ጎበዝ፡ መፈላለጋችን አይቀር ለሰላም እንፈላለግ!

ሰላምን አጥብቀን እንሻ። ችግርን በችግር ለመፍታት መሞከር ሌላ ችግር መፍጠር ነው የሚሆነውና በእውነቱ ነገር ችግር ውስጥ መሆናችን የምናውቅ ከሆነ ራሳችን ከችግር እንዴት ማውጣት እንዳለብን ነው ማሰብና መትጋት የሚገባን እንጅ በችግር ላይ ችግር ለመፍጠር እንቅልፍ ማጣት አይገባም። ደም መፋሰስ፣ መተላለቅ፣ ጦር መማዘዝ ሆነ ሌላ ውድመትን የሚያስከትል የአመጽ መንገድ መከተልና ማነፍነፍ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ለመሆኑ እኛ እርስ በርስ የምንተላለቀው ማን እንዲደለው ነው? መቼም በእኛ የእርስ በርስ መተላለቅ ደስ የሚለው ጠላት እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም። ጎበዝ! መፈላለጋችን አይቀር፡

  • ሰላምና እርቅ ለማውረድ፤
  • ለመነጋገር፤
  • ለመመካከር፤
  • የጋራ የሆነች አገራችን ለማልማት፤ 
  • የታሪክ ጠባሳ ያለው ሕዝብ ለመፈወስ እንፈላለግ፤ ከዚህ ውጭ የምንከተላቸው መንገዶች ሁሉ የሚያመሩት ወደ ጥፋት ነውና።

እርስ በርስ ተጨፋጭፈን ለመተላለቅ የምናወጣው ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ፤ ተኮራርፈን ከመሸግንበት ስፍራ ተጠራርተን እርስ በርስ በመደማመጥ፣ በመቻቻልና በመቀራረብ ጥያቄ ያለው ጥያቄውን አስተናግደን ለምን ዕርቅና ሰላም ለማውረድ አናውሎውም? ዓይናችን ከፍተን ለማየት ፈቃደኞች ከሆን ሰላማዊ መፍትሔ የሌለው ችግር የለም። ደም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብርቃችን የሚሆንበት ምክንያት ምንድ ነው? አገሪትዋ ራሱ የተመሰረተችው በደም ነው። የምድሪዋ ታሪክ የደም/የጦርነት ታሪክ ነው። ታድያ መቼ ነው አመጽን አጥብቀን የምንጸየፈው? እንግዲያውስ አሁን ባለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሳ ማንኛውም ዓይነት የአመጽ እንቅስቃሴ እንደ ግብጽና እንደ ሌሎች ዓረብ አገራት ሁኔታ ይፈጠራል ብለህ እንዳታስብ።

ግብጽና ሌሎች ህዝባዊ አመጽ የተካሄደባቸው ዓረብ አገራት መንግሥትን መገልበጥ ተችሎ ይሆናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው ሁኔታ ግን ከተጠቀሱ ዓረብ አገራት የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲፈጠር ኦሮሞ የመቶ ዓመት ታሪክ ዘክሮ በቀሉን ለመወጣት አማራን ስያድን፤ አማራ ትግሬን ሲፈልግ በዚህ መኸል አንዱ ሌላውን ቆሞ የሚጠብቅበት ምክንያት አይኖርምና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው ሁኔታ የእርስ በርስ እልቂትና ደም መፋሰስ ነው ሊሆን የሚችለው። ይህ ደግሞ የምድሪቱ ፍጻሜ የሚያበስር አሳዛኝ ታሪካዊ ክስተት ይሆናል። 

በዚህ አጋጣሚ ማንም የማያውቅ ሕዝብ ማተረማመስ፣ የሕዝብ ሀብትና ንብረት ማውደምና የገዛ ራስህን አገር ኦና ማድረግ ጅግንነት አይደለምና በዚህ ረገድ በአንድም በሌላም መንገድ የመሪነት ስፍራ የያዙ የተቃዋሚ ፓርቲ የፖለቲካ መሪዎች አመጽ ለመፍጠር ሳይሆን የሌሊት ዕንቅልፍ ማጣት የሚጠበቅባቸው ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት ተከትለው ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድ ጥርዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።

በተረፈ ሕዝብ ከቀሰቀስን፣ ካስተማርን፣ ካስተባበርን፣ ከሰበሰብንና ከሕዝብ ጋር መምከራችን አይቀር ሰላም ለማውረድ እናድርገው። አሁንም ከዚህ ያለፈ የምናደርገው እንቅስቃሴ ማንም የሚበጅ አይሆንምና በድጋሜ ሊታሰብበት ይገባል ለማለት እወዳለሁ። ወዳጄ! ሕዝብ ለጸብና ለጦርነት በአንድ እግሩ ለማስቆም ረጅም ጊዜ አይጠይቅም። ትክክለኛ ሰዓቱን ጠብቀህ መልቀቅ ብቻ ነው። ሁኔታዎች አስገዳጆች ሲሆኑ ደግሞ አንዱ ሌላውን የሚለማመጥበትና ደጅ የሚጸናበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

February 6, 2014

Advertisements