በቱሪስት ተጎበኘህ ማለት እግዚአብሔር ታውቃለህ ማለት አይደለም! (ክፍል ሦስት)

ካለፈው የቀጠለ … 

ክፍል ሁለት “እግዚአብሔር ማወቅ እንዲህ ከሆነ እሱም ባያውቀኝ እኔም ባላውቀው ይሻለኛል! ምንም አይቀርብኝም፡” ለማንበብ (http://wp.me/p3MQOW-jE) ይጫኑ!

ጎበዝ! ሳውዲ ድረስ ሂደን በፈላ ዘይት/ውሃ እየተቀቀልን፣ ከፎቅ እየተወረወርን፣ በመኪና እየተገጨን፣ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወደ ውህኒ እየተጣልን፣ በሰለጠኑ ውሾች እየተቦጫጨቅን፣ እንደ እባብ በበትር እየተቀጠቀጥን፣ በኤሌክትሪክ በግፍ እየሞትንና እያለቅን ያለነው “እግዚአብሔር የማያውቀን” እኛም የማናውቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። እስቲ አሁን አገር አርቀን የምንቀበር ዜጎች የእግዚአብሔር ስም እያነሳን ድንፋታ ምን ይሉታል? በሆነ ባልሆነ መመጻደቅ ምን አመጣው? በሌለን ነገር ድንፋታ ለምን አመል/ልማድ ይሆንብናል? መሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ ነው። ይኸውም፥

  • ኢትዮጵያውያን ማለት “ሰማይና ምድር የፈጠረ አምላክ እናመልካለን” እያልን “ስሙን” እየጠራን ሰማይና ምድር እንደ እንደተደፋብን ያለን ዜጎች ነን። 
  • በእጃችን ጠፍጥፈን ያልሰራነው ሆድ ለመሙላትና ለማስታገስ ፍዳችን እያየን ያለነው፣ የመከራ መዓት እየተፈራረቀብን ያለ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። 
  • የአገር ቤቱ ማኅበረሰብ የኑሮ ሁኔታ አንስተን መነጋገሩ ቀርቶብን የኢትዮጵያዊያን ኑሮ በምዕራቡ ዓለም  ያለውን ገጽታ ይብራራ ከተባለ – ኑሮ የሚኖር ዜጋ እያኗኗርን የምንኖር ዜጎች ነን። 
  • ለምን አሜሪካውያን አገራችን ድረስ መጥተው አያገለግሉንም? ለምን “አውሮፓዊ” ወደ አገራችን እንጀራ ፍለጋ አይሰደድም? መኖር መብት ከሆነ ለምን ሰው የሚኖረውን የኑሮ ዓይነት የመኖር “መብት” ተነፈግን? መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። ይኸውም፥ በምድራችን ሰርተን እንዳንለወጥ እርስ በርስ መግባባት ተስኖን ስንነካከስ እየተንከራተትን ያለነው እኛ ኢትዮጵያውያን ነንና።
  • ሰው ያደረገን “እግዚአብሔር እግዚአብሔር!” የሚል ምላሳችን ሳይሆን እግዚአብሔር “የማያውቅ” ዜጋ እያልን አፋችን ሞልተን የምንሰድበውና የምናቋሽሸው ምዕራባዊ ዜጋ በሚሰጠን ዕድል ነው። ጥያቄው የአንደበታችን ቃል የት ቢገባ ነው?
  • ኢትዮጵያውያን በምላሳችን “እግዚአብሔር! እግዚአብሔር!” በማለት የሚስተካከለን የለም። “እግዚአብሔር” እንደምናመልክ አውርተን ውለን ብናድርም አይደክመንም ቁምነገሩ በማለታችን ምን አተረፍን? ሌላውስ “በራሱ መንገድ” በመሄዱ ምን ቀረበት? ቀረበት ብለን የምንመጻደቅበት ሀገርና ሕዝብ ተከትለን ሰው መሆናችን አንዘጋ። የሚገርመውም ይህ ነው። ሰባት ወደ ግራ፣ ሰባት ወደ ቀኝ፣ ሰባት ወደ ላይ ዘር ሀረጋችን ተቆጥሮ ይቅር የመኪና* ባለቤት  ዘመድ ሊገኝብን መኪና የሚነዳ ጎረቤት የሌለን፤ በዘራችን ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ለመንዳት የታደልን።  ታድያ ዕድሉ የሰጠን ማን? የት ሂደንስ ቢሆን ነው? [*እንደው ረስተውት እንደሆነ ነው እንጅ መኪና ለምዕራቡ ዓለም ከምግብ፣ ከውሃና፣ ከመጠሊያ ቀጥሎ ጫማ ማለት ብትሆንም ሀገራችን ጨምሮ ለሦስተኛው ዓለም ማኅበረሰብ ግን መኪና ማለት አሁንም የሀብት መለኪያ ቅንጦትም ናት።]
  • አውሮፓና አሜሪካ የምንሰደደው እንደ ሰው አገር ሳይኖረን ቀርቶ ነው ወይ? አገርማ አለን። ታድያ ወይ ያለን የሚባርክልን አምላክ የለም አልያም በረከታችንን ማየት ተስኖን በገዛ እጃችን ተቅበዥባዦች ሁነናል።  ከሁለቱም አንዱ ላይ ነን።
  • የአገሬ ሰው የሚበላ ቢያገኝ አገሩ ጥሎ ይኮበልል ነበር ወይ? ሳውዲ ምን ልትሆን ሄድክ? አሜሪካና አውሮፓ? ሌላው ይቅር ህንድና ኬንያ ምን እያደረግን ነው? እግዚአብሔር ብናውቅ ነው? ለእግዚአብሔር የተለየን፣ ብርቅዬዎች ምናምን ምናምን ብንሆን ነው? ተው ባክህ በቱሪስት ተጎበኘህ ማለት እግዚአብሔር ታውቃለህ ማለት አይደለም። ቱሪስትማ ለበረከት ሳይሆን ትንግርት ሁኖበት በድህነት እባጭ የተመታች “ሀገረ እግዚአብሔር” ለማየት ነው የሚመጣው። በአንድም በሌላም ያጠራቀመው ገንዘብ እንዲህ ያሉ ቦታዎች በመጎብኘት ይበትነው እንጅ ምንስ ያድርግ ብለው ነው። 

 ይቀጥላል

አጉል ተስፈኞች አንሁን፤ ተመጻዳቂዎች ከመሆን ህይወትም እንውጣ! 
(ክፍል አራትና የመጨረሻ) 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email:yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 22, 2013

Advertisements