ዳያስፖራ፡ በጀን ወይስ ፈጀን?

ጥብቅ ማሳሰቢያ፥ 

 • አንደኛ፡ ጸሐፊው ማንንም የመንካት (የማጥቃት) ዓላማ የላቸውም።
 • ሁለተኛ፡ ጸሐፊው ሁሉን በአሉታ የመፈረጀና አንድንስኳ መልካም የለም የሚል ጭፍን አቋም አራማጅም አይደሉም። ስለሆነም ንጽሑ ሰው በንጽሕናው ደስ ሲለው አበር ያለበት ደግሞ በእውነታው መነካቱ እንደማይቀር ስለሚያውቁ የሚከተለውን ሦስተኛ ማሳሰቢያ ለመጻፍ ተገደዋል።
 • ሦስተኛ፡ ጽሑፉ በይዘቱ የሌለ ነገር የሚያትት የፈጠራ ጽሑፍ ወይንም ልብ ወለድ ድርሰት ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን በአሜሪካ የሚኖሩ “ኢትዮጵያያን” [በደፈናው ሁሉን አያጠቃልልም] እውነተኛ ማንነትና ከሌሎች ተለይተው የሚታወቁበት ልዩ መታወቂያ የሚያትት፤ ግን ደግሞ ነገሩ የራሳችን ጉድለትና ደካማ ጎን ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎቻችን አፍ አውጥተን መናገር እንዲሁም ርዕሰ ጉዳዩ በምንም ዓይነት መልኩ እንዲነሳ ካለመፈለጋችንም የተነሳ አንድም አንስቶ የሚያወያይ ሰው አዳምጠን ራሳችንን ለመፍትሔ ከማዘጋጀት ይልቅ ሃሳቡን ያነሳ ግለሰብ ያለ ስሙ ስም መስጠትና በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ መደብደብና መጨፍጨፍ ስለሚቀናን ነው እንጅ ሌላ ታሪክ የለውም።

የጽሑፉ ዓላማ፥ 

በውጭ ዓለም በተለይ ጎልቶ የሚታየውን በአሜሪካ የከተመው ኢትዮጵያ ዜጋ “ከሩቅ ተቀምጬ ለውጥ ማምጣት እችላለሁ” ብሎ የሚያስብ ከሆነ መጀመሪያ ራሱን እንዲመረምር፣ መንገዱን እንዲሰልል፣ በአጠቃላይ በሚያደርጋቸው ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ሁላ ትግል ሲባል ከባላንጣ ብቻ ሳይሆን ትግል ከራስ እንዳለ በመገንዘብ ተሃድሶ ለመጥራት የተጻፈ ጽሑፍ ሲሆን በግልጽ ቋንቋ ከሰፈረው ዓላማ ውጭ ጽሑፉን ሌላ ትርጉም መስጠት አግባብነት እንደሌለው ስገልጽም በእክብሮት ነው። 

የጽሑፉ ውሱንነት፥ 

በተነሳ/ቀጥሎ በሚነሳ ርዕሰ ጉዳይ ዜጎች እርስ በርሳቸው (ለመልካምና ለመፍትሔ) ይወያዩ ዘንድ የሚጋብዝ ፍንጭ ሰጪ ጽሑፍ እንጅ ርዕሰ ጉዳዩ ተያይዘው ሊነሱ የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎችን መልስ አይሰጥም። 

ሐተታ፥

ዳያስፖራ የሚለው ቃል ሥርወ ቃሉ የተገኘ ከሁለት የግሪክ ቃላት ሲሆን ዳያስፖራ የሥነ መለኮት ቋንቋ/መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃልም ነው። ዳያስፖራ በዋናነት ከምርኮ ዘመን ጀምሮ ከፓላስታይን/ፍልስጤም ግዛት ውጭ የሚኖሩ ወይም የተበተኑ አይሁዳውያን የሚያመላክት ሲሆንም በተለምዶ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገሩ የኮበለለ ዜጋ በዘልማድ “ዳያስፖራ” ብሎ መጥራት ወይም መጠራትም እየተለመደ መጥተዋል።

ያም ሆነ ይህ የጽሑፉ ዓላማ ትርጓሜን ማጥራት አይደለምና በቀጥታ ወደ ፍሬ ነገሬ ልለፍ። ምን ያህል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሀገሩ ውጭ እንደሚኖር [በቁጥር ማለቴ ነው] ምንም ዓይነት ፍንጭ የለኝም። ከዚህ ማኸልም የፖለቲካ ጥገኝነት የፈቃድ ወረቀት ስላገኘ ወይም ስለተሰጠው ሳይሆን ምን ያህል በእውነት በፖለቲካ አመለካከቱና ከሚከተለው መንፈሳዊ እምነት የተነሳ ሳይወድ በግዱ ተገዶ አገሩን ጥሎ በውጭ ለመከተም የተገደደ ዜጋ ቁጥርም የተባበሩት መንግሥታት ሳይሆን ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያወቀው። 

በውጭ አገር በተለይ በአሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምን ዓይነት መልክና ገጽታ እንዳለው አላፊው አግዳሚው ወጪ ወራጁ የሚያውቀው ሐቅ ነው። እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዜጋ ብቻ አይደለም የዳይስፖራ* ጭኸት ሊገባው ያልቻለ እዚህ ያለ ከፊሉም ተጮኸ ብሎ ከመጮህ ያለፈ ለምን እንደሚጭህም በውል አያውቅም አይገባውምም። ይህን የምለው ከመሬት ተነህስቼ ሳይሆን ስለገጠመኝ ነው። ይቅር ፖሊሲዎች ለይቶ ሊያውቅ የኢትዮጵያ መንግሥት ምን ዓይነት መንግሥታዊ መዋቅር እንዳለው የማያውቅ በዋሽንግተ ዲሲ ሰልፍ በተራ ቁጥር ግን የሚቀድመው የሌለው ሰው አውቃለሁ። እንደው በዳያስፖራ ዘንድ እሪ ተብሎ የሚጮህላት ኢትዮጵያ አገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ አያውቃትም። እናንተ ሰዎች ያማችኋል እንዴ? የዘወትር የአገር ቤት ኢትጵያውያን ጥያቄ ነው።

ደግሞም እውነት ነው። የታደለ ከየትና ከየት እየተሰባሰበ አገር ስያቆም አለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ* ደግሞ በልቶ ስላደረ ብቻ ሲያገሳ የሚያሰማው ድምጽ የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የሁከትና የክፋት ብሎም አገር ለመበተን እንደሚተጋ ምንም ሊያከራክረን አይገባም። ይህን መካድ የለብንም። ለነገሩ ጠቢቡ “የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል” ( ምሳሌ 21፥ 2) ብሎ የለ። 

የዳያስፖራ* ማናቸውም ዓይነት የዕለተ ዕለት እንቅስቃሴዎች ቀበሌ ተኮር ናቸው። የብሔርተኝነት ችግር አለ። ዳያስፖራ* እንደ ቫይረስ የሚዛመት የብሔርተኝነት በሽታ ታማሚ ነው። የዳያስፖራ* ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን የብሔር የበላይነት ጥያቄ፤ የሥልጣን ጥያቄ ነው። ዲያስፖራ እንደው የያዘው ይዞት ነው እንጅ እጁ ምክሩን መፈጸም የሚያስችል አቅም ቢኖር በጠላትነት የሚፈርጀው ህዝብ በጅምላ ከመጨረስና ከመፍጀት ወደኋላ የማይል ዜጋ ነው። መሬት ላይ ያለው እውነት በመናገሬ ማንም ሊረግመኝ አይገባም። የመራገም አመል ያለበት ሰው ደግሞ ከተራገመ አይቀር እኔን ሳይሆን እውነትን ይርገም! 

ታድያ እንዴት ነው ይህ ችግር መቅረፍ የሚቻለው? ችግር መኖሩን እየታወቀ እንደ መልካም ነገር ተጠብቆ ይኑር?ይህ ነው የሚፈለገው? ከሆነስ እስከ መቼ? ለመሆኑ ምንድ ነው የምንፈልገው? ግባችን ምንድ ነው? እንዴትስ ነው ፍላጎታችንን ሟሟላት እንችላለን ተብሎ የሚታመነው? በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንወክላለን የሚሉ ፖለቲካውን እየመሩ ያሉት ግለሰቦች እውነት ከሌሎች የተሻለ እውቀት፣ አቅምና ብቃት ኖራቸው ነው ጎልተው ይወጡ ዘንድ የቻሉ ወይስ ዋናው ቀድሞ መገኘት ስለሆነ ነው? ከጩኸት የዘለለ ፍሬ ነገር የሌለው ፖለቲካ እስከ መቼ? ለመሆኑ እስከ መቼ ነው የሚጮኸው?  ጎበዝ! ሃያ ዓመት ፍሬ አልባ ጩኸት መጮህ ማለት የሚያሳፍር እንጅ የሚያኮራ አይደለም። 

ለምን ካለፈውን “አንማርም?” ለምን በግትርነት፣ በንዴት፣ በቁጣና በጩኸት የሚሆን/የሚለወጥ ነገር እንደሌለ ያለፉት ሃያ ዓመታት ትምህርት “አንወስድም?” ለችግሮች መፍትሔ ያለው/የሚገኘው በሰከነ መንፈስ በማሰብና በጭምትነት በመመላለስ ውስጥ ነው። ፖለቲካ በሞቅታ ሳይሆን ፖለቲካ በእውቀት የሚከናወን ለመሆኑን እንዴት ማሰብ ተሳነን? ዓመታዊ ወርሐዊም አይደለም በየዕለቱ ራሱን ማለትም ሥራዎቹንና እንቅስቃሴዉን የማይገመግም ግለሰብ ሆነ ድርጅት የለውጥ መሳሪያ ሊሆን ቀርቶ እንደው ሁነኛ አጥፊና አውዳሚ መሳሪያ ነው።

በበኩሌ በልዩነት “በተመሰረተችው” ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነት የአንዲት አገር ዜጋ እስከሆኑ ድረስ በመሪነት ደርጃ ስለ ሚቀመጥ አካል የተሻለ እውቀትና ብቃት ያለው እስከተቀመጠ ድረስ ኦሮሞ ሆነ ትግሬ አማራም ሆነ ደቡብ – አፋር ሆነ ሀረሬ ለእኔ ችግር አይደአለም። ችግሩ፥ 

 • በተለወጠ አገር ተቀምጦ የማይለወጥ፤ 
 • ልኩንና አቅሙን የማያውቅ፤ [አስተዋጽዖን ነው የሚያመላክተው]
 • ከማሰብ ይልቅ ማውራት የሚቀናው፤ 
 • ጉራና ፉከራ ስንቁ፤
 • ትምህርት እንደ ጦር የሚፈራ፤ [የተማረውን የሰው ኃይል፣ ብዙ ነገር መለወጥ የሚችልና ሚዛናዊ የሆነ ዜጋማ ስፍራው በአፈ ጮሌዎች ከመያዙ የተነሳ መግቢያ አጥቶ የራሱ ኑሮ እየመራ ነው የሚገኘው። ቀለም ቆጠሩ የሚባሉ ጥቂቶቹ ደግሞ ከስም ያለፈ ሰብዓዊ ሞራል የሌላቸው ናቸው።]
 • ቁምነገር የሌለው፤
 • በወሬ አገር የምትቀና የሚምስለው፤
 • የምዕራቡ ዓለም ኑሮ ናላው ያዞረበት፤ 
 • ሃያና ሣላሳ ዓመት ተቀምጦ አሁንም ወጥ ወጥ የሚሸት፤ [ያልተለወጠ ማህበረሰብ አለ ተብሎ የሚታመን ከሆነ ለለውጥ የሚነሳ አካል መጀመሪያ ለራሱ መለወጥ አለበት]
 • ወግ ማረግ ያየበት አገር (አውሮፓና አሜሪካ) ለመተቸት ያማያፍር፤ 
 • ቁጭ ብሎ ሲያወራ “ሐበሻና ‘እግዚሃሩ’ ምን ለያቸው?” የሚያስብል፤ 
 • አፉ እንደከፈተ ዘመኑ ያለፈበት፤ 
 • በጥላቻ የሰከረ፤ 
 • በገንዘብ ብዛት የሚታመንና የሚመካ፤
 • ይቅር መንግሥት የሚያክል ግዙፍ አካል ሊያሳደደው የቀበሌ ሊቀ መንበር በውል የማያውቀውና ራሱን በቅጡ የማይገልጽ፤
 • አሜሪካ ስለኖረና የአሜሪካ ዜግነት ስለያዘም የወደደውን ማድረግ የሚችል የሚመስለው ትኩስ ድንች ዳያስፖራ* የሚሉት አእምሮው እሾህና አመኬላ የበቀለበት አሽክላ ዜጋ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ በቀላሉ አትደርስም።

[ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ዳያስፖራ* የሚለው ቃል በደፈናው ሁሉንም አያጠቃልልም። ማንን እንደሚያመላክት የበሽታው ሰለባ የሆነ ዜጋ ራሱ ያውቀዋል።] 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 2, 2013 

Advertisements