ኢሳት፡ በሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የቆፈረው ጉድጓድ እራሱ ገባበት! ክፍል ፪

እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ?

“ሰላም ጤና ይስጥልኝ ተመልካቾቻችን እንደምን ሰነበታችሁ። ሰማያዊ ፓርቲ ከተመሰረተ በጣም አጭር ጊዜ ቢሆንም በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ በማበርከት ስሙ ይጠቀሳል። … ኢ/ር ይልቃል ወደ ስቴድዮችን [ሰው ሥጋው ተበልቶ አንጥንቱ ወደሚፈጭበት የስልቀጣ ስቴድዮችን]* እንኳን በሰላም መጣህ!” አቶ መሳይ መኮነን/ኢሳት

እዚህ ላይ ኢሳት ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ያለው አመለካከት “መልካም ነው!” በማለት በኢሳት የግብር ይውጣ ፕሮፖጋንዳ ተጠልፎ በቀላሉ የሚሳሳት አድማጭ ቁጥር ቀላል አይሆንም። የኢሳት ግብዝነት የተሞላበት አቀራረብ ምን ማለት እንደሆነ ቀለል ባለ በምሳሌ ላስረዳዎት።

“ … ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ። እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? …” (ማቴ. 22: 15- 18)

ፈሪሳውያን ኢየሱስን በነገር ለማጥመድና ጠልፈው ለመጣል “ስማ አንተ የጠራቢ ልጅ ምን እዚህ ሰዎች እየሰበሰብክ የሆነውን ያልሆነውን ያስለፈልፈሃል?” አላሉም። የሄዱበት መንግድ ይመልከቱ።

  • መጀመሪያ “መምህር” በማለት በሰዎች ፊት ለመካብ ሞክረዋል። ይህም የክብር መጠሪያ ነውና።
  • “እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን” አሉ፤ ፈሪሳውያን ኢየሱስ እውነተኛ መምህር የእግዚአብሔር ልጅም እንደሆነ ከልብ አምነው ቢቀበሉት ነው ጠልፈው ለመጣል ሸማቂዎች የላኩበት?
  • ለማንምም የማታዳላ፥ የሰውን ፊት የማትመለከት ነህም አሉት። ይህ ማለት አንተ ጻዲቅ ነህ ማለታቸው ነው። እንግዲህ ይህን ሁሉ እያወቁ ከእግዚአብሔር መልዕክተኛ መጣላትና ይህን ጻዲቅ ሰው ማሳደድ ማለት መጽሐፍ “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ” እንዲል ኢየሱስን ማሳደድ፣ ኢየሱስን ጠልፎ ለመጣል ማሴርና ተንኮልን መሸረብ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ማለት እንደሆነ ስተውት ነው? “ዶሮን ስያታሏት ሙቅ ውሃ ለገላች ነው!” አልዋት አለ ያገሬ ሰው የሚባለው። እንግዲያውስ አንባቢ ሆይ! እንዲህ ያለ መሰሪነትም እንዳለ ከነቁ ዘንዳ የኢሳት የሽንገላ አነጋገር በጥሩ ዕቃ የተዘጋጀ መርዝ ለመሆኑ አይስቱትም።

*   *   *   *   *

“በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጣም ስማችሁ እየተነሳ ነው ሰማያዊ ፓርቲ በጣም አጭር ጊዜ ነው ዕድሜችሁ። ነገር ግን ስራችሁ ወይም ስማችሁ ልበለው ገዝፎ ነው የሚሰማውና ምን ሰራችሁ ነውና ነው ይሄ ሁሉ ሰማያዊ ፓርቲ የተባለው?” አቶ መሳይ መኮነን/ኢሳት 

“ስራችሁ ወይም ስማችሁ ልበለው” እዚህ ላይ አንባቢ፡ “በስራና” “በስም” መካከል ያለውን ልዩነት ያጡታል ብዬ አላምንም። መሳይ “ስራችሁ” ማለት ትቶ “ስማችሁ” በማለት ጠበቅ አድርጎ መናገርና ሃሳቡንም ያስተካከለበት ምክንያት

  • አንደኛ፡ “ሰማያዊ ፓርቲ እየተቀዳጀው ያለ ክብር፣ ዝናና አድናቆት አይገባውም!” ብሎ ደረቅ አቋም ማንጸባረቁና መከራከሩ ብቻ ሳይሆን “በሰማያዊ ፓርቲ አቅም እንተም ሆንክ በዙሪያህ ያሉ ወጠጤዎች ምንም የሚገባችሁ መልካም ነገር የለም።” ብሎ በአራት ነጥብ ስለ ዘጋው ነው።
  • ሁለተኛ፡ የመሳይ/የኢሳት የኩርፊያ መንስኤ “ሰማያዊ ፓርቲ ምን የሰራው ስራ ቢኖር ነውና ነው ከግንቦት 7 ይልቅ ገድሉ ልቆ የሚነገርለት? ሰማያዊ ፓርቲ የሰራው ስራ እንደሌለ እኛ አሳምረን እናውቃለን” ነው።
  • ሦስተኛ፡ በተጨማሪ መሳይ ኢንጅነሩን ጥያቄ እየጠየቀ ሳይሆን ያለው እንደ ፓርቲ ሆነ የፓርቲው አመራሮች እንደ ግለሰብ የሰራችሁት ስራ ሳይኖር በአጨር ጊዜ ውስጥ ግንቦት 7ና ዶክተር ብርሃኑ በሚያስረሳ ሁኔታ ስማችሁ የጎላበት ምክንያት ምንድ ነው? በማለት እየሞገተ ነው ያለው። በነገራችን ላይ የመሳይ አነጋገር አንድምታ ወደኋላ ከራሱ ከመሳይ አንደበት ይሰሙታል። ይኸውም፥ ስማችሁ የገነነበት ምክንያት ምስጢሩ ለእኛ ለኢሳቶች የተሰወረ አይደለም። የሰማያዊ ፓርቲ ስም መግነን ፓርቲያችሁ (ሰማያዊ ፓርቲ) ወያኔ ያዘጋጀው፤ ከዚህ ሁሉ (የሰማያዊ ፓርቲ ስም መግነት) ጀርባ ያለው ወያኔ ራሱ ነው! ሲል የሚሰጠውን ፍጥጥ ያለ ድምዳሜ ያገኙታል [07:50]።

የሃይለ ቃሉ አነጋገር ወይንም “ቶኑ” ልብ ማለት በራሱ ሌላ የተናጋሪው የንግግር መንፈስ ለይተን እንድናውቀው ይረዳናል። በዚህ መሰረት “ምን ሰራችሁ ነውና ነው ይሄ ሁሉ” የሚለው የመሳይ ልቅ አነጋገር የኢንጅነሩ ፖለቲካዊ ስብእና በአደባባይ ማሳጣት/ቱ ነው።

ኢሳት/መሳይ ከበደ ኢንጅነሩ ይጠይቅበት በነበረበት መንፈስ ዶክተር ብርሃኑን “ድርጅታችሁ ግንቦት 7 የኢትዮጵያ ሕዝብ በተራ ወሬና ፕሮፖጋንዳ ከማደንቆርና ከማድከም ያለፈ ምን የሚታይ ወይም የሚጨበጥ ስራ ቢሰራ ነውና የኢህአዴግ መንግሥት የእንደራደር ጥያቄ የሚያቀርብለት? ለመሆኑ ግንቦት ሰባት አሉኝ የሚላቸው ሦስት ፍሬ ወታደሮች የሚያሰማራበት ቢሮ አለው?” በማለት ሲያፋጥጣቸውና ዶክተር ብርሃኑም መሳይን “ስማ አንተ … ትሰማለህ ሁለተኛ እዚህ ስፍራ እንዳለይህ። ውጣ ኮተታም! ቆማጣ!” በማለት እንደ ውሻ ሲያባርሩት ነው የሚታየኝ። ለሲሳይማ “ምን ይመስላል!” ሳይጨምሩበት አይቀሩም።

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

February 3, 2014 

Advertisements