“አንድ ነን” እየተባለ እርስ በርስ እየተነካከስን ከምንጠፋፋ ተለያይተን ብንለማ አይሻልም ወይ?

ጥብቅ ማሳሰቢያ፥

የጽሑፉ ሙሉ ይዘት ፖለቲካ እናውቃለን የሚሉ ልሒቃን [ዳያስፖራ] ብቻ ያነጣጠረ መልዕክት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕዝብ ይህን መልዕክት አይመለከተውም፤ አግኝቶ ቢያነበውም አይገባውም።

ሐተታ፥

የራሱ ቋንቋ፣ የራሱ ባህል፣ የራሱ የአመጋገብ ሥርዓት፣ የራሱ ታሪክ፣ የራሱ ሥልጣኔ ያለው የአማራ/የኦሮሞ/ትግራይ ሕዝብ ራሱን ችሎ እንደ አንድ መንግሥትና ሉዓላዊ ሕዝብ/አገር ቢቆም ማን ነው ቅር የሚለው? የራሱ ቋንቋ፣ የራሱ ባህል፣ የራሱ የአመጋገብ ሥርዓት፣ የራሱ ታሪክ፣ የራሱ ሥልጣኔ ካለው የትግራይ/የአማራ/የኦሮሞ ሕዝብ በአጠቃላይ አንዱ ከሌላው ምን የሚያገናኘው ነገር አለው? አንዱ ከሌላው ምን ያገናኘቸዋል? ለመሆኑ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸው በመያዛቸው [የየራሳቸው መንግሥት በማቆማቸው] የሚጎዳ ማን ነው? ልዩነቶቻቸውን አጥብበው እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑባት አገር ፈጥረው አንድ በመሆናቸውስ ተጠቃሚው ማን ነው?

ጎበዝ! የማያባራ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግርግር ከዚህ ቀደም እንዳብራራሁት በአጭር ቋንቋ ሲገለጽ ጥያቄው የሥልጣን ጥያቄ ነው። ጥያቄው የአንድ ብሔር የበላይነት ጥያቄ ነው። ታድያ እንዲህ ያለ ግልጽ የሆነ ጥያቄ (ችግር) ሙሉ በሙሉ ማለትም በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ሁሉንም የየራሱ በመስጠት በግል ንብረቱ ላይ ያሻውን እንዲሆን በመፍቀድ ነው። አይመስሎትም? 
አይደለም የጋራ ብሎ ነገር ሊኖራቸው፤ ጠባሳና የግፍ በደል ምልክት ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀርቶ አብራምና ሎጥም ተለያይተዋል። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘመን አገናኛቸው ዘመን ደግሞ ይለያያቸዋል። ወይስ በጦርነት የተገናኙ ሕዝቦች በጦርነት መለያየት አለባቸው ነው ነገሩ? ተመራርቀን ብንሸኛኝ አይሻልም? 
ጎበዝ ተለያይተህ በሰላም መኖር ከተቻለ መለያየት ምንም ነውር የለውም። እግዚአብሔር የማይወደው ሁከት፣ ጸብ፣ ደምነት፣ ግብዝነት፣ ረብሻና አመጽ ነው። ሕዝቦች የራሳቸው በመያዛቸው ብቻ እነዚህ ነገሮች ማስወገድ ከተቻላቸው ደግሞ “አንድነት” ምን ያደርግላቸዋል? ያይደለን ዳሩ ግን ለይስሙላ “አንድ ነን” እየተባለ እርስ በርስ ከምንጠፋፋ ተለያይተን ብንለማ አይሻልም ወይ? አንድነት ብሎ ደም መቃባትስ በምን ሂሳብ ነው ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው?

ግለሰቦች ሲባርቅባቸው መፎክር ስላስተጋቡ ሳይሆን ህጋዊ የሕዝብ ውክልና ያላቸው አካላት የሕዝባቸው ጥያቄ ይዘው ቢነሱና  ለምሳሌ፥ የኦሮሞ ሕዝብ ራስን የመቻል ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ኦሮሚያ አሁን ካለችበትና ከምትገኝበት በተሻለ ሁኔታ የሚያኖራት ከሆነ ምቀኝነት ካልሆነ በስተቀር የኦሮሞ ሕዝብ እድገት፣ መለወጥ፣ ሰላምና ብልጽግና የማይወጥለት ማን ነው? አማራ ሆነ ትግሬ ከኦሮሞ ሕዝብ ምን ጉዳይ ቢኖረው ነው የኦሮሞ ጥያቄ የማይዋጥለት? 

መጀመሪያውኑ እነዚህ ተጠቃሽ ሕዝቦች ልዩነታቸው አንድ ካላደረጋቸው በስተቀር አንዳችም አንድ የሚያደርግ የጋራ ነገር የላቸውም። ልዩነቶቻችችን በማጥበብ በወንማማች ፍቅር እርስ በርስ በመቀባበል አበረን ለመኖር  ከተሳነን፤ አንድ ሆነን ያቃተንን ተለያይተን ማስመዝገብ ከተቻለን  ለመለያየት ዘግይተናል ባይ ነኝ። ምን ነው? ቢሉ አንድም ራስን መቻል የአገር አንድነትን ማፍረስ አይደለምና። ራስን መቻል የራስህ የሆነ ነገር በራስህ ማከናወን እንጅ።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

March 1, 2014

Advertisements