ነጻ ሚድያ መንግሥትንና የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የምታብጠለጥልበት፣ የምትወርፍበትና የምትዘረጥጥበት መሳሪያ አይደለም!

የጽሑፉ ዓላማ፥

“ነጻ ሚድያ” ምን ማለት እንደሆነ መጠነኛ ግንዛቤ ሰጪ ሃሳቦችን በማካፈል ሕዝብ በርዕሰ ጉዳዩ የጠራ ምስል እንዲኖረው በማድረግም ያይደሉ ዳሩ ግን “በነጻ ሚድያ” ስም የህቡዕ አጀንዳ አስፈጻሚዎችና የፖለቲካ ድርጅት የፕሮፖጋንዳ ማሰራጫ ልሳኖች ለይቶ እንዲያውቅ በመርዳት (እንዲለይ በማድረግ) ራሱና ሀገሩን ከጥፋት ያተርፍና ይጠብቅ ዘንድ ተጻፈ።

የጽሑፉ ውሱንነት፥

ጽሑፉ በይዘቱ ነጻ ሚድያ የሚባል ነገር በምድር አለ “Vs.” የለም? የሚለውን ጥያቄ አይመልስም። የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ “ነጻ ሚድያ” በትርጓሜ ደረጃና ተግባራዊነቱ “በእኛ” መካከል ምን ይመስላል? የሚለውን አንኳርና ወቅታዊ ጥያቄ መዳሰስና ስለ ነጻ ሚድያ መሰረታዊ “ባህሪያት” ማስቀመጥ ብቻ ነው።

ሐተታ፥

“ነጻ ሚድያ” ምን ማለት ነው? ወደሚለው የቃሉ ትርጓሜና ተግባራዊነቱ ከማለፋችን በፊት “ነጻ ሚድያ” ስለሚለው ቃል ልናውቃቸው የሚገቡን ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን እናይ ዘንድ እወዳለሁ።

አንደኛ፡ ሙሉ ቃሉ የሁለት ቃላቶች ድምር ውጤት እንደመሆኑ መጠንና አንደኛውም “ነጻ” የሚል ቃል ስለሆነ በአጠቃላይ “ነጻ ሚድያ” ማለት አቅጫ ሳይለይ እንደሚነፍስ ነፋስ እንዲሁ መያዣ መጨበጫ የሌለው ልቅና ዝሩው አሰራር የሚከተል ነው ማለት እንዳይደለ። 
ሁለተኛ፡ “ነጻ” የሚለውን ቃል ተጠያቂነት የሌለው ማለት እንዳይደለም፤ ይህ ማለት “ነጻ” የሚለውን ቃል ከሥርዓት አልበኝነትና ከልቅነት ጋር ምንም የሚገናኝ፣ የሚያቆራኝና የሚያያይዝ አንዳች ነገር አለመኖሩን ማወቁ/መረዳት “ነጻ ሚድያ” የሚለውን ቃል መሰረታዊ ትርጓሜውን በአግባቡ እንረዳው ዘንድ የለቀ አስተዋጽዖ አለው። 

ነጻ ሚድያ ዜጎች ያለ መከልከል፣ ያለ ገደብና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በሥርዓቱ ሃሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበት፣ የተፈተነ ተሞክራቸውንና እውቀታቸው ያለ አንዳች ስጋት የሚያካፉልበት፣ የዜጎች ምክንያታዊ ነጻ ሃሳብ በገፍ የሚንሸራሸርበትና ሃሳብ ለሃሳብ የሚፈጭበት መድረክ ማለት ሲሆን ነጻ ሚድያ ማለት ያይደለ ደግሞ በንጽጽር የሚከተለውን ይመስላል፥

 • ነጻ ሚድያ ከምንም በላይ ሥርዓትን ጠብቆ የሚሄድ፤ የራሱ የሆነ ግልጽና የማያሻማ የሞያ ሥነ ምግባር ሕጎችና ደንቦች ያሉት ከሕግ ሥር/በታች የሆነ የሕዝብ ድምጽ እንጅ ነጻ ሚድያ የተራ ስድብና የውርጅብኝ ዓይነት የሚዥጎደጎድበት መድረክ አይደለም።
 • ነጻ ሚድያ ጥግ ይዘህ በጠላትነት የፈረጅከውና የምትፈርጀውን አካል ማብጠልጠል፣ ማቃላል፣ መዝለፍና የጥላሸት መቀባት ማለት ሳይሆን ነጻ ሚድያ “ባላንጣዎች” ጭብጦቻቸውን ይዘው ለሕዝብ የሚቀርቡበት ሕዝብም አሸናፊውን ይሁንታውን የሚሰጥበት መድረክ ነው። 
 • ነጻ ሚድያ በሆነ ባልሆነ/በረባ ባልረባ መንግሥት የምትቃወምበትና በባዶ ቃላት የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የምትወነጅልበት መሳሪያ ሳይሆን ነጻ ሚድያ የመንግሥትም የህዝብም ድምጽ ነው። 
 • ነጻ ሚድያ መንግሥትና የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በዘፈቀደ የምታብጠለጥልበት፣ የምትወርፍበትና የምትዘረጥጥበት መሳሪያ ሳይሆን ባለ ሥልጣናቱ እንደ ባለ አደራ እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የሚድያ አሰራር ነው። [ያጠፋ በጥፋቱ አይጠየቅ አላልኩም]
 • ነጻ ሚድያ ሕዝብንና ሀገርን የሚያገለግል መሳሪያ እንጅ ሕዝብንና ሀገርን እያደነዘዝክ “በነጻ ሚድያ” ስም ሕዝብን እያደናገርክ በምትሰበስበው የሕዝብ ገንዘብ አይሱዝ ገዝተህ ኪስህን የምታሳብጥበትና ቤትህን የምትገነባበት  የግል መጠቀሚያም አይደለም። 
 • ነጻ ሚድያ ምን ጊዜም የሕዝብና የሀገር ጥቅም ማዕከል አድርጎ የሚሰራ እንጅ የድብቅ አጀንዳ ማስፈጸምያም አይደለም።
 • በአጭሩ ነጻ ሚድያ የጥቂቶች አጀንዳ በዜጎች ጆሮ ላይ የምትቆረቁርበት መጠቀሚያ መሳሪያ ሳይሆን የሕዝብ ይሁንታ ያለው ሚዛናዊና ፍትሐዊ ተቋም ነው።

የነጻ ሚድያ ተልዕኮና “ባህሪ”፥

የነጻ ሚድያ ዋና ተልዕኮ የተሻለ ትውልድ፣ የተሻለችና የበለጸገች አገር፣ ያደገና የተለወጠ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው። ነጻ ሚድያ ከማንም ወገን ጋር ሳይወግን የሕዝብና የሀገር ጥቅም በማስቀደም ከሁሉም ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ በገለልተኝነት የሚሰራ ተቋምም ነው። ነጻ ሚድያ “በባህሪው” የማንም አጀንዳ ተሸካሚ፣ አስፈጻሚ፣ አራጋቢና ተላላኪም አይደለም። በሌላ አነጋገር ነጻ ሚድያ በወሬና በአሉባልታ የሚታጀብ የሞቅታ ፖለቲካ መጠቀሚያ አይደለም።

ነጻ ሚድያ አተረፈ የሚባለው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ፥ የነጻ ሚድያ ትርፍ ሕዝብ ነው። ሕዝብ ነጻ ሚድያዎች በሚሰጡት ፍትሐዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሲሆን ነጻ ሚድያ አተረፈ ይባላል። የሕዝብ ኪስ እያራቆተና እየቦረቦረ ሕዝብንና ሀገርን እያደቀቀ ራሱን የሚያሳብጥ መዥገር ግን ነጻ ሚድያ ሳይሆን የልዩ አጀንዳ አስፈጻሚ የፕሮፖጋንዳ ማዕከል ነው። ኢሳት ደግሞ ለዚህ አባባላችን ሁነኛ ተጠቃሽ ምሳሌ ነው።

ነጻ ሚድያ የወደመች ሀገር፣ የተራቆተ ሕዝብ ለማልማትና ለማልበስ ተግቶ የሚሰራ ተቋም እንጅ ሀገርንና ሕዝብን ለማውደምና ለማራቆት እንቅልፍ አጥቶ የሚያድር የሁከተኞች ስብስብ ማለትም አይደለም። ነጻ ሚድያ ለሚያገለግለው ሕዝብና አገር ምን የሚቆጠር መልካም ነገር አደረግኩ በማለት በየጊዜው ራሱን የሚፈትሽ፣ የሚጠይቅና ሥራዎቹን የሚገመግም ኃላፊነት የሚሰማው የሕዝብ አካልም ነው። ታድያ፥

 • ሕዝብን እየነጠልቅ ማጥቃትና ማንቋሸሽ፤ 
 • በሕዝብ ላይ መሳለቅና ማላገጥ፤  
 • ሕዝብን መስደብና ማቃለል፤  
 • ጸረ ሕዝብ የሆኑ መፈክሮች ማሰማትና ማስተጋባት፤ 
 • ጸረ ሀገር አቋም ማንጸባረቅና መደገፍ፤  
 • ያልተባለውን እንደተባለ፡ ያልተደረገውን እንደተደረገ በማስመሰል በፈጠራ ወሬ ሕዝብ ማደናገር፣ ማሸበርና   ማወክ የነጻ ሚድያ መታወቂያ የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው?
 • ነጻ ሚድያ ማለት ከምድሪትዋ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ግንባር በመፍጠር ዜጎችን መውጋት ማለት የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው?

እንግዲያውስ ነጻ ሚድያ ማለት ለእርስዎ ይህ ከሆነ ጸረ ህዝብና ጸረ አገር  ልሳን ኢሳትን በመደገፍ ሀገርን በመበታተና ሕዝቦችዋንም ደም ለመቃባት በሚደረገው ርብርብ የድርሻዎን ለመወጣት ገንዘብዎን ቢሰጡ ፍጥረት ሁሉ ላይገርመው ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 26, 2013

Advertisements