እግዚአብሔር ማወቅ እንዲህ ከሆነ እሱም ባያውቀኝ እኔም ባላውቀው ይሻለኛል! ምንም አይቀርብኝም፡ (ክፍል ሁለት)

ካለፈው የቀጠለ … 

ክፍል አንድ “ድሃና ሥራ አጥ ኃይሞኖት ያከራል!” ለማንበብ (http://wp.me/p3MQOW-jx) ይጫኑ! 

ማሳሰቢያ፥ ጽሑፉ በይዘቱ ምሬት ወይም ስሜት አይደለም። የሚጨበጥና የሚዳሰስ የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን ዜጎች የዕለተ ዕለት ኑሮአችን የህወታችንም ምስል ገጽታና እውነታ ነው። በተጨማሪም ጽሑፉን ከዓውዱ በማውጣትና በመቆራረጥ ማንበብ እንደማይፈቀድ ስገልጽ በእክብሮት ነው። 

ሐተታ፥

ምን ጊዜም፤ የትም ቦታም ቢሆን በግለሰብ ደረጃ ሆነ የትኛውም ሕዝብ ላይ ግፍ መፈጸምና አለ አግባብ መበደል ወይም በደልን ማድረስ ጊዜውን ጠብቆ ግፈኞች የእጃቸው የሚያገኙበት፤ ሥልጣናቸው መከታ በማድረግ ለፈጸሙት ግፍም ይብዛም ይነስ በጊዜው በግፈኞች የሚያደርሰው ኪሳራ የሚያስከፍለውም ዋጋ አለው። 

ይህ በእንዲህ ሆኖ ሳለ በተለየ መልኩ “ኢትዮጵያ የነካ ይፈለጣል ይቆረጣል!” እያልን የምናቀነቅናት ነጠላ ዜማና የምናስቦካው ነገር ግን አይገባኝም። የማን ዜጋ ሲነካ አገር ስትወድምና ስትፈራርስማ በዓይናችን እያየን ነው። ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ አቅምን ያላገናዘበ መፎክር አነግበን ማፏጭት ከማን እንደ ተርማርነው፣ ከየት እንዳመጣነውና ያገኘነው መገለጥ ለመሆኑም እርግጠኛ አይደለሁም። 

ከዚህም በመነሳት እኛስ ማንን ነካክተን ይሆን እንዲህ የተንኮታኮትነውና ተንከራታች፣ ተመጽዋቾች፣ ብሎም እርስ በርስ ፍቅር የሌለንና የማናውቅ፣ ነገረኞችና በሄድንበት ምድር ሁሉ ሰላም የማናውቅ ሁከትና ብጥብጥ የሚቀናን ነፈዞች ሆነን የቀረነው? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ምላሽ ሊኖረን እንደማይችል እርግጠኛ ነኝ። እስቲ አሁን በዚህ ድህነታችን ሌላውን በእግዚአብሔር ስም የምናስፈራራው የጤና ነው ብሎው ያምናሉ? ወይስ ራሳችን ቁጠር ውስጥ ከማይገቡ የወደሙ አገሮች ከኤርትራና ከሶማሊያ ጋር እያነጻጸርን ይሆን ግዝፈታችን ጎልቶ እየታየን የተቸገርነው? ሁሉም ነገር በልክ ሲሆን ነው የሚያምረው ጎበዝ።

ጉዳዩ ካነሳነው አይቀር ለፈውስ ይሆነን ዘንድ እስቲ ነገሩን በደንብ ጠበቅ አድርገን እንየው። ቁምነገሩ፡ኢትዮጵያውያን ምን አለን ነውና እንዲህ የምንመካው? ምን ዓለም የማያቀው ነገር ቢኖረን ነው በትምክህት ልባችን አብጦ ሌላውን መውጫ መግቢያ የምናሳጣው? ፊደል እንደሆነ ቀቅለን አንበላው። ስለ አክሱም፣ ስለ አብርሃ ወአጽብሃ፣ ስለ ካሌብ፣ ስለ ላሊበላ፣ ስለ ፋሲለደስ፣ ስለ ሐረር … ወዘተ ስናወራ ምድር የመሸብን ዜጎች ከመሆናችን አልፎ ዓለም እኛን የሚያውቅበት የትኛው ስልጣኔ ቢኖረን ነው? ርሃብ፣ ድህነት፣ የእርስ በርስ ጦርነት እንደ ስልጣኔ ካልቆጠርናቸው በስተቀር። ኧረ ለመሆኑ የትኛው ኑሮአችን ነው እንዲህ የሚያንገበግበንና ቁጭ ብድግ የሚያደርገን? 

ጥጉ፡ ኢትዮጵያውን ማለት ከድህነታችን ብዛት ድህነት የረሳን የነጣን ድሆች ነን። ድሆች መሆናችን ካልገባንና አምነን ካልተቀበልን ደግሞ መቼም ቢሆን ለልማትና ለለውጥ አንነሳም። ኢትይዮጵያዊነት ድህነት ነው ብሎ በተጨባጭ መናገር ደግሞ ስድብ አይደለም። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ድሆች መሆናችን አምነን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወጥረን ስራ መስራት እንደሚገባ፤ ለስራም እጃችን እንድናበረታ ያነሳሳናል ያበረታታናልም እንጅ “ኢትይዮጵያዊነት ድህነት ነው” አለ በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት የሚፈይደው ቁምነገር አይኖረውም። 

እንዲያውም ኢትዮጵያዊነት ማለት “ቱጃርነት/ባለጠግነት” ነው በማለት ብዘፍንና ዘራፍ ብል ነው ሽንገላ፤ ብሎም ኢትዮጵያዊነትን መስደብ የሚሆነው። ሕዝብ ያልሆነውንና የሌለውን ነህ! ማለት ነው ወንጀል። ምን ነው? ቢሉ ሕዝብ እንዲዘናጋ በማድረግ በቃሌ መንፈሱን ገድየዋለሁና። የሰው ማንነቱ በቃል የሚቀናና የሚጎብጥ፣ የሚነቀልና የሚተከል፣ የሚታነጽና የሚፈርስ፣ የሚቆምና የሚፈርስ፣ የሚጸናና የሚገዘገዝ መንፈሱ ነው። ስጋ አካላዊ ማደሪያ ነው ሌላ ምንም ተአምር የለውም። ሰው መንፈሱ ከተያዘ፣ ከፈዘዘ፣ ከደነዘዘ፣ ከነቀዘ፣ ከተንኮታኮተ፣ ከተቦረቦረ፣ ከተሸረሸረና ከሞተ ስጋ  በራሱ ወደምሄድበት የለውም።  ወጣም ወረደ ኢትዮጵያውያን “ሲፈጥረን” ለመኖር የሞት ዋጋ የምንከፍል ዜጎች ነን። ታድያ ይህ ምኑ ያስመካል? አንገት ያስደፋል እንጅ። 

ለምኔ?

የሳውዲ ወይም የሌላ አገር ዜጋ (ኤርትራና ሱማሊያ አይጨምርም) አይደለም እንጀራ ፍለጋ ኢትዮጵያ ድረስ የሚመጣ። ለመኖር ስንል (እየወቀስኩ አይደለም) የሰው አገር ድረስ ሂደን ህይወታችን እያጣን/እየሞትን ያለነው እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። ኑሮውን ለማሻሻል እንጀራ ፍለጋ ወደ አገራችን የሚገባ የምዕራብ ዜጋ የለም። የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያ ምድር ቢሞት ለዕረፍት ወይም በስራ ምክንያት መጥቶ ገንዘቡን ለመዝረፍ በሰንጢ ወግተን አልያም በጥይት ሹተን ካልገደልነው በስተቀር በእጦት አይሞትም። ይህ እውነት ነው። 
እንግዲያውስ “እግዚአብሔር” ማወቅ እንዲህ ከሆነ ባያውቀኝስ? ምን ይቀርብኛል? ምንም አይቀርብኝም።   “እግዚአብሔር” ማወቅ እንዲህ የከፋና የከረፋ ኑሮ እንድገፋ ካደረገኝ/የሚያደርገኝ ከሆነ ይህ ዓይነቱ “እግዚአብሔር” ባለማወቄ አልቆጭም። ደግሞም ምንም ከዚህ የከፋ የሚገጥመኝ ነገር የለም። አንዳች ከዚህ የተለየ ነገር አይገጥመኝም። ዚሮ አምስት ሳንቲም አይቀርብኝም እያልኮት ነው። እንደውም እንዲህ ያለ መዘዝ ያለውማ እኔም ባላውቀው እሱም ባያውቀኝ ነው የሚሻለኝ። ጨርሶ አልፈልገውም። ለምኔ? 
እኔ እንደሆንኩ እስከሚገባኝና እስከማውቀው ድረስ ራሴን አበጃጅቴ በምርጫዬ ፍቃዴ ታክሎበት ወደዚች ዓለም የመጣሁ ሰው አይደሉም። ይህ ባለ መሆኑም ምንም ዓይነት ቅሬታ የለኝም። ተሰምቶኝም አያውቅም። ልቤ፣ ኩላሊቴ፣ እጅና እግሬ … ያለ ስህተት ተሰርቶ የተሰጠኝ ብቻ ይዤ የመጣሁ ግለሰብ ነኝ። ውብና ድንቅ አድርጎ የፈጠረኛ አምላክ ደግሞ ከሌላውን ወገን እኩል ዕድል ሰጠኝ እንጅ አንድንስኳ አላጎደለብኝም። እዚህ ላይ ቤተሰቦቼ የጨመሩልኝ ነገር ቢኖር “ሙሉጌታ” ብለው ስም ብቻ ነው ያወጡልኝ። 
ታድያ “እኔ*” [እኔ የሚለው ቃል ወገንን ያመላክታል] ለሐዘን፣ ለስብራት፣ ለሰቆቋ፣ ለውድቀት፣ ለመከራ፣ ለስደት፣ ለውርደት፣ ለባርነት፣ ለልመና፣ ለእንግልት፣ ለማያባራ ለቅሶና ዋይታ ሌላው ለጌትነት፣ ለደስታና ለፌሽታ “የምፈጠርበት” ምክንያት ምንድ ነው? ምን ሊበጀኝ? “እግዚአብሔር” ያውቀኛል እኔም አውቀዋለሁ ብዬ ሳበቃ በሆነ ባልሆነ፣ ዓላማ በሌለው ነገር ሰማይ በላዬ ላይ ተደፍቶብኝ ቁም ሰቅሌን የማየው፣ የሰቆቋ ህይወት፣ የመከራ እንጀራ የምበላና የምኖረው ምን ብበድልና ባጠፋ ነው?፣ ብረገዝም ጭንጋፍ ሁኜ ብሸበለል ብሄድስ?(ይህኔ “ጥርግ በል!” ብሎ የሚመጻደቅ ሰው አይጠፋም እኔ ግን እየቀለድኩ አይደለም። የእያንዳንዳችን ጓዳ ነው እየተናገርኩ ያለኹተይ)፣ ያደግኩ እንደሆነም ባላውቀው ባያውቀኝስ? በቁሜ ከምሞት ያየሁትን ሳላይ አንዳፍታው ባልፈጠርስ? ባላውቀው ባያውቀኝስ ምን ይቀርብኛል? አይመስሎትም ውድ አንባቢ? 
ሞት እንደሆነ የወረፋ ጉዳይ እንጅ የፈጀ ጊዜ ይፍጅ ደንበኞቹን አንድ በአንድ ሳያስተናግድ ደጆቹን አይዘጋም። በሌላ አነጋገር ድግሱ ማናችንም አይቀርልንም። እኩል ነው የምንሞታት። የበላም የተራበም፣ የጠጣም የተጠማም፣ የለበሰም የተራቆተም፣ ያጌጠም የተማረረም ሥጋ ለባሽ ሁሉ በልተን እንዳልጠገብን፣ ጠጥተን እንዳልረካን፣ ለብሰን እንድላማረብን፣ አጊጠን እንዳልተሽሞነሞን ተንጫጭተን ተንጫጭተን ውበታችንና ደም ግባታችን ፈራርሶ መጨረሻችን “ሞት” ነው። “በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ደግሞ ከሞት በኋላ ስላለው ምስጢር”* አብረን የምናየው ይሆናል።  
አንዳንድ ጊዜ ይህ ዳያስፖራ* የሚሉት ትኩስ ድንች ዜጋ በሞቱት ላይ አፉን ሲከፍት እግዚኦ! ሞት የሚቀምስ/የሚሞት አይመስልም አይመለውምም። ከአንደበቶቻቸው ፍሬ የተነሳም በእነሱ ፈንታ ባልዋልኩት ነገር ያለ ኃጢአቴ እኔ እሳቀቃለሁ። ሐቁ ግን አይደለም አሜሪካና አውሮፓ ጨረቃ ላይ ብትወጣም ሳትጎተት በራስህ ጊዜ ከወጣህበት ከፍታ ትወርዳለህ። ድሮስ ሞት ብሎ ሌላ ተለዋጭ ስም ባይገኝለትና ባይኖሮው አይደል ሞት የተባለ።

በክፍል ሁለት ጽሑፌ ለማስተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት ሳገባድድ፥ ይህ ሁሉ ውርደትና መዓት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ በልዩ ትዕዛዝ ከፈጣሪ የተቸረልን ዕድል ፈንታ ሳይሆን በራሳችን ጊዜ ያመሰቃቀልነው የሆነ ነገራችን ከመስመር መውጣቱና መበላሸቱ አምነንና ተቀብለን ካለፈው፣ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ከሆነው፣ ልንመልሰው  ከማይቻለን ታሪካችን የማያዳግም ትምህርት በመውሰድ፤ አንዱ ሌላውን መውቀስ፣ ተጠያቂ ማድረግ፣ ማጥቆርና  እርስ በርስ መተነኳከልና መባላታችንን ትተን እንደ ሕዝብና/እንደ አገር ጉዳዩ በጥሞና አስበንበት አገራችንና ሕዝባችን ከገቡበት ረግረግ ለማውጣት ለመነጋገር፣ ለመወያየት፣ ለመቀባበልና ሃሳብ ለሃሳብ ለመለዋወጥ ራሳችንን መግዛት አቅቶን በነበርንበት የእንቢተኝነት፣ የእልከኝነትና የትዕቢት መንፈስ በመጽናት መፍትሔ ፍለጋ መወያየትን አሻፈረኝ ካልን እስከ ዛሬው ዕለት በምድሪቱና በሕዝቦችዋ የሆነው፣ የተደረገውና የተፈጸመው አስከፊና አሰቃቂ መዓት ሁሉ ሊመጣ ያለውን ማንም ይደርስልን ዘንድ የማይቻለው ዋይታ እሪታ ምጥ ነው! ብዬ በአጭር አገላለጽ ከማስቀመጥ ውጭ በበኩሌ የምለው አይኖረኝም። እንደ ዜጋ ልለግሰው የምችል ምክሬም ይህ ነው። 

ይቀጥላል

በቱሪስት ተጎበኘህ ማለት እግዚአብሔር ታውቃለህ ማለት አይደለም!

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 22, 2013

Advertisements