ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ “ከኢትዮጵያ ጋር መታረቅ ስለሚባለው ባልሰማውና ባላስበው እመርጣለሁ” አላሉም!

Salsaywoyane PIA

ሰው ሞተ ሲባል እንዲህ ያምርበታል ወይ?

ፈላስፋው አምሮባቸዋል። ሰውነታቸው ብቻ ሳይሆን ቀልድም ጨምረዋል። ከጥቂት ወራት በፊት መሆኑ ነው የፕሬዝዳንቱ ለጥቂት ቀናት ከቴሌቪዥን መስኮት መሰወር ተከትሎ ይሁን ከጀርባው ሌላ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ተሰልቶ የተሰራጨ የፈጠራ ወሬ ለመሆኑ በውል በማይታወቅ ኢሳይያስ አፈወርቂ ዳግም ሊያንሰራሩ በማይችሉበት ሁኔታ አልጋ ላይ መውደቃቸው የሚያስተጋባ በበርካታ የአማርኛ ድረ ገጾች የምዋርት ዜና አንብቤ ነበር። ብዙ አልቆየም በቀናት ውስጥ ፕሬዝዳንቱ ከነ ሙሉ ጤናቸው በሱዳን መታየታቸው የሚያስነብብ በፎቶ ግራፍ የተደገፈ ዜና ሳነብ በስማ በለው የወሬ  መጋኛ ክፉኛ የተለከፈ ማህበረሰብ በመታዘብ ነበር ነገሩን ያለፍኩት።

እ.አ.አ 2013 በዓመቱ መጨረሻ በኬንያ ዋና ከተማ በናይሮቢ በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ በርካታ ኤርትራውያን በተገኙበት በኤርትራ ኤምባሲ ቅጽር ግቢ ተገኝተው ያደረጉት ረጅም ንግግር ብቻ ሳይሆን በኤርትራ ምድር በህልም ካልሆነ በስተቀር በውን የማይታሰብ ጥይት የማይበሳው ቂጣ ሲገምጡ የተመለከተና ያደመጠ ሰው፤ ሰውዬው አይደለም ለሞት የሚያበቃ በሽታ ሊኖራቸው ቀርቶ ጭራሽኑ የታመመ ሰው እንደማያውቁ ነው ልያረጋግጥ የሚችለው። በበኩሌ ምሥጢሩ ባይገኝም ሰው ሞተ ሲባል እንዲህ ያምርበታል ወይ? ቢያለሁ።

ስለ ፈላስፋው በጥቂቱ፥

ስለ ፈላስፋው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አጠቃላይ ሁኔታ “በሃሳብ ደረጃ” አንድ ነገር ልበልና በቀጥታ ወደ ቁምነገሬ አልፋለሁ። አዲስቷ አገር የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት መንስኤዎችና መፍሔዎቹ በተመለከተ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ  በእውነቱ ነገር ሊቅነታቸው አስመስክሯል። አሜሪካንም አላስቀሩላትም። በአሜሪካ መንግሥት ሴረኝነት መንግሥታቸውና አገራቸው ኤርትራ ምን ያህል እንደተጎዱ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ቀልዱንና ስላቁን ትተው ከአንጀታቸው አምርረው ሲናገሩ የሰማሁ ገና ዛሬ ነው። ፈላስፋው ሰሚ ጆሮ ላለው ሰው ብዙ ትምህርት የሚገኝበት ቁምነገር አስጨብጠዋል። አቅም ቢኖራቸው ምጽዋ ላይ ተቀምጠው “አሜሪካ፡ መካነ ሰይጣን ይህም ሲያንስሽ ነው!” እያሉ አፈር ድሜዋን ከማብላት የሚገታቸው አንዳች ምክንያት እንደሌለ ጠቆም አድርገው አልፈዋል። የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ አንስተውም ማለፍያ ትንተና ሰጥተዋል። 

ምን አለፋዎት፥ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የአገር መሪ ሳይሆን የፖለቲካ ተንታኝ ቢሆኑ ኖሮ በእውነቱ ነገር ፕሬዝዳንቱ የተዋጣለት ዓለም አቀፍ ስመ ገናና ተንታኝ ይወጣቸው ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን በዓቃቤ መቃብርነት የምታውቃቸው ዓለም በአስተዋይነታቸው፣ በፖለቲካ ሊቅነታቸው፣ በማህበራዊ ፈልስፍናቸው በአጠቃላይ በመልካም ስም ታውቃቸውና የላቀ ክብር ትቸርላቸው ነበር። ዳሩ ግን ፈላስፋው ከልጅነት እስከ እውቀት የተመገቡት ትምህርት ከሰውም ከፈጣሪም፤ ከቅርቡም ከሩቁም የማያግባባና የማያስማማ ሆነና ለዚህ ሁሉ ክብር አልታጩም። ታድያ ፈላስፋው አገር ገንብተው ትውልድ ሊያቀኑ ይቅርና ጣሊያን ሰርቶ በአደራ ያስረከባቸው አገር ውኃና መብራት አሳጥተው፤ ብሎም ሰው አልባ አድርገው ለዘፈን የበረታ ምላስ ብቻ አስከትለው ብቻቸው መቅረታቸው ሳይዘነጋ ነው።

ክፉ ወሬ “በባህሪው” ነፋስ ነው!

ክፉ ወሬ “በባህሪው” ነፋስ ነው። መጀመሪያውኑ የክፉ ወሬ ሰለባ ላለመሆን ራስህን መጠንቀቅ ነው እንጅ አንዴ ስምዎ በክፉ ከተነሳ የፈሰሰ ውሃ ብቻ ሳይሆን የማይታፈሰው ድውይ የተነፈሰው ወሬም እንዲሁ ፈረሰኛ አይመልሰውም። ይህ ደግሞ በዕለት ዕለት ኑሮአችን የምናየው እውነታ ነው። አንዳንዶቻችንም የክፉዎች ጎጆ ማሞቅያ የክፉ ወሬ ሰለባዎችም ነን። 

በስነ ጽሑፍ ዓለም የሰውን ስም በመጥቀስ ለመጻፍ ቢያንስ ቢያንስ አንደኛ፡ ሰውዬው ቃል በቃል የተናገረው ቃል ሊኖር ይገባል። ሁለተኛ፡ የተናጋሪው ሃሳብ በመጭመቅ አጠቃላይ መልዕክቱን (ጭብጥ) ለማስቀመጥ የተፈለገ እንደሆነ ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም የፈጠራ ሥራ ግን ጋጠወጥነት ብቻ ሳይሆን በሕግ ፊት የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው። 

የጋዜጠኛው ጥያቄ ቃል በቃል የሚከተለውን ይመስላል፥ 

“ኤርትራንና ኢትዮጵያን ለማቀራረብ የሚካሄድ የዕርቅ ሙከራዎች እንዳለ የሚያመላክቱ የሚዲያ ምልከታዎች አለ” ይህ እውነት ነው? እውነትነት አለው? እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ ጉዳይ የመጣ አዲስ ዕድገት አለ? 

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጥያቄው ሲመልሱ እንዲህ ይላሉ፥ 

“የለም! እንደዛ የሚባል ነገር የለም። እንዲህ ያለ ሙከራ አለ፤  እንዲህ ተባለ፤  ምናምን የሚባል ወያኔ እስክትጠፋ ድረስ እንደዛ እያለች የሕዝብ ግንኙነት ብልጫ ታገኝ ዘንድ እንደሆነ ነው።” ይቀጥላል። 

ዋናው ቁምነገሩ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ሦስት ቁምነገሮች ነክተው አልፈዋል። 

  • አንደኛ፡ የመንግሥታቸው አቋም 
  • ሁለተኛ፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እስስታዊ ባህሪ 
  • ሦስት፡ የአሜሪካ መንግሥት ቀላዋጭነትና ሴራ በማስመልከት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አንደ አንድ የአገር መሪ በውጭም በውስጥም የሚገኝ የኤርትራ ሕዝብ እንደህ ዓይነቱ ተራ ተባራራ ወሬ በማሰላሰልና በማመላለስ ራሱን ጠልፎ እንዳይጥል፣ በአሉባልታ እንዳይጠመድና ጊዜውን በከንቱ እንዳያባክን መምከራቸው እንጅ አንድም ቦታ ላይ በሪፖርተር ጋዜጣ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ “አሉ” ተብሎ ለንባብ የበቃ ጽሑፍ ከፕሬዝዳንቱ አንደበት አይሰማም።

ሪፖርተር፡ የግል ጋዜጣ መሆኑ ቀርቶ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው?

በነገራችን ላይ ሪፖርተር ጋዜጣ እ.አ.አ የካቲት 12/2014 “ከኢትዮጵያ ጋር መታረቅ ስለሚባለው ባልሰማውና ባላስበው እመርጣለሁ” ሲል ለንባብ ያበቃው ህትመት ከድረ ገጹ ከማንበቤ በፊት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ከአገሪቱ ሁለት የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጋዜጠኞች ጋር ያደርጉትን ቃለ ምልልስ መሉ ይዘት ተከታትያለሁ።

ሪፖርተር ጋዜጣ ካነበብኩ በኋላም እንደሆነ ጋዜጣው በርዕሱ ይዞት የወጣው ዐረፍተ ነገር ተገርሜ “እንዴት ይህን ቃል ሳልሰማ?” በሚል መንፈስ ቃለ ምልልሱን ለማዳመጥ ያባከንኩት ሁለት ሰዓት ሙሉ እንደ እሳት እየበላኝና እያንገበበኝ በቁጭት ነበር ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ለማድመጥ የተገደድኩ። ይህን ያደረኩበት ዋና ምክንያት ሪፖርተር ጋዜጣ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ “አሉ” ብሎ ያስነበበው ጽሑፍ አለማለታቸው እርግጠኛ ስለ ነበርኩ ነው። ሁለት ሰዓት ሙሉ ቁጭ ብዬ የሰው ንግግር ሳደምጥ መጎለት አምሮብኝ እንዳልተቀመጥኩም እርግጠኛ ነበርኩ። 

ጥያቄው ሪፖርተር ጋዜጣ ይህን የወረደ ሥራ ይዞ ለመውጣት ሲወስን ምን አተርፋለሁ ብሎ ነው? ሪፖርተር  የግል ጋዜጣ መሆኑ ቀርቶ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው? ለመሆኑ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ቃል በቃል “ከኢትዮጵያ ጋር መታረቅ ስለሚባለው ባልሰማውና ባላስበው እመርጣለሁ” ብለው የተናገሩበት ቦታ ሊኖር ቀርቶ “አሉ” ተብሎ የተጻፈውን ቃል በፍቺ ደረጃ “ብለዋል” ለማለት የሚያስችል የሰነዘሩት አስተያየት የት ስፍራ ነው? የት ቦታ ነው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ “አሉ” ተብሎ በሪፖርተር ጋዜጣ ለንባብ የበቃ ጽሑፍ የተናገሩት? ፕሬዝዳንቱ ለጸሐፊው ለብቻው [በህልም መሆኑ ነው] በሰጡት ቃል መጠይቅ ካልሆነ በስተቀር ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ለኤርትራ ጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ አንድም ቦታ ላይ ይህን ቃል አልተናገሩም። ይህን ሐቅ ለማረጋገጥ ከተፈለገ ሪፖርተር ያለውን አሜን ብሎ ከመቀበል ይልቅ “እውነት ኢሳይያስ አፈወርቂ ይህን ብለዋልን?” በማለት ራሳችን በመጠየቅ የተናጋሪው ሙሉ ቃል በማዳመጥ ሐቁ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። 

እውነት ለመናገር ከሁሉም በላይ ያሳዘነኝ ነገር ቢኖር የሪፖርተር ጋዜጣ የወረደ ሥራ ሳይሆን ያገኙትን ሳያላምጡ ከመለጠፍ የማይቦዝኑ ድረ ገጾች ሁኔታ ነው። ይህኔ የሚጠጣ መዝርም ቢሆን ግራ ቀኝዋን ሳታጣራ መለጠፍ የለመደች ነፍስ መርዝኑም ሳታይ መጨለጥዋ አይቀርም ነበርና የመዋች ቁጥር ለቀባሪዎች ከባድ ዕዳ ነበር የሚሆነው። በነገራችን ላይ አሜሪካ ሂሮሽማን ናጋሳኪን እንዳልነበረች ያወደመችበት ዋና ምክንያት በአሜሪካውንያንና በጃፓናውያን መካከል በዘመኑ በነበረው የቴሌ ግራም ግኑኝነት በተፈጠረ የትርጉም ስተት የተነሳ ነበር። 

የዚህ ጽሑፍ ዋና መልዕክት ሪፖርተር ጋዜጣ እ.አ.አ የካቲት 12/2014 ዕትሙ ላይ የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ “እንዲህ ሲሉ ተናገሩ” በማለት ይዞት የወጣ በሬ ወለደ ጽሑፍ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ቃል በቃል ሆነ በአንድምታ ደረጃ አላሉም ለማለት እንጅ ኢሳይያስ አፈወርቂ ሰላም ወዳድ ናቸው አላልኩም። ፈላስፋው ሰላም ብሎ ነገር “ለባህሪያቸው” እንደማይስማማቸውማ ድፍን ዓለም የሚያውቀውና የሚስማማበት ሐቅ ነው። ጦርነት፣ ሁከት፣ ወከባና የሽብር ድርጊት እንደሆነ የህግደፍ ህገ መንግሥት ነው። 

ጸሐፊው የፕሬዝዳንቱ ቃል ሲተረጉም በአእምሮው ውስጥ ምን ይመላለስ እንደነበረ ‘እግዚሃር’ ብቻ ነው የሚያውቀው፡ 

በሰው አእምሮ ውስጥ ዕብደት፣ ዝና፣ ልቅ ወሲባዊ አመንዝራነት፣ ገንዘብ፣ ታላቅነት ጨምሮ ብዙ የሚመላለስ  ከንቱ ሃሳብ አለና “ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ “ከኢትዮጵያ ጋር መታረቅ ስለሚባለው ባልሰማውና ባላስበው እመርጣለሁ” ‘አሉ’ ወይም ‘ብለው የተናገሩ” ብሎ ከትግርኛ ወደ አማርኛ የመለሰ ወይም የተረጎመ እንዲሁም የጻፈና ያሳተመ ግለሰብ በአእምሮው ምን ይመላለስ እንደ ነበረና ምን እያሰበም እንደ ነበር ለመገመት በጣም ከባድ ነው። ጸሐፊው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከአገሪቱ ጋዜጠኞች በትግርኛ ቋንቋ ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ከፍቶ በሚሰማበት ወቅት በአእምሮው ውስጥ ምን ዓይነት ምናባዊ ሃሳቦች ይመላለሱ እንደ ነበር ግለሰቡ/ጸሐፊውና እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቁት። 

በተረፈ ጽሑፉን ያቀረበ ግለሰብ ምንም እንኳን ስሙ በተደጋጋሚ በሪፖርተር ጋዜጣ ባየውም ግለሰቡ መደበኛ ጋዜጠኛ ይሁን ተባራራ ዓምደኛ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም። ወጣም ወረደ የሪፖርተር ጋዜጣ ኢዲቶሪያል ክፍል የእንዲህ ዓይነት ዓይን ያፈጠጠ ርካሽ ፕሮፖጋንዳ ተባባሪ ካልሆነ በስተቀር ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚሻቸው ጉዳዮች ያሳየው ንህዝላልነት እጅግ የሚያሳዝን ነው። በአንባቢዎቹ ዘንድ ሊኖረው የሚችለው ተአማኝነትም ያጎድልበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሳት የወሬ እሳት አንሶት ሪፖርተር ይጨመርበት?

“ሁላችንም ዜሮ” ጋብዦታለሁ፥ 

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ “የለም! እንደዛ የሚባል ነገር የለም።” ሲሉ የኢፌዲሪ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው የኤርትራ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ እስካላደረገ ድረስ ምንም ዓይነት የሁለትዮሽ ድርድር እንደሌለና ሊኖርም እንደማይችል በሚድያ ቢገልጹም ሁሉቱም መንግሥታት በሁለቱ አገራት መካከል ስላለ ነባራዊ ሁኔታ ተጠይቀው በየፊናቸው በሚድያ የሰጡት ቃል ብቻ አምነን በመቀበል በኢትዮ – ኤርትራ ጉዳይ ሁለቱም መንግሥታት ፖለቲካዊ ድርድር ወይም ስምምነት ላይ ለመድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም! ወይም ሊኖርም አይችልም! ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ የዋህነት ነው። መንግሥት የሚሰራው ሥራ ህዝብ የማወቅ መብት ቢኖረው ኖሮ መንግሥት ብሎ ነገር ባላስፈለገ ነበር።

ጎበዝ! በሁለቱ መንግሥታት መካከል ምን እየሆነና እየተሰራ እንዳለ በቂ መረጃ ያለው የጨዋታው ባለ ቤቶች የሆኑ ሁለቱም መንግሥታት ብቻ ናቸው የሚያውቁት። በተረፈ ሁላችንም ዜሮ ጋብዦታለሁ። 

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

February 18, 2014

Advertisements