አጉል ተስፈኞች አንሁን፤ ተመጻዳቂዎች ከመሆን ህይወትም እንውጣ! (ክፍል አራት)

ካለፈው የቀጠለ … 

ክፍል ሦስት ለማንበብ በቱሪስት ተጎበኘህ ማለት እግዚአብሔር ታውቃለህ ማለት አይደለም! (ክፍል ሦስት) ይጫኑ!

በተረፈ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘመን በአሁን ሰዓት ሥራ ሰርተን በልተን ማደር፣ ራሳችንን መለወጥ፣ ከልመናና የተመጽዋችነት ህይወት መውጣትና መላቀቅ ነው እንጅ ሆዳችን ተርቦ ቀደዳ፣ ጉራና ድንፋታ አያምርብንም። በእምነት ረገድ እንደሆነም አሁንም ከኃይማኖተኝነት ያለፈ “የለም እማኞች ነን!” ከማለት የማንመለስ ከሆነ የምናምነው/የምናመልከውን አምላክ በጥንቃቄ ልንመረምር ይገባል።

አያምርብንም!

ቀድሞውኑ እንደ ጎሚስታ ነፋስ ማብዛት ማንን በጀ ነውና? እስቲ ከሁከተኛዋ ጎረቤት አገር ከኤርትራ የፖለቲካ መሪዎች ምን እንማራለን? በማለት ራሳችንን እንጠይቅ። በ“ድምጺ ሐፋሽና” “ቲቪ ዕረ” ፕሮፖጋንዳ የደነቆረ ካድሬ ከኤርትራ ውጭ አገር ከኤርትራዊ በቀር ዜጋ/ሕዝብ ያለ አይመስለውም። ታድያ ይህ ሁሉ ባዶ ፉከራና ጭፈራ ምድሪቱ አሽከርክሮ አሽከርክሮ ምን ውስጥ እንደጨመራትና በካቶም ብትጎተት የማትወጣበት አዘቅት ውስጥ በቁምዋ እንደቀበራት አለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው። 

ወገን! ከዚህ የበለጠ መማሪያ ምሳሌ የለምና ይህ የጎረቤት አገር ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት ሊሆነን ይገባል። ወርቁንና ጨርቁን ሽጦ ለነጻነቱ የታገለ ሕዝብ ምድሪቱ ሲዖል ሆናበት በተመሳሳይ ወርቁንና ጨርቁን እየሸጠ ከአገሩ እየተሰደደ ከሚገኘው ሕዝብ ኢትዮጵያውያን ትምህርት ልንወስድ ይገባል። እደግመዋለሁ ኢትዮጵያውያን በአሁን ሰዓት ስራ ሰርተን ኑሮአችንን ማሻሻል እንጅ በባዶ መቀመጫችን ድስኩር መንፋት አያምርብንም። ምንም የሚያስመካ መንፈሳዊም ቁሳዊም ነገር የለንም። እንዲኖረን መስራትና መፍጋት ግን ይጠበቅብናል። “አባቶቻችን እንዲህና እንዲያ ነበሩ!” ብሎ ወሬ ማብዛት ግን በመቃብራቸው እንድንቀበር ያደርገን እንደሆነ እንጅ ኖሮው ያለፉትን ህይወት እንድንኖር አያደርገንም። 

እናማ፥ አጉል ተስፈኞች አንሁን፤ ተመጻዳቂዎች ከመሆን ህይወትም እንውጣ። አጉል ተስፈኝነት ሆነ ተመጻደቂነት የድሃ መታወቂያ ነው። ድሃ ደግሞ ስለሌለውና ስለማያገኘው ነገር ከንፈሩ እየመጠጠ እየተመጻደቀም በአጉል ተስፋ ከመኖር ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ የለውም። ከነተረቱም “ዶሮ የሌለው በቅሎ ይንቃል” እንኳ ይባል የለ።

ድሃ ረጅም ዘመን የመኖሩ ምስጢርም ዓለም እሱን እሽርሩ የምትልበት ጊዜ እንደሌላትና ኑሮውን “አሜን!” ብሎ ተቀብሎ ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው አሳምሮ ስለሚያውቅ ነው። በዚህ ማኸል ካለፈለት አለፈለት ይባላል። ከዚህ ያለፈ ድሃ በአጉል ስሜት ተነሳስቶ በህይወት ያመጸ ዕለት ግን ‘ለ’ ና ‘ሐ’ ብሎ ምርጫ አይኖረውም። ‘ሀ’ ብሎ ሞት ነው። ራሱን የሚያጠፋበት መንገዶች በግለሰቡ ምርጫ የሚወሰን ይሆናል። በእኛ መካከል እየሆነ ያለውም ይህንኑ ነው።

ምን እናድርግ? 

ማንም ሁን ምን መሆን የሚገባህን በመሆን የቋንቋ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት ልዩነትህ እውቅና ሰጥተህ፣ ማንም ከማንም እንደማይበልጥና እንደማያንስም ተገንዝበህ፣ ተስማምተህ፣ ተግባብተህና ተቀባብለህ ፈግተህ የሰራህ እንደሆንክ የትም መንከራተት ሳያስፈልግ ‘ክብርህ እንደ ጠበቅህ’ እትብትህት ተቆርጦ በተቀበረባት ምድር ለውጥን ታያለህ።

ከዚህ ያለፈ ግን በስለት ሆነ በመመጻደቅ አንዳች የሚመጣ ቁሳዊ/የአእምሮ እድገት ሆነ ለውጥ እንደሌለ ብቻ ሳይሆን ሊኖርም እንደማይችል አውቀን እርማችን ልናወጣ ይገባል። በዚህ የተካን ኢትዮጵያውያን ደግሞ “ከእግዚአብሔርና ከመላዕክቱ” ጋር እንዲህ ዓይነቱ ቁማር መጫወት ልናቆም ይገባል። ይህ ዓይነቱ አሰራር በሐዲስ ኪዳን ቦታ የለውም። እንዲህ ብታደርግልኝ ይህን አድርግለሃለሁ ማለት በራሱ ሙስና ነውና። 

በመጨረሻ: አገራችን ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ተብላ ከተሰየመችበት ጊዜ አንስቶ ለመቶ ዓመታት የቆየና የከራረመ ብሔርን ያማከለ የአንድ ብሔር የበላይነት ጥያቄ ሽኩቻና የእርስ በርስ ሥር የሰደደ ጥላቻ ችግር ያለባት አገር ናት። ይህ ችግር ደግሞ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻውን የሚያስተካክለው በአንዲት ሌሊት የሚፈታ ቋጠሮ/ችግር ሳይሆን አገሩ ሆና ማየት የሚናፍቅ ግን ደግሞ ህልሙና መልካም ምኞቱ በዘመኑ ለማየት ባይታደልም ፍሬ የሚያፈራ መልካም ዘር ዘርቶ በመስዋዕትነት የሚያልፍ አንድ ራሱን የሚሰጥ ከእኔነት በሽታ አእምሮው የተፈወሰ ትውልድ ያስፈልጋል። ይህ ትውልድ የመፍጠር ኃላፊነት ደግሞ የነጭና የህንድ ድርሻ ሳይሆን የዜጎች ሁሉ (የእኔና የእርስዎ) ግዴታ መሆኑን በማወቅ ልንነቃና ልንባንን ያስፈልጋል።

 ተፈጸመ

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 24, 2013

Advertisements