የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፖለቲካ የኢያሪኮ ግንብ አይደለም በጩኸት የሚፈርሰው!

የድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራም ለመከታተል የGRE ፈተና ለመውሰድ በቂ ጊዜ ለመሸመት ያክል ከተሰውርኩ ሁለት ወራት ለመድፈን የቀረኝ አንድ ሳምንት ብቻ ነው። ታድያ በትናንት ዕለት በጠፋሁባቸው ሰባት ሳምንታት ውስጥ አዲስ ነገር ያለ/ይኖር እንደሆነ ብዬ ስጎለጉልና ኢትዮጵያን በተመለከተ ምንም የማያመልጠው ብቻ ሳይሆን በሰዓታት ውስጥ ኢትዮጵያ ነክ ዜና ከምንጩ መረጃ የማያጣ ወዳጄ በስልክ ሳጠያይቅም ሁኔታው ድርቅ የሚለው ቃል አይገልጸውም።

እውነትም መዋቹ በቁማቸው ሳሉ ካደነዘዙት ይልቅ በሞታቸው በቁሙ የቀበሩት ዜጋ ቁጥሩ እልፍ ጊዜ ይበልጣል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ገንዘብ፣ ሥልጣንና ዝና ያሳበዳቸው ከአስመራ እስከ መቃድሾ ከአውሮፓ አስከ አሜሪካ ተሰማርቶ የሚንቀለቀለው ትውልድ ገዳይ ፖለቲካ አቀንቃኞች ነገራቸው በጥሞና ያስተዋለ ጭምት ዜጋ በአግራሞት “በውኑ ሰው በቁሙ ይህን ያህል ይገማል ወይ!?” ሲል መያዣ መጨበጫ የሌለው የዳያስፖራ የጩኸት፣ የሁከት፣ የውድቀት፣ የሌብነት፣ የቅጥፈትና የእልቂት ፖለቲካ መሪዎች ድርቀትና አመንዝራነት ሳይደነቅ አይቀርም።

ዳያስፖራ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገጽታ ለመለወጥ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ለለውጥ በሚደረገው “ሰላማዊ ትግል”  ሊያበረክተው የሚችለው አስተዋጽዖ ከዚህ ቀደም በማያሻማ ቋንቋ በሰፊው ጽፌአለሁ። በነገራችን ላይ ሰላማዊ ትግል ማለት ምን ማለት ነው? ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ትግል የሚባል ነገር አለ ወይ? አቅም ማጣትና ሰላማዊነት ምንድና ምንድ ናቸው? የሚለው ሙግት ውስጥ አልገባም። የኢትዮጵያ ፖለቲካና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ፖለቲካዊ ዕንቅስቃሴ በተመለከተ ግን ጥቂት ማለት እወዳለሁ። ወደ ርዕሰ ነገሬ ከመሄደ በፊት ግን አንድ በጣም የሚደንቀኝ ትንግርት የሆነበኝ ነገር አካፍላችሁ ዘንድ እወዳለሁ። ይኸውም፥

ደንቆሮ፣ ያልተማረ፣ መሃይም፣ እረኛ፣ በረኛ፣ የበርሃ ዳኛ፣ መናኛ፣ መጋኛ … ተብሎ የሚታውቀው “ወያኔ” አገር ሰጥ ለጥ አድርጎ ሲመራ በአንጻሩ ደግሞ በጃንሆይ ጊዜ የተማሩ፣ አገር ያፈራቻቸው በኩራዝ ተፈልገው የማይገኙ ምሑራን፣ አሜሪካ በሚገኘው ምናምን ዩኒቨርስቲ የምናምን መምህር፣ ኢኮኖሚስት፣ ተንታኝ፣ ሊቅ፣ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ኦፊሰር ተብሎ የሚታወቅ የወየበ የዳስፖራ ጉጅለ ደግሞ ካንሰር ሆኖውብን “ዋልድባ!፣ ሳውዲ!፣ መጅልስ!” እያሉ ስያፏጩና ሲነጅሱን፤ ትንተናቸው አይደለም የተበተነ ሊሰበስብ የተሰበሰበ የሚበትን፣ እውቀታቸው ከሰፈር ቃሊቻ የማይሻል፣ ያገሬ ሰው “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” እንዲል ትምህርታቸውና ሊቅነታቸው ከራሳቸው ከርስ ያለፈ ፋይዳ የሌለው ሆነው ሳያቸውና ሳገኛቸው እንዴት አይገርመኝም? ይገርሞታል በጣም ነው የሚደንቀኝ።

ልጅ እያለሁ ትዝ ይለኛል ሰፈር አከባቢ አንዲት የታመመ እፈውሳለሁ፣ ሀብት አሰጣለሁ፣ ወርቅ አሸልማለሁ፣ ገንዘብ እፈለፍላለሁ፣ ትዳር አቀናለሁ … የምትል ቃልቻ/ጠንቋይ ነበረች። ታድያ ዘወትር ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ማለዳ ፲ ሰዓት እየተነሳሁ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስገሰግስ ተስፋ ሰንቆ ደሮ፣ በግ፣ ፍዬል … በአጭሩ ከራማው እንዳዘዘው ይዞ የሚንጋጋው ቁጥር ሥጋውን በልታ አጥንቱን ያደቀቀች ጠንቋይዋ ራስዋ ትቁጠረው። 

ታድያ በምዕራቡ ዓለም ኑሮአቸውን አደላድለው ሲያበቁ ሕዝብን ማደናገር፣ ያላቡትን ሀብትና ንብረት በአቋራጭ ለማግበስበስ ታጥቀው የተነሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አሳፋሪ ድርጊት የራስዋ ያፈጠጠ እባጭ/ቁስል የማታክም ነፈዝ ዳሩ ግን “የታመመ እፈውሳለሁ” እያለች ገንዘባቸው ዘርፋ በየጊዜው በልዩ ትዕዛዝ የምታስገብራቸው ምርጥ ምርጥ ዶሮና በግ መብላትዋን አንሶ ገላቸውን በፈርስ እያጠበች (በውሸት ፕሮፖጋንዳ) የታማሚዎች (የዜጎች) ዕለተ ሞት የምታፈጥን የሰፈር መተተኛ ለይቼ ላያቸው አልቻልኩም።

ወደ ርዕሳችን ስንመለስ። የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ማዶ ላይ ተቀምጦ የሚያሳየው መወራጨትና የሚያደርገው መረኑን የለቀቀ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ በኢትዮጵያውያን የዕለተ ዕለት ኑሮ በቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ ከመሆኑ አልፎ የውጣ የሚፈይደው/የሚረባ ቁምነገር እንደሌለ ጨምሬ ዳያስፖራ በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ ሊጫወተው የሚችል ሚና እጅግ በጣም ውሱን ከመሆኑ የተነሳ ያለው ዕድልም በአግባቡ ካልተጠቀመበት ከሚያለማው ይልቅ የሚጠፋው፣ ከሚተክለው ይልቅ የሚነቅለው፣ ከሚገነባው ይልቅ የሚያፈርሰው፣ ከሚበጀው ይልቅ የሚፈጀው አጥፊ አውዳሚና አፍራሽ ኃይል ሆኖ የገዛ አገሩና ሕዝቡ ሊያወድምና ደም ሊያቀባ እንደሚችል ቀደም ባሉ ጽሑፎቼ ገልጫለሁ።

አሁንም ቢሆን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ባለበት ለመርገጥ ልቡን ካደነደነ አገሩ ራሱ (አሜሪካ ማለቴ ነው) ላውራበት ካሉ በልጅ ላይ ልጅ እየፈለፈሉ በልጆች ስም የመንግሥት እጅ እየመነተፉ ያለ ሃሳብ ተዘለው እየበሉና እየጠጡ ቀን ተሌሊት ፓልቶክ ላይ ተጥደው/ተወትፈው እየተገለባበጡ የሚያገሱበትና የሚያወሩበት፣ ለመልማትም (ራስህን ለመለወጥ) አጥፍቶ ለመጥፋት በምርጫ የሚኖርባት ያልደከምንባት ለምለም አገር ናት። 

ዳያስፖራ እውነት ስለ አገርና ስለ ሕዝብ የሚቆረቆር ዜጋ ከሆነ ወዶ ሳይሆን ተገዶ ሊያውቀው፣ ሊቀበለውና ሊተገብረው የሚገባ እውነት አለ። ይኸውም፥ አውሮፓና አሜሪካ ተቀምቶ “ሞረሽ! … ማነሽ!” እያለ ጉሮሮው ከትናጋው ጋር እስኪጣበቅ ድረስ መጮህና መሸለል፤ የድሃ አድግ ልጆች ደም እንደ ውሃ ለመጠጣት የቀን ዕረፍት የሌሊት ዕንቅልፍ ያጡ ወፋፍራሞች እየተደለለ ከበሮ መቺ ሆኖ ነፈሰ ገዳዮችን ከማጀብ ተቆጥቦ ያዋጣል የሚለውን እጀንዳ ይዞ የኢትዮጵያ ምድር አፈር መርገጥ ይጠበቅበታል። ምን ነው? ቢሉ የኢህአዴግ  ፖለቲካ የኢያሪኮ ግንብ አይደለምና በጭኸት የሚፈርሰው።

  • ኢሳትን በተመለከተ: ኢሳት ማለት ግርድፉንም፣ ቆሻሻውንም የነፉበትን ሁሉ እየተቀበለ የሚያስተላልፍ ቀዳዳ ወንፊት! በሚል ቅልብጭ ያለች ዓረፍተ ነገር ብንቋጨውስ? አይመስሎትም? 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

January 30, 2014

Advertisements