የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ!

ጥብቅ ማሳሰቢያ፥

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ህገ መንግሥት አንቀጽ 39 ለማራገብ አይደለም። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንደተለመደው ግላዊና ሞያዊ አመለካከታቸው ከማተት ያለፈ ከተጠቀሰው አካል ምንም የሚያገናኝ ምዕራፍ የላቸውም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጽሑፉ በይዘቱ በምንም ዓይነት መልኩ መገንጠልን የሚያበረታታ ጽሑፍ አይደለም። ታድያ ነባራዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግምት ውስጥ ያላስገቡ በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ በሚኖሩ አንዳንድ በንጹሐን ዜጎች ነፍስ የሚቆምሩ ለትርፍ የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መሪዎችና ተከታዮቻቸው ዘንድ በሰፊው የሚራገበው አንድን ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻና የልዩነት አቀንቃኞች ልከኛ መልስ ይሰጣል።

ቅምሻ፥

የመማር ዕድል ያላጋጠመው የኢትዮጵያ ገበሬ፤ እንዲሁም በቀንም በሌሊትም ከቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ የማይታጡ ደጋግ እናቶችና ከእንቅልፍ እንደተነሱ አፈር በራሳቸው ላይ እያቦነኑና እየነሰነሱ ለመጫወት የሚቸኩሉ ግራ ቀኛቸውን ለይተው የማያውቁ ህጻናት፥ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፣ አገር፣ ማንነት፣ ዜግነት እና የመሳሰሉ በይዘታቸው ከመላ ጎደል ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ቁልፍ ቃላቶች ትርጓሜና ፊቺ አብጠርጥረው እንዲያውቁ አይጠበቅባቸውም። ብዙ ከሚያውቅ ብዙ እንደሚጠበቅበት ሁሉ ግን “ፖለቲካ አውቃለሁ!” ከሚል ግለሰብ አጉል ድፍረት የሚወልደው ደመ ነፍሳዊ አነጋገር አስወግዶ ፖለቲካዊ ቃላቶች በፖለቲካ መንጽር ማየትና ማስቀመጥ ይጠበቅበታል። 

  • በትርጉም ደረጃ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፣ አገር፣ ማንነት፣ ዜግነት በተናጠል ግልጽ በሆነ ቋንቋ ለይቶ የማያስቀምጥና የማይተረጉም ግለሰብ፤ [ዋላ ጋዜጠኛ/ፕሮፌሰር] አይደለም በግንባር ቀደምትነት ለተቃውሞ ሊሰለፍ በእውነቱ ነገር በራሱ ሊያፍር ይገባዋል። እንዲህ ያለ የፖለቲካ ዝቅጠት ውስጥ የተነከረ፤ በተጨማሪም የግልና የቡድን (የብሔር – ብሔሰቦች) መብት የማይለይ (ለይቶ የማያውቅ) ስመ ፖለቲከኛ ግለሰብ ሊኖረው የሚችል መብት አፉ እንዳመጣለት መናገርና መጻፍ ሳይሆን ራሱን በገመድ አንቆ የመግደል መብት ብቻ ነው ሊኖረው የሚችለው። አንዳንዱ አጉል ተመጻዳቂ ተማርኩት የሚለውን ትምህርት አይደለም አደበባይ ሊወጣና ሊታይበት ተማርኩት የሚለው ትምህርት ራሱ መልሶ መማር ይጠበቅበታል።   አይመስሎትም?

መጽሐፍ “ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ” እንዲል በዚህ አጋጣሚ አንዳንድ ከሰፊው ሕዝብ የተሻለ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ዳሩ ግን በአንድም በሌላም መንገድ በፖለቲካ የአመራር ቦታ ላይ ሳይቀር የተቀመጡ ግሳንግስ ግለሰቦች የወረደ አሳፋሪ ፖለቲካዊ ስብእና የሚሰማኝኝ ጥልቅ ሃዘን ለመግለጽ እወዳለሁ። 

ሐተታ፥

ዓለም በፀሐይ ብርሃን ፍጥነት ወደ ፊት በምትገሰግስበት ረቂቅ ዘመን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ወደኋላ ተመልሰው በዘውዳዊና ደርጋዊ ዓይነቱ ጨፍላቂ፣ አውዳሚና በዥባዥ የባርነት ሥርዓት ዳግም በቀንበር የሚያዙበት ምክንያት ምንም አይታየኝም። 

የፈለግነውን ስም እንስጠው ዋላ “የብሔር ፖለቲካ” በለው፦ ኢትዮጵያ እንደ አንዲት ሉዓላዊት አገር እንድትቀጥል፤ ሕዝቦችዋም በእኩልነት፣ በሰላምና በመቀባባል እንዲኖሩ ከተፈለገ ብሔር ብሔረሰቦች እንደ አንድ ሉዓላዊ ሕዝብ እውቅና የሚሰጥና ህልውናቸው በውል የሚያረጋግጥ በራስ-ገዝነትና በጋራ አገዛዝነት (ፌደራላዊ ሥርዓት) በሚገባ ከመያዝና ከመገንባት ውጭ ለጊዜው ሌላ ምንም ዓይነት ምድራዊ አማራጭ አይኖራትም። ወደድንም ጠላንም በኢትዮጵያ ምድር ዘላቂ ሰላም ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ከተፈለገ ያለው አማራጭ ይህ ነው።

ፌደራሊዝም ሲባልም እንዲሁ ቀላል አይሆንም፤ አይደለምም። በፌደራሊዝም የፖለቲካ ስርዓት በምትዋቀረው አገር “ኢትዮጵያ ብሎ ትግሬ፣ ኢትዮጵያ ብሎ አማራ፣ ኢትዮጵያ ብሎ ኦሮሞ” ወዘተ ሳይሆን ብሔር ብሔረሰቦች በማንነታቸው ያለ ገደብ እኩል የመጠራት መብት ይኖራቸዋል። ይህ የማይሸረፍ፣ የማይቆረስና የማይቀነስ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የቋንቋቸው አጠቃቀም ጨምሮ ባህላቸው በእኩልነት የመግለጽና የማስተዋወቅ መብት ያጠቃልላል። የብሔር ፖለቲካ በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። ይኸውም፥

የብሔር ፖለቲካ በራሱ ምንም ዓይነት አደጋ የለውም። የብሔር ፖለቲካ አደጋ የሚሆነው ፖለቲካውን በሚመሩ ልሒቃን መካከል ዘንድ እርስ በርስ በሚደረገው ፖለቲካዊ ሽኩቻ የብሔር ፖለቲካ እንደ ጆከር መጫወቻ ሲሆንና የብሔር ፖለቲካ እንደ ጋሻና ጦር መጠቀሚያ ሆኖ ሲያገለግል ብቻ ነው።

አባባሌ ያልገባዎት እንደሆነ ወይንም አልያም በአባባሌ ተቃውሞ ያሎት እንደሆነ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሰማይዋ የሚደፋባት ጎረቤት አገር ኬንያ እንዲሁም በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች ያለቸው አዲስትዋ አገር የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት መንስኤ በማጥናት መልሱ ያገኙታል ብዬ አምናለሁ። 

እንግዲያውስ፥

  • አንደኛ፡ በሕግ መነጽር – ሕዝቦች አንደ አገርና እንደ ሕዝብ የመቆም ወይም ራስን የመቻል መብት እንዳላቸው ያለምንም ማቅማት አምነን ልንቀበል ይገባል። ራስን የመቻል – የብሔር ብሔረሰቦች ቀዳሚና ተከታይ የሌለው ሕጋዊና ሞራላዊ መብት ነው። 
  • ሁለት፡ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው የሚያነሱት የመብት ጥያቄ የህልውና ጥያቄ ነውና ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው የሚያነሱት ጥያቄ አንድ ከእንቅልፉ የነቃ/የባነነ ዜጋ የሚያነሳው ተገቢ ጥያቄ መሆኑ ምንም ሊያጠያይቀን አይገባም።
  • ሦስት፡ ሕዝብ/አንድ ብሔር “በማንነቴ የሚገባኝ ድርሻዬ!” ካለ ድርሻውን ይዞ አንደ አገርና እንደ ሕዝብ የመቆም ሕጋዊና ሞራላዊ መብት እንዳለው ማወቅ  ብቻ ሳይሆን የሕዝብ የጥያቄ ፋይል ሊዘጋ የሚችለው ለጥያቄው ተገቢ መልስ በመስጠት ብቻ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል።
  • አራት፡ ሕዝቦች መጻኢ ዕጣፈንታቸው የመወሰን ሕጋዊም ሞራላዊም መብት አላቸውና አንድ ብሔር/ሕዝብ “ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ተዛማች ጉዳዮች በተመለከተ ዕጣ ፈንታዬ የምወስነው እኔው ራሴ ነኝ!” ካለ በጊዜ ተመራርቀህ መሸኛኘት ዘመኑ የሚሻው ጥበብ ነው። ከዚህ ውጭ መሆኑ ላይቀር ትርፉ ደም መፋሰስ ብቻ ነው የሚሆነው። ምን ነው? ቢሉ፥ አንድም ይህ ዓይነቱ መብት በዓለም አቀፍ ድንጋጌ መሰረት አንድ ግለሰብ በህይወት የመኖር መብቱ የማይገረሰስ ነው ተብሎ የሚገለጽ/የሚታወቅ ዓይነት የሕዝቦች መብት ነውና። 

በነገራችን ላይ ራስን መቻል (መገንጠል) የአገር አንድነትን ማፍረስ አይደለም። ራስን መቻል የራስህ የሆነ ነገር በራስህ ማከናወን ነው። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com 

February 13, 2013 

Advertisements