ለኢሳት ፀሐይ – ለታማኝ በየነ እንጀራ ወጣላቸው! (ክፍል አንድ)

ዓለም በራስዋ ሁለት መልክና ገጽታ ያላት ትርጓሜዋና ፍቺዋም ለየቅል የሆነች ትንግርተኛ ነች። ፍጹም ደስታ ፍጹም ሐዘን የማታውቅ ብትኖርም ዓለም ራስዋ ብቻ ትሆናለች የሚል እምነት ነው ያለኝ። ሐዘንዋና ደስታዋ አንጻራዊ ናቸው። በአንድ ሰው ሐዘን፣ ለቅሶና ዋይታ ለሌላው ጥይት የማይበሳው ወፍራም እንጀራ ስትሆንለት፤ በሌላ ሰው ደስታ ደግሞ ለአንዱ የደም ተቅማጥ ስታስቀምጠው፣ በሐዘን ምጣድ ስትጠብሰው ማየት የተለመደ ነው። 

የሰሙኑ አሳዛኝ ሁኔታ ማለት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሳውዲ አረብያ የደረሰባቸውና እየደርሰባቸው ያለ ግፍና በደል ሰለባዎች፣ የግፉ ሰለባዎች ቤተ ዘመድ፣ በአጠቃላይ ዜጎችን በመላ አንገት አስደፍቶ ሲያስለቅስ ደቂቀ ፈሪሳውያን ደግሞ የአዞ እንባ እያነቡ ሕዝብ ወደ አላስፈላጊ ግጭትና ትርምስ ይገባ ዘንድ በቀንም በሌሊትም ነገር በመቆስቆስ ተጠምደዋል። ለኢሳት ጸሐይ ለታማኝ በየነ እንጀራ ወጣላቸው! ያስባለኝም ይህ ነው። 

ለነገሩ ቅኖችና አዋቂዎች ዝምታን በመረጡ ቁጥር ታማኝና ኢሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳሻቸው ቢፈነጩበት ምን ይደንቃል? ኢሳት ሆነ ታማኝ በየነ ዛሬ አልቃሾች ሆኖው እሪ በማለት ሙሾ የሚያወርዱት ግፍና በደል በደረሰባቸው ወገኖች ተከፍቶውና አዝነው ሳይሆን ይህን በማድረግ የሚያገኙት ትርፍና የሚያግበሰብሱት ዳጎስ ያለ ያልደከሙበት ገንዘብ ለማግበስበስ አልመውና አቅደው ትርፋቸው አስልተው ነው። 

ጥቅምት 12, 2013 “ማን ይሁን እውነተኛ፡ ኢሳት ወይስ አሰና?” በሚል ርዕስ ለንባብ በበቃ ጽሑፍ የሚከተለውን ቁም-ነገር አስፍሬ ነበር፥ 

የኢሳት ደስታ፣ ትርፍ፣ ዕድገትና ገበያ የሚደራና የሚሞቀው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውን ለቅሶና ዋይታ፣ ኪሳራ፣ ስብራት፣ ሽንፈት፣ ድክመት፣ ውድቀት፣ ድቀት፣ ሰላም ማጣትና መታወክ ተከትሎ ለመሆኑ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው እውነታ ነው። ይህ አስደንጋጭ ክስተት (በላምፔዱዛ ደሴት የሰመጡ በቁጥር ‘360’ ኤርትራውያን ሁኔታ ማለት ነው) መላ የዓለማችን ሕዝብ የሐዘን ድባብ ሲያለብስ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መልካም ማየት የማይሆንለት ኢሳት ግን በተቃራኒው ክፉኛ አበሳጭተዋል አስቆጥተዋልም። ያለቁት ኢትዮጵያውን ቢሆኑ ኑሮ ኢሳት አጋጣሚው እንዴት ለፖለቲካ ፍጆታ ያውለው ይችል እንደነበር እያሰላሰለም “ያልቀረ ምን ነው ኢትዮጵያውያን ባደረገው!” ዓይነቱ ምዋርት እያሟረተ ከፈጣሪ ጋርም  ጸብ ውስጥ ገብተዋል።

ይሄው አልዋለም አላደረም በሳውዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሳውዲ መንግሥት በአውጅ ባደረሰባቸው ግፍና እየደረሰባቸውም ባለ መከራ የተነሳ ሁኔታው የብዙሐን ኢትዮጵያውያን ዜጎች አንገት ሲያስድፋ ለኢሳት ጸሐይ ለታምኝ በየነ ደግሞ በአንጻሩ እንጀራ ወጣላቸው። ፖለቲካ የሰው ርህራሄ ባልፈጠረባቸው ወረበሎች እጅ ሲወድቅ የሚኖረው መልክና አስቀያሚ ገጽታ ይህን ይመስላል።  

ዘመንኛ ፈሪሳውያን፡

እቺ እያለቃቀስክ እንጀራህን ማብሰልና ኪስህን ማሳበጥ እንደሆነ ከፈሪሳውያን ግብዝነት የተሞላ የዕለተ ዕለት ፖለቲካ በደንብ ትምህርት ወስደንባታል። በዚህ በዚህ ፈሪሳውያን አይታሙም። ተክነውበታል። ሰው ሞተ ሲባል ማንም ሳይቀድማቸው ቀድሞ በመገኘት “ወዮ ወንድሜ!/ወዮ እህቴ! ምን አገኘህ/ምን አገኘሽ፤ ምነው እኔን … ኡ!  ኡ!” እየተባለ ፊት እየቧጨርክ፣ ደረት እየደቃህ፣ መሬት ላይ እየፈረጥክ፣ ልብስ እየቀደድክ፣ ጸጉር እየነጨህና ከግራ ወደ ቀኝ – ከቀኝም ወደ ግራ እየተመላለስክ ለቅሶና ዋይታ ፈሪሳውያን በእሳት ተጠምቀውበታል። ይችሉበታል ያውቁበታልም።

ታድያ “ሞተ” ተብሎ “ልጄ ወዳጄ ምን ነው እኔን ባደረገው … አ ኡ!” እየተባለ ብዙ ያለቀሱለት መዋች በኢየሱስ ደግነት ከሞት የተነሳ ዕለት “ለምን!” በማለት እሳት የሚጫንባቸው፣ የሞተ “ወዳጃቸው” ከሞት በመነሳቱ ግርግር የሚፈጥሩና የውሸት እንባቸው ከዓይናቸው ጠርገው ድንጋይ፣ ቆመጥና ዱላ ይዘው ይህን ያደረገ ኢየሱስ በድንጋይ ለመውገርና በበትር ቀጥቅጠው ለመግደል የሚሰለፉ/የሚወጡ አምባጓሮ የሚፈጥሩ ነውራሞች እነሱ (ፈሪሳውያን) ናቸው። እናማ በመዋች የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ተገኝቶ እንባውን የሚያፈስ አልቃሽ ሁሉ ወዳጅ/አዛኝ እንዳይደለ መቼ ሳትነውና  ነው በኢሳትና በታማኝ በየነ የአዞ እንባ ሆዳችን የሚባባው? ይህችን ይህችን ገንዘብ የማሰባሰቢያ ድራማ ‘ጥርሳችን ነቅለንባታል።’

ኢሳት ነው በኢትዮጵያውያን ሐዘን የሚያዝነው?

  • ኢሳት ስለ ሀገራች የሌለ ነውርና ጉድፍ ከማውራት አልፎ ኢትዮጵያውያን አንድ የሚያደርግ፣ የሚያስማማ፣  የሚያግባባና የሚያፋቅር ይዘት ያለው ሥራ የሰራ መቼ ነው?
  • ኢሳት ሁከትና ትርምስ በኢትዮጵያ ምድር ለማንገስ ከመትጋት አልፎ መቼ ነው ከአንደበቱ የሰላም ድምጽ የሰማነው? 
  • ኢሳት የኢትዮጵያውያን ሰላም የሚነሳ/የሚያውክ እንጅ ዜጎችን የሚያሳርፍ ሥራ የሰራ የት ቦታ ነው?
  • ኢሳት የየትኛው ዕለት ዘገባው ነው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ሸትቶ የሚያውቀው? ኢትዮጵያዊነት ወገን የሆነ የትግራይ ሕዝብ ማስጠቆርና በትግራይ ሕዝብ ላይ የጦርነትና የጥላቻ ዘመቻ ማካሄድ ካልሆነ በስተቀር።
  • ኢሳት በባዶ የቃላት ጋጋታ ኢትዮጵያውያን ለማሸበር ከመልፋት አልፎ ሀገርና ሕዝብ የሚበጅ ሥራ የሰራው መቼ ነው? እንግዲያውስ ይህ ተቋም የኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪ መስሎ በኢትዮጵያውያን ሐዘንና የልብ ስብራት  ያዡኝ ልቀቁኝ እያለ እያጓራ የሚገኘው። ይህን የሚያደርገውም ከምር ሐዘን ተሰምቶት ሳይሆን ለጥቅሙ ነው።  ይህኔ ውስጡ በደስታ ፈርሰዋል። 

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ኢሳት ሆነ ታማኝ በየነ ዛሬ ላይ ደርሰው በኢትዮጵያውያን ስብራት ላይ ስቅስቅ ብሎው የሚያለቅሱ ማን ቤት ናቸው? የነቀሉ የህግደፍ መሪዎች በአደባባይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሲገሸልጡና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያዋርዱ አብሮው በውስጥ ጥርሳቸው ከት ብሎው ሲስቁ የነበሩ አይደሉም ወይ? ኢሳት ሆነ ታማኝ በየነ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ያልተገራ አንደበታቸውን ሲያላቅቁ ምን አሉ? እኮ ምን አሉ? አብረው ሲስቁብንና ሲሳለቁብን ነበር። ታድያ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ቢፈጠር ነው በኢትዮጵያውያን ጉዳይ ስራ የሚበዛባቸው? በአሁን ሰዓት በሳውዲ መንግሥት ግፍና በደል እየደረሰበት ያለ ሕዝብ ሌላ የተለየ ሕዝብ ሳይሆን ትናንት በህግደፍ መንግሥት አንደበት የተዋረደ ኢትዮጵያዊ ነው። ኢሳት ሆነ ታማኝ ትናንት በውርደቱ ከጠላት ጋር አብረው የሳቁበት ሕዝብ ዛሬ ደግሞ የአዞ እንባ እያፈሰሱ ቢያለቅሱለት ነገሩ ከሸቀጥ ያለፈ እውነትነት የለውም ሊኖረውም አይችልም። 

ሌላው ቢቀር ታማኝ በየነ በዚህ ታዝቤዋለሁ። ታማኝ በየነ የሰፈር አሮጊት የተናገረችው ሳይቀረው ለቃቅሞ ከመናገር የማይመለስ ግለሰብ ለመሆኑ ሁላችን የሚያስማማ እውነት ነው። ታድያ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ለዛውም እሞትላታለሁ የሚላት “ኢትዮጵያ” በማስመለከት ያሰሙት ጽርፈት አልሰማሁም አይመለከተኝም ከሚል አጋድሞ ቢያድረኝ ነው የሚቀለው። 

ስለሆነም ኢሳት የኢትጵያውያን በሳውዲ መንግሥት መገፋት ከሚገባው በላይ በማራገብና ያለ ተጨባጭ ማስረጃም እንዲሁ በ አሉ የሚያናፍሰው በሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ፤ በተጨማሪም የታማኝ በየነ የውሸት ለቅሶና መሽቆጥቆጥ ሕዝብ ስሜት ውስጥ በመክተት ወዳልሆነ አቅጣጫ ለማምራትና ቀልድ መሆኑን ብቻ ነው አበከሬ መልዕክቴ ለማስተላለፍ የምወደው። 

በተመሳሳይ ርዕስ ይቀጥላል (ክፍል ሁለት)

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email; yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 19, 2013

Advertisements