“ኢሳት የእኔ ነው!” በማለት ለሚንጣጣና ለሚንቀለቀል ዜጋ መድኃኒቱ: የትግራይ ሕዝብ ማንቃት፣ ማደራጀትና ማስታጠቅ ነው!

ትርጓሜ፥ 

  • “ማንቃት”፥ ያለፈውን የሕዝቡ ታሪክ ማለትም የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለመቆም ያፈሰሰው ደምና የከፈለው የህይወት መስዋዕትነት ጨምሮ አሁን ያለው ተጨባጭ የሀገሪቱ የፖለቲካ መስመር፣ አሰላለፍ፣ ከምንም በላይ ደግሞ በታሪክም ሆነ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አንዱ ሌላውን የሚያይበት መስኮት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ወጥ የሆኑ ትምህርቶችና ሥልጠናዎች በማዘጋጀት ግልጽ በሆነ ቋንቋ በይፋ በየተዋረዱ ማንነቱን ማስተማር፣ ማሰልጠና በእውቀት ማስታጠቅ።
  • “ማደራጀት”፥ አንድ የራሱ የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ቋንቋ፣ አስተሳሰብ፣ ወግና ልማድ ያለው ሕዝብ ቀዳሚ ሥልጣንና መብት ራሱን እንደ ሕዝብ ማደራጀት ነውና ለክፉም ለደጉም በመዋቅር ማደራጀት፣ ማሰለፍ፣ ማሰባሰብና የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀትም መከታተልና ማነቃቃት።
  • “ማስታጠቅ”፥ የሚለው ቃል የጽሑፉ አዘጋጅ ከዚህ ቀደም በሰፊው ጎልተው የሚታወቁበት ጸረ ጦርነት አቋማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሃይለ ቃሉ በንባቡ ዓውድ መሰረት ከጽብ ጫሪነትና ከጦርነት ጋር ምንም የሚያገኛኝ የሌለው ራስህን  የራሱ ያልሆነ ለማግበስበስ ከሚቃጣውና የሚፈልግ ጨፍላቂ ወይም ከአመጸኛ ኃይል ራስህን መከላከል፣ መጠበቅ የሚያመላክት ነው።

ሐተታ፥

ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ሳይሆን የአንድ ክልል ሕዝብ ውክልና ያለው ጉጅለ ነው ከተባለ፤ በጣም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር ይህ የአንድ ጠቅላይ ግዛት ብቻ ውክልና ያለው ቡድን ከትግራይ ሕዝብ አፍ እየመነተፈ የተቀሩት ጠቅላይ ግዛቶች ማልማቱ ነው። ይህ ደግሞ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከዚህ ቀደም ከፈጸማቸው ጉልህ ስህተቶችና ግድፈቶች እንዲሁም በአሁን ሰዓት “እያደረሳቸው ያሉ ኪሳራዎች” ይልቅ የከፋና የላቀ ስህተት እየፈጸመ ነው ያለው። ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአንድ አከባቢ (የትግራይ ሕዝብ) ብቻ የሚወክል ነው ከተባለ ፥

  • አንደኛ፡ ይህ መንግሥትከትግራይ ውጭ የተቀረ የኢትዮጵያ ክፍል የማልት ግዴታ የለበትም። የሚሳዝነው ግን ይህን ሲያደርግ ለማየት ባለ መታደላችን ነው። 
  • ሁለት፡ የትኛውም ሕዝብ/ብሔር የማይወክሉ ዳሩ ግን አሉባልታ ለመንዛት የሚስተካከላቸው የሌለ ነፈዞች እምነትና አመለካከት “የትግራይ መንግሥት” ተብሎ የሚፈረጀው ባለ ሥልጣን አይደለም አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ ደብረ ብርሃን፣ አዳማ፣ ሀረር፣ ድሬዳዋ፣ ጎንደር፣ ሰመራ … መሰረተ ልማቶች መዘርጋትና ማፋጠን ቀርቶ ተቃውሞ ማስተናገዱ ያልቀረ ከምኒልክ ጀምሮ እስከ የደርግ መንግሥት ጊዜ ቀደም ስል በተጠቀሱ ከተሞችና በሌሎች የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች በአጠቃላይ ከትግራይ ክፍለ ግዛት ውጭ የተገነቡ ተቋማትና የተተከሉ ፋብሪካዎች ካሉ ከቀድሞ ይዞታቸው እያፈናቀለ፣ እያፈረሰና እየነቀለ ኮረም፣ ማይጨው፣ አላማጣ፣ ዓዲ ጉዶም፣ ኩሐ፣ መቐለ፣ ተንቤን ዓብዪ ዓዲ፣ ውቅሮ፣ ስንቃጣ፤ ዕዳጋ ሐሙስ፣ ዓዲ ግራት፣ ዛላንበሳ፣ ኢሮብ- ዓሊተና፣ ዓድዋ፣ አኽሱም፣ ሽረ፣ ሑመራ፣ ወልቃይት ጸገዴ መትከልና መገንባት ነበረበት። ምን ነው? ቢሉ ነገር ሁሉ ከልኩ አያልፍምና። አይመስሎትም?

ሰው በምንም ዓይነት ሁኔታ ቢሆን ተቃውሞ ማሰማቱ አይቀርም። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እንደ ፕሬዝዳንት፤ አሜሪካ እንደ አገር ከውስጥም ከውጭም ተቃውሞ አላቸው። ፕሬዝዳንት ኢሳያይስ አፈወርቂ አገራቸው ኤርትራ አገር መሆንዋ ቀርታ በርሃብና በፍትህ አጦት አቆራምደው አገሪቱ ምድራዊ ሲዖል አድርገው ሲፈላሰፉበት ማን ጠየቃቸው? ማንም። የሚገርመው ግን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የአምልኮ መስዋዕት ሲቀበሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ ማስተናገዱ ነው። የሰው ያለህ!

  • የአንድ ክልል ሕዝብ ብቻ የሚወክል ነው እየተባለ መከሰሱና ተቃውሞ ማስተናገዱ ያልቀረ/ያልቀረት በግልጽ ሌሎች ክልሎች እያራቆጠ የትግራይ ክልል በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ፣ በህክምና፣ በትምህርትና በወታደራዊ አቅም በሚገባ በማደራጀት በማይገፋ መልኩ አቅሙን ማፈርጠም ነበረበት። በዚህ ወቅት “ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካና የሃብት ክፍፍል ወይም እኩልነት የለም!” በማለት መከፋታችን “ወያኔ አፓርታይድ ነው!፣ ወያኔ የዱር አራዊት ነው!፣ ወያኔ … !”  እያልን መፈክሮች እያሰማን ብንጮህና ብንጫጫ ያኔ ያምርብናል። 
  • በተጨማሪም በተጨባጭ ሳይሆን ኢሳትና  የትግራይ ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ለመቃባት የሚተጉ የፕሮፖጋንዳ  ድረ ገጾች፣ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ መቆም የለበትም፣ ዘር ማንዘሩ ተጠራርጎ መጥፋት አለበት ብሎው የሚያምኑ የሻዕቢያ ተላላኪዎች/የግንቦት 7 አመራሮች እንደሚነግሩን፤ ትግራይ በእድገትዋ በምስራቅ አፍሪካ የሚስተካከላት የሌላት እንደ ፓሪስ የምታበራ አገር ብትሆንና የኢትዮጵይያ መንግሥትም የቆመ ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ ብቻ  ለማልማት የቆመ መንግሥት ቢኖን ኖሮ ሥልጣን ላይ ያለው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ  ላለፉት ሃያ ዓመታት እያስተናገደው ከመጣ የተለየ ጩኸት አያስተናግድም ነበር። 
  • ከልኩ ላያልፍ የኢ.ህ.ዴ.ግ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ ዓመታዊ ገቢ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ አስር እጥፍ በማሳደግ ወገኝተኝነቱን ቢያሳይ አሁን ከሚሰማው ተቃውሞና ጩኸት የተለየ የሚፈጠር ነገር የለም፤ አይኖርምም። የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ አበባ ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ የዘረጋው የልማት መስመርና እያፋጠነው ያለው ዕድገት የምቃወምበት ምክንያትም ይህ ነው።* [*መቼም ምን እያልኩ እንደሆነ ይገባዎታል]

አንድ ምሳሌ ልጨምር። ይኸውም፥ የዓባይ ግድብ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት የአባይ ግድብ ለመገደብ ገንዘብ ልመና በመላ ዓለም በሚጠራቸው ስብሰባቸው በአመዛኙ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ተወላጆች (እንደ ኢሳት ዘገባ) እየተገኙ ለምን ገንዘባቸው እንደሚሰጡ በጣም ይገርመኛል። ነገሩ ዛሬም ድርስ ያልተመለሰልኝ ጥያቄ ነው።

የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ተወላጆች ለዓባይ ግድብ ግንባታ እያሉ የሚሰጡት ገንዘብ ስለተረፋቸው ካልሆነ በስተቀር ነገ ለአሥርና ለአስራ ምናምን ቦታ መከፋፈልዋ የማይቀርላት አገር (እንደ ዳያስፖራ ምኞት) ለምን ገንዘባቸውን አውላላ ሜዳ ላይ ለመበተን እንደሚቀኑ ምንም አይገባኝም [አንባቢ በጉዳዩ የሚያውቁት ምሥጢር ካለ በአድራሻዬ ቢጽፉልኝ አስተናግዳለሁ።]

ጎበዝ! የትግራይ ሕዝብ ከሰው በተለየ ልማት የሚያምረው ልዩ ዜጋ ከሆነ ከሌላው በከፋ መልኩ የተጎዳ የራሱ ክልል ነውና ለምን የራሱ ክልል አያለማም? በማለት የማይጠቅ አእምሮ ካሎት ንባቡ እዚሁ እንዲያቆሙ ይመከራል። በተረፈ ግን የዓባይ ግድብ ግንባታ በትግራይ ክልል ይዞታ እንዳይደለ ይዘነጉታል ብዬ አላምንም። 

አሁንም እንደ ዳያስፖራ ምኞት ኢትዮጵያ ለዘጠኝና ለአስራ አራት ይዞታ በምትሸነሸንበት ማግስት የትግራይ ሕዝብ በአብላጫ በገንዘቡ የገነባው የሃይል ማመንጫ ባለቤትነቱ የሌላ መንግሥት ንብረት ነው የሚሆነውና በዚህ ወቅት የትግራይ መንግሥት የሃይድሮ ኤለክትርክ ተጠቃሚ ለመሆን ያማረው እንደሆነ እኩል እንደ ሱዳንና የኬንያ መንግሥት ክፍያ ፈጽሞ ነው የአገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው። ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮኸለች! 

ሌላው የትግራይ ሕዝብ በተመለከተ ይሆናል። እዚህ ላይ ቀጥተኛ በሆነ አነጋገር ሃሳቤን ላስረዳ። የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድምር ውጤት የሆነች፣ የተባበሩት መንግሥት በህግ የሚያውቃት፣ አንዲት ህጋዊ እውቅና ያላት ኢትዮጵያ የሚልዋት አገር እስካለች ድረስ በኢትዮጵያ ምድር በስጋት የሚኖር ሕዝብ/ብሔር ሊኖር አይገባም። ትክክልም አይደለም። 

ዜጎች እንደ ሕዝብ እርስ በርስ በሚገባ መተዋወቅ፣ መፈታተሽና መነቃቃት አለባቸው። ከዚህ ቀደም አይተዋወቁም ማለቴ አይደለም። ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ የትውልድ መተካካትም አለና ይህ ትውልድም መተዋወቅ ባለበት መንገድ መተዋወቅ አለበት ባይ ነኝ። በሚገባ ካልተዋወቁ መጠባበቅ ሆነ መከባበር ብሎ ነገር አይኖርምና። ይህ የምለው ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ብቻ ሳይሆን ለዘልአለም የሚጸና መንግሥትነት የለምና መንግሥት አልፎ መንግሥት በሚተካበት ወቅትም ቢሆን ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሚሰጋበት አንዳች ምክንያት ሊኖር አይችልም፤ አይገባምም እያልኩ ነው። አይመስሎትም?

ለመሆኑ አንዱ ሌላውን ማለትም የትግራይ ሕዝብ አማራን፣ አማራ ኦሮሞን የሚፈራበት ምክንያት ምንድ ነው? ለምን? ማን ምን ስለሆነ? በውኑ አንዱ ሌላውን የሚፈራበት/የምንፈራራበት ዘመን ነው ያለነው ብለው ያምናሉ? በበኩሌ እንደ ሕዝብ አንዱ ሌላውን የሚፈራበት ምክንያት ምንም አይታየኝም። የጥቂቶች የማያባራ ጭኸትም መድኃኒቱ: የትግራይ ሕዝብ ማንቃት፣ ማደራጀትና ማስታጠቅ ነው! ይህ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ህገ መንግሥታዊ መብቱ ነው። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com 

February 1, 2014

 

 

 

Advertisements