አባቱ የደርግ ወታደር የነበረ ግለሰብ ህ.ወ.ሐ.ትን ቢራገም አይደንቀኝም!

ስለ ህ.ወ.ሐ.ት በጻፍኩ ቁጥር በህ.ወ.ሐ.ትና በህ.ወ.ባ.ት [ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ Vs. ህዝባዊ ወያነ ባርነት ትግራይ] ያለውን መጠነ ሰፊ ልዩነት፣ መገለጫና ምንነት እንደገና እንደ አዲስ የመጻፍ፣ የማብራራትና የመደጋገም ግዴታ አለብኝ ብዬ አላምንም። አሁን ከእንደገና ህ.ወ.ባ.ት [ህዝባዊ ወያነ ባርነት ትግራይ] ደግሞ ማን ነው በማለት ጥያቄ ለሚያነሳ ይህን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሰፊው በተከታታይ ለንባብ በበቁ ጽሑፎቼ በማያሻማ ቋንቋና አገላለጽ ግላዊ አቋሜን ግልጽ አድርጌአለሁ። 

ይህ በእንዲህ ሆኖ ሳለ ህወሐት 39ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አከበረ ተብሎ በአንዳንድ ‘ወገኖች’ ዘንድ እየተሰማ ያለው የማጉረምረም ድምጽ ተገቢና ፍትሐዊ እንዳልሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ። እንደ ህዝብ የትግራይ ሕዝብ ዋጋ ለከፈለበት የህይወት ምዕራፉ ቀን ሰይሞ የማክበር፣ ሰማዕታቱን የመዘከርና ልጆቹን የማሰብ ለድርድር የማይቀርብ የማይሸረፍ የማይቀነስ ሙሉ መብት አለው። ሌላው የሚያከብረው ስለሌለው የትግራይ ሕዝብ በዓሉን ማክበር የለበትም ብሎ የሚያምን ግለሰብ ሆነ ድርጅት ካለ ደግሞ የተጸናወተው በሽታ አድጎ ራሱን አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ ከመጨመሩ በፊት በአእምሮው የሚሰላስለውና የሚስበው ክፉ ሃሳብ ይመረምር ዘንድ የተገባ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ሻምፓኝ እየተራጨ አልነበረም/ተራጭቶ አይደለም በደም የሰከረና የተጨማለቀ፣ አንድ ትውልድ ሙሉ የቀሰፈ፣ ከሰው እንዳልተፈጠረ ለሰው ክብር የሌለው ወታደራዊ የደርግ መንግሥት የገረሰሰው። ዋጋ ተከፍሎበታል። ህይወት ተከፍሎበታል። ደም ፈሶበታል። ወላጆች ልጆቻቸው ፡ ልጆች ወላጆቻቸው አጥተውበታል። ታድያ ሐቁ ይህ ከሆነ፤ ህ.ወ.ሐ.ት ብሎ 60 ሺህ የትግራይ ልጆች ሰማዕታት እንጅ ህ.ወ.ሐ.ት ብሎ ግለሰብ አስከሌለ ድረስ፤  በተጨማሪም በሕዝብ ላይ ያለህን መራራና ስር የሰደደ ጥላቻ ለመግለጽ ካልሆነ በስተቀር ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም/መራገም ምን አመጣው? 

ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም፥ 

  • አራትና አምስት ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋ የቀበረች እናት ጡት አንደ መቁረጥ ነው።
  • ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም፥ በ60 ሺህ የትግራይ ልጆች መቃብር የስላቅ ዳንኬራ እንደመምታት ብሎም ሽንትህን እንደ መሽናት ነው።
  • ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም፥ የትግራይ ሕዝብ ለፍትህ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ እንደ እንድ የራሱ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ሥልጣኔና አስተሳሰብ ያለው ሕዝብ ለመቆም ያፈሰሰው ደም እንደ መቀለድ ነው። 
  • ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም፥ የትግራይ ሕዝብ ለ17 ዓመታ የከፈለው የህይወት መስዋዕነት ዋጋ እንደማሳጣት ነው። 
  • ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም፥ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እውቅና የመንፈግ፣ የማቃለል፣ የመስደብ፣ ብሎም በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጦርነትን እንደማወጅና መክፈት ይቆጠራል። 
  • ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም፥ የቀኝ ፖለቲካ አራማጆች [የጽንፈኞች] ልዩ መታወቂያ ነው። ጽንፈኝነት ደግሞ አገር ይበትናል እንጅ አንድ አያደርገንም።

ጥጉ፥ አገጣሚዎች ቢመቻቹ ረጋሚ ተረጋሚውን ሕዝብ ዳግም በባርነት ቀንበር ስር አውሎ በጭቆና አድቅቆ ለመግዛት የማይመልስ ኃይል ነው። ህ.ወ.ሐ.ትን መርገም ይሉት ይሄ ነው። የትግራይ ሕዝብ ታሪክ አለመቀበል  ማለት በሌላ አነጋገር የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ አለመቀበል ነውና። አይመስሎትም?

እንግዲያውስ፥ አባቱ የደርግ ወታደር የነበረ፣ በሩስያ ዱቄትና ዘይት ያደገ (ልጆቹን ያሳደገ)፣ የተባለውን ሳያላምጥ ከማራገብ የዘለለ የጠለቀ ግንዛቤ፣ መረዳትና ማስተዋል የሌለው ግለሰብ ካልሆነ በስተቀር ይህ ይሆን ዘንድ የሚፈቅድ ግለሰብም ሆነ ሕዝብ ማን ነው? የለም! አይኖርምም። 
 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Feb. 26, 2013

Advertisements