ሻዕቢያ የዋለው ዕለት ቀይ ባህር መቃብሩ ይሆናል!

ኤርትራ፡ እስከ 1890 የትግራይ መንግሥት ግዛት የነበረች፤ ከዚያ ዘመን በፊት አሁን በምትጠራበት ሀገራዊ ስም ህልውና ያልነበራት፤ በዘመኑ አጠራር ትግራይ ትግርኚን የመዳከምና የመበጣጠስ ጣሊያን ከመከረው ሰይጣናዊ ምክርና አጀንዳ  እንዲሁም ከዶለተው ሴራ የተነሳ ለባዕድ (ለራሱ ለጣሊያን) ተላልፋ የተሰጠችና የተሸጠች፤ ከኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት እስከ የደርግ መንግሥት ውድቀት ድረስ የኤርትራ ህዝብ እንደ ሕዝብና ኤርትራም እንደ ሀገር ለመቆም የማንነት ጥያቄ አንስቶ ከ30 ዓመት በላይ የወሰደ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ነጻ ሕዝብ ነጻ ሀገር መሆኑን/መሆንዋን በውል ያረጋገጠ/ያረጋገጠች ሕዝብ/አገር ነው/ናት።

ኤርትራ እንደመሸ ያልነጋላት፣ በለጋነትዋ የቀጨጨችና በገዛ እጅዋ መቃብርዋን ቆፍራ ራስዋን የቀበረች አገር ብትሆንም ኤርትራ ነጻና ሉዓላዊት አገር ናት። ይህ ሐቅ የማናችንም የፖለቲካ አስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነት የማይሸርፈው የማይቆርሰውና የማይለውጠው ሐቅ ነው። የኤርትራ ሕዝብ በቀደሙ ሥርዓቶች ያልተጠቀመና የተመሰቃቀለ ሕዝብ መሆኑን ቢታወቅም የኤርትራ ሕዝብ አሁን ያለበትና የሚገኝበት አሰቃቂና ዘግናኝ የሕዝቡ ነባራዊ ሁኔታ ግን ከማናቸው ያለፉ ታሪኮች በማይነጻጸርና በማይወዳደር እጅግ በከፋ መልኩ የግፍ አገዛዝ ሰለባ ለመሆኑም ምንም የሚያጠያይቀን ጉዳይ አይደለም።

ዓለም ኤርትራን እንደ አንዲት የሰው ልጆች አገር ሳትሆን እንደ ትልቅ እስር ቤት፣ የሰው ልጆች የማረጃ ቄራ፣  ለአከባቢው ሰላም መታወክና ማጣት ጠንቅ (rogue state) አድርጋ መመከት ከጀመረችም ዓመታት አልፈዋል። የፖለቲካ መሪዎችዋ ስብእና እንዲሁ ምንም እንኳ ምላሳቸው ሲዘረጋ የማይደርስበት፣ የማያስሰውና የማይልሰው የዓለማችን ክፍል አለ ለማለት ቢከብድም የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ አገርን የመምራት ብቃት ለመገምገም መሬት ላይ ያለቸው የሐዘን፣ የለቅሶ፣ የዋይታና የሞት ጥላ ያጠላባት ምስኪንዋ አገር ሀገረ ኤርትራ ማየት በቂ ነው። ሰውዬው አለ ቦታው ቢቀመጥ ነው እንጅ አምስትና ስድስት ሚልዮን ሕዝብ የቁም እስረኛና ስደተኛ ባላደረገው ነበር።

ኤርትራ ከድህረ ነጻነት እስከ በባድመ ሰበብ የለኮሰችው ጦርነት ድረስ በነበሩ ዓመታት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበራት ግኑኝነት በተመለከተ እንደ አንዲት ነጻ አገር ግልጽ በሆነ መንገድ ሕግን የተከተለ ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ እኔ የምመልሰው ጥያቄ አይደለም። እንዳልነበረም በዝርፍያና በተራ የሌብነት ድርጊት የተሰማራ የከሰረ የኤርትራ መንግሥት መልስ ይሰጥበት ዘንድ ባንጠብቅም ጉዳዩ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ግልጽ ነው።

በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት በቀንድ አፍሪካ ሃያል፣ የተፈራችና የበለጸገች ኤርትራ ለመፍጠር ያልም የነበረ የኤርትራ መንግሥት ይህን ህልሙ እውን ለማድረገ የተቻለውን ሁሉ አድርጎም ሳይሆንለት ሲቀር ድንበር አመካኝቶ ኢትዮጵያን ለመውረር ቋምጦ እንደነበር ትውልድ ያልተሻገረ የቅርብ ታሪክ ነው። በደረሰበት ወታደራዊና ሁለመናዊ ኪሳራ፤ ተጋድሞ ያለመውን ህልሙም ዝናብ እንደ ሌለው ደመና ተስፋ ሰጥቶ ሲበንበት ሀገራችን የማፈራረስና ዜጎችዋም ለማተረማመስ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶችና ባንዳዎች መሰብሰብ ጀምሯል።

ሐቁ ይህ ነው። ሻዕቢያ ማለት ያላየነውና የማናውቀው ገና ከማርስ የሚመጣ የመናፍስት ሠራዊት ማለት ካልሆነ በስተቀር ኤርትራ (የከሰሩ የህግደፍ መሪዎች/ሻዕቢያ) ለኢትዮጵያ ስጋት የምትሆንበት አንዳች ነገር የለም። ቀድሞውኑ ሻዕቢያ ከስም ያለፈ ህልውና ሲኖሮው አይደል? ህግደፍ አሁን ባለበት በሞት ጥላ ስርም ቢሆን ዘመነ ሥልጣኑ ማራዘም ከፈለገ ባለበት ደርቆ መቅረት ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ድምጹ ያሰማ ዕለት የሞት ሞት ለመሞቱ ምንም አያጠራጥርም። ቁምነገሩ በገዛ አገራችንና መሬታችን የሰለጠኑብን እነማን ቢሆኑ ነው ጥያቄው።

ከባድመ፣ ጾረና፣ ቡሬ፣ ዛላንበሳ፣ ኢሮብ ዓሊተና፣ ገዛ ገረላሰ … ወዘተ የማይማር ነፈዝ ተማሪ ሻዕቢያም ሆነ በሻዕቢያ ትክሻ ተፈናጥጠውና በህግደፍ ጀርባ ታዝለው እግራቸው የሚያነሱ ኃይሎች ሁሉ የዋሉት ዕለት መቃብራቸው ቀይ ባህር ይሆናል። ኤርትራ ከተማዎችዋ ጭር ከማለታቸው የተነሳ የጠፉባት ልጆችዋን ስትፈልግ የልጆችዋ ሬሳ እንደ ፈርዖን ሰራዊት በቀይ ባህር ዳርቻዎች ተሰጥቶ ለሰማይ ወፎች ሲሳይ ሆኖ ታገኘዋለች። 
ሻዕቢያ የቀረ ያልተወራረደ ሂሳብ ካለው አሁንም በድጋሜ ያለ ማይክራፎን በሜዳው/መሬቱ ላይ እናስዘፍነዋለን። ሞት የናፈቃት፣ መቃብር ያማራትና በህይወት መኖር ያንገሸገሻት ክብር የማታውቅ የቀረች ሀብቱ ምላሱ ናትና። ከዚህ ያለፈ ከሞት የተረፈ ማለትም መሳሪያውን እንደተሸከመ በታላቅ ፍርሃትና መንቀጥቀጥ በምርኮ እንደሆነ እንጅ ሻዕቢያ ቀና ብሎ የኢትዮጵያ መሬት አይረግጣትም።

በተረፈ የሰው ልጅ በሞት ጣር ሲያዝ ያምርበታል ይባል የለ በተለይ የመጨረሻ ሦስትና አራት ቀናት በጣም እንደሚፈካና ፊቱ እንደሚወዛዛም ይነገራል። ሻዕቢያም እንደዚሁ በኢትዮጵያውያን መካከል መነጋገሪያ ርዕስ የመሆኑ ጉዳይ በእኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሞገስ ስላገኘ ሳይሆን ግብዓተ መሬቱ ለመቃረቡ ምልክት ነው።

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 31, 2013

Advertisements