ህወሐት የማይቀበል የትግራይ ሕዝብ ደመኛ ነው!

“የማይቀበል” የሚለውን ቃል “የማይስማማ” ተክቶ የሰፈረ ቃል ነው። የህወሐት ታሪክ የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት ያደረገውን ከራሱም አልፎ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተረፈ የትግል አርማ/ታሪክ መሆኑን አምኖ የማይቀበል በዚህ ሐቅ የማይስማማ ለማለት ተፈልጎ ነው።

ጦርነት ውድመት ነው። ጦርነት እልቂት ነው። ጦርነት ሞት ነው። ከዚህ የጦርነት “ባህሪ” የተነሳም ጦርነት በምንም ዓይነት መንገድ የሚደገፍ ድርጊት አይደለም። ጥሎባት ኢትዮጵያ ተብላ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ግን አገራችን ከጦርነት ያረፈችበት ዘመን የለም። ምድሪቱ እስከ መቼ ድረስ የጦርነት ዓውድማ እንደሆነች እንደምትቀጥል፤ በጦርነት እንደምትታመስና እንደምትታወከም አይገባኝም። ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር ባለበት እየረገጠ ያለ ዜጋ ቢኖርም እኛ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚዎች ነን። ይህ ጉልህ መታወቂችን ለመለወጥ በመትጋት ፈንታም በበደል ላይ በደልን መፈጽም ለምን “እንደሚስደስተን” ሌላ ትንግርት የሆነብኝ ማንነታችን ነው።

Salsaywoyaneሐተታ፥

ህወሐት ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ባለፈው ጊዜያችን በህወሐት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው “ህወሐት የደም ዋጋ የተከፈለበት የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ነው!” እና “መስማት የማይፈልጉት የህወሐት ታሪክ!” የሚሉ ሁለት ዓበይት ተከታታይ ርዕሶች በሰፊው መዳሰሳችን የሚታወስ ነው። በዛሬው ዕለት ደግሞ ካለፈው በመቀጠል የትግራይ ሕዝብና የህወሐት ቁርኝነት በተጨማሪም የህወሐት ምንነት በተመለከተም እጥር ኩልል ባለ መልኩ አብጠርጥረን እንመለከታለን።

ህወሐትና የትግራይ ሕዝብ ምንና ምን ናቸው? 

  • ህወሐት ታቦት አይደለም። ህወሐት የትግራይ ሕዝብ ተአምራዊ ታሪክ ነው። ይህን ታሪክ (ህወሐትን) ፍለጋ ደግሞ የትም መንከራተት አያስፈልግም። ህወሐት በእያንዳንዱ በማንነቱ የማያፍር የትግራይ ብሔር ተወላጅ ደም ውስጥ ነው ያለው። 
  • ህወሐት ግለሰብ አይደለም። ህወሐት ወንዱም ሴቱም፣ ትልቁም ትንሹም፣ ከተሜውም ገጠሩም፣ ቄሱም ምእመኑም፣ የተማረውም ያልተማረውም፣ በውጭም በውስጥም ያለና የሚገኝ “አምስት – ስድስት” ሚልዮን  የሚገመት የትግራይ ሕዝብ ራሱ ነው። የትግራይ ምድር ፍሬ ለመብላት (ያልዘራውን ለመሰብሰብ) የሚቋምጥ ኃይል ካለ ደግሞ ይህን ደም ተሻግሮ ነው። 
  • ህወሐት የትግራይ ሕዝብ ታሪክ አንድ ክፍል ነው። 
  • ህወሐት የትግራይ ሕዝብ የልጆቹ ደም ነው። የትግራይ ሕዝብ በስለት ያገኘው ነጻነት የለም። የትግራይ ሕዝብ የደም ዋጋ የተከፈለበት ታሪክ ባለቤት ነው። ይህ ደግሞ ህወሐት ይባላል።
  • ህወሐት የትግራይ ሕዝብ የአጥንቱ ፍላጭ የሥጋው ቍራጭ ነው። ህወሐት የማንም አይደለም። ህወሐት የትግራይ ሕዝብ ሥጋና ደም ነፍስም ነው። እንግዲያውስ ይህ ግልጽና እንደ በረዶም የነጻ የህወሐት ማንነት የማይቀበል ማንም ይሁን ማን የትግራይ ሕዝብ ደመኛ ነው። 

ጎበዝ! ይህን የተገለጠ የህወሐት ማንነት መቀበልና አለመቀበል ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ እንደ ህዝብ የሚቀበል ህወሐትን ይቀበላል። የትግራይ ሕዝብ የማይቀበል ደግሞ ህወሐትን አይቀበልም። እውነቱ ይህ ነው። ዳያስፖራ* “ሙሉጌታ ኢትዮጵያዊ ነው” አለኝ አላለኝ የትኛው ሱቄ ይከስራል። ካርታው በጠፋበት ማኅበረሰብ ዘንድ “ኢትዮጵያዊ” ተብዬ ለመጠራት የምለውጠው፣ የምሸጠው፣ የምሸቀጠውና የምሸቃቅጠው እውነት/ማንነት የለኝም። [ዳያስፖራ* የሚለው ቃል በጥላቻ የሰከሩና ‘ቢል’ ናላቸው ያዞሮባቸው የወሬ መዓድ (ፓልቶክ) ላይ ተጥዶ የሚውሎውን የተኮላሸ ዜጋ እንጅ “ጭዋውን” ኢትዮጵያዊ ሁሉ አይመለከትም።]

ህወሐት እስካለ ድረስ አይደለም፡ የትግራይ ሕዝብ እስካለ ድረስ ህወሐት አለ!

  • ሰዉ እንዴት እንዴት ነው የሚያስበው። ህወሐት አይደለም የትግራይ ሕዝብ የፈጠረ። የትግራይ ሕዝብ ነው በአባቶቹ ዘመን የነበረውን ክብርና ማንነት ለማስጠበቅና ለመመለስ በልጆቹ ደም ህወሐትን የፈጠረ። 
  • ህወሐት “የሴት ፍቅረኛ” አይደለም የሚመጣ የሚሄደውም። የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እስካለ ድረስ ህወሐት አለ። ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ የመጣ ዘመን ብቻ ይህን የትግራይ ሕዝብ የጀግንነት ታሪክ/የህወሐት ህልውና ሊደበዝዝ የሚችለው [መደብዘዝ መጥፋት አይደለም]። የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እስካለ ድረስ ትውልድ አባቶቹ የሰሩት ትንግርታዊና ተአምራዊ ታሪክ (የህወሐት ታሪክ) በታላቅ ደስታና ፌሽታ የራሱን ታሪክ እየዘከረና እያወሳ ይኖራል። 
  • ህወሐት እስካለ ድረስ አይደለም የትግራይ ሕዝብ የሚኖረው። የትግራይ ሕዝብ ከነ ክብሩ እስካለ ድረስም ሆነ   ከዚያ ባሻገር የህወሐት ታሪክ አለ። ታሪክ አይደም ሕዝብን የሚፈጥር። ህዝብ ነው ታሪክ የሚሰራ። ህወሐት የትግራይ ሕዝብ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያደረገውን የትግል ታሪክ ነው። የትግራይ ሕዝብ የትግሉ የድል ምሥክርነት ነው። ቀላል! 
  • ይህ ሕዝብ ዳግም ለባርነት እጁን የሰጠ፣ ማንነቱን የሸጠና የተኮላሸ ዕለትም ቢሆን የህወሐት ታሪክ የትግራይ ልጆች የጀግንነት ታሪክ ነውና የታሪክ ምስክርነቱ ህያው ነው። ይህ አገላለጽ በህወሐትና በትግራይ ህዝብ ያለውን ታሪካዊ የደም ትስስር እንዲሁም ከህወሐት ህልውና ጋር ተያይዘው የ/ለሚነሱ ማናቸውም ዓይነት ጥያቄዎች በቂ መልስ ነው አምናለሁ። 
  • የትግራይ ሕዝብ በቁሙ የሞተ ዕለት ህወሐት ይሞታል። ይህ ትውልድ ግን ህወሐት! ህወሐት! እያለ የቀድሞ ትውልድ/ህወሐት በሰራው ታሪክ ተኩራርቶ የሚዘናጋ ትውልድ አይደለም። ይህ ትውልድ ታሪክ እንደማያድነውና እንደማያተርፈው ጠንቅቆ የሚያውቅ እንደ አስፈላጊነቱ የራሱ ታሪክ ለመስራት በተጠንቀቅ የሚመላለስ የነቃ ትውልድ ነው። ቀልድ የለም። 

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 29, 2013

 

Advertisements