ድሃና ሥራ አጥ ኃይማኖት ያከራል! (ክፍል አንድ)

የአስተሳሰብ ድህነታችን ሥር እየሰደደ ጥልቀቱ በጨመረ ቁጥር በሌለን ነገር ቱሪ ናፋችንም እንዲሁ ከመቼው ጊዜ በበለጠ እየጨመረ መጥተዋል። ብለን ብለን ደግሞ “ኢትዮጵያ የነካ ዋ!” እያልን ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ቅርበትና ዝምድና እንዳለን አድርገን በመቁጠር ሌላውን ማስፈራራት ተያይዘነዋል። ስለ ሌላው የውጭው ማኅበረሰብ (ዜጋ) ባይገደኝም እንዲህ ያለ ፕሮፖጋንዳ ኃላፊነት የጎደለበት፣ አግባብነት የሌለው ከመሆኑ በላይም ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለውና ሕዝብ ባልሆነ ተስፋና ጭብጥ የሌለው ድንፋታም  ማደናገርና ማጭበርበር ሕዝብ በቁሙ የመቅበር ያህል በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባ አደገኛ፣ መርዛማና ገዳይ ጸረ ትውልድ ዲስኩር በመሆኑ አስከፊነቱ ለጽሑፉ መዘጋጀት ግድ ብሏል። 

ሐተታ፥

በወገኖቻችን የደረሰው ግፍና በደል እንደተጠበቀ ሆኖ ባይገባን ነው እንጅ ሳውዲም ሆነ ኢትዮጵያ ላይ የምትወጣ ጸሐይ መልኳም ቅርጽዋም አንድ ነው። እግዚአብሔርም እንደሆነ ኢትዮጵያውያን አብልጦ የሳውዲ ዜጎች አሳንሶ የሚያይበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም። እንደ አንድ የቅድሳት መጻህፍት ተማሪና የሥነ መለኮት አጥኚም እግዚአብሔር በአባትነቱ አንዱን ከሌላው አበላልጦ የሚያይበት ዓይን አለው ብዬ አላምንም። ሁሉም በአርአያው እንደ ምሳሌው የፈጠራቸው እኩልና የማይበላለጡ የራሱ ፍጥረቶች ናቸው። 

ለመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሳውዲዎች ይልቅ ለእግዚአብሔር ቅርቦች ነን የሚያስብለን ምን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ወይም ሥነ መልኮታዊ ጭብጥ ቢኖረን ነው? መለኪያ ሚዛናችንስ ምን ይሆን? እንደዛ ቢሆን ኖሮማ፥  

 • የተጎዳነው “እግዚአብሔር የማያወቀን” እግዚአብሔር የማናውቅ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። 
 • በድህነት እየተናጥን ያለን የሰውም የህይወትም ባሪያዎች እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። 
 • ከሰው ተርታ ወጥተን በልመና ስንዴ የሚተዳደር ሕዝብ እኛ፤ 
 • ኃያላን በቀየሱልንና ባበጃጁልን መንገድ ከመሄድ ውጭ ምንም ዓይነት አማራጭ የሌለን አቅመ ቢስ ሕዝቦች እኛ፤
 • በገዛ አገራችንና ምድራችን ሳይቀር የሰው ፈቃድና ትዕዛዝ ለሞምላትና ለማስፈጸም የተሰለፍን ዜጎች እኛ፤ 
 • ታሪክ ከማውራት በሽታ ያልተላቀቅን፤ የራሳችን ፖለቲካ የሌለን፤ በኑሮአችን አፍረንና ተሳቀን የምንኖር ዜጎች እኛ፤ 
 • እንደ ሰው ተፈጠረን እንደ ሰው ለመኖር ያልታደልን የአእመሮም የምንም ድህነት ያጎሳቀለን ከርታታ ዜጎች እኛ፤  
 • “የምናመልከው አምላክ ባለጸጋ ነው!” እያልን እየዘመርን ሰባት ትውልዳችን በድህነት እንደተቆራመደ የሚያልፈው እኛ፤  
 • “አምላኬ የጌቶች ጌታ የነገስታት ንጉስ” ብለን ስናበቃ ዝንተ ዓለማችን የሰው ባሪያዎች እኛ፤  
 • ቤት ንብረታችን ሽጠን ከሞት የተረፈችውን አካላችን ይዘን አገር ጥለን እንጀራ ፍለጋ የምንሰደደው እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። ታድያ ይህ ሁሉ መዓት ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር ጋር ትውውቅ ቢኖረን ነው? እግዚአብሔር ብናውቅ ነው ወይ?  ከእግዚአብሔር ጋር ቅርበት/ትውውቅ ያለው ሕዝብና ሀገር እንዲህ ከሆነ ባያውቀን ባናውቀውስ ምን ይቀርብናል? ምን አለፋዎት፡ ድህነትና ስራ አጥነት ነው ለዛውም በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ እንዲህ እያስቃዠን ያለው።

ኢትዮጵያውያን ምን አለን ነውና ደግሞ ሌላውን እየኮነን የምንመጻደቀው? የእግዚአብሔር ዘመድ ማለት ኢትዮጵያዊ ከሆነ ጨርቄ ማቄ ሳንል ከሞት ጋር ተናንቀን የምንሄድባቸው አገራት ምዕራባውያኑስ የማን ዘመድ ይሆኑ? ነገሩ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ድህነት አያድልም እንጅ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሔር የሰጠንን የድህነት ልዩ “ጸጋ” ጥለን መኮብለላችን አግባብነት የለውም ማለት ነው። 

እንደዚህም ሆኖ በምዕራቡ ዓለም ተቀምጠን ስናበቃ የተሻለ ኑሮ አለን በማለት የምንመካ ሰዎችም ብንሆን በሰው አገር የሰው ዝቅተኛ ‘የጉልበት ሰራተኞች’ ነን። [እዚህ ላይ ሁለት ዓበይት ነጥቦች ለማውሳት እወዳለሁ። አንደኛ፡ ‘የጉልበት ሰራተኞች’ የሚለውን አባባሌ ከሥራ ክቡርነት ጋር ምንም እንደማይገናኝ ሁለተኛ፡ ከሺህ አንድ ቢሆንም የተማረ ሰው እውነትም የተማረ ነውና እዚህ ሁሉ ንትርክ ውስጥ የማይገባ መሆኑን ስገልጽ በአክብሮት ነው።] ውጭው ዓለም ተቀምጠን የምናፈራው ሀብት ሆነ አለን የምንለው፤ አገር ቤት ሄደን በዘመድ አዝማዶቻችንና በጎረቤቶቻችን ፊት የምንጎርርበት ኑሮ ምንጩ ከሰው የተደበቀ አይደለም። 

 • “ሴትና ሴት”፣ “ወንድና ወንድ”፣ ያልደረሱ፣ ባለ ትዳር ከትዳሩ/ርዋ ኮብልለው ሲማግጡበት ያደሩት በአጠቃላይ ማንም ሲላፋበት ያደረ አልጋ ወገባችን ቁርጥ እስኪል ድረስ አንጥፈን፤
 • ሰው ደስ ብሎት የበላበት ሳህን አጥበን፤ 
 • በሞት አፋፍ ላይ የተቀመጡ ዜጎች ቁስላቸው ጠርገን፤ 
 • ለተፈጠረበት ዓላማ እየኖረ ያለውን ዜጋ ከስፍራ ወደ ስፍራ ከቦታ ወደ ቦታ በማመላለስ (ሾፉረን)፤ 
 • ባለ ሀብቶች በዕረፍት ጊዜያቸው ደስ ብሎአቸው የሚዝናኑበት የጓሮ አትክልት ኮትኩተን፤ 
 •  የልጆቻቸው … አጥበንና አጸዳድተን፤
 • ውሾቻቸውን አዝናንተን፤ 
 • የመናፈሻ ቦታዎቸቸው ቆሻሻ ለቃቅመንና አሰናድተን፤
 • መኪኖቻቸው አጥበንና ጠብቀን፤
 • ክርታስና አትክልት ተሸክመን፤
 • ከመላ ጎደል ለስራው የማይታመን፤ በማጭበርበር ድርጊት ተሰማርቶ የራሱ ያልሆነውን ሀብት የሚያግበሰብስ ዜጋም በቁጥር ቀላል አይደልም። 

ኧረ ስንቱን ህልውናችንን የሚፈታተን የምዕራቡ ዓለም የኑሮችን ሁኔታ ዘርዝሬ እዘልቀዋለሁ። ብቻ ግን እኛ ማለት ይህ ነን። ዜጋ ተዘሎ ሲበላና ሲጥጣ ኢትዮጵያውያን አጥማቂ ሳያስፈልገን እንደ ቆምን በኑሮ የምንጠመቅ ዜጎች ነን። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የየራሱ የህይወት ውጣ ውረድ ቢያሰፍር ያን ጊዜ እግዚአብሔር ወይ ከኢትዮጵያውን አልያም ከሳውዲ/ከምዕራቡ ዓለም መሆኑን ያየዋል። 

የሚኖሩትን እያኗኗር ለመኖር የምንከፍለው ዋጋስ ቀላል ነው እንዴ? ሳውዲ ለመግባት በምድረ በዳ የሚያልቀው፣ የዓሣ ነባሪ ቀለብ የሚሆነው፣ በርሃብና በውሃ ጥም መንገድ ላይ የሚቀረው፣ የሌሊት አውሬ ሲሳይ የሆኖው፣ በሽፍቶች የሚዘረፈው፣ በነፍሰ ገዳዮች ዓይኑ እያየ ጆሮው እየሰማ በቁሙ የሚተለተለው የሀገሬ ሰው ሰው ከሚያውቀው ይልቅ የማያውቀው ይበልጣልና ፈጣሪ ራሱ ይቁጠረው። 

የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ብናውቅና እሱም ‘የሚያውቀን’ ዜጎች ብንሆን ኖሮ እኛን እንደ ሰው ለማኖርና ለመባረክ ሳውዲ፣ አሜሪካና አውሮፓ ድረስ ባላንጋጋን ነበር ይልቁንስ የምናመልከውን አምላክ እንመርምር። ይህን ሃሳብ ወደሚቀጥለው “እግዚአብሔር ማወቅ እንዲህ ከሆነ እሱም ባያውቀኝ እኔም ባላውቀው ይሻለኛል! ምንም አይቀርብኝም፡” በሚል ርዕስ ወደ ተዘጋጀ ጠለቅ፣ ጠንከር ያለ ሥነ መለኮታዊ ይዘት ያለው ጽሑፍ ይወስደናል። 

ይቀጥላል

“እግዚአብሔር ማወቅ እንዲህ ከሆነ እሱም ባያውቀኝ እኔም ባላውቀው ይሻለኛል!
ምንም አይቀርብኝም፡”  (ክፍል ሁለት)

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 21, 2013

Advertisements