ከእንግዲህ ወዲህ …

(አምስተኛና የመጨረሻ ክፍል)

  • ከእንግዲህ ወዲህ ተቀላቅለህ ኑሮ የለም፤ አይኖርምም። አገር ወደኋላ እየጎተተ ያለው ድርጊትም ይህ ነው። አንድ ግብና አንድ ዓላማ የሌላቸው አካላት አንድ ላይ መሄድ አይችሉም። ይህ ማለት ሁለት ባላንጣዎች  ችግሮቻቸው ለመቅረፍና ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ አንድ ላይ መቀመጥ የለባቸውም ማለት አይደለም። እየተቃወምኩ ያለሁ መመሳሰልን ነው። ድብቅ አጀንዳ ይዘህ ስለ መቀላቀል ነው እያብራራሁ ያለኹትይ። እናም ችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ከተሳነን አማራጭ መንገዱ ሁሉም የየራሱ መንገድ ይጠብጥብ ዘንድ ይመከራል። 
  • ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አይደለም በአንድ ብሔር የበላይነት ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ አስተሳሰብና ወግ ተጨፍልቀው ሊኖሩና ሊገዙ ቀርቶ በፌደሬሽን ሆነ በኮንፌደሬሽን አማራጭ የጥምረት/ውህደት ፖለቲካዊ አስተዳደር እንደ አገር ለመቀጠልም ሆነ አብረው ለመኖር ሕዝቦች ስምምነት ላይ የደረሱ እንደሆነ ብቻ  ይሆናል። አንዱ ለጌትነት ሌላው ለባርነት የተፈጠረ ሕዝብም ሆነ ብሔር የለምና።
  • ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሶችና ሕዝቦች መካከል ኃያል፣ ብርቱና አሸናፊ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው።  ከዚህ ያለፈ ኢትዮጵያ ተያይዘህ ሞት፣ ጥፋትና ውድመት ይጠብቃታል።
  • ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ምድር የአንድ ብሔር የበላይነት ብሎ አስተሳሰብ ከህልም ያለፈ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።  ለመሆኑ አንዱ ሌላውን በበላይነት የመግዛት መብት ከየት የተገኘ ሥልጣን ነው? የማታውቀውን፣ በምንም የማትመስለውን ሕዝብ እኔ አውቅልሃለሁ ማለት ዕብደት ነው።
  • ከእንግዲህ ወዲህ አንዱ ሌላውን ተከትሎ የሚገነባ ሥርዓት ሳይሆን የሚኖረው እያንዳንዱ ክልል/ብሔር በእኩልነት በሚያበረክተው አስተዋጽዖ ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና አገር እንገነባለን።
  • ከእንግዲህ ወዲህ (እዚህ ደረጃ ከተደረሰ) ፌደሬሽን ሆነ ኮንፌደሬሽን ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስምምነት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንጅ ግዴታ አለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል። ይህን ያደርጉ ዘንድም የሚያስገድዳቸው  ሀገራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ ህግ የለም።
  • ከእንግዲህ ወዲህ አንዱ እንደፈለገ አፉ ሲከፍትና ሲመጻደቅ ሌላው አንገቱ የሚያቀረቅርበት፣ ቁሞ የሚሰደብበት፣ የሚናቅበትና የሚቃለልበት አንዳች ምክንያት አይኖርም። እንደ ህዝብ ማንም በማንም ላይ የመጮህ ልዩ መብት ሆነ ስልጣን የለውም። የአንድ ሕዝብ መብትና ሥልጣን ራሱን መጠበቆ መንገዱን መጠብጠብ ብቻ ይሆናል። ይህ ማለት ሌላውን ባከበረ ቁጥር ይከበራል ማለት ነው። መስመሩን ያለፈ ቅጽበት ደግሞ በሰፈረው መስፈሪያ ይሰፈርለታል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ማንን እንደማይጠቅም ማናችንም እንስተዋለን የሚል እምነት የለኝም። “ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት” የሚለውን የጌታ ኢየሱስ ትምህርት ምን ማለት እንደሆነ ከዚህ ቀደም አመሳጥሬ እንደገለጽኩት አስፈላጊ ከሆነም ለበረከት ይሆነን ዘንድ መድገም ይቻላል።

በመጨረሻ ብሔር ብሔረሰቦች ማንም (ሌላውን) በማይነካ መልኩ የራሱ ሕዝብ ይህ ማለት በቋንቋ፣ በባህል፣ በአስተሳሰብና በታሪክ የሚመስለውን ማኅበረሰብ እንደ ሕዝብ ባህሎቹንና ወገቹን ማሳደግና ማበልጸግ በሚስችለው ሁኔታ የማንቃትና የማደራጀት ባለ ሙሉ መብት ነው። ይህን ሕዝባዊ መብት የመከልከልም ሆነ የመቃወም መብትም ሥልጣንም ያለው አካልም የለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ የሚደረገውና የሚካሄደው ዘመቻም ሆነ  የጦርነት ቅስቀሳ ግን ሁላችን በአንድ ድምጽ ልንኮንነው የሚገባ የአመጽ መንገድ ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 22, 2013

Advertisements