisements