የኤርትራ ጉዳይ፡ አንድ ነበርን ማለት ነን ማለት አይደለም!

ትኩረት ሰጥተን ለማስተላለፍ የምንፈልገው መልዕክት ቁርጥ ባለ መልኩ ካላስቀመጥነው በስተቀር “አንድ፣ አንድነት፣ አንድ ነን፣ አንድ ነው፣ አንድ ናቸው …” የሚሉት ቃላቶች፣ አነጋገሮችና አባባሎች ትርጓሜአቸውና ፍቺአቸው ስፍር ቁጥር የለውም። እየተነጋገርን ያለነው ስለ ፍጹም አንድነት ከሆነ ደግሞ በከፊል መመሳሰልና መስተካከል የሚስተዋልበት ነገር ሁሉ በተለምዶ አንድ ነው፣ አንድ ናቸው  … ማለት የተለመደ ቢሆንም ሐቁ ግን አንድ ከራሱ ከአንድ ብቻ ነው አንድ ሊሆን የሚችለው። ኤርትራ ኤርትራ ናት ኢትዮጵያ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት።

Ethio-Eritrea

የኤርትራ ጉዳይ፡

የኤርትራ መንግሥትና የኤርትራ ሕዝብ “ኤርትራ፡ ነጻ አገር! ነጻ ሕዝብ ነው!” ሲል የመገንጠል ጥያቄ አቅርቦ የተገነጠለ፤ የራሴ ነው ለእኔ ይገባኛል ያለውንና የሚለውን የሚገባው ድርሻውን ይዞ የሄደ ሕዝብና መንግሥት ነው። በዚህ መልኩ ነጻ አገር ነጻ ሕዝብ መሆኑና መሆንዋን ያረጋገጠ/ች ሕዝብና መንግሥት (አገር) ደግሞ ከሌላው ሉዓላዊ ሕዝብና መንግሥት ሊኖረው የሚችለውና የሚገባ ግኑኝነት በተመለከተ ለሁላችን ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ።

ኤርትራ ራስዋን ችላ እንደ አገር ለመቆም ጥያቄ አቅርባ ለጥያቄዋ መልስ ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ  ላይ ምንም ዓይነት ርስት ጉልት የላትም። ኤርትራ አሁን የምትገኝበት የጣረ ሞት ህልውና ይመቻት አይመቻት፣ ይድላትም ይክፋት ምርጫዋን ተከትላ የሄደችበት መንገድ እስከ ሆነ ድረስ ኤርትራ ራስዋ የቻለች ሉዓላዊት አገር ናት። 

ኤርትራ እንደ አገር ከጎረቤት አገር ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራት የሚችለው ማንኛውም ዓይነት ግኑኝነት በተመለከተም ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከኬንያ ያላትን ግኑኝነት ባልተለየ ዓለም አቀፍ የሀገራት ግኑኝነት በጠበቀ መልኩ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። አንድ ነበርን ወይ? አዎን! ኤርትራ የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት ነበረች። አሁንስ? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ግን አእምሮውን የጣለ ግለሰብ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት የተለያዩ አገራትና መንግሥታት ናቸው። በሌላ አነጋገር አንድ አይደሉም አይደለንም።* ኤርትራ ኤርትራ ናት ኢትዮጵያ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። ኤርትራዊ ኤርትራዊ ነው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው። የተባበሩት መንግሥታትም ኢትዮጵያ ሆነች ኤርትራ አንደ ሁለት አገራት አንጅ ኢትዮጵያ ብሎ ኤርትራ ኤርትራ ብሎ ኢትዮጵያ ቅይጥ አገር አያውቅም። [*ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት አልነበረችም፤ ለወደፊቱም ወደ ቀድሞ ስፍራዋ ልትመለስ አትችልም፣ አንድ ልንሆንም አንችልም አላልኩም። ለሃያ ዓመታት የዘለቀውና አሁን ባለው የሁለቱም አገራት ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝባቸውም ሆነ ምናቸው አንድ አይደሉም።  አንድ ነበርን ማለት ነን ማለት አይደለም! ነው የጽሑፉ ፍሬ ነገር።]

ለመሆኑ አንድ ብንሆን ነው የኤርትራ መንግሥት አገራችን ኢትዮጵያ የደም መሬት ለማድረግ የሌሊት እንቅልፍ ያጣው? ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር አንድ መሆንዋን የምትገልጽበት መንገድ በከተሞቻችን ፈንጆች በመቅበርና በማፈንዳት ሆነ እንዴ? ኤርትራ ንጹሐን ኢትዮጵያን ዜጎች በደም በማጨቅየት ነው ወይ አንድ መሆንዋን የምታስመሰክረው? የኤርትራ መንግሥት ማለት ንጉሥ ዳዊት በመዝሙር 41፥ 9 ላይ  “እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ” ሲል አንድም ልጁ በገዛ አባቱ የፈጸመበትን በደልና ያሴረበትን የመፈንቅለ መንግሥት ሲገልጽ አንድም በእግዚአብሐር መንፈስ ተመርቶ ነገሩን በሩቅ ተመክቶ በትንቢትም ይሁዳ በጌታ ኢየሱስ ለሚፈጽመው ክህደት ሲያመላክት እንደተናገረው የኤርትራ መንግሥት ነገርም እንዲሁ ነው።

በአጭሩ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስላት አንዳች ነገር የላትም። እንደ ሀገርና እንደ መንግሥት የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት የሚያመሳስል የኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካ መዋቅር የለንም። ኢትዮጵያና ኤርትራ ማለት ሁለት ጽንፍ ላይ የተቀመጡ የተለያዩና ራሳቸው የቻሉ መንግሥታት ወይም አገሮች ናቸው።

“ዓደቦይ” Vs “እናት አገሬ!”

ሕዝብ በተመለከተ አይደለም የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ አንድ ዓይነት ሥነ ልቦና ሊኖረው “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ተብሎ የሚታወቀው ሕዝብም በፖለቲካ ረገድ አንድ ዓይነት ስነ ልቦና ያለው ዜጋ አይደለም። ስለ ጦርነት ወይም ስለ እግር ኳስ አይደለም እያወራን ያለነው። እየተወያየን ያለነው የአንድ ሕዝብ ሁለመና መገለጫ ስለሆነው ፖለቲካ ነው እየተነጋገርን ያለነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነ የኤርትራ ሕዝብ ሁለት የተለያየ ፖለቲካዊ ሥነ ልቦና ያለው ሕዝብ እንጅ አንድ ሕዝብ አይደለም። 

ኤርትራዊ “ዓደቦይ” የሚላት ኤርትራ ስትኖረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድምር ውጤት የሆነችው ኢትዮጵያ የምትባል እስካለች ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያውያን “እናት አገሬ!” የሚሏት ኢትዮጵያ ነው ያለችው።

ኤርትራ አሁን የምታስተጋባው የማንነት ድምጽ እንደሆነም የኤርትራ ሕዝብና “መንግሥት” ራሱ የፈጠረው ማንነት እንጅ ምንጩና መሰረቱ በታሪክ “ኤርትራዊ ማንነት” የሚባል ኖሮ አያውቅም። የታሪክ መዛግብት እንደሚመሰክሩትም የአሁኒትዋ ኤርትራ በትግራይ ክልል ሥር ትተዳደር የነበረች የትግራይ ክልል ግዛት እንጅ በታሪክ “ኤርትራ” የምትባል ራስዋን የቻለች አገር እንደማትታወቅ ነው የሚያሳዩት። 

ያም ሆነ ይህ ኤርትራ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረችበት ምዕራፍ በሕዝቦችዋና በመንግሥትዋ ጥያቄ የተዘጋ ፋይል ነው። ድጋሜ ፋይሉ ሊከፈት የሚችልበት አጋጣሚ ቢኖርም በዘፈንና ማንነታቸው በማይታወቁ አንዳንድ አጨብጫቢዎች፣ ከበሮ መቺዎችና ሰልፈኞች በሚያሰሙት ውሃ የማይቋጥር ጥሬ መፈክር ሳይሆን የኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ውህደት ፍለጋ አግባብ ባለው መልኩ በሚያቀርበው ጥያቄ ብቻ ይሆናል።

በነገራችን ላይ ኤርትራ በጥያቄዋ መሰረት ስትስተናገድ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠውን ምላሽ ተገቢና ዲሞክራሲያዊ ቢሆንም በኤርትራ በኩል ለቀረበው ጥያቄ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው መልስ ግን በከፊል ኤርትራን የጠቀመ ያክል የእኛ የኢትዮጵያውያን ጥቅም በጠበቀ መልኩ የተወሰነ ውሳኔ እንዳልነበረ መዘንጋት የለበትም። ‘ስሙኒ’ የምታክል አገር (ኤርትራ) ሁለት የባህር በሮች ይዛ እንድትሄድ ሲደረግ ኢትዮጵያ የምታክል ግዙፍ አገር ደግሞ በደቀቅ መሬት ታጥራ እንድትቀር የተደረገ ውሳኔ መቼም ቢሆን አግባብነት የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ይህን ስል ግን መላ መፈጠር ነበር ማለቴ ነው እንጅ ቀድሞ በኤርትራ ክፍለ ግዛት ሲተዳደር የነበረ አከባቢና ሕዝብ ኢትዮጵያ በኃይል ማስቀረት ይገባ ነበር እያልኩ አይደለም። 

አንድነት አይጠላም!

ሌላው ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ መሆን ይገባቸውል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው። አንድ መሆን ለሁለቱም መንግሥታትና ሕዝቦች የሚያመጣው ጥቅም ካለው አንድ የማይሆኑበት ምክንያት የለም። አንድነት አይጠላም። የሀገራትና የመንግሥታት መክሰምና መወደቅም ዋና ምክንያት የአንድነት እጦት ነው። አንድነት ሲባል ግን አንዱን ወገን ጠቅሞ ሌላውን የሚያኮሰምንና የሚያደቅ መሆን የለበትም። የአንድነት አስኳል የጋራ ጥቅም ነው። የጋራ ጥቅም ያማከለ የሚደረግ አንድነት ደግሞ አስፈላጊና መሆንም ያለበት ነው ብዬ ነው የማምነው። ታድያ በዘፈንና በጭፈራ ሳይሆን በሕግ ነው። ዘፋኝ ስለ ዘፈነ “ነው” ማለት አይደለምና። ዘፋኝ ገበያ ማዕከል ያደረገ የሚመስለው ስሜቱን ነው የሚገልጸው። ፓለቲካ ደግሞ ስሜት አይደለም። ጥጉ ዘፋኝ ከመዝፈን ያለፈ የፖለቲካ መሪ ሊሆን አይችልም። አይደለምም።

ወደ ነጥቤ ልመለስ። ሊፈጠር የሚችለው ውህደት/አንድነት በተመለከተ ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመጥቀም ብላ ራስዋን በመጉዳት የምታደርገው ጉዞ ይኖራል ብዬ አላምንም። በዚህ መልኩ የነበረ የሁለቱ አገራት ግኑኝነት መጨረሻው ምን እንደነበር ለሁላችን ግልጽ ነው።

ኤርትራ ራስዋን ችላ በቆመችባቸው የብቸኝነት ዘመናት በቂ ትምህርት መውሰድዋን፤ የመሪዎችዋ በትዕቢት የተወጠረ ልብና ጣራ የማይነካ ብልጣብልጥነት የትም እንደማያደርሳቸው፤ የመሪዎችዋ አጉል ትምክህትና መሰሪነት ለዚህ ሁሉ ውድቀትና ኪሳራ እንደማገዳት አምናና ተቀብላ በጋርዮሽ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ለሚነደፍ የጋራ ፖሊሲ ይህ ማለት ኤርትራ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛት ሆና እንደ 15ኛ ክልል ለመቀጠል ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስር ጣቶችዋ ስትፈርም “የኤርትራ ሕዝብ ሕዝባችን መሬቱም መሬታችን ነው!” ብለን የማንቀበልበት ምክንያት አይኖረንም። 

ማጠቃለያ፥

ኤርትራ ራስዋን የቻለች አገር ሆና እስከቀጠለች ድረስ ኤርትራ ማለት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከኬንያና ከሱዳን እንዲሁም ከሌሎች አገራት ያለንን ግኑኝነት የተለየ ምልከታም ሆነ ፖለቲካዊ ግኑኝነት አይኖረንም። ይህ ደግሞ ለሁላችን የሚጠቅም አሰራር እንጅ ጠላትነት ማለት አይደለም። ከዚህ ያለፈ ኤርትራ በኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት አላስችል ብሏት ትንኮሳዋን የማትተው ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅድላት መንገድ የኤርትራ መንግሥት በሚገባው መልኩ የማስተማር፤ ሉዓላዊነትዋና የሕዝብዋ ክብር ጠብቃ ለማስጠበቅም አስፈላጊውን እርምጃ የማትወስድበት ምክንያት አይኖርም። 

በመጨረሻ እንደው “ሥልጣን የሕዝብ ነው” ስለ ተባለ ብቻ እንደ ሕዝብ ሥልጣናችን አለ አግባብ ባንጠቀመምበት፤ መስመሩ የሳተ ድርጊት ላይ ባንሰማራና አልባሌ እንቅስቃሴ ውስጥ ባንገባም ይመከራል። እንደ ዜጎች ከህገ ወጥ ድርጊቶች ራሳችንን መግታትና መቆጠብ ግዴታችን ነውና። ምን ነው? ቢሉ በፖለቲካ ውስጥ ሁሉም የየራሱ ድርሻ አለውና። ለደጉም ለክፉም በአንዲት አገር ፖለቲካ ሁለም የየራሱ ድርሻ አለው። ሕዝብ የራሱ ድርሻ አለው። የሕዝብ ሹማምንቶች ማለትም የፖለቲካ መሪዎችም እንደዚሁ የራሳቸው የሆነ ድርሻ አላቸው። የሥልጣን ባለ ቤት የሚባለው/የሆነው ሕዝብም ቢሆን ለእንቅስቃሴው ገደብ አለው። ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ቢሆንም ወይም ነው ቢባልም ከህግ በላይ ነው ማለት ግን አይደለም። 

አባባሉ ግልጽ ይሆንልን ዘንድ በዚህ መልክ እናስቀምተው። አማረኝ ተብሎ የሚጎረስ እሳት የሚላስ ምጥሚጣ ይኖር እንደሆነ ነው እንጅ አማራኝ ተብሎ የሚጣስ ሕግ የለም። ህግን መጣስ መብት አይደለም። ሕግን መጣስ በወንጀል የሚያስጠይቅ ህገ ወጥ ድርጊት ነው። መብት የሚባለው ነገር ደግሞ ግዴታውን ለሚወጣ ዜጋ እንጅ መብት ብሎ እስከ ሰማይ ጣሪያ ድረስ የሚዘረጋ ጥላ የለም አይደለምም።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 26, 2013

Advertisements