የነጻ ሚድያ ያለህ!

  • የአለቆቹ አጀንዳ የሚያራግብ፣ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው፣ የፕሮፖጋንዳ ማሰራጫ ማዕከል ሳይሆን ሀገሬ: ሕዝቤ: ወገኔ የሚል እውነትን ይዞ ስለ እውነት የሚቆምና የሚሟገት የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • ዜጎች “በኢትዮጵያዊነታቸው” ብቻ ያለ አድልዎ የላቀ አስተሳሰባቸውና አመለካከታቸው ለሕዝባቸው የሚያካፍሉበት፤ ዜግነታዊ ድርሻቸው የሚወጡበትና ሃሳባቸውን ያለ ገደብ በነጻነት የሚያንሸራሽሩበት፣ የሚገልጹበትና የሚስተናገዱበት የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • በሥራው እውነትንና ጽድቅን እንጂ ትርፉንና ኪሳራውን እያሰላ በሽፍጥ አፉን የማይከፍት ትውልድ የማይረግመው የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • አንድ ሰው አማርኛ (ሌላ ቋንቋም እንዲሁ) ማውራት ስለ ተቻለ ብቻ ሳይሆን ሥራውን የሚመዝንና የሚሰራውንም የሚያውቅ ሞያው በሚጠይቀው እውቀትና ጥበብ ብቃትም ያለው የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • ከተራ አሉባልታ የዘለለ በቋንቋ በነገድና በባህል በየዓይነቱ የሆነው ማህበረሰብ ወደ ሰላም: አንድነትና ሕብረት የሚያመጣ የሰሚ ጆሮ ልብ የሚያሳርፍ ሙሑራዊና ሳይንሳዊ አገላለጽ ጎልቶ የሚታይበት የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • መረጃዎችን በማዛባትና በመሸቃቀት የሀገርንና የሕዝብን ሰላም የሚነሳ፣ ጫፍ ይዞም አገር ምድሩ በውሸትና በቅጥፈት የሚያስስ ሁከት ፈጣሪ ሳይሆን የእውነት ቅናት የሚበላው መንገድ አዳሽ የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • በአጉል አዋቂነት በአሽሙርና በምጸት ሕዝብን ከሕዝብ ወገንን ከወገን እየነጠለ አንዱን እያሟካሸ ሌላውን የማንያኳስስና የማይዘነጥል ከጥላቻ ፖለቲካ የጸዳ ዕንባ አባሽ የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • ማናቸውንም የዜጎች የአእምሮ ውጤቶች የግለሰቦችንና የድርጅቶችን ልዕልና፣ ክብርንና ዝናን በማስቀደም ሳይሆን ሥራዎች ሁሉ ሀገራዊ ጥቅማቸውና ሕዝባዊ ፋይዳቸውን እየመዘነ ግልጽና ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ ኃላፊነት የሚሰማው የነጻ ሚድያ ያለህ!
  • ለእውነት የሚቀና የነፃ ሚድያ ያለህ!

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail yetdgnayalehe@gmail.com

Advertisements