ግራ ጉንጬን መልሼ ልሰጥህ ይቅርና ቀኜስ ቢሆን እስክታጮለኝ ድረስ ለምን እጠብቃለሁ?

ኢትዮጵያውያን ከዓለም ሆነ ከአህጉራችን ከአፍሪካ አንደኛ ያልሆንበት መስክ ፈልገህ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። መነጋገሪያ ሆኖ በሚነሳ ርዕሰ ጉዳይ/አጀንዳ ሁሉ አንደኛ መሆናችንን ማወጅ ነው የሚቀናን። ነን ብለን የምናምነው ሆነ የምንናገረው ነገር ምን ያህል እውነትነት አለው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ዳኛ መሰየም አያስፈልገውም። የአገሪትዋና የሕዝቦችዋ ነባራዊ ሁኔታ መመለከት በቂ ነው ብዬ ነው የማምነው። ነገር ለማሳጠር ያክል፥ ኢትዮጵያውያን መጽሐፍ ቅዱስ በተሳሳተ መንገድ ማንበብና መተርጎም ብሎም መሰረት በሌለው አንድምታ ማንበልበል እውነትም አንደኞች ነን ለማለት ፈልጌ ነው።

 • “ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል።”
አንደኛ፡ ይህ የመልዕክት ክፍል ኢየሱስ ከሕግ አንጻር (የፍርድ ቤት ሂደት ማዕከል ያደረገ) የሰጠው ትምህርት ነው። በሙሴ ዘመን አንድ ሰው የሰው ጥርስ ስላወለቀ መንገድ ላይ አግኝተህ/ጠብቀህ ጥርሱን አውልቀው ወይም ማውለቅ ማለት አይደለም። በሙሴ ዘመን የሰው ጥርስ ያወለቀ ሰው ጥርሱ የሚወልቀው ራሱ የቻለ የፍትህ ሂደት አለው። ዳሩ ግን የኢየሱስ በነበረበት ዘመን ይህን የሙሴ ሕግ አለ አግባብ የመጠቀም አዝማምያ በሰፊው ይታይ ስለ ነበረ ኢየሱስ የሰጠው ትምህርትም ከዚህ አንጻር ነው። የኢየሱስ ብሉያትን መሰረት ያደረገ ምሳልያዊ አነጋገር ለመረዳት ደግሞ የሙሴ የሕግ መጻህፍት ፍቺና ትርጓሜ ጠንቅቆ ማወቅ ይጠይቃል። ካልሆነ ደግሞ መጠነኛ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል።

ሁለተኛ፡ በአይሁድ ባህል ሰውን በጥፊ ማጮል ማለት ጥፊው ሊያደርሰው ስለሚችል ጉዳት ሳይሆን ዋናው ነገሩ ሰውን በጥፊ ማለት ከፍተኛ የውርደት ምልክት ወይንም ስድብን ነው የሚያመላክተው። በኢየሱስ ዘመን አንድ አይሁድ ከምትሰድበው ይልቅ አካላዊ ጉዳት ብታደርስበት ነው የሚሻለው ወይም የሚመርጠው። ታድያ ኢየሱስ እያለ ያለው አንድ ሰው  ከመሬት ተነስቶ በስድብ መዓት ቢያጣድፍህ አንተም አጸፌታውን ለመመለስ ቁመህ እሳት አታንድድ፤ ነገር አብርድ! ነው እያለ ያለ እንጅ ስትደበደብ ቁመህ ተደብደብ አይደለም እያለ ያለው። 

ሦስተኛ፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የህይወት ቃል (ትምህርት) የተለወጠ ሰው አዲስ ማንነት መግለጹ ነው። በክርስትና ማመን ወይም ክርስቲያን መሆን ማለት ሞኝ ነህ/ነው ማለትም አይደለም።
አራተኛ፡ ይህ ቃል በምንም ዓይነት መልኩ በዳይ ወይም አመጻኛን የሚያበረታታ ቃል አይደለም።
አምስተኛ፡ ከዚህ የተነሳ የዚህ ቃል ወይም የኢየሱስ ትምህርት አንኳር መልዕክት – በቀልን ተዉ፤ ለነገር አትፍጠኑ፤ መታገስን ተማሩ፤ ነገርን ማሳለፍ ተለማመዱ የሚል ትምህርት እንጅ ሞኝነትን አይሰብክም። እነዚህና ሌሎች በዚህ ጽሑፍ ያልተካተቱና ያልተዘረዘሩ ጭብጦች በሚገባ መረዳት ኢየሱስ በምሳሌ የተናገረው ቃል ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት በቀላሉ ይገባን ዘንድ ይረዳል።

ወጣም ወረደ፡ ኢየሱስ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን/አማኝ በሚሰነዘርበት ማንኛውም ጥቃት ራሱን መከላከል የለበትም ብሎ አያስተምርም። በአጠቃላይ የዚህ ቃል ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሥነ መለኮታዊ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድምታ የተመለከትን እንደሆነ ስለ አካላዊ ጥቃት አይደለም የሚናገረው። ክፉን በክፉ አትመልስ ነው መልዕክቱ። ለነገር  ቁመህ አትጠብቅ ነው። ከበቀል ራስህን አርቅ/ጠብቅ ነው። ግትርነትን ወጊድ በል ነው። ለነገር ዕድል ፈንታ አትስጠው፤

 • ዘወር ማለትን፣ 
 • ነገር ማሳለፍ፣ 
 • መታገስ፣ 
 • መቻል፣
 • ሆደ ሰፊ መሆን፣ 
 • በቀላሉ ቱግ አለማለትን፤ አንድ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምን የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ/ደቀ መዝሙር ተለይቶ የሚታወቅበት የአዲስ ሰው ማንነት መገለጫ ነውና ይህን በምሳሌ ማስተማሩ ነው።

“ምን ታየኛለህ?” ብሎ ነገር የሚቆሰቁስና እሳት የሚያነድ ነገረኛ ፍጥረት እኮ ሞልተዋል። ታድያ ለእንዲህ ዓይነቱ ትምክህተኛ/ነገረኛ ሰው “ምን ይላል ይሄ  … ምን የሚታይ ፊት አለህ ነውና … ሰው መሳይ .. ወዘተ” በማለት ለጸብ ዕድል ከመስጠት ዞር ማለትን ምርጫ ስለ ማድረግ ነው የኢየሱስ ትምህርት ዓላማ።

ጥጉ፥

 • ስለ ጠላኸኝ መልሼ አልጠላህም፤
 • ስለ ረገምከኝም መልሼ አልረግምህም፤  
 • በአሉባልታ ስሜን ብታጠፋና ብታሳድደኝ ስለ አንተ መጸለይን አልተውም፤
 • ዳሩ ግን አካላዊ ጉዳት ታደርስብኝ ዘንድ ታጥቀህ ስታበቃ “ሙሉጌታ” [እዚህ ቦታ ላይ የራስዎን ስም/የብሔርዎ መጠሪያ ያስገቡ] ቁሞ ይጠብቀኛል ብለህ ራስህን እንዳታታልል። ሐቁ፥ ግራ ጉንጬን መልሼ ልሰጥህ ይቅርና ቀኜስ ቢሆን እስክታጮለኝ ድረስ ለምን እጠብቃለሁ? ነው ጥያቄው። እንግዲያውስ ያን ጊዜ የእኔ ሳይሆን የአንተ ነው ይዞር ዘንድ የሚገደደው።
ጠቃለያ፥

ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ሕዝብ ራሱን ከጥቃት የመከላከል ተፈጥሮአዊ ህጋዊና ሞራላዊ መብት አለው! የሚል እምነት የዛሬ ዕለት ጽሑፌ ዋና መልዕክት ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

February 25, 2013

Advertisements