“ቀዳማዊ ምኒሊክ” የሚባል ሰው ሳይኖር ዳግማዊ ምኒሊክ?

ቅምሻ፥

ታሪክ የሌለው ሕዝብ የለም። ይነስም ይብዛም በህልውናው ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ እጅግ የላቀ ህልውና ያለው የሰው ልጅ ሁሉ በግልም በጋራም የሚያወራው ያለፈ የህይወት ምዕራፍ [ታሪክ} ያለው ብቸኛ የታሪክ ባለቤት ነው። ታድያ በጽሑፍ መልክ ሆነ በቃል የሚነገር የአንድ ሕዝብ/አገር ቀደም ብሎ የሆነውንና ያለፈውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ (ወታደራዊ)፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የሕዝቦች አስተዳደር፣ የአኗኗር ዘዬ፣ ጥበብ … ወዘተ በአጠቃላይ ሁለመናዊ ቅርጽ ወይም ገጽታ ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም። 

ውሃ ብረትን እንደሚያዝግ ሁሉ ታሪክም እንዲሁ ጊዜን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የመከለስ፣ የመበረዝና ብሎም ነባር እውነታውን በሌላ “እውነታ” (ተለዋጭ ውሸት) ደብዛው የሚጠፋበት፣ መልኩ ቀይሮ አዲስ ቅርጽና መልክ የሚይዝበት፣ የሚደበዝዝበትና በተፋለሶች የሚጠላለፍበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። ኢትዮጵያም የእንዲህ ዓይነቱ የታሪክ ግራ መጋባትና መፋለስ ሰለባ ከሆኑ መካከል በቀዳሚነት ልትጠቀስ የምትችል አገር ለመሆንዋ ምንም አያጠይቅም። 

የሚያስገኘው ጥቅም አይኖርም እንጅ በአንድም በሌላም መንገድ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ መጻህፍት በኩል በምክንያት ተሰንጥረው ሲያበቁ በማስረጃነት ብሎም እንደ ማጣቀሻ መልክ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ ለሚነገረው ጭብጥ ላይ ያልተመረኮዘ የፈጠራ ፕሮፖጋንዳ በማዳመቅ ረገድ በቀዳሚነት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ አንዳንድ ሰርጎ ገብ የትርጉም መጻህፍት አንድ በአንድ ነቅሰን በጥንቃቄ፣ በማስተዋልና በእውቀት ያጤናቸው እንደሆነ አይደለም የሩቁ የቅርቡ ሳይቀር ብዙ እንከን ያለበት ነው። ውጤቱም ከነተረቱ “አጥብቆ ጠያቂ የናቱ ሞት ይረዳል” እንደሚባለው ነው የሚሆነው።

ሐተታ፥

በኢትዮጵያውያን መካከል “በአከራካሪነቱ” የሚወሳ የምኒሊክ ታሪክ የተመለከትን እንደሆነ አጼው ከልጅነታቸው ይዘውት ያደጉት “ምኒሊክ” የሚል ስም ከወደዱትና “ምኒሊክ” ተብለው መጠራት ካማራቸው ለምን “አጼ ምኒልክ” ብቻ ተብለው መጠራቱን ትተው “ዳግማዊ” ምኒሊክ ተብለው ይጠሩ ዘንድ ወደዱ? ለመሆኑ “ቀዳማዊ ምኒልክ” ማነው? ከነ አካቴው “ቀዳማዊ ምኒልክ” የሚባልስ ሰው ነበር? ካልነበረስ ማን የፈጠረው ተረት ነው? ፖለቲካዊ አንድምታውስ ምንድ ነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ነው። “ቀዳማዊ ምኒልክ” የሚባል ሰው ከነበረስ፥

 • የት አገር የነገሠ ወይም የየት አገር ንጉሠ ነገሥት ነበር?
 • በየትኛው ዘመን የነገሠ? (እንደው “ቀዳማይ ምኒልክ” የሚባል “ንጉሥ” ከነበረ ማለቴ ነው)
 • ከማን የተወለደ? አባቱ ማን ነው እናቱስ ማን ትባላለች? 
 • “ቀዳማዊ ምኒሊክ” የሚባል ሰው በታሪክ እንዴትና በምን ምክንያት/መንገድ ልናውቀው ቻልን? 
 • ትውልዱ “የእኛ አገር” ሰው ካልሆነ እንዴትና በምን ምክንያት ወደ አገራችን ሊመጣ ቻለ? 
 • አገር በቀል ሰው ከሆነም የየት አከባቢ ተወላጅ ነበር? 
 • “ቀዳማዊ ምኒሊክ” የሚባል ሰው በታሪክ ለመኖሩ ምንድ ነው ማስረጃችን? 
 • መጽሐፍ ከሆነ የትኛው/ምን የሚባል መጽሐፍ? 
 • በማን የተጻፈ? 
 • የት የተጻፈ? 
 • ለምን ዓላማ የተጻፈ? 
 • በምን ቋንቋ ተጻፈ? 
 • መቼ ተጻፈ? 
 • እንደ ማስረጃ ሊቀርብ የሚችለው መጽሐፉ ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው (ምድቡ) ሃይማኖታዊ ወይስ ሀገራዊ መጽሐፍ? 
 • መጽሐፉ በራሳችን ቋንቋ ካልተጻፈስ በማን ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ነበር? 
 • መቼ ተተረጎመ? 
 • በማን አማካኝነት? 
 • ለምን? 
 • በወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥስ ምን ይመስል ነበር?
 • የዋናው ቅዢ ባለቤት አገርስ በወቅቱ ከሀገራችን ጋር ምን ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነት ነበራት? 
 • በዋናነት እንደ ማስረጃ ከሚቀርበው አንድ መጽሐፍ ውጭ ሌላ ተጨማሪ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው መጽሐፍ አለ ወይ? [አንደኛውም ቢሆን ከኢትዮጵያ ውጭ በአሁን ሰዓት ጽፈው የሰጡን ሳይቀር አያውቁትም]
 • አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘትና ዓላማ ምን ይመስላል? 
 • ተአማኝነቱ ምን ያክል ነው? 
 • ሆነ ተብሎ ምድሪትዋ ቁቁል ለመድፋት የተከተበ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው የጠላት ሃሳብ/ትብታብ ወይም የፈጠራ ድርሳን ወይም ተረት ላለመሆኑ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል? … 

እንግዲህ እነዚህና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ከአፈ ታሪክ ያለፈ በተጨባጭ መልስ ካልተሰጣቸው መፋጠጣችን ነው። የተነሱ ጥያቄዎችም እንደው አንባቢን ተስፋ ለማስቆረጥና ሰው ለማድከም ሳይሆን “ቀዳማዊ ምኒልክ” የሚባል በዓለም ደረጃም ሆነ በየትኛውም የታሪክ መዝገብ ህልውና የሌለውና የማይታወቅ ሰው ሆኖ ሳለ በብቸኝነት የሚያስተዋውቅ በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ የሚታወቅ ከሌላ አገር ቋንቋ የተተረጎመ በማስረጃነት የሚቀርብ ብቸኛ መጽሐፍ በሚገባ ስለማውቀውና ስላጠናሁት ነው። በተጨማሪም እነዚህ ጥያቄዎች ለመመለስ – ክርስትና በሰሜኑ ክፍል ብቻ ለምን ተጠናከረ? ለሚለው ጥያቄ በቂ ምላሽ ሊኖሮት ይገባል። ምን ነው? ቢሉ የምድሪቱ ታሪክ ያለው እዚህ ሳጥን ውስጥ ነውና።

የአገሬ ሰው ቅንነቱ “በስመ አብ …” ብሎ የሚጀርምር ሁሉ ከሰማይ ይመስለውዋል። ዳሩ ግን ጠላቶቻችን ስስ ጎናችንን በደንብ በሚገባ ስላወቁና ስለተረዱ ምድሪትዋ “በክርስትና” ስም ቆላልፈው ለማስቀመጥ አንዳች የሚያግዳቸው ኃይል አልነበረም። ይህ መጽሐፍ ከጥንት ጀምረው ሀገራችን ሲተናኮሉና በቻሉት ሁሉም ጠልፈው ለመጣል፣ ለማኳላሸትና ለማዳከም እንቅልፍ የማይወስዳቸው የሀገራችን ልማት፣ እድገትና ብልጽግና ማየት የማይሆንላቸው መንግሥታት በኃይማኖት ስም/ሽፋን ተጽፈው ወደ ሃገራችን ሸልኮው ከገቡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሃይማኖታዊ የትርጉም መጻህፍት መካከል አንዱ ነው። በዚህ አጋጣሚ ፖለቲካዊ ይዘት ስላላቸው በቤተ ክርስቲያን ስም ወይም በቤተ ክርስቲያን መጻህፍት ውስጥ ተሰንጥረው ስለሚገኙ አንዳንድ ድርሳኖች ወይም የታሪክ መጻህፍት አንድ ቁምነገር ላካፍላችሁ።

በጥንት ዘመን የነበረ ትውልድ ቤተ ክርስቲያንን የመጠየቅ አቅሙም ሆነ ወኔው አልነበሩም። አይደለም ቤተ ክርስቲያንን/በቤተ ክህነት የሚመጣ ጉዳይ በቤተ መንግሥት የሚነገር አዋጅም ብዙ ለጥያቄ የሚቀርብ አልነበረም። “ንጉስ የቆረጠው እጅ ካለ ይቆጠራል” እንኳ ይባል የለ። ይህ ልክ ያለፈና መጨረሻ የሌለው የመሪዎች የተጋነነ ልዕልናና ሥልጣን ነገሥታቱ አጋጣሚውን በመጠቀም በሕዝቡ ላይ እንዳሻቸው ይሆኑ ዘንድ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓዋል። በሕዝቡ በኩል ሕዝቡ ለመሪዎቹ የነበረው እምነትና የልብ ቅንነት የሚያመላክት እንጅ ሌላ ትርጉም የለውም።

ታድያ የሕዝቡን የልብ ትርታ ጠንቅቀው የሚያውቁ የታሪክ ጸሐፍትና የአገር መሪዎች ነገስታት በሕዝቡ ስስ ጎኑ በመግባት ቤተ ክርስቲያንን መጠቀሚያ በማድረግ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት ሕዝብ ሳይጠይቅና ሳይመራመር እንዲሁ በእምነት አሜን ብሎ ይቀበል ዘንድ በድርሳንም በምንም እያስገቡ፤ አንብበው እያስነበቡም ሕዝቡን ገረፉት እንጅ ይህ ሕዝብ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ቅንና የዋኅ ሕዝብ ነው በማለት አላዘኑለትም። የኢትዮጵያ ነገሥታት የማይገናኝ እያገናኙ በሽፍጥና በዓመጽ ሕዝብን መግዛት ሌላ ልዩ መታወቂያቸው ነው። ስለሆነም በጥንት ዘመን የኢትዮጵያ ነገስታት በቤተ ክርስቲያን ስም/በኩል በቃልም በጽሑፍም የፈለጉትን ፕሮፖጋንዳ ሲነፉ የነበሩ መዘዙም አሁን ድረስ ይህን ትውልድ እንደለበለበ፣ እየፈጀና እየገደለ ያለ መርዝ ለመሆኑ ምንም አየጠያይቅም። እንግዲያውስ “ቀዳማዊ” የሚባል ሳይኖር “ዳግማዊ” የሚለውን መጠሪያ ምንጩ ምን እንደሆነ አግኝተውኛል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

ያም ሆነ ይህ ግን በዚች ምድር (በሀገራችን) ላይ ከዘመናት በፊት በተሸረበ ሴራ፣ ክህደትና ወንጀል እስከ መቼ ነው እርስ በርሳችን እያባላን የሚኖረው? መቼ ነው አገር እርምዋን የምትቆርጠውና ዜጎችዋም በሰላም የሚኖሩ? ወይስ ይሄ ነው የሚፈለገው? እርስ በርስ መበጣበጥና መነታረክ? እስቲ ከጓደኛ፣ ከወዳጅ ዘመድ በቆሙበትና በተቀመጡበት ስፍራ ይወያዩበት። አይመስሎትም?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 23, 2013

Advertisements