ኢሳት፡ በሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የቆፈረው ጉድጓድ እራሱ ገባበት! ክፍል ፩

ኢሳት፡ በሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር  ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የቆፈረው ጉድጓድ እራሱ ገባበት!

http://ethsat.com/video/esat-yesamintu-engida-with-engineer-yilikal-getinet-part-i/

ማሳሰብያ፡ 

  • ከሚመለከተው አካል ህጋዊ ፈቃድና እውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀስ ሰማያዊ ፓርቲ በግሌ ጊዜ ውስጄ የፖለቲካ ፕሮግራሙን አላነበብኩም። የፓርቲው መሪ በተመለከተም የተለየ ግኑኝነትም ሆነ እውቀት የለኝም። ስለሆነ የጽሑፉ ይዘት ፓርቲው ሆነ የፓርቲው ሊቀ መንበር ከኢሳት ባደርጉት ቆይታ ብቻ አተኩሮ የሚያትት እንጅ የፓርቲው ቅድመ ታሪክ ሆነ ፓርቲው ከአሁን በኋላ ለሚኖረው ክፉም ደጉም ገጽታ የሚዳስስ አይደለም።
  • ኢንጅነሩ “ወይ የእናንተ ነገር! በል እስቲ አለቆችህ ጭነው የላኩህ ተንፍስ” እያሉ በፈገግታ የሰጡትን መልስ አያካትትም።
  • የጽሑፉ ዓላማ የኢሳት የወረደ ሥራ ለአንባቢያን ፍንጭ ለመስጠት ያክል የመጀመሪያ ጥቂት ደቂቃዎች የሚዳስስ እንጅ ሙሉ ዝግጅቱን አይዳስስም። ሙሉ ዝግጅቱ ልብ ብለው ያደምጡት ዘንድ ግን ጸሐፊው በዚህ አጋጣሚ ለማበረታታት ይወዳሉ።

ሐተታ፥

በቅድሚያ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከኢሳት በነበራቸው ክፍል አንድ ቆይታ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ላስመዘገቡት ድል ከምንም በላይ ደግሞ አንድም ቦታ የመረበሽ ምልክት ሳያሳዩና የሃሳብ መቆራረጥ ሳይስተዋልባቸው ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ላሳዩት ታጋሽነት፣ ቁጥብነትና ግልጽነት በዚህ አጋጣሚ አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።* [ይህ አባባሌ ኢንጅነሩ ከኢሳት ባደርጉት ቆይታ ብቻ ይመለከታል]

አንድ ሰው የክርስትና እምነት ተከታይ ነኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስንም አውቃለሁ ብሎ ሲያበቃ መጽሐፈ አስቴር  ሳያውቅ ይኖራል ብሎ ማመን ይከብደኛል። መጽሐፈ አስቴር ማለት ከብሉይ ኪዳን መጻህፍት መካከል አንድ ሲሆን፥

በምዕራፍ 1 ቁጥር 1 ላይ “በአርጤክስስም ዘመን እንዲህ ሆነ ይህም አርጤክስስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባት አገሮች ላይ ነገሠ።” እንዲል ኢትዮጵያ በታሪኳ በቅኝ ግዛት ተገዝታ አታውቅም የሚል የእኛ የኢትዮጵያውያን  የተሳሳተ እምነት በቂ ምልሽ የሚሰጥ መጽሐፍ ነው። መልካም ዜናው፥ የዛሪትዋ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ (፵፫ ጊዜ) ከተጠቀሰ የሕዝቦች ቀለም (ኢትዮጵያ) ምንም ዓይነት ግኑኝነት የሌላት/የሌላቸው መሆኑ ነው። በበኩሌ የዛሪትዋ ኢትዮጵያ ታሪክ በተመለከተ የማያውቀው መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) አስታኮ ለመናገር ሆነ ለመጻፍ ወይም ለመሞገት የሚቃጣው ምሑር ነኝ የሚል ዶክተር/ፕሮፌሰር ይኖራል ብዬ አልገምትም። ያለ እንደሆነም አይፈረድበትም።

መጽሐፈ አስቴር ሐማ የተባለ ሰው በፋርስና ሜዶን ሕግ በንጉስ ቀለበት ላይ ማህተም አሳትሞ በአዋጅ የእስራኤል ዘር ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ስለ ጠነሰሰው ሴራ በሰፊው የሚያትት መጽሐፍ ነው። በነገራችን ላይ ሐማ ማለት የስሙ ትርጓሜ ታማኝ/ሰላማዊ ማለት ነው። ኢሳት ማለት “የኢትዮጵያውያን ዓይንና ጆሮ ነው!” እንደ ማለት ነው። በአይሁዳውያን ላይ የተጠነሰሰው ሴራ በመቃወም  ሰላማዊ ትግሉን ይመራ የነበረ ሰው ደግሞ መርዶክዮስ ይባላል።

ኢሳትና ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ ያጠማመዳቸው በግሌ የማውቀው ነገር የለም። ኢሳት ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ አጥምዶ የያዘበት የሞት ድግስ ደግሶ የጠበቀበት ምክንያትም ኢሳትና የኢሳት ባለቤት ዶክተር ብርሃኑ ነው የሚያውቁት። ያም ሆነ ይህ የጸቡ ምክንያት ለአፈወርቅ አግደው ትቸዋለሁ። ሐማና መርደክዮስ ግን ምን አገናኛቸው? በማለት የጠየቁኝ እንደሆነ። መጽሐፉ የሚለውን ላስነብቦት ይኸውም፥ “በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ ባሪያዎች ሁሉ ተደፍተው ለሐማ ይሰግዱ ነበር መርዶክዮስ ግን አልተደፋም፥ አልሰገደለትም። … በዚያም ቀን ሐማ ደስ ብሎት በልቡም ተደስቶ ወጣ ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ያለ መነሣትና ያለ መናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቈጣ።” (መጽ. አስቴር 3: 2; 5:9) ከዚህ የተነሳ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ ቂም ሊቋጥር ችለዋል። መቼም ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በክብራቸውና አንድ ጊዜ ፈጽመው ዓይን የጣሉባት ሥልጣን የሚመጣባቸው ሰው እንደማያስችላቸው የአደባባይ ሚሥጢር ነው።

ሐማ በመርዶክዮስ ጉዳይ ሰላሙን ማጣቱ የተመለከቱ ሚስቱና ወዳጆችም በለገሱት ምክር ተስማምቶ ሐማ መርዶክዮስ የሚያንጠለጥልበት ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ ያዘጋጃል [ልብ ይበሉ! “ግንዱ” በዘመንኛ አጠራር “የሳምንቱ እንግዳ ፕሮግራም” መሆኑ ነው።] በዚህ መኸል የእስራኤል አምላክ ምን ተስኖስት ንጉሥ አርጤክሲስን የሌሊት እንቅልፍ ያሳጣዋል። ነገሩ ከላይ ነውና ንጉሡ የዘመኑ ታሪክ መጽሐፍ ያመጡ ዘንድ በማዘዝ በንጉሡ ፊት እንዲነበብ ያደርጋል። በንባቡ ውስጥም ለንጉሡ ታላቅ ነገር ስላደረገ  ሆነም ግን ምንም ዓይነት ውለታ ስላላገኘ አይዳዊ መርዶክዮስ ታሪክ ይገኛል።

ንጉሡም ሐማን “ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ምን ይደረግለታል? … ሐማም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግ ንጉሡ የለበሰው የክብር ልብስ፥ ንጉሡም የተቀመጠበት ፈረስ ይምጣለት፥ የንጉሡም ዘውድ በራሱ ላይ ይደረግ ልብሱንና ፈረሱንም ከንጉሡ አዛውንት በዋነኛው እጅ ያስረክቡት ንጉሡም ያከብረው ዘንድ የሚወድደውን ሰው ያልብሱት በፈረሱም ላይ አስቀምጠውት በከተማይቱ አደባባይ ያሳልፉት በፊቱም። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ አዋጅ ይነገር። ፍጠን፥ እንደ ተናገርኸውም ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ በንጉሡም በር ለሚቀመጠው አይሁዳዊ ለመርዶክዮስ እንዲሁ አድርግለት ከተናገርኸውም ሁሉ ምንም አይቅር አለው።”

ረጅሙን ታሪክ ለማሳጠር ያክል ነገሩ ተገለበጠና አዋጅን ባዋጅ ገልብጦ ሐማ መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው ግንድ ራሱ ሲንጠለጠልበት መርዶክዮስ ደግሞ “ሐማም በልቡ። ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ያከብር ዘንድ ይወድዳል? አለ።” እንዲል ቅዱስ ቃሉ፤ ይሁንለት ሲል የተናገረው መልካሙን ሁሉ ለመርዶክዮስ ተከናውኖሎት ታሪክ ይቀጥላል።

የኢሳት ጸረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ፤ ሸረኝነትና ምቀኝነት መጨረሻው ራሱን ጠልፎ እንደሚጥለው ዛሬ አይደለም የማውቀው/ያወቅኩት። ኢሳት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀስው/በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ተብሎ የሚታወቀው የፖለቲካ ፓርቲ በሊቀ መንበርነት የሚመሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጣል ጣል የማድረግ፣ የማቃለል፣ የማኮላሸት፣ የማሳጣት በአጠቃላይ ግለሰቡ ከነ ፓርቲአቸው በቁማቸው ገድሎ ለመቅበር የደገሰው ድግስ የውርደት ድግስ የተደገሰላቸው ግለሰብ  ሙሉ ቃለ ምልልሱን (ክፍል አንድ) የተከታተለ ሰው ኢንጅነሩ ኢሳትን እንደ እባብ ተጫምተው እንደትብያም አራግፈው በክብር መውጣታቸው ሳያስተውል አይቀርም።

ኢሳት በኢንጅነሩ ያሴረው ሴራ የሚጀምረው ኢንጅነሩ አሜሪካ እንደሚመጡ ተረጋግጦ ኢሳትም በጉብኝታቸው ከጣቢያው ቆይታ እንዲያደርጉ ባቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት መስማማታቸውን ከተረጋገጠ በኋላ ግለሰቡ ማን ያስተናግዳቸው? ከሚል ጥያቄ ነው የሚጀምረው። ከአስመራ አመስተርዳም የተቀመጡ የተቋሙ ባለቤቶች ባደረጉት ውይይትም ቃለ ምልልሱ በወሬ መጋኛ የተከፈ፣ ያልተጨበጠ በሬ ወለደ ዜና ይዞ አፉን ለመክፈት ነፋስ የማይቀድመው፣ ሞያው የሚጠይቀው እውቀትና ሥነ ምግባር ያላለፈበት፣ በነገር ያልበሰለ፣ ጋዜጠኛ ተብሎ ለመጠራ በራሱ የአንድ ትውልድ ዕድሜ የሚያስፈልገው መሳይ ከበደ በተባለ ተራ መልዕክተኛ ግለሰብ አማካኝነት እንዲደረግ/እንዲካሄድ ከተላለፈው ውሳኔ ነው የሚጀምረው። ይህ የሚያሳየው ኢሳት ለሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም ፓርቲው በሊቀ መንበርነት በመምራት የሚታወቁት ግለሰብ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ያለውን ንቀት ለማሳየት ነው።

አይተውልኛል!?! ሲሳይ አጌና ለፕሬዝዳንት ኦባማ ‘ሴቭ’ መደረጋቸው እኮ ነው። እስቲ አሁን ማን ይሙት በደርግ ዘመነ መንግሥት የፕሮፖጋንዳና የቅስቀሳ ክፍል ሰልጣኝ/ካድሬ ሻምበል ሲሳይ አጌና ከአቶ መሳይ ከበደ በምን ቢሻሉ ነው? አይ አንቺ ኢትዮጵያ! ሲሳይም በአቅሙ “Executive!” ነኝ አለ!?! ከነተረቱ “ዶሮ የሌለው በቅሎ ይንቃል!” ሆነ ነገሩ።

መስማትና ማንበብ የሚሹት በክፍል ሁለት ይቀጥላል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

February 2, 2014

Advertisements