አሜሪካ ገፋ ቢል ማድረግ የምትችለው ነገር ቢኖር ግንቦት 7 አስታጥቃ የኢትዮጵያ ከተሞች ባግዳድ ማድረግ ብቻ ነው!

አሜሪካ ድፍን ዓለም የሚስማማበት በኢኮኖሚና ወታደራዊ አቅምዋ ያለ ተቀናቃኝ ለበርካታ ዓመታት ስትመራና ያሻትን ስታደርግ የመጣች አገር ናት። የሰው አገር በማፈንዳት መልሳ እርዳታ በመስጠትም አሜሪካ የሚስተካከላት የለም። በአንጻሩ ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት፣ መፈንቅለ መንግሥት፣ ዓይነቱ የማይታወቅ መድሃኒት አልባ በሽታ እየተናጠች ያለችና ዕረፍት የሌላት አህጉረ አፍሪካ አካል ናት። 

በድህነትዋ የተመሰከረላት አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ በየትኛውም መልኩ ከአሜሪካ ጋር መፎካከር ማለት ገና ከእናቱ ማህጸን የወጣ ህጻን ልጅ ከአንድ የከባድ ሚዛን ቦክሰኛ ለፍልምያ ቀለበት ውስጥ እንደመጨመር ነው። እንግዲያውስ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ወሳኝ አጀንዳ አለመስማማት ሊገጥማት የሚችለው አደጋ በአጭር ቋንቋ ለመግለጽ ያክል “ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነበረች ብለን ማውራት” ይቀላል ብሎ ማለፉ ነው የሚቀለው።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መንግሥት አሰራር ለመረዳት እንደሚቻለው አሜሪካ ያለ አንዳች ምክንያት የሰው አገር ፋይል በአደባባይ አትገልጥም። እውነትም ያማራት ነገር ቢኖር ነው እንጅ ከመሬት ተነስታም የስም ጥሪ አታደርግም። አሜሪካ ያለ ምክንያት/ያለ አጀንዳ ሕዝብ የምታተረማምስበት፣ አንድን መንግሥት የጥላሸት የምትቀባበት፣ አገር የምትወርበትና የምታወድምበት ምክንያት የላትም። የምታደርገው ነገር ሁሉም ብሔራዊ ጥቅምዋን ማዕከል ያደረገ ነው። ከሀገራዊ በጀትዋ በማንኪያ ቀንሳ ወጪ ስታደርግም የታክስ ከፋዮች ዜጎችዋ ገንዘብ በከንቱ ማባከን ስለሚያምራት ሳይሆን በአካፋ የምታገኘው ትርፍ ሲኖራት ብቻ ነው። 

የፓን አፍሪካኒዝም ዋነኛ አቀንቃኝ መሆናቸው የሚነገርላቸው፤ በወቅቱ በቅኝ ግዛት የነበሩ የአፍሪካ አገራት ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል በመደገፍም ይታወቃሉ “የሌሊን ፒስ ፕራይዝ” ተሸላሚ የጋናውን ክዋሜ ንክሩማህ። ንክሩማህ ከነጻነት በኋላ የመጀመሪያ የጋና መሪ ሲሆኑ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን በፖለቲካ ረገድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲሁም በኢኮኖሚም ተመሳሳይ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገቡ መምጣታቸው ይነገርላቸዋል። ንክሩማ ፊታቸው ከምዕራብ አገራት በማዞር ከሶቬት ሕብረት፣ ከቻይናና ከምሥራቅ ጀርመን ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ግኑኝነት በመመስረታቸው አሜሪካ ጥርስ ውስጥ ገብተዋል ከዚህም የተነሳ ንክሩማህ መጨረሻቸው አበላሽተዋል። 

ንክሩማ ከሶቬት ሕብረት፣ ከቻይናና ከምሥራቅ ጀርመን ጋር ከመሰረቱት ግኑኝነት በተጨማሪ ለሀገራቸውና ለዜጎታቸው ያሳዩት ቀናኢነት እ.አ.አ 1966 አሜሪካ በጠነሰሰችውና ባስተባበረችው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተወግደዋል። ንክሩማ እስከ ዕለተ ህልፈታቸውም ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ ቀሪ ዘመናቸው በጊኒ ለማሳለፍ ተገደዋል። 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቻይና በአፍሪካ አገራት እያሳየችው የመጣ ፍላጎትና ከዚህም አልፎ ከመላ የአፍሪካ አገራት የጀመረችው ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት የአሜሪካ መንግሥት እንቅልፍ ከነሱ ጉዳዮች በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ይህንኑ አስመልክተው አላስችል ያላቸው የሚመስሉ ሂላሪ ክሊንተን በአፍሪካ ጉዞቸው የቻይና መንግሥት በቃላት መወረፋቸው የቅርብ ትዝታችን ነው። 

ሁላችን እንደምናውቀም እንደ ድመት ሁሉንም እንደ ፊቱ በእኩልነት ማስተናገድ የተቻለው የኢትዮጵያ መንግሥት ሳንቲም ሳትጎድለበት ከምዕራቡ ዓለም የሚቃርመው በዕርዳታ መልክ ሆነ በብድር የሚገኝ ገንዘብ እንደተጠበቀ ሆኖ ከቻይና መንግሥት ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማስያዊ ግኑኝነት ከመሰረቱ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚ አገር ናት። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁምነገር ቢኖር ምዕራባውያን እርዳታ ሲሰጡ እነሱ አድርግ የሚሉህን እያደርክህ፤ የጠሉትን ጠልተህ፤ የወደዱትን ወድደህ፤ ከዓመት ዓመት የእነሱ ተመጽዋች ሆነህ እንድትኖር እንጅ የሰጡህን እየተቀበልክ እንድትለወጥና ራስህን እንድትችል አይደለም። 

ከእነሱ (ከምዕራባውያን) የምትፈልገው ነገር እየቀነሰ በመጣ ቁጥር ለእነሱ በሚፈልጉት መጠን የመታዘዝ ጉዳይም እንደሚቀንስ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ አንድ የሦስተኛ ዓለም መንግሥት በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ራስን ወደ መቻል በሚያኮበኩብበት ሰዓት የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ መሰናክሎች በማዘጋጀት ራዕዩን ማጨናገፍና አገሪቱ ወደ ነበረችበት የድህነት አዘቅት መመለስ የታወቀ ስልታቸው ነው። በሌላ አነጋገር እንዲለማም ሆነ እንዲለውጥ የሚፈለግ የአፍሪካ ሕዝብም ሆነ መንግሥት የለም። 

እንዲመክን ብሎም የጦርነት አውድማ ሆኖ እንዲኖር የሚፈለገው የዓለማችን ክፍል ማዕከላይ ምስራቅ በዋናነት ደግሞ የዓረብ አገራት በተያያዘ አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ (ቀይ ባህርን በተያያ) ምንም ዓይነት ፍላጎት የላትም ብሎ የሚያምን ግለሰብ ካለ በእውነቱ ነገር ከእንቅልፉ የሚነቃበት ሰዓት አሁን ነው። በምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ራሱን የቻለ በኢኮኖሚ የበለጸገ ህዝብና ጠንካራ መንግሥት መቆምና መምስረት ደግሞ ምዕራባውያን በአከባቢው ካላቸው የረጅም ጊዜ ዕቅድ አጀንዳ ፈጽሞ የሚቃረን ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ በምግብ ራሱን ለመቻል አገሩን ለማልማት በተነሳ ማግስት በአከባባው ጠንካራ መንግሥት የማየት ፍላጎት የላልቸው ኃያላን መንግሥታት ጥርስ ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው።

ወደድንም ጠላንም፤ ተስማማን አልተስማማን ኢትዮጵያ አይደለም የዛሬ ሃያ ዓመት የዛሬ አስር ዓመት የነበረችበት ሁኔታ አይደለም ያለችው። በነገራችን ላይ በድህነት ውስጥ እስካለን ድረስ ይህ ማለት አድርጉ ያሉንን ለማድረግ፤ ወደ አዘመቱን ያለ ጥያቄ ለመዝመትና የዜጎቻችን ደም በከንቱ ለማፍሰስ ምችዎች እስከሆን ድረስ በነጻም ይሁን በርዳታ መልክ ገንዘብ ማግኘታችን ይቀጥላል። ወዳጆች ተብለን መጠራታችንም ይቀጥላል። መቼም ምን እያልኩ እንደሆነ ይገባዎታል።

ወጣም ወረደ ኢትዮጵያውያን አገራችን ለማልማት ስንነሳ ፋይላችን የሚገለጥበት የጊዜ/ወረፋ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው። እኛም እንደሌሎች በቀጥታም በተዘዋዋሪም በጊዜ ውስጥ ሰለባ ለመሆናችን ሳይታለም የተፈታ ነው። ኢትዮጵያ የምዕራባውያን ሰለባ ለመሆን ደግሞ የግድ የነዳጅ ወይንም የፕላቲንዬም ማዕድን ባለቤት መሆን አይጠበቅባትም። የሚፈልጉትን ለማድረግም ኢትዮጵያን በጅምላ ጨርሽ መሳሪያ አይከስዋትም። ክስ ለመመስረትና ለሚድያ የሚሆን ዜና ለመፍጠር ያውቁበታል። የሚያሳዝነው ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ አፍሪካውያን ምዕራባውያን በምድራችን ማድረግ ለሚፈልጉት ሁሉ ምችዎች መሆናችን ነው።

  • የአሜሪካ መንግሥት ለእያንዳንዱ ኤርትራዊ ዜጋ F- 16 ተዋጊ ጀት አስታጥቃ ብታሰልፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅንጣት ታክል ስጋት አያድረውም። ሻዕቢያ እንደሆነ ከምን ጊዜ በላይ እጁንና እግሩን ሰብስቦ አርፎ መቀመጥ እንዳለበትና እንደሚገባው የማናችንም ምክር አያስፈልገውም። በዚህ ጉዳይ ሻዕቢያ ሆነ ሌሎች የውጭ ኃይላት በኢትዮጵያ ላይ እግራቸውን ያነሱ ዕለት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ቀስቃሽ አያስፈልገውም። ደግሞም ለጦርነት!! የኢትዮጵያ መንግሥት ድርሻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተባበር ብቻ ነው የሚሆነው። ውጊውያን የሚዋጋው የሰውን የማይፈልግ የራሱንም አሳልፎ የማይሰጥ፤ ለነገር የዘገየ፤ ድልን እንጅ ሽንፈትን የማያውቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

አሜሪካ ጦርዋን በምጽዋ በኩል አስገብታ የኢትዮጵያ ሕዝብ የምትወጋበት ምክንያትም የላትም። አትውሎውምም። ቀደም ሲል በሊቢያ ግዴታቸውን በአግባቡ የተወጡ በቅርቡ በስሪያ ግዴታቸውን ሲወጡ የነበሩ የአፍጋን ሰልጣኞች በኢትዮጵያ ምድር ማሰማራትም  አያስፈልጋትም።

  • ስስ ብልታችን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ገንዘብና ሥልጣን እያሸተተ አገር ለማፈራረስና የዜጎች ደም ደመ ከልብ ለማድረግ የማይተኛ የሻዕቢያ ግርፍ ግንቦት 7 አስታጥቃ ማሰማራት ብቻ ነው የሚጠበቅባት። ይሄ እኮ ግልጽ ነው። የመን ላይ በድሮን እየታደነ ይገደልና ይደበደብ የነበረ አሸባሪ ነው፤ ስሪያ ላይ ዓይነቱ የማይታወቅ መሳሪያ እስከ አፍንጫው ድረስ ያስታጠቀችውም አሸባሪ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት እንደ እነ ግንቦት የመሳሰሉ የሥልጣን ጥማቸው ለመወጣት በየትኛውም መመዘኛ ኢሞራላዊ የሆነ አስነዋሪ ድርጊት ከመፈጸም የማይመለሱ ግለሰቦች መግነዛቸው ፈትቶ ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ድረስ ቦንብና ፈንጅ አስታጥቆ የኢትዮጵያ ጎዳናዎች ባግዳድ ማድረግ ይችላል። እዚህ ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ ሊፈጠርብን አይገባም። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን የሚያየውና የሚያውቀው እንደ አንድ ክብር ያለው ሕዝብ ኃላፊነት የተሸከመ ሉዓላዊ መንግሥት እስከሆነ ድረስ የዋሽንግተን መንግሥት ባማረው ሰዓት እየተነሳ  በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የወደደውን የሚያደርግበት ዕድልም ሆነ አጋጣሚ የለውም። 

ክንደ ብርቱ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ቅድሳት መጻህፍት “በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል እጁንም የሚከለክላት ወይም ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።” ሲል የሚገልጸው እግዚአብሔርን እንጅ አሜሪካን አይደለም። ጎበዝ! የወደደውን ማድረግ የሚችል አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው።  ከፍ ሲል እንደገለጽኩት አሜሪካ ገፋ ቢል ማድረግ የምትችለው ነገር ቢኖር ግንቦት 7 አስታጥቃ የኢትዮጵያ ከተሞች ባግዳድ ማድረግ ብቻ ነው! አሜሪካ በቀላሉ ማድረግ የምትችለው ይህንኑ ነው። 

አሜሪካ በገንዘብዋ ብዛት ማድረግ የምትችለው ነገር ቢኖር ይህ ነው፤ ይኸውም፥ ባንዳ ገዝታ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ማተረማመስና ማጨራረስ ብቻ ነው። እስከ አሁን ድረስ ስታደርገው የመጣችውም ይህ ነው። ከምትታወቅባቸው በርካታ ገጽታዎችዋና ሥራዎችም በግንባር ቀደምትነት የምትታወቀው በዚህ ረቂቅ ስራዋ ነው። ይህ ደግሞ የአሜሪካ የበላይነትና ትልቅነት የሚያሳይ ሳይሆን የእኛ አንድ መሆን ያቃተን፣ በመቻቻልና በመነጋጋር መፍታት የሚቻለው የውስጥ ችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረን መፍታት አቅቶን በባዶ ቂጣችን መተላለቅ የሚያምረን እንደ ሰው ማሰብ ያቆምን ጎደሎ ፍጥረቶች መሆናችን ብቻ ነው። 

ጎበዝ! ጊዜው አማራ ትግሬን፣ ኦሮሞ አማራን የሚጠማመድበት ጊዜ አይደለም። ጊዜው ለውስጥ ችግሮቻችን በመደማመጥ መፍትሔ የምንሰጥበት፤ የሀገራችንና የህዝባችን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚጋፋ ማናቸውም የውጭ ሃይላት እርዳታቸው ቀርቶብን እንደ አንድ ሕዝብ ቁመን ሀገራችን ከወረራ ህዝባችን  ከውርደትና ከባርነት የምንታደግበት ጊዜ ነው። 
 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል 

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

February 4, 2014

Advertisements