የትግራይ ሕዝብ ለኢሳት የመለመኛ ቅላጼው ነው!

ከዕለት ወደ ዕለት ክፉኛ እያሽቆለቆለና እየቀጨጨ የሚገኘው፤ የቀድሞ ሠራተኖቹ ጥለወት እየሄዱ ያሉት፤ አሁን አሁን የሚያወራው ሲያጣም የግለሰቦች ስብእና በማብጠልጠል ስራ ላይ ተጠምዶ የሚገኘው ንብረትነቱ በጠመንጃ ኃይል፣ በጦርነት፣ በሁከትና በሽብር ሰላምን አወርዳለሁ ብሎ  የሀገራችን ታሪካዊ ጠላት ከሆነው የህግደፍ መንግሥት ግንባር ፈጥሮ ከተሞቻችን በፈንጅ ለማጋየትና ዜጎቻችን በሽብር ድርጊት ለመጨረሽና ለማድማት ያደባ ቀቢጸ ተስፋ የግንቦት 7 የሆነ ኢሳት ጸረ ሕዝብና ጸረ ሀገር ማንነቱ በብዙሐን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ዘንድ እየታወቀና እየተነቃ በመምጣቱ ከዚህ ቀደም ሽር ብትን እያለ እዩኝ እዩኝ ሲል የዘለለው ያክል አሁን አሁን ደግሞ ራሱን የሚደብቅበት ስፍራ ያጣ እስከሚስመስልበት ድረስ እየተሽመደመደና እየተጥመለመለ ለመምጣቱ ምንም አያጠያይቅም።

ሁላችን እንደምናውቀው ይህ ፍሬ አልባ ገለባ የሳይበር የሬድዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በልዩነታቸው ተከባብረውና ተጠባብቀው እንዳይኖሩ የሕዝቦች ልዩነት እንደ ልዩ አጋጣሚ በመጠቀም ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር፣ ዜጎች ደም ለመቃባትና አገር ለማተረማመስ አቅዶና ተልሞ ተግቶ ሲንቀሳቀስ እንደ ነበረና በተለይ ወገናችን የሆነው የትግራይ ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆና ዒላማ አድርጎ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃና ደረቅ መረጃ በጅምላ ሲከስና ሲወነጅል መኖሩንም የሚታወቅ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜያት ወዲህም ኢሳት በማን አለብኝነት መንፈስ ሰክሮ ቀረርቶ ሲያሰማ፣ በባዶ ሜዳ ሲፎክርና ሲክለፈለፍ እንደ ነበረም ለሁላችን ግልጽ ነው።

ታድያ “ስንቅና ውሸታም እያደር ይቀላል” እንደሚባለው ኢትዮጵያን ብትቱ/አድፋም ልብስ በማልበስና የኢትዮጵያ መንግሥት ስፍር ቁጥር/ማለቂያ የሌለው የክሰ መዓት በማሸከም ተለይቶ የሚታወቀው ኢሳት አንገቱ ተሰብሮ ያቀረቅር ዘንድ ግድ ነውና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ራሱን መደበቅና በራሱ ስራዎች ማፈር መጀመሩና የሚሆነው ሲያጣም ኢሳት በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ሽንት ቤቶችና በአሜሪካ የስታር ባክስ ውሎዎች ማነብነብ መጀመሩ ዕጹብ ድንቅ ላይሆነን ነው።

ESAT - loser!

ለመንደርደሪያ ይህን ያህል ካልኩ ዘንዳ ወደ ፍሬ ነገሬ ስመለስ መቼም ሰው በተለያዩ መንገዶችና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከቀድሞ መንገዱ መመለሱ ወይም ከስህተቱ መማሩ የማይቀር ነው። [“መንገዶች” የሚለውን አንድም በፈሊጥ አልያም በፍልጥ ለማለት ተፈልጎ ሲሆን “በልዩ ልዩ ምክንያቶች” የሚለውን አገላለጽ ደግሞ አንድም በውዴታ አንድም በግዴታ ማለትም ሌላ አማራጭ ስሌለው ተገዶ ይማራል  ለማለት ተፈልጎ ነው።]

ኢሳት በሚገባው መንገድ ወዶ ሳይሆን ተገዶ እየተማረ ለመምጣቱ ምንም አያጠያይቅም። ከፍ ሲል ከላይ የምንመለከታቸው ሁለት የተለያዩ የኢሳት የዝርፍያ ዝግጅት ማስታወቂያዎች ኢሳት ለጉድ ሲያደነቁረን ከርሞ ሲያበቃ እንደ ወትሮው ግን የዝግጅቶቹ ውሎዎች ምን ይመስል እንደነበር ልያሳየን ያልደፈረበት ምክንያትም ኢሳትና ጭፍሮቹ ለኃያልም ኃያል እንዳለው በማያዳግም መልኩ የመማራቸው ውጤት ነው። የዋህ ካልሆነ በስተቀር ለምን? ሲል የሚጠይቅ ሰው ካለ ኢሳት ከማስታወቂያ ያለፈ ሙሉ የዝግጅቶቹ ይዘት ለማሳየት ያልደፈረበት ምክንያት “ከመቀመጫው ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ አይጮህም” ከሚለው የአበው ተረት ለጥያቄው በቂ መልስ ያገኛል።

ኢሳት እነዚህ ዘመቻዎች ብቻ አይደለም ሊያሳየን ያልወደደው። ከእነዚህ ዝግጅቶች ቀደም ሲል እ.አ.አ መስከረም 19/2013 ዓ/ም በእስራኤል ያዘጋጃው አዝማሪ ታማኝ በየነ አንድ ጊዜ ብቻም አይደለም ሁለቴና ሦስት ጊዜያት በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለውን ፍጥጥ ያለ ጥላቻና በቀል ያሳየበትና አሳፋሪ በሆነ መልኩ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለውን መራራ ጥላቻ የገለጸበት ዝግጅትም ቢሆን በሌሎች ድረ ገጾች ቀድሞ አምልጦ ስለ ተሰራጨና ከኢሳት ቁጥጥር ውጭ ስለሆነ እንጅ ኢሳት በራሱ ድረ ገጽ አለጠፈውም። የኢሳት የዝርፍያ ዝግጅት በእስራኤል ምን ይመስል እንደነበረ ለማንበብ ሊንኩን (አዝማሪውም አለ …! http://wp.me/p3MQOW-75)  በመጫን ለማንበብ ይችላሉ።

በነገራችን ላይ ታማኝ በየነ ራሱ “አዝማሪ ነኝ፣ የማልረባ ትቢያ ነኝ፣ አፈር ነኝ፣ ትል ነኝ፣ ተራ ነኝ፣ ዶማ ነኝ፣ አካፋ ነኝ፣ ሸክላ ነኝ፣ ድስት ነኝ፣ ምጣድ ነኝ … ወዘተ እያለ በአጉል ትህትና ራሱን ለማቅረብ ስለሚከጅለውና ራሱን በዚህ መልኩ ስለሚጠራ ነው እንጅ በግሌ “አዝማሪ ታማኝ በየነ” ብዬ የመጥራትም ሆነ ግለሰቡን “የመዘንጠል” ፍላጎት ሆነ ዝንባሌ የለኝም። በግሌ “አዝማሪነት” ሞያ እንጅ ስድብ ነው ብዬ ባላምንም ብዙዎች በዚህ መልኩ ላያዩት ስለሚችሉ ግን ራሴን ግልጽ ማድረግ ግድ ብሎኛል። ወንድም ታማኝ እንደው አርፎ ስለማይቀመጥ ነው እንጅ እኔም እንደሆንኩ እጄን አከብድበት ዘንድ አልወድም። ማለትም በዙሪያው የመጻፍ ፍላጎቱ የለኝም። ወንድም ታማኝ ቆሞም ሆነ ተቀምጦ (ብቻ እንደሚያመቸው ሆኖ) እንግዶቹን ቢያስተናግድና ሳክስፎኑን ቢነፋ በእውነቱ ነገር ችግር የለኝም።

ለማንኛውም ግን ኢሳት በየስፍራው እየዞረ የሚደርጋቸው የዝርፍያ ዝግጅቶች ውሎ ለአየር አላበቃም ማለት ግን ኢሳት በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለውን ሥር የሰደደ ጥላቻና ተሸክሞት የሚዞረው የህግደፍ የጦርነት ዘመቻ አጀንዳ አቆመ ማለት አይደለም። በዚህ አጋጣሚ እያንዳንዱ ዜጋ ሊያውቀውና ሊረዳው የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ግን ኢሳት ማለት ሌላ ማንም ማለት ሳይሆን ኢሳት ማለት የትግራይ ሕዝብ ጠላት፣ ዘሩን ለማጥፋት ከሚቋምጡ የውስጥም የውጭም የሞት ጥላ ናፋቂ ኃይሎች ድምጽና ደመኛ ተቋም ለመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ልያሰምርበትና ልብ ሊለው የሚጋባ ተጨማሪ ማስረጃ የማስፈልገው ሐቅ ነው።

ሌላ “ለሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” እንደሚባለው የኢሳት የውሸትና የቅጥፈት እንቅስቃሴ ባለበት ለማምከንና ከምንጩ ለማድረቅ ምንም ዓይነት ጋጋታም ሆነ የሰራዊት ብዛት አንደማያስፈልገው ይህ በቂ ትምህርት ሊሆን ይገባል። አንድ ሰው በብዙ የመንግሥታት እጆች የቆመ ድርጅት እንደዚህ ማሽመድመድና ማጥመልመል ከቻለ እያንዳንዱ ዜጋ   ባለበት ኃላፊነት ተሰምቶት ለአመጻ እንቢ! በማለት ለእውነት ቢቆምና ከእውነት ጋር ሕብረት ቢፈጥር ምንኛ አገር ትቀና እንደነበርም ከዚህ ለመማር እንችላለን።

ሰው ከፈራ ውሸት፣ ቅጥፈትንና ሌብነትን ነው መፍራት ያለበት እንጅ እውነት ካለውና/ከያዘ ከእውነት ጋር ከተጣበቀ አንዳች የሚስፈራው ነገር ሊኖር አይገባም። ገፋ ቢል እውነት የገባችበት ስፍራ ይገባል። እውነት ጉድጓድ ወይም ሲዖል ውስጥ ገብታ ሰምጣ አልቀረችም እንጅ። ታድያ የሐሰት አባት የዙፋኑ መቀመጫ ኢሳት ፊት ለፊት በግልጽ መቃወምና መገሰጽ የሚያስፈራንና የሚያሽቆተቁጠን ምንድ ነው?

ኢሳት ጤና ቢኖረው ኖሮ በገንዘቤም በእውቀቴም ኢሳትን በሁለት እግሩ ለማቆም ማንም አይቀድመኝም ነበር። ዳሩ ግን ኢሳት ራሱን በአመጽ ስለ ገለጠ እኔም ከአመጸኛ መዓድ ጋር የምካፈልበት ምንም ዓይነት ምክንያት ስለ ሌለኝ ለሞቱም እንዲሁ መቅረዜን በዘይት ሞልቼ ከፊቱ ላይ ቆሜለሁ። ፈጽሞ እስከሚወድቅ ድረስ ደግሞ እገዘግዘዋለሁ። ይህ ደግሞ መንፈሳዊ ዜግነታዊም ግዴታዬ ነው

በተረፈ የአብነት ተማሪ “ስለእመብርሃን ስለ ወላዲተ አምላክ” ብሎ የዕለት እንጀራውን እንደሚያገኝ ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለኢሳት የመለመኛ ቅላጼው ነው። ኢሳት የትግራይ ሕዝብ ስም ሳያጎድፍ፣ የጥላሸት ሳይቀባ፣ ሳይቦጭቅ፣ ሳይዘባበት፣ ሳያቃልል፣ ሳይሳደብ፣ ሳይዘረጥጥ፣ ሳይኮንን፣ ሳይራገም፣ ሳያጣጥል፣ ሳያማ፣ ሳይዘልፍ፣ ሳያሽሟጥጥና ሳያዋርድ የሚሰበስባት ዜሮ አምስት ሳንቲም የለችም። ታድያ ይህ የኢሳት የተበላ ቁብ እንቅስቃሴ ለትግራይ ወጣቶች በአጠቃላይ ለትግራይ ሕዝብ የሚያስተላልፈፍ መልዕክት አይኖርም ብሎ ማመንም ሆነ መገመት በራስ ላይ እንደመሽናት ነው የሚቆጠረው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 28, 2013

Advertisements