በዓለም ታሪክ፥ በጾታ የተደራጀ ሕዝብም ሆነ የተገነባ አገር የለም ለወደፊቱም አይኖርም!

“የተደራጀ” የሚለው ቃል “ውህደትን” ወይም “መገንባትን” የሚያመላክት አጠቃቀም ነው።

የጽሑፉ ዓላማ፥

በዚህ ጽሑፍ በግርድፉ ለማስተላለፍ የተፈልገው መልዕክት፥ የጋራ ማንነትና መገለጫ የሌላቸው በልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የምትገነባ አገር ሊፈጠር ስለሚችለው አለመግባባትና በአገራችን በኢትዮጵያ ለዘመናት ስናየው የመጣንና አሁንም እንደቀጠለ የሚገኘው የብሔር የበላይነት ጥያቄ ይህ ትውልድ እንዴት እንደሚያየው፣ ችግሩም እንዴት ማስቆምና መግታት እንደሚችል ከብዙ በጥቂቱ ለመጠቆም ነው።

ሐተታ፥

በቀጥታ ወደ ርዕሴ ከመዝለቄ በፊት ግን በጃንሆይም በደርግም የአዙሪት ፖለቲካ ልክፍት ያልተለከፈና ያልተነካካ  ስለ አዲሱ ትውልድ (የእኔ ትውልድ) አንዳንድ ጭብጦች ለማለት እወዳለሁ። እንደሚታወቀው ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር ከሰማይና ከምድር በቀር የማያልፍና የማይተካ ነገር የለም። ከሚያልፉና ከሚተኩ በርካታ ነገሮች መካከል ትውልድ አንዱ ነው። ትውልድ ሲባል እንደው በቀላሉ ዘር ተክተህ ከማለፍና ዘርን ከመቀጠል ያለፈ ትርጉም ያለው የማይመስለን ጥቂቶች አይደልንም። ዳሩ ግን ትውልድ በዘመን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የሚታይና በጊዜውም የሚያልፍ፣ የሚተካ፣ ከዚህም ያለፈ ማቆምያው ዘመን በውል የማይታወቅና ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ የሰው ዘር ክፍል ትልቁ ምሥጢር ነው። ትውልድ የሰው ልጅ ህልውና መስተዋት ሲሆን ክፉና ደግ ተብሎም በሁለት ተከፍሎ ማየት ይቻላል። በጥንት ዘመን፥ ዘመንን በትውልዱ ዝቅጠትና ዕድገት መጥራትና መሰየም የተለመደ አገላለጽ ነበረ።

ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ። ኢትዮጵያ እንደ አገር ከቆመችበት ዘመን በፊት የነበረውን የሕዝቦች ሁኔታ ትተን ኢትዮጵያ እንደ አገር ከቆመችበት ወዲህ ያለውን ትውልድ የተመለከትን እንደሆነ በአመዛኙ አሳፋሪ መገለጫ ሆኖ ነው የምናገኘው። በአኩሪነቱ ሊነገር የሚችል አንድ ቁምነገር ቢኖር ሕዝቦች ለባዕድ ወራራ እጅ ላለመስጠት በአድዋ ጦርነት ላይ ያሳዩትን ወኔና ጀግንነት ነው። ይህም ቢሆን ሙሉ አልነበረም። ከዚህ ያለፈ ግን የኢትዮጵያ ታሪክ በትውልድ መካከል በኪሳራ ላይ ኪሳራ፣ በውድቀት ላይ ውድቀት ሲደራረብበት ዛሬ ላይ የደረሰ የእርስ በርስ ጦርነት፣ የድህነት፣ የልመና፣ የርሃብ፣ የስደት፣ የሁከትና የብጥብጥ ታሪክ ነው ያለን። እንዲህ ዓይነቱ ኪሳራ ደግሞ መቋጫ ካልተበጀለት በራሱ ጊዜ የሚቆም ዓይነት ዕዳ አይደለም።

ይህ ትውልድ ማን ነው? ወደሚለው ጥያቄ ልመለስና በዙሪያውም አንዳንድ ነጥቦችም እንዳስቀመጥኩ በቀጥታ ወደ ርዕሰ ነገሬ በማለፍ ጽሑፌን ልቋጭ። ይህ ትውልድ ማን ነው?

 • ይህ ትውልድ ከምንም በላይ ሰላምን አጥብቆ የሚሻ ትውልድ ነው። 
 • መሻት ብቻም አይደለም ይህ ትውልድ በነገር ሁሉ ራሱን ለመስጠትና ሰላምን ሊያወርዱ የሚችሉ አማራጮች ለመጠቀም የይማቦዝን ሰላም ወዳድ ትውልድም ነው።
 • ይህ ትውልድ በልዩነት ለሚመሰረተው አንድነት የማይከፍለው መስዋዕትነት አይኖርም።
 • ይህ ትውልድ ምን ይሁን ምን ልዩነቶቹን አቻችሎ እርስ በርሱ ተዋዶና ተቃቅፎ መሄድ የሚያስችል ዓቅምና ጉልበት ያለው ትውልድ ነው። 
 • ይህ ትውልድ አይቻልም ብሎ የሚያምነው አንድ ነገር ብቻ ነው ይኸውም፥ “በእግዚሃር” ወንበር መቀመጥ ብቻ። ከዚህ ውጭ ይህ ትውልድ አይቻልም ብሎ የሚደመድመው አንዳች ነገር የለውም። በዚህ አጋጣሚ ይህ ትውልድ ቀቢጸ ተስፋዎችን አጥብቆ እንደሚቃወምና ከእንዲህ ዓይነት ስብስቦችም ምንም ዓይነት ሕብረት እንደሌለው ግልጽ ለማድረግ ይወዳል።
 • ይህ ትውልድ የሚበጀውንና የማይሆነውን ለይቶ የሚያውቅ፤ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ አስተሳሰቦች ያለውና የገነባ ትውልድ ነው።
 • ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የሚቀበለውና ሊጠብቀውም የሚገባው ቁምነገር እንዳለ ሁሉ የማይስፈልገውና ፈጽሞ ሊቆርጠው የሚገባው እርም እንዳለም የሚያምን ትውልድ ነው።
 • ይህ ትውልድ እኔነትን አጥብቆ የሚጸየፍና የሚቃወም ትውልድ ነው።
 • ይህ ትውልድ በልዩነቱ በሚመሰርታት (በሕብረት በሚገነባት) አገር የበላይ ከየትም ይበቀል ከየት የአስተሳሰብና የአመለካከት ልቀት ያለው ዜጋ ብቻ ነው ብሎ ያምናል። 
 • ይህ ትውልድ ካለፈው ትውልድ የጦርነት ምዕራፍ ጉዳይ የሌለውና ማንኛውም ዓይነት የቀደመውን ትውልድ የኪሳራና የውድቀት ታሪክ አጥብቆ የሚቃወምና የሚጸየፍ ትውልድ ነው። 
 • ይህ ትውልድ ምኒልክ የእናቴ ጡት ቆርጠዋልና የምኒልክ ነገድ እናቶች ጡት ልቁረጥ የሚል ትውልድ አይደለም። 
 • ይህ ትውልድ ምኒሊክ የአገሬ አብያተ ክርስቲያናት ዘርፈዋልና የምኒሊክ አገር አብያተ ክርስቲያን ማራቆት አለብኝ ብሎ የሚያምን ትውልድ አይደለም። በአጭሩ እገሌ እገሌን ገደለ የዚህ ትውልድ አጀንዳ አይደለም።
 • ይህ ትውልድ ዛሬ ላይ ቆሞ ያለፈውን መናኛ ታሪክ የሚናፍቅ ትውልድ አይደለም። 
 • ይህ ትውልድ “ከመጥፎና” “ብልሹ” ታሪክ መልካምን ነገር ለመማር የሚሻ ትውልድ እንጅ ክፉን ለመድገም “የአባቶቼ” ብሎ የሚጠብቀው ቅርስም ሆነ ታሪክ የሌለው ትውልድ ነው። 
 • ይህ ትውልድ በዕድሜ ታላላቆቹን ያከብራል ለአባት የሚገባ ተገቢ የሆነ ክብርም ይሰጣል። ይህ ማለት ግን አባቶቹ በህይወቱ ላይ ይሾማል ማለት አይደለም። አይደለም ምድራዊ መለኮታዊ ግዴታም የለበትም። 
 • ይህ ትውልድ አባቶች ልጆቻቸውን የሚወዱ ከሆነ ስፍራውን ለልጆቻቸውን መልቀቅ ይጠበቅባቸዋል ብሎ ያምናል። 
 • ይህ ትውልድ፥ ልጆች ለአባቶቻችን ያለን ፍቅርና መውደድ የምንገልጸው የአባቶቻችን አሮጌ አስተሳሰብና አመለካከት በማፍረስና እንቢ በማለት ነው ብሎ ያምናል። 
 • በአጭር ቋንቋ ይህ ትውልድ ሽማግሌዎቻችን እኛ ልጆቻቸውን በማሳረፍ ፈንታ ምጥ/አሽክላ ሆነውብናል ብሎ ያምናል። [“ሽማግሌዎቻችን” የሚለው ቃል “ሥልጣን ወይ ሞት!” ሲል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጣብቆ የሚገኘው የጃንሆይና የደርግ ትውልድ የሚያመላክት ነው።]

የዚህ ትውልድ እምነትና አቋም በግርድፉ፥

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደ ሕዝብ በቋንቋቸው፣ በብሔራቸው፣ በባህላቸው፣ በታሪካቸውና በአስተሳሰባቸው ራሳቸውን ችለው በተናጠል የመደራጀትና የመሰባሰብ መብት አላቸው። [ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከፋፍለህ ለመግዛት የሚደረገውን ተንኮልና ሴራ ግን መቼም ቢሆን ተቀባይነት የለውም።] በአንድም በሌላም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሥር ተጠቃልለው የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከዘመናት በፊት የራሳቸው መንግሥት፣ ታሪክና ሥልጣኔ የነበራቸው ሉዓላዊ ሕዝቦች እንደመሆናቸው መጠን በእነዚህ ሕዝቦች የጋራ ስምምነት/ውህደት (ህብረት) የምትፈጠር አገር ደግሞ የሕዝቦች ሙሉ መብትና ሥልጣን ሊሆን እንደሚገባ ሊያከራክረን አይገባም።

የብሔር ብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና ሥልጣን እንዲሁም መንግስታዊ መዋቅርም ይህን መስመር ተከትሎ ይሄዳል። በዚህ መልክ የሚዋቀር መንግሥም ሆነ የሚወሃድ ሕዝብ ደግሞ ነጻ ሕዝብ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዓይነቱ ደልዳላ መሰረት የምትገነባ አገር ሆነች በዚህ ዓይነቱ መንፈስ የሚወሃድ ሕዝብ ነጻ፣ ፍትሕዊትና ዲሞክራሲያዊት አገር እንደሚፈጥር ምንም አያጠያይቅም። ይህን ሐቅ የማይቀበልና የማይዋጥለት አካል ቢኖር ግን ይህ ግለሰብ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት ጸረ የሕዝቦች መብትና ነጻነት የቆመ ጨፍላቂና ሥርዓት አልባ አምናገነን ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ጸረ ሕዝቦች መብትና ነጻነት፡ እምነትና አቋም የሚያራምዱና የሚያንጸባርቁ ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች የመቃወም፣ የማሳጣት፣ ሕልማቸውን የማጨናገፍና ዓላማቸውን የማምከን ድርሻ ደግሞ የሕዝቦች ሁሉ ግዴታ ነው።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው ካልተደራጁና የፌደራል ሥርዓትም ይህን የሕዝቦች ልዩ መታወቂያና ማንነት መሰረት አድርጎ ካልተዋቀረ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብትና ሥልጣን ሊረጋገጥ የሚችል ሌላ አማራጭ ምንድ ነው? እንግዲያውስ ከዚህ ቀደም በዓለም ታሪክ፥ በጾታ የተደራጀ ሕዝብም ሆነ የተገነባ አገር የለም ለወደፊቱም አይኖርም! በጾታ የተደራጀ ሕዝብ ሆነ የተገነባች አገር እስከሌለ/ች ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያ በጾታ የምትደራጅበት ምክንያት ከዕብደት ያለፈ እውነት ሊሆን አይችልም

በመጨረሻም ጸሐፊው፥ አገር እያወከ ያለ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የጃንሆይና የደርግ ትውልድ ሳይሸጋሸግ ይህ ትውልድ ሰላም ያገኛል ማለት ሲበዛ የዋህነት ነው ብለው ያምናሉ። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 24, 2013

Advertisements