ለዳይስፖራ ድረ ገጾችና የድረ ገጽ ባለቤቶች በሙሉ!

ካለፈው “ሁለተኛ ግፌ ጫንቃዬን ተገርፌ ልብሴን መገፈፌ!” (ክፍል 1) የቀጠለ ጽሑፍ።

ጽሑፎቼ ለእውነት ፈላጊ ለሰፊው ሕዝብ እንጅ በሕዝብ ስም ለሚነግዱ ለጥቂቶች ብሎም የጥቂቶች ዓላማ ማስፈጽምያ መሳሪያ ለሆነው ለሚድያ እንደማይሆኑና እንደማያመቹ አሳምሬ አውቃለሁ። እንዲህም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ፣ ሃገራዊ፣ ማህበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች እንደ አንድ ግለሰብና እንደ ዜጋ ሃሳቤን በነጻነት የምገልጽበትና የማንጸባርቅበት የቀረችን አንድ ኢትዮጵያን ሪቪው “Ethiopian review” ወደማጣት እየተጠጋሁ መምጣቴ እየገረመኝ ነው። እየሆነ ባለው ነገርም አንዳች ቅር የሚለኝ ነገር ባይኖርም በሀገሪትዋ መጻኢ ዕጣ ፈንታ ግን እጅግ አዝናለሁ።

አቶ ኤልያስ ክፍሌ ይህን ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም። ለዓመታት በዘለቀ ከሰጠኝ ዕድል በመነሳት ስለ አቶ ኤልያስ ክፍሌ ስብእና [የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ በተመለከተ] የማውቀው ነገር ቢኖር አቶ ኤልያስ በሃሳብ ፍጅትና ፍጭት እንደሚያምንም ነው እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ የማውቀው። ይህ ባይሆን ኖሮ  በግለሰብ ደረጃ አቶ ኤልያስ ከነ አካቴው የእኔ ጽሑፎች የማስተናገድ ግዴታውም የለ ብዬ ነው የማምነው። እንደሌለቹ ደጁን ቀርቅሮ የመዝጋት ስልጣን በእጁ ነው። 

አንድ ዜጋ በህግ ከሚጎናጸፋቸው መብቶች መካከል “የአንድ ዜጋ መብት ነው” ተብሎ ብዙ የሚነገርለትና የሚወራለት የመጻፍም ሆነ የመናገር መብት ከቃል ያለፈ ሰጪና ነሺ አካል ማንነት በውል ባይታወቅም፤ በበቂ ሁኔታ መልዕክት የማስተላለፍና በሥራዎቼ ተጽእኖ የመፍጠር አቅሙና እውቀቱ እስካለኝ ድረስ በሀገሬ ጉዳይ በፖለቲካ አነጋገር እንደ ዜጋ ጭብጥ ላይ ተመርኩዤ በስርዓቱ ሃሳቤን የመግለጽ መብት አለኝ። ሁል ጊዜ የእኔ ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው ማለት አይደለምና በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ የተለየ ሃሳብ ያለው፤ በእኔ ሃሳብ የማይስማማና ሌላ አመለካከት የሚያራምድ ግለሰብ ደግሞ ሃሳቤን በሃሳብ በመቃወም ሃሳቡን የመግለጽ እኩል መብት አለው። አሁን ያጣሁትና የተነፈግኩት መብት ቢኖር ግን በዜግነቴ ግላዊ  ሃሳቤን መግለጽ  ጨምሮ የማይመስለኝን ሃሳብን በሃሳብ መቃወም ጭምር አለመቻሌ አሳስቦኛል።

ከዕይታ የተሰወሩና ከስፍራቸው የተነቀሉ ተከታታይ ንባቦች፥ 

 • NOVEMBER 15, 2013 – “እስልምና ብሎ ሰይፍ እንጅ ፍትህ የለም!” [http://wp.me/p3MQOW-ig]
 • NOVEMBER 18, 2013- “ታማኝ በየነ፡ ፈሪ ብቻ ሳይሆኑ ጎበዝ ተማሪ መሆናቸው ጭምር                               አስመሰከሩ!” [http://wp.me/p3MQOW-j0]
 • NOVEMBER 19, 2013 – “ለኢሳት ፀሐይ – ለታማኝ በየነ እንጀራ ወጣላቸው!” (ክፍል 1) [http://wp.me/p3MQOW-jb]
 • NOVEMBER 20, 2013 – “ለኢሳት ፀሐይ – ለታማኝ በየነ እንጀራ ወጣላቸው!” (ክፍል 2) [http://wp.me/p3MQOW-ji
 • NOVEMBER 21, 2013 “ድሃና ሥራ አጥ ኃይማኖት ያከራል!” (ክፍል 1) [http://wp.me/p3MQOW-jx)]
 • NOVEMBER 22, 2013 – “እግዚአብሔር ማወቅ እንዲህ ከሆነ እሱም ባያውቀኝ እኔም ባላውቀው ይሻለኛል! ምንም አይቀርብኝም፡” (ክፍል 2) [http://wp.me/p3MQOW-jE]
 • NOVEMBER 23, 2013 – “በቱሪስት ተጎበኘህ ማለት እግዚአብሔር ታውቃለህ ማለት አይደለም!”  (ክፍል 3) [http://wp.me/p3MQOW-jQ]
 • NOVEMBER 24, 2013 – “ኢሳት የእኔ ሊሆን አይችልም!” [http://wp.me/p3MQOW-jY]
 • NOVEMBER 27, 2013 – “አጉል ተስፈኞች አንሁን፤ ተመጻዳቂዎች ከመሆን ህይወትም እንውጣ!”   (ክፍል 4) [http://wp.me/s3MQOW-1268]

እንደ ዜጋ የማልስተናገድበት ምክንያት ምንድ ነው?

ከዚህ ቀደም ያለ ጭብጥና በቂ መረጃ የጻፍኩት ጽሑፍ የለኝም፤ ወደ አንዱ ወገን የሚያደላ የሽፍጥ ሥራም አልሰራሁም፤ ተራና የወረደ ንትርክ አልፈጠርኩ፤ በሐሰት ማንንም አልወነጀልኩም፤ ግለሰብ አላንጓጠጥኩ፤ በግለሰብ ግለ ህይወት ገብቼም አልፈተፈትኩ፤ የፖለቲካ መሪዎች አልሰደብኩ … ያለውን እውነታ ሳልጨምር ሳልቀንስም ለአንባቢያ በማቅረቤ የምታገድበት፣ የምከለከልበትና የምወገዝበት ምክንያት ምንድ ነው? ድረ ገጾች በእነዚህና መሰል ጽሑፎች እንደውም በብዕር (የሐሰት) ስም በሚጻፉ ጽሑፎች ሲጣበቡ እኔ እንደ ዜጋ የማልስተናገድበት ምክንያት ምንድ ነው?

ለመሆኑ የእነዚህ “በኢትዮጵያውነት” ስም እንደ አሸን የፈሉ መቀመጫቸው ዳያስፖራ ያደረጉ ድረ ገጽና የድረ ገጽ ባለቤቶች ዓላማና ተልዕኮ ምን ነው? ጥይቄው የባለቤትነት ጥያቄ ከሆነ ድረ ገጹን ያቋቋመበት ዓላማ የሚያውቀው ባለቤቱ ራሱ ነውና በተለይ አንዳንድ “ግዕዝና አግአዚ” የማይለይ የድረ ገጽ ባለቤት ለምን ጽሑፌን አልተቀበልክም ወይም ለንባብ አላበቃህልኝም ብዬ ሙግት ውስጥ የምገባበት አንዳች ምክንያት የለኝም። ከሌሎችም ቢሆን እንዲሁ። ጎመን በጤና! በዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚያምን ግለሰብ (የድረ ገጽ ባለቤት) ግን የአንድ ዜጋ አመለካከት ላለማስተናገድ የሚያቀርበው ምክንያት የለውም።

የሰው ጽሑፍ እያደንክ መለጠፍ ጋዜጠኝነት አይደለም!

ኢትዮጵያውያን የድረ ገጽ ባለቤቶች ወቅቶችን በማስመልከት ርዕሰ አንቀጽ ጽፈው ማስነበብ ብርቅ ነው። እርግጥ የተሻለ የሚሉት ነገር ሳይኖራቸው ቀርቶ የሚወስዱት እርምጃ ከሆነ ነገሩ ምንም ስህተት የለውም። ያልሆነውን ጽፈህ ራስህን ከማስገምገም ዝምታን መምረጥ በራሱ በተለምዶ አነጋገር እውነትም ‘ጥበብ’ ነው። ቢሆንም የዜጎች ነጻ ሃሳብና አመለካከት ማፈንና መግታት ግን የአንባገነኖች እኩይ ጸባይ መገለጫ ተግባር ከመሆን አልፎ ጥበብ ወይም እውቀት አልያም የነጻ ፕሬስ ልዩ መታወቂያ ሊሆን አይችልም።

ጋዜጠኛ ማን ነው? ጋዜጠኝነትስ ምንድ ነው? ብዬ ማተት የጽሑፌ ዓላማ አይደለም። በቀላሉ ግን ጋዜጠኝነት ሰፊው ሕዝብ ያላየውን ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል ማህበራዊ አልያም ኢኮኖሚያዊ ሃሳቦችና አመለካከቶች ከላይ ወደ ታች ከታችም ወደ ላይ በሕዝብ መካከከልም እንዲሁ ማንሸራሸር፣ ማመንጨት፣ ማፍለቅና ማስተዋወቅ እንጅ እንደ ባልቴት ከሰፈር ሰፈር እየዞርክ ወሬ መለቃቀም ማለት አይደለም።
እንደ አንድ ጋዜጠኛ ሕዝብና አገር የሚጠቅም ስራ መስራት ማለት የወሬ መጋዘን ከመሆን ጋር ምንም ዓይነት ግኑኝነት የለውም። የሰው ጽሑፍ በየደቂቃው በመለጠፍ ብቻ በራሱም ጋዜጠኛ አያስብልም። ነገሩን ያሰፋነው እንደሆነም ጋዜጠኝነት በሰው አእምሮ እንጀራህን መጋገር በጭምቶች ትክሻም መንጠላጠል ማለት ሳይሆን  ጋዜጠኝነት እውቀት፣ ትምህርትና ጥበብ የሚጠይቅ ሞያ ነው።

ከዚህም በመነሳት አንድ በሙያው የሰለጠነ ጋዜጠኛ ከተጨባጭ ሁኔታዎች በተያያዘ ቢያንስ ቢያንስ በቀን ውስጥ የሚለው/የሚጽፈው አስተማሪና ገንቢ የሆነ ቁምነገር ይኖሯል። በተሰማራበት ልዩ የሞያ መስክም ጥራቱ በጠበቀ መልኩ ከአምስት አስከ አስር ገጽ – በዓመት ውስጥ በቁጥር 365 ርዕሰ አንቀጽ፣ ሐተታ፣ መጣጥፍ፣ ትርጓሜ፣ አንድምታና ምልከታዎች የመጻፍ ግዴታ አለበት። “ሰው ሲታጣ. ይመለመላል ጎባጣ” ካልሆነ በስተቀርም በዓመት 365 ጽሑፎች የማያዘጋጅ ሰው ራሱን በጋዜጠኝነት ስም ባይጣራና ባያስተዋውቅ ነው የሚሻለው።

በዳስፖራ የድረ ገጾችና የድረ ገጽ ባለቤቶች የሚስተዋለው ችግር እንከኖችና መንስኤዎቻቸው፥ 

ወደ ርዕሴ ስመለስ፥ በዳስፖራ ድረ ገጾች የሚስተዋሉ አንኳር ችግሮችና እንከኖች በስሱ በመጠቆም፤ ለድረ ገጽ ባለቤቶችም በጉዳዩ ዙሪያ እንዲያስቡበትና የቆሙበት መንገድ ይሰልሉ ዘንድም ጥሪዬን በማቅረብ ጽሑፌን እቋጫለሁ።

በዳያስፖራ ድረ ገጾች መካከል እንደ ወረርሽን የተጋባው የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የማፈንና የማሳፈን ኢ-ዲሞክራሲያዊ እኩይ ድርጊት እንደ ዋነኛ መንስኤ ችግር ሆኖ የሚታየኝ (የሁሉም ደረ ገጾችና የድረ ገጽ ባለቤቶች ባይባልም) ከሞላ ጎደል ግን በዳያስፖራ የድረ ገጽ ባለቤቶች በአብዛኛው ከሙያው ጋር ምንም ዓይነት የጠለቀ ግኑኝነት የሌላቸው፤ በዘልማድ “ጋዜጠኛ” ተብሎ ከመጠራት ያለፈ በሞያው (በጋዜጠኝነት ሞያ) መሰረታዊ 101 የጋዜጠኝነት ሞያ ስልጠና የማግኘት ዕድሉ ባያልገጠማቸው ግለሰቦች እጅ በመወደቁ ነው ባይ ነኝ። በጠራራ ጸሐይ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ክፉኛ ሲሸረሸር፣ ሲተረማመስና ዜጎችም ክፉኛ ሲበደሉና ሲጎሳቆሉ የሚስተዋለው ምክንያቱ ከዚህ አልፎ ሌላ ሊሆን አይችልም። በተጨማሪም፥

 • አንዳንዶቹ (የድረ ገጽ ባለቤቶች) ለሚሰሩት ሥራ በራሳቸው እምነት ስለሌላቸው ከዚህም የተነሳ ለሚሰሩት ስራ የሌላ ወገን ይሁንታ ይሻሉ፤
 • ከፍተኛ የሆነ የእርስ በርስ መፈራራትም አለ (በድረ ገጽ ባለቤቶች መካከል ማለቴ ነው)፤
 • እርስ በርስ አለመተማመን በሽታም የተለከፉ ናቸው፤
 • “ወያኔ” የሚባለው የጋራ ጠላታቸው እንዳለ ሆኖም ሁሉም ደረ ገጾች ከወያኔ በተጨማሪ በተናጠል በጠላትነት የሚፈርጁት ተቃዋሚ ግለሰብ/ድርጅት አሏቸው። ጽሑፎች የሚቀበሉበት ሚዛንም አንዱ ይህ ነው። መምታትና ማስመታት የሚፈልጉት አካል ሲኖር በውትወታ ሁላ ሊያስጽፉህ ይችላሉ።
 • በተጨማሪም ሁሉም ድረ ገጾች የየራሳቸው የሚያመልኩት ጣዖት (ግለሰብ ሊሆን ይችላል ድርጅት) አሏቸው። ጽሑፎች የፈለጉ ሚዛናቸው ቢጠብቁና ሀገርንና ሕዝብን በሚጠቅም መልኩ ቢዘጋጁም የእነዚህ ግለሰቦች/ድርጅቶች ጥቅም የማይጠብቅ ከሆነ ጌቶቻቸው ማስከፋት ስለማይፈልጉ የዜጎች ነጻ ሃሳብ ማፈንና ማሳፈን የተለመደ ተግባር ሆኖ መጥተዋል።  
 • በራሳቸው በመቆም ፈንታም የመለጠፍ አባዜም በተጨባጭ ይታይባቸዋል፤ እነዚህና ሌሎች በርካታ ያልተዘረዘሩ ችግሮች ተዳምረው ዜጎች በዜግነታቸው ሃሳባቸው በነጻነት እንዳይገልጹ ትልቅ እንቅፋት ሆኖዋል ባይ ነኝ። 

ማጠቃለያ፥

በዳስፖራ የድረ ገጽ ባለቤቶች ሆይ! እናንተ ሌላውን “የዜጎች ድምጽ በማፈን” በአፋኝነትና በአምባገነንነት ስትከሱና ስትወነጅሉ ከስር ደግሞ እናንተው ራሳችሁ በቃላችሁ አለመገኘታችሁ ያየና የተመለከተ እንደው በከፋ መልኩ የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በማፈንና በተጨማሪም ታፔላ በመለጠፍ መሰማራታችሁን ያሳሰበው ትውልድ ደግሞ በግብር ይውጣ ሥራዎቻችሁ ተማሮ አቤት! በማለት ፍትህን ፍለጋ ሲጣራ ነገሩ ድራማ አይሆንም? 

ለመሆኑ በጽሑፎቼ የተሳሳተ አስተሳሰብና አመለካከት የማንጸባርቅ ዓይነት ሰው ከሆንኩ ሰው የእኔን ሃሳብና አመለካከት አንብቦ ሃሳቡን ካልገለጸ እንዴት ነው ታድያ ከስህተቴ ለመማር የምችለው? የሃሳብ ልዩነት በማይብላላበት (ለበጎ) ማኅበረሰብ መካከል ምን ዓይነት ለውጥ/የተሻለ ነገር ሊመጣ ነው የሚፈለገው? አፈና እንደ መፍትሔ ሆኖ የሚዘልቀውስ እስከ መቼ ነው?

 

የኢትዮጵያ ችግር በወሬ ሳይሆን በስራ የሚያምን ትውልድ ሲመጣ የሚፈታ ችግር ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Dec 4, 2013

Advertisements