ኢትዮጵያዊ ማንነት ሆነ ኢትዮጵያዊነት ብሎ ደም የለም!

ቅምሻ፥

በክርስትና እምነት አከባቢ ቁጥሩ በቀላሉ የማይናቅ ሃይማኖተኛ (ሰንበተ ክርስቲያን) የክርስትና እምነት ማዕከል የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ በተመለከተ መጽሐፍ የሚለውን ማለትና መናገር፤ ኢየሱስ በባህሪው፣ በማንነቱ ሆነ በስራው ሐዋርያት ያስተማሩት፣ የሰበኩትና የገለጡት ትምህርት መስበክ፣ መመስከር፣ ማስተማርና መጻፍ ኢየሱስን ማሳነስ፡ በክርስትና አለማመን ተደርጎ በመውሰድ ግለሰቡን ጭራቅ አድርገህ መሳል፣ መኮነንና መራገም፣ ግለሰቡ በአካለ ሥጋ የተገኘ እንደሆነም እንደ እባብ በድንጋይና በበትር ወግረህና ቀጥቅጠህ መግደል በኢትዮጵያ የሃይማኖት ታሪክ የታወቀና የተለመደ ነው። 

በተመሳሳይ አገር፣ ሕዝብ፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፡ ዜግነት፣ ማንነት፣ ቋንቋ … በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አመሰራረርና ታሪካዊ አመጠጥ በተመለከተም እንዲሁ ፖለቲካዊ አንድምታ መስጠትና በርዕሰ ጉዳዩ ተገቢ ሞያዊ ትንተናና ሐተታ መስጠት እንደ ትኩስ ድንች በሚፋጁ ዜጎች ዘንድ ብዙ ስም ሊያሰጥ እንደሚችል ሳያውቅና ግምት ውስጥ ሳያስገባ ቀደም ሲል በተጠቀሱ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ መናገር ሆነ መጻፍ የሚደፍር ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም። ስለሆነም በበኩሌ ጽሑፉ ተከትሎ በብዕር ስም ሆነ በምንም በጽሑፉ አዘጋጅ ሊሰነዘር የሚችለው ማንኛውም ዓይነት መሰረተ ቢስ የጥላቻ መልዕክቶችና የሚላቀቀው አፍ ቢኖር ድርጊቱ የተለመደና የሚጠበቅ ድርጊት ነውና ጸሐፊው በሚሰነዘረው አሉባልታ ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌላቸውና እንደማይሰማቸው ሲገልጹ በአክብሮት ነው። 

መግቢያ፥

በትርጉም ደረጃ ሆነ በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የሚስተዋለው፣ የሚንጸባረቀውና ያለው ተጨባጭ እውነታ በመንተራስ “ማንነትና ኢትዮጵያዊነት” በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሰፊው ስለተዳሰሰ ወደኋላ ተመልሼ ትርጓሜ ማስቀመጥ አንባቢን ማሰላቸት ብቻ ነው የሚሆነው። ማንነት፣ ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያዊነት በተመለከተ ከዚህ ቀደም “ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንጅ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም!” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃ ጽሑፍ የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ሙሉ የጽሑፉ ይዘት ማንበብ ይቻላል “ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንጅ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም!  P- 123”።

ጽሑፉ በይዘቱ በማንነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን አንድን ሕዝብ በተለይ የትግራይ ሕዝብ ዒላማ አድርጎ ለሚነዛው የጥላቻ ፕሮፖጋንዳና የሚናፈሰውን የደም መፋፈስ ቅስቀሳ ግልጽና ቀጥተኛ መልስ ይሰጣል።

ሐተታ፥

በምስራቅ አፍሪካ 1.14 ሚሊዮን ስኩዌር ኪ.ሜትር የቆዳ ስፋት የተንጣለለች፣ 80 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ተብላ ስለምትታወቀው አገር ስንናገር አንዱ የጭዋይቱ (ተቆርቋሪ ለማለት ነው) ሌላኛው ደግሞ የባራይቱ ልጅ ዓይነት አቀራረብ ባለው መልክ መናገር እየተለመደ መጥተዋል። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር አስንተን የኢትዮጵያ ሕዝብ 80 ሚልዮን የሚጠጋ ህዝብ ነው ስንል/ሲባል ይህ ሕዝብ የአማራ፤ የትግራይ ወይም የኦሮሞ … ሕዝብ ቁጥር ብቻ  አለመሆኑ ክፉኛ ተዘንግተዋል። ጥጉ! 80 ሚልዮን ተብሎ የሚታወቀው የሕዝብ ቁጥር አንድ ዓይነት ባህል፣ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ፣ አንድ ዓይነት ታሪክ፣ አንድ ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ማኅበራዊ ስነ ልቦና፣ አንድ ዓይነት ስልጣኔና አመጣጥ የለውም፤ ያለው ሕዝብም አይደለም። 

ስለሆነም 80 ሚልዮን ተብሎ የሚታወቀው የሕዝብ ቁጥር እንደ አንድ ሕዝብ በተናጠል “እኔ” ማለት የሚያስችለው፤ ራሱ የቻለ፤ በማንኛውም ጊዜና ወቅት ራሱን ችሎ መቆም የሚችል – ማንነት፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህልና አስተሳሰብ ያለው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቁጥር ድምር ነው። ከዚህም በመነሳት “ኢትዮጵያ ማን ናት/ምንድ ናት?” በተጨማሪም ኢትዮጵያዊነትና ማንነት በሚሉ ሁለት ምንም የሚያገናኝ ነጥብ የሌላቸው መሰረት አድርገው ለሚነሱ ጥያቄዎች –

  • ኢትዮጵያ፦ አረንጓዴ፡ ብጫና፡ ቀይ ቀለም ባለው ባንዴራ ተለይታ የምትታወቅ፤ ራሳቸው የቻሉ፣ በማንነታቸው ሙሉ ሥልጣንና ምርጫ ያላቸው፣ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ አገር እንጅ ኢትዮጵያ የአንድ ሕዝብ አገርም አይደለችም። ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊነት የሚለው አነጋገር ሆነ አገላለጽም ዜግነትን (መብት ነክ) ብሎም በህግ የታወቀ “መንግሥነትን” የሚያመላክት፣ የሚያሳይና የሚገልጽ አነጋገር፣ አገላለጽና አባባል እንጅ ኢትዮጵያዊ ብሎ ማንነት ሆነ ኢትዮጵያዊነት ብሎ ደም የለም፤ በታሪክም አልነበረም።
  • ማንነት በእሪኩም ዘፈን፣ በጦርነት ወይም በእግር ኳስ ቴፎዘነት የሚለካ የአፍአ መታወቂያ አይደለም። ማንነት አንድ ሕዝብ የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ አስተሳሰብ፣ ሥልጣኔ … ኖሮት ሥነ ልቦናውም በዚሁ ልዩ በሆነ መልክ ተቀርጾ ከሌላ ሕዝብ ተለይቶ የሚታወቅበትና ራሱን የሚገልጽበት የህልውናው መገለጫ ነው። ይህ መሬት ላይ ያለ ሐቅ የማይገባውና የማይዋጥለት ስም ያለው ግለሰብ ሆነ ማንኛውም ዓይነት ድርጅት ስለማንነቱም ሆነ አገሬ ስለሚላት አገር ራሱን ሊጠይቅና መረዳቱንም ሊገመግም ይገባዋል እንጅ ባልገባው ነገር ሌላውን መዝለፍና ሟሽማጠጥ የውድቀት ሁሉ ውድቀት ከመሆኑ አልፎ እውቀት ሊሆን አይችልም።

ወጣም ወረደ ብዙሐን ሳለን ለጋራ ጥቅም ልዩነቶቻችንን አቻችለን ከአንዲት ባንዴራ ሥር ታቅፎ እንደሚኖር ሕዝብ መኖር፣ ማሰብና መናገር፤ እርስ በርስ ተጠባብቀን፣ ተከባብረን፣ ተቀባብለንና ተግባብተን መኖር ካቃተንና ከተሳነን የራሳችን የምንለው በቋንቋ፣ በባህል፣ በመልከዓ ምድር አቀማምመጥ፣ በአመጋገብ … ወዘተ የሚመስለን ሕዝብ ይዘን ጎራ ለይተን እንደ ሕዝብ ለመቧቀስ እንዲያመቸን ግልጽ የሆነ አጀንዳ ይዘን ብንወጣ ከሃያ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የአዙሪት  ጉዞ “በሁለት ቀናት” ውስጥ ውጤቱን ለማየት በታደልን ነበር። እስከ አሁን ድረስ “ሞረሽ”፣ “ኦሮሞ ፈረስት” የሚሉ ብሔር ተኮር እንቅስቃሴዎች አይተናል ማን ያውቃል በቅርቡ ደግሞ የደቡብ ልጆች “ሐራምቤ”፤ የትግራይ ክልል ተወላጆች ደግሞ በፊናቸው “ትግራይ ለምለም” በማለት በተጠንቀቅ ለመቆማቸው ያሳዩን ይሆናል። በግሌ በእነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች ምንም ዓይነት ቅሬታ የለኝም። ጉዳዩ ጥሩምባ ከመንፋት አልፎ መሬት ስይዝ ውጤቱ የምናየው ይሆናልና። አይመስሎትም? 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

January 31, 2014

Advertisements