የቀን ቅዠት ያበላሸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከማንዴላ ምን ይማራል፡

Salsay woyane Mandela Prison

የጽሑፍ ዓላማ፥

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንዴላን ማወደስና መቀደስ አይደለም። የእኔ ውዳሴና ቅዳሴ ለማንዴላ በዓባይ ወንዝ ምራቅ እንደ መጨመር ነው። ታድያ “የእኛ ሰዎች ከማንዴላ ምን ይማራሉ?” ተብሎ ለቀረበውና ለሚሰነዘረው ጥያቄ ግን ጽሑፍ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ መልስ ይሰጣል።

መንደርደሪያ፥

የምዕራብውያን የፖለቲካ ግብዝነት እንደሆነ ማለቂያ የለውም። የምዕራባውያን ሚድያዎች ታላቁ ሰው: ጀግናው: አፍሪካዊ: … ማንዴላ በዛሬው ዕለት በ95 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተሰናበተ ሲሉም የአዞ እንባ እያፈሰሱ ናቸው። ማንዴላ ታሪኩ ብዙ ነው። ማንዴላና ምዕራባውያን በተመለከተ ከይዘቱ ጥልቀትና ስፋት አንጻር በሌላ ርዕስ በሌላ ጊዜ በሰፊው እመጣበታለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ለጊዜው ግን እ.አ.እ በ1962 ዓ.ም ማንዴላን ወደ ሮቢንስ ደሴት (ለ18 ዓመት የማቀቀበት ቦታ መሆኑ ነው) ለግዞት የዳረገ/ያወረደ የአሜሪካ ግዙፉ የስለላ ተቋም ባደረገው ከፍተኛ እገዛና እርዳታ ለመሆኑ የማይካዱ መረጃዎች በተጨባጭ ያመላክታሉ። ከዚህም የተነሳ ማንዴላ ሆነ በማንዴላ ይመራ የነበረ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (African National Congress/ANC) በአሜሪካ የሽብርተኝነትና ሽብርተኞች መዝገብ በአሸባሪነት መዝገብ ሰፍሮ መዝገቡም ሳይፋቅ እ.አ.እ እስከ 2008 ዓ.ም መዝለቁን ይታወቃል። 
ይህ ብቻም አይደለም ማንዴላ በእስር በነበረበት ዘመናት “የሰብዓዊ መብት ተማጋች” ተብሎ የሚታወቁ በወቅቱ የነበረ ምዕራባዊ ተቋም “Amnesty International” ዘንድ ማንዴላ “የህሊና እስረኛ” ተብሎ መታወቁ ቀርቶበት ለመታሰሩም እውቅና የተነፈገበት ሁሉን ችሎ ያለፈ ሰው ነበር ማንዴላ ማለት። ጥቁሩ ሰው ማንዴላ ታግሎ ያልጣለውና ያላሸነፈው ነጭ የት ይገኛል ብለው ነው። ለመዋች ‘ዕረፍተ ነፍስ’፤ ለቤተ ዘመድ ለወዳጆቹና ለደቡብ አፍሪካ ዜጎች በመላ ደግሞ እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጥ ዘንድ ጸሎቴ ነው። 

በመቀጠል አጠር አጠር ባለ መልኩ ስለ በፖለቲካ ህይወቱ ምን ይመስል እንደነበር በስብዕናው ዙሪያ ጥቂት ነጥቦችን አናነሳለን፤ አያይዘንም በንጽጽር መልክ መሆኑ ነው የቀን ቅዠት ያበላሸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ደግሞ ምን እንደሚመስል በተመሳሳይ አጠር አጠር ባለ መልኩ እንወያያለን። በመጨረሻም የማንዴላ የቀብር ሥነ ሥርዓት እያየ በተቀመጠበት በዓይነ ህሊናው እያለቀሰ የራሱን ሬሳ የሚሸኝና የሚቀብር የሀገራችን ፖለቲከኛ ምክር ቢጤ ለግሰን እንለያያለን።

ሐተታ፥ 

ቀይ ካርፔት ተነጥፎልህ በዝግታ ስትንጎራደድ፤ የዓለም መንግሥታት በሃገራቸው ብሔራዊ መዝሙር ታጅቦው በክብር ሲቀበሉህና ሺሸኙህ፤ በታላቂትዋ ሀገርና በሰፊው ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መሰል ወሳኝ ጉዳዮች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያልክ መንግሥታዊ ቃልህን ስትሰጥ፤ ደስታና ፌሽታ በማይለይበት ዘወትርም ግብዣና ዳንኬራ በሆነበት በምኒልክ ቤተ መንግሥት ተቀምጠህ “እዘዝ በገላዬ!” እያልክ ያለ ሃሳብ ስትበላና ስትጠጣ እየታየህ ሌሊቱን ማንጋት በእርግጥ ቀላል ነው። በአንጻሩ ደግሞ ማንዴላን ማንዴላ ያስባለ ህይወት/መንገድ መሄድና ማለፍ ደግሞ እንደው የማይታሰብ ሊሆንብን እንደሚችል ሁላችን እንደምንስማማ አምናለሁ።

የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ደረሰብኝ በማለት በገፊዎቹ ላይ የሚቆጥረው ግፍና በደል አለ ከተባለ ከማንዴላ ትክሻ የተረፈ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከማንዴላ በላይ ተገፋሁ ማለት የሚችል ደቡብ አፍሪካዊ ዜጋም ይኖሯል ብዬ አላምንም። ማንዴላ የሞተና ራሱን የቀበረ የዛሬ 51 ዓመት ነበር።

ማንዴላ ስኬታማ ውጤታማም ሰው ነበር። እንዲህም ሆኖ ግን የማንዴላ ህይወት ምንም አያስመኝም!! ዓለም ለማንዴላ ያሳየችው ክብርና ፍቅር ለማግኘት የሚመኝ ሰው ካለም አንድ ማለፍያ ምክር እለግስለት ዘንድ እወዳለሁ ይኸውም፥ ማንዴላ ባለፈበት ህይወት እንድያልፍ እመክረዋለሁ። ሰው ያገኘውን ለማግኘት ሰው የሄደበትን መንገድ መሄድ ነው። አይመስሎትም? በነገራችን ላይ አሁን ይሄ ምኑ ይከብዳል? ሰው “መመኘትን” የማውራት ያህል ከቀለለው “መሆንን” እንዴት የሞት ያህል ይከብደዋል? እንግዲያውስ “መሆንን” የሚጠላ ሰው ካለ አንዳፍታው “መመኘትንም” አጥብቆ ይጸየፍ ዘንድ ነው ሁለተኛ ምክሬ የምለግስለት።

ማንዴላ ማለት፥ 

 • በወጣትነት ዘመኑ ሁለመናው መስዋዕት አድርጎ ለዜጎቹ ሕይወት የሰጠ፤
 • ጨለማ ውስጥ ራሱን ጥሎ ለዜጎቹ ብርሃን ያበራ፤
 • በለቅሶው፣ በሐዘኑና በስብራቱ ዜጎቹን ጮቤ ያስረገጠ፣ ደስታንና ዕረፍትን የሰጠ፤
 • ማዶ ተቀምጦ ሳይሆን በአገሩ በሕዝቡ መኸል ሆኖ ታግሎ ሕዝቡን ያታገለ፤
 • ማንዴላ ማለት ራሱን ከሰው ተርታ አውጥቶ ለዜጎቹ እኩልነት ያጎናጸፈ፤
 • ማንዴላ ማለት ራሱን አዋርዶ ለዜጎቹ ፍትህ ያወረደ፤
 • ማንዴላ ማለት ለራሱ አጥቶ በገዛ አገሩ በእጦት ሲንገላታ፣ ሲናጥና ሲዋረድ የነበረ ዜጋ የሀብት ባለ ቤት ያደረገ፤
 • ማንዴላ ማለት በቃል ሳይሆን በኑሮው የሕዝብ መሪነቱን ያረጋገጠ፤
 • ማንዴላ ማለት የጠላቶቹን ልብ በጥበብ፣ በእውቀትና በምህረት የገዛ፤
 • ጎበዝ፡ ማንዴላ – “ነጻነት!፣ ፍትህ!፣ ዲሞክራሲ! …” ምናምን ምናምን እያለ ባንዴራ እያውለበለበ የሕዝብ ሀብትና ንብረት የሚዘርፍ ሌባ አልነበረም።
 • ማንዴላ ጥዋት የተናገረው ከሰዓት የማይደግመው ሸምጣጭ፣ ለቃሉ የማይታመን፣ አታላይና ወመኔ ዓይነት ሰው አልነበረም። ማንዴላ ለሕዝቡና ለሀገሩ የነበረው ታማኝነቱ እስከ ሞት ድረስ በመታመን በህይወቱ የገለጸ ሰው ነበር።
 • ማንዴላ እምነት የማይጣልበት፣ አውደልዳይ፣ ወፍራም ዱሩዬ ዓይነት ግለሰብም አልነበረም። ማንዴላ እኔና እርስዎ ለመግለጽ ከሚቃጣን በላይ ለቆመለት ዓላማና ሕዝብ ጽናቱንና እምነቱን ያሳየ ሰው ነበር። [ማንዴላን ጀግና ብዬ ብሎ መግለጽ የማንዴላ ሥራ ያቀለዋል ብዬ ስለማምን ነው በሰውነቱ ብቻ ለመግለጽ የተገደድኩ።]
 • ማንዴላ ዶክተር ወይም ፕሮፌሰር አልነበረም። ማንዴላ ማለት ግን ዶክተርና ፕሮፌሰር የማይሰራውን ስራ ሰርቶ ያለፈ፤ ዶክተርና ፕሮፌሰር ተብሎ መጠራት የማይሻው የሕዝብ ንብረት ነበር።
 • ማንዴላ፡ የፈጠራ ወሬ እየፈበረከ በሐሰት፣ በቅጠፈት፣ በፕሮፖጋንዳና በውሸት ሳይሆን በነፍሱ ተወራርዶ ነበር አፓርታይድን ድባቅ የመታ።
 • ማንዴላ፡ የመብት ሕጋዊ ትርጉም ያልገባቸውና መቼም የማይገባቸው፣ ስለ ሰብዓዊ መብት የመናገር ሞራል የሌላቸው ሞራለ ቢሶች፣ አሉባልተኞች፣ ወረኞችና ነፈሰ ገዳዮች አሰማርቶና አስከትሎ አልነበረም ጠላቱን ታግሎ የጣለ። ማንዴላ ዓላማ የነበረው ለምያምነው ዓላማም ሞት ደጆቹን በናስ ብረት ዘጋበት እንጅ እስከ ሞት ድረስ በመታመን ለራሱና ለዜጎቹ መብት የቆመ ግለሰብ ነው። 
 • ለማጠቃለል ያክል፡ ለፍጡር አምልኮ “ይገባዋል” ብሎ የሚያምን ሰው ካለ ለማንዴላ ታቦት ቀርጾ ቢሰግድለት ተቃውሞ የለኝም! ማናቸውም ቢሆኑ ከዚህ የተለየ/የሚሻል ሥራ አልሰሩምና። [ይገባዋል አላልኩም]

የቀን ቅዠት ያበላሸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ደግሞ በአንጻሩ ይህን ይመስላል፥

 • አንዳንዱ፡ በውጭው ዓለም እንጀራውን ሲያደላድልና የራሱን ኑሮ ሲኖር ጉልበቱ የተበላ፣ በጥሮታ ተገሎ ሲያበቃም የፈዘዘ ዓይንና የደነቆረ ጆሮ ይዞ በስተርጅናው ኢትዮጵያ ግብቶ “እኔ ልምራህ!” በማለት ዘራፍ! የሚል አጀበኛ ነው።
 • አንዳንዱም፡ ቢቆጠር ሁለት ዓመት የማይሞላ ጊዜ አተካራ ገጥሞ “ስለማዊ ትግል ከእኔ በላይ ላሳር!” የሚል ወፍራም ዱርዬ ነው።
 • ገሚሱም፡ “የሕዝብ መሪ ነኝ” ብሎ ሲያበቃ ስራውን ሕዝብ እንዲሰራለት የሚፈልግ ጉልት ነው። 
 • ከፊሉም፡ ሁለት ዓመት የማይሞላ ጊዜ ታሰርኩ ተብሎ ሆድ የሚብሰው ሆደ ባሻ፣ ስቅስቅ ብሎ የሚያለቅስና የሚነፋረቅ አልቃሽ “ፖለቲከኛ” ችላ የተሸከመች አገር ናት እኮ ኢትዮጵያ ማለት። ለመሆኑ የትኛው ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ነው ከሕዝቡ የተሻለ እውቀት ያለው? ፖለቲካ ማለት ማይክ ይዘህ እንደ ሽሮ መንተክተክና እንደ ጀበና ገንፈል ገንፈል ማለት ካልሆነ በስተቀር። 
 • የተቀረው ደግሞ ገና በአንድና ሁለት ዓመት ውስጥ የጀመረውን መንገድ አስመርሮት “የአሜሪካ ያለህ!” ሲል ድምጹን ከፍ አድርጎ አሜሪካን ይጣራል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ትልቁ ስህተት ብዬ የማምነው ከሆነ ካለሆነ ጋር መሯሯጡ ነው። ይሄ አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጦ የሚያፏጨው ዜጋ* [በጅምላ ሁሉን አላልኩም] ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርጎ አይደለም አገር ቀበሌ መምራት እንደማይችል ማሳየት ይጠበቅበት ነበር። እግዚአብሔር የወንድማችን የማንዴላን ነፍስ ያሳርፍ!!

የቀን ቅዠት ላበላሻቸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ “ፖለቲከኞች” ምክር፥

 • ማንዴላ ያተረፈውን ዝና ለማትረፍ፤
 • ዓለም ወድዳ ሳይሆን ተገዳ ለማንዴላ የሰጠችውን ክብር ለመጎናጸፍ፤
 • ማንዴላ የደረሰበት ለመድረስ፤
 • ማንዴላ ያገኘውን ስም ለማግኘት፤
 • ማንዴላ የሰራውን ስራ ለመስራት፤
 • እንደ ማንዴላ ለመክበር፤
 • እንደ ማንዴላ ስምህን ለማስጠራት፤
 • እንደ ማንዴላ የዓለም ቀልብ ለመሳብ፤
 • እንደ ማንዴላ አለጋጋሪ ለመሆን፤
 • እንደ ማንዴላ ስምህን በወርቅ መዝገብ ለማስፈር፤
 • እንደ ማንዴላ የዓለም ሕዝብ ከመቀመጫው ተነስቶ በታላቅ ክብርና በደማቅ ጭብጨባ ለመስተናገድ፤
 • እንደ ማንዴላ በዓለም ታላላቅ ሚድያዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ለመሞገስና ብሎም ለመወደስ፤
 • በአጠቃላይ ማንዴላ የተጎናጸፈው ዘመን የማይሽረው ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ ለመጋራት – ማንዴላ የሄደበት መንገድ መሄድ ማንዴላ የሆነውን መሆን ነው። ቀላል! በተረፈ ስለ ማንዴላ በማውራት ማንዴላ ያስመዘገበውን ድል ማስመዝገብ አይቻልም። ህልም ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Dec 6, 2013

Advertisements