ለኢሳት ፀሐይ – ለታማኝ በየነ እንጀራ ወጣላቸው! (ክፍል ሁለት)

ካለፈው የቀጠለ፥ Screen Shot 2013-11-20 at 12.59.16 PM

ክፍል አንድ “ለኢሳት ፀሐይ ለታማኝ በየነ እንጀራ ወጣላቸው!” ለማንበብ http://wp.me/p3MQOW-jb ይጫኑ።

የት ስላለ መንግሥት … 

በስሜት ሆነ በእውቀት አንድ ጊዜ “ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ አገር!” በማለት በመድሪትዋ ያለው መንግሥት እውቅና ነስተን ፋይሉ ዘግተን ስናበቃ ይህን ሁኔታ ሲፈጠር ተመልሰን የማናውቀው የኢ.አ.ህ.ዲ.ግ መንግሥት የምንወቅስበት ምክንያት ምንድ ነው? መንግሥት! መንግሥት! እያልን አበክረን የምንጮኸው የት አገር ስላለው መንግሥት ነው? የማንቀበለው፣ ህልውናውን የሰረዝነውና የደመሰስነው ገዢ ምን አድርግ ነው? የኢትዮጵያ መንግሥት የሚባል አናውቅም ከተባለ የማናውቀውን መንግሥት በመጥራት ጊዜአችንና ጉልበታችን በከንቱ አናባክን።

የድንች ልጣጭ ከቆሻሻ ማጠራቀምያ ስፍራ ላይ ጥሎ ሲያበቃ ተመልሶ “የድንች ልጣጭ ያለህ!” በማለት የድንች ልጣጭ ፍለጋ የሚሰማራ ሰው አእምሮው የሳተ፣ የለቀቀ፣ የነቀለና የቀዠበ እብድ ብቻ ነው። ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ምንም ዓይነት ግኑኝነት ሆነ እውቅና እስከሌለን ድረስ በተፈጠረው ሁኔታ ሥልጣን ላይ ያለው የኢ.አ.ህ.ዲ.ግ መንግሥት ተጠያቂ የምናደርግበት ምክንያት የለንም። የፖለቲካ ቅኝት እንዲሁ ነውና።

የአገሬ ሰው ሆይ፥

  • በጩኸት፤ 
  • በፉከራና በሽለላ፤
  • ዘራፍ በማለት፤
  • በስሜት፤
  • ግርግር በመፍጠር፤
  • የሻማ መብራት ፕሮግራም በማዘጋጀት፤
  • ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በመወንጀልና የእርግማን መዓት በማውረድ፤ 
  • በኢትዮጵያ የሚኖሩ የሳውዲ ዜጎች አጸፌታዊ እርምጃ በመውሰድ (አካላዊ ጉዳት በማድረስ) የሚመጣ መፍትሔ የለም። 

በህግ የተጠበቀ የሰው ልጆች መብት ነዋሪነታቸው በሳውዲ ባደረጉ የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በሳውዲ መንግሥት ይሁንታ የሳውዲ ሕዝብና የጸጥታ አስከባሪ ሃይሎች አማካኝነት መደፈሩና መጣሱ ሊስተካከል የሚችለው በተመሳሳይ ሕገ ወጥ መንገድ በመከተል ሳይሆን ሕግን ተከትለን ጉዳዩ በህግ ይታይ ዘንድ በሚመለከተው አካል በኩል ለሚመለከታቸው የፍትህ/የፍርድ አካላት በማሳወቅ በምንወሰደው ሕጋዊ የሆነ እርምጃ ነው። ኢትዮጵያውያን ያለን አማራጭ ይህ ነው። የፈጀ ጊዜ ይፍጅ ጉዳዩን በህግ ፊት ቀርቦ የሳውዲ መንግሥት በድርጊቱ በህግ የሚጠየቅበትና እኛ ተገፊዎች ደግሞ በህግ የምንዳኝበት መንገድ ነው መፍጠር ያለብን። በሰው ተበድለን ስናበቃ ተመልሰን ሰው ለመበደል ከመዶለት ሕግ በድጋሜ ይበድለን። 

እውነት ነው በወገኖቻችን ላይ በደረሰ ግፍና በደል ቁጣችን ነዶዋል። የነደደው ቁጣችን በሳውዲዎች የምናበርድበት መንገድ ግን ሕግና ሕግ ብቻ ይሆናል። ገፊዎቻችን እንደምንችል የምናሳይበት መንገድ ሕጋዊ መንገድ በመከተል ብቻ ነው። “ተበድለናል” በማለት ሕዝብን ለአመጽ መቀስቀስ ግን ድርጊቱ ራሱ ሕገ ወጥነት ነው። ኢትዮጵያ ልትወስደው የምትችለው ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ እንደሆነም አቅማዋን ባገናዘበ መልኩ እንጅ እንዲሁ ከሳውዲ መንግሥት ያላት ግኑኝነት እንዳለ ሙሉ በሙሉ በጣጥሳ ትቀመጥ ማለትም አይደለም። ፖለቲካ እንደሱ አይሰራም። [በነገራችን ላይ ሁኔታው ራስን ከመከላከል ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ራስን መከላከል ሲባል የራሱ የሆነ መመዘኛና መልክ አለው።]

የሰልፍ ወዳጆች አንሁን፡ 

ትርጓሜ፡ ‘ሰልፍ’ የሚለውን ቃል በአውዱ መሰረት በሰራተኛ አገር መንገድ ላይ ወጥተህ የሚደረገው ትዕይንትና  የሚፈጠረው ግርግር ያመለክታል። 

የሰልፍ ወዳጆች አንሁን። በተለይ ዳያስፖራ በስህተት ላይ ስህተት በመፈጸም ነው ተለይቶ የሚታወቀው። እንደው ዳያስፖራና ሰልፍ ከአንዲት ማኅጸን የወጡ የአንዲት እናት ልጆች እስኪመስሉ ድረስ ሲበዛ ፍቅራቸው ቃላት አይገልጸውም። ለነገሩ ሰልፍ ማለት በምዕራቡ ዓለም በከተመ ወገን ዘንድ ድርጊቱ የተለመደና የኑሮውም አንድ ክፍል ነው። ስልፍ ሲጠራ ወጣቱ ፎቶ ግራፍ ለመነሳት፤ ሸምገል ያሉትይ ደግሞ ‘ኦፍ’ ቀኑን (የዕረፍት ቀኑን) የሚያሳልፍበት በአራድኛ አነጋገር በአሪፍ የሚደበርበት መዝናኛው ነው። እንዲህ ግን መሆን የለበትም። በዚህ መልኩ የሚደረገው ማንኛው ዓይነት እንቅስቃሴ የሚያመጣው ለውጥ የለምና። 

እውነት እውነቱ እንነጋገር ከተባለም ዳፓስፖራ ያልተሰለፈበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተፈልጎ ለመድኃኒት አይገኝም። የሚያሳዝነው ግን በዳያስፖራ ሰልፍ የተለወጠ አንዳች ነገር አለመኖሩ ነው። መንግሥት ያሰበውን ማድረግና መፈጸም ዳያስፖራ ደግሞ ጩሆ መክሰር “የተፈጥሮ ህግ” ያክል የታወቀ ነው።

እኔ የምለው ግን የምናደርገው ነገር ካደረግነው አይቀር በእውቀትና በማስተዋል ለውጤት እናድርገው ይቻለን ዘንድ እንዴት አእምሮ አጣን? ከታገልን አይቀር ለመጣል እንታገል ካልሆነ አርፎ መቀመጥ። ጩኸ ተጫጩኸህ ያለ ፍሬ መበተን ምን ዋጋ አለው? ዘሩን እንዲሁ ደረቅ መሬት ላይ በትኖ ሲያበቃ ፍሬ የሚጠብቅ ገበሬ የት አገር ነው?

ኢሳት እንደሆነ በባህሪው (ዓላማውና ግቡ) በህገ ወጥ የሚገኘው ትርፍ ማግበስበስ ስለሆነ አጋጣሚው ተጥቆሞ ህገ ወጥነት በመበረታት ድርጊት ላይ መጠመዱ የሚጠቅመው ራሱን እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። በታሪክ በህገ ወጥ ድርጊት ሕዝብ ምን ጊዜ ተጎጂ እንጅ ተጠቃሚ ሆኖ አያውቅምና። 

በተረፈ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚሆን ነገር ካለ ታማኝ በየነ ዲሲ ስቲድዮ ተሸጉጦ ያለ አቅሙ እየተሽቆጠቆጠ፣ እየተቅለሰለሰና የተሽኮረመመ ከሚንጣጣና ከሚዘበራርቅ ለምን ሳውዲ ድረስ ሂዶ የሳውዲ መንግሥት አያነጋግርም? የቀረውም ይህ ነው። በበኩሌ ክንፍ ባልሰካለትም ውሎውን እዘግብለታለሁ። ታድያ የዋለው ዕለት የሳውዲ መንግሥት እሱንም ጨምሮ እሱን መሳዮች አጀበኞች ወደ ግዞት እንደሚጨምራቸው እያጠያይቅም። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email; yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 20, 2013 

Advertisements