እቴጌ፡ ሲጣሩ ውለው ያድሯታል እንጅ አቤትማ አልልም!

ባርነት ውርደት ነው!

አብርሃም ሊንከን “በሰው ላይ ጌታ መሆን የማልፈልገው ያህል የሰው ባሪያ መሆን አልፈልግም” እንዲል በግሌ ከባርነት በላይ ጠላት የለኝም። እጅግ  የምጸየፋቸው ድህነትና “ሰይጣን” እንኳ ቢሆኑ ደረጃቸው ከባርነት ቀጥሎ ነው። ሰው ለባርነት ተላልፎ የተሰጠ ዕለት አንዳች የሚቀርለት ነገር የለም። ሁለመናው ማሸጋገሪያ ድልድይ ደረቅ መሬትም ነው። ነፍሴ ደግሞ ሲፈጥራት ባርነትን እጅግ ትጸየፋለች። አይደለም በውኔ በህልሜም እጅ የሰጠሁበት፣ ለሁኔታዎች የተንበረከኩበትና አንገቴን ያቀረቀርኩበት ቀን/ሌሊት የለም። 

ለእኔ: በየትኛውም ስፍራ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆንም የቀረው ይቀርብኛል እንጅ ራሴን ሁኜ መኖርና መመላለስን የመሰለ የነጻነት ህይወት የለም። ነጻነቴን በጭኸት ሳይሆን በተግባር እውን ማድረግ በህይወቴ ቀዳሚ ተልዕኮየ ነው። ለነጻነቴ በማደርገው ትግል ደግሞ እያንዳንዷ የአካሌ ብልቶች ለመስዋዕትነት ዝግጅዎች ናቸው። ባርነትን የሚሸከም ችክሻ፤ ግፍና ዓመጻን የሚያስችል ማንነት የለኝም። ለራሴ ያለኝኝ ክብር ያህልም ለባለ እንጀራዬ ማንነት ክብር (ልብ) ያለኝና ግድ የሚለኝ ሰው ነኝ። እንዲህም ሆኖ ያለ ምክንያት (ያለ ዓላማ) ማንም በማንነቴ ላይ እንዲቆምር ግን አልፈቅድለትም ብቻ ሳይሆን ዕድል አልሰጠውም። ከቅድሳት መጻህፍት የተማርኩት፣ ከአባቶቼ የወረስኩትና የተቀበልኩት አደራ ይህ ነው።  ከውሃና ከመንፈስ ዳግም ስወለድም በነፍስ ብቻ ሳይሆን በስጋዬም ጭምር ዳግሞ በባርነት ቀንበር ላልወድቅና ላልያዝ ነጻ የወጣሁና የተፈታሁ ሰው መሆኔን ብቻ ነው የማውቀው።

ክርስትናም እንደሆነ በዋናነት ከነገር መራቅን እንጅ ሊገድልህ፣ ሊያጠፋህና ሊያርድህ የሚመጣ ጠላት እጅና እግርህ አጣምረህ አልያም የአበባ እቅፍ ይዘህ ቁመህ ጠብቀው የሚል ትምህርት የለውም። ሰብዓዊ ክብሬና መብቴን ለወንጌል አገልግሎት አሳልፌ እጥል እንደሆነ ነው እንጅ ለባርነት አልውለውም። ባርነት ውርደት ነው።  ባርነት ኪሳራ ነው። ባርነት የሞት ሞት ነው። ባርነት ውድቀት እንጅ ባርነት ክብር ነው የሚል መጽሐፍ አላነበብኩም። ቀድሞውኑ በባርነት የደቀቀ፣ የፈዘዘና የደበዘዘ ሕዝብ እንጅ በባርነት ውስጥ ደስ ብሎት ያደረ ሕዝብ ሲኖር አይደል።

የምን አቤት ማለት ነው?

ነውር የማያውቅ፣ ጌትነት የሚያምረው፣ ጨፍላቂ ነፍጠኛ* ካለ ሬሳዬን ከስፍራ ወደ ስፍራ በማንከራተት፤ በመቃብሬ ላይም ወንበሩን በማኖር  ጥሙን ይወጣ እንደሆነ እንጅ በህይወት እያለሁ ዓይኔ እያዬ ጆሮዬ እየሰማ አሽከር፣ ባሪያ/ሎሌ አድርጎ ይገዛኝ ዘንድ በጽድቅ ቃሉ አስቦ የወለደኝ እግዚአብሔር አያድርግብኝ። የሚገዛኝ የፈጠረኝ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው። የምን አቤት ማለት ነው? አቤት ለማለት አለመፈጠሬ ብቻ ሳይሆን ማንም አቤት እንዲለኝም አልፈልግም። ወንጀልም ነው።

ለነጻነቴና ለመብቴ እሞግታለሁ። “የነጻነት ዋጋ” የሚል መጽሐፍ በመጻፍም ራሴን አላታልልም። ለነጻነቴ ነጻነት የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍዬ ራሴንና ትውልዴን ነጻ አወጣለሁ። በዚህ መሃኸል ብሞት እንኳ አተረፍኩ እንጅ ኪሳራ አያገኘኝም። በሰው ልጅ ታሪክ ማንነቱን ከማጣትና በቁሙ ባሪያ ከመሆን በላይ የከፋ ውርደት የለም። ለማንነቱ የማይቆም ግለሰብ ሆነ ሕዝብ ደግሞ ጎደሎ ፍጥረት ነው። [ነፍጠኛ* ስል ሥርዓትን እንጅ የትኛውም ብሔር አያመላክትም።]

ፈሪና ልበ ድንጉጥ ወደኋላ ይመለስ!

እንግዲያውስ በታሪክ አጋጣሚ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ከአንዲት ባንዴራ ስር የተጠለሉት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደ ሕዝብ ለመቀጠል ያላቸው አማራጭ መስማማት፣ መደማመጥ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገርና መመካከር ከመሆኑ አልፎ አንዱ ለሌላው የሚሰግድለትና የሚለማመጥበት ሁኔታ አይኖርም። በተጨማሪም ኮከቡ በጠፋበት በዳያስፖራ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቁ የመወያያ አጀንዳ የሆነው የትግራይ ሕዝብም ቢሆን እቴጌ ተጣሩ ብሎ ወዲያ ወዲህ የሚልበትና አጎንብሶ “አቤት!” ሲል ድምጹን የሚያሰማበት ምክንያት አይኖረውም። እቴጌ ሲጣሩ ውለው ያድሯታል እንጅ “አቤት!” ማለት የለም!

በአንድም በሌላም ምክንያት “አቤት!” የተባለበት ያ የግፍ፣ የአመጻና የጭቆና ዘመን ተመልሶ ላይመጣ በደም ታትሟል። ዘመኑ ሕዝቦች ከመስመር ሳይወጡ ማንነታቸው ጠብቀው መንገዳቸውን የሚጠበጥቡበት፤ በልዩነታቸው ሕብረት የሚፈጥሩበት ዘመን ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም በባንዴራ ስም ሕዝብን ጨፍልቄ እገዛለሁ ብሎ የሚያልም ካለ ግን ቁርጡን አውቆ እርሙን ሊያወጣ ይገባዋል። ደግሞስ እስከ መቼ ነው የሚጣሩ? በተጣሩ ቁጥር እንደለመዱት “አቤት!” ብሎ የሚደፋላቸውና የሚታዘዛቸው ሰው ሲጠፋ እቴጌም መጣራቱ ማቆም ይገባቸዋል። ካልሆነ ታመዋል ማለት ነው። ለታመመ ሰው ደግሞ ‘ጻድቃኔ’ ወስዶ ሁለት ሰባት መንከር ነው። 

ጎበዝ! ህይወት ምርጫ ናት። ስለሆነም ተከባብረን እንኖር እንደሆነ ዓለም የደረሰበት እንደርሳለን። ከዚህ ውጭ ግን በቃላት ጋጋታና በተረት ብዛት ጉልበቱ የሚብረከረክ/የሚዝል  እንዲሁም ወዶ ራሱን ለባርነት አሳልፎ የሚሰጥ ሕዝብ የለምና ተያይዘን መጥፋታችን የማይቀር ነው። የትግራይ ሕዝብ እንደሆነ የፈለገውን ሁኔታ ቢፈጠር እንደ ማንኛውም ሕዝብ ለክብሩና ለሉዓላዊነቱ የሚደራደር ሕዝብ አይደለም። ሕዝብ ወረቀት አይደለም እንዲሁ የሚጠቀለለው/የሚቀደደውና ስለ የትግራይ ሕዝብ ከሚገባ በላይ ማሰብና መጨነቅም ተገቢ አይደለም። 

የትግራይ ሕዝብ በማንኛው ሰዓት ከየትኛውም ወገን ሊሰነዘርበት የሚችለውን ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ለመመከትና ለማምከን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አቅምና ብቃት ያለው፤ ቁጥርና ጭኸት (ተረት) የማያስደነብረው፤ በወሬ ብዛት ሳይሆን በሥራ የሚታወቅ/የተፈተነ ሕዝብ ነው። ይልቁንስ እያንዳንዱ እርምጃውን ይመረምር ዘንድ ነው የሚመከረው። ፈሪና ልበ ድንጉጥ ወደኋላ ይመለስ!

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Nov 1, 2013

Advertisements