“ኢትዮጵያ” ለትግራይ ሕዝብ ምኑ ናት?

ትግራይ፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሆነች የተቀሩት ብሔር ብሔረሰቦች ወደ ህልውና ከመምጣታቸው በፊት የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው የአክሱም ስልጣኔ ባለቤት ክልል ወይም ሕዝብ ለመሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። የሕልውናውም ያክል በተለያዩ ዘመናት የራሳቸው ያልሆነ ነገር ለማግበስበስና ያልዘሩትን ለማጨድ ለተነሱ ጨቋኝ ነገሥታትና አንባገነናዊ መንግሥታት በነፍሱ እየተወራረደ ለክብሩና ለነጻነቱ ሲታገልና ሲፋለም ዛሬ ላይ የደረሰ፤ ለህልውናው የማይደራደርና ለዓይኖቹ መኝታ ለሽፋሽፍቶቹም እንቅልፍ የማይሰጥ በታሪክ የተፈተነ ሕዝብም ነው። 

ሐተታ፥

ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ፍትህ! ነጻነት! ዲሞክራሲ! ወያኔ! እጄ! እገሬ! ወገቤ! ምናምን ምናምን … ሲባል እውነት መስሎኝ/ይመስለኝ ነበር። ታድያ ይህ ሁሉ ሲጮህ ንቅንቅ የሚል ነገር አለመኖሩ የያስተዋልኩ ዕለት ስለ ተጮኸ ከመጮህ ይልቅ ጊዜ ወስጄ በሰከነ ልብና በተረጋጋ መንፈስ አጠቃላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰጣ ገባ ወይም ችግር ለመረዳትና ለማጤን ወሰንኩ። በርካታ ጥይቄዎች በመዘርዘርም ጥናቱ የጀመርኩት በእኔ በራሴ ነበርና ባነሳኋቸው ጥያቄዎችም ራሴን በሚገባ ለማየት በመቻሌ የተቀረውን በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ለመዳሰስና ለመገምገም ብዙ አልከበደብኝም።

በአመዛኙ ነባራዊ ሁኔታ ያለፈውን ታሪክ ነጸብራቅ እንደሆነ (በመልካም ሊሆን ይችላል በክፉ ሊሆን ይችላል)፤ ሊያሳድረው የሚችለው ተጽዕኖም የጎላ ሊሆን እንደሚችል፤ እንዲሁም ያለውን ለመረዳት ያለፈውን መዳሰስና ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም በማስመር ወደኋላ መለስ ብዬ አንዳንድ ታሪኮቻችን መየትና ማገለባበጥ የግድ ስለ ነበር ባስቀመጥቁት የጊዜ ሰሌዳ ይህን በመጠኑ ለማሳካት እንደቻልኩ ነበር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከምን ጊዜ በላይ በሚገባ ኩልል ብሎ ሊታየኝ  ሊገባኝ የቻለ። ወደ ዋና ርዕሳችን ስንመለስ፥

ምኒልክ በዘመነ ንግሥናው በትግራይ ሕዝብ አደረሰው የሚባለው ግፍ፣ የፈጸመው ወንጀልና የአብያተ ክርስቲያናት (የንዋያተ ቅድሳት) ዘረፋ ለጊዜው ትተን የቅርቡ የምድሪቱ ታሪክ አንስተን የትግራይ ሕዝብ በእነዚህ አስጨናቂ ዘመናት ምን ይመስል እንደነበር በግርድፉ እንመልከት።

ጃንሆይ (ንጉሥ ኃይለስላሴ) ኢትዮጵያን ለአርባ ዓመታት ያክል ሲገዙ አንድ ስንኳ መልካም ነገር አላደረጉም ማለት አይደለም። ቢሆንም ግን ከአመጣጣቸው (ከአነሳሳቸው) ጀምሮ ጃንሆን በቅንነት ወደ ንግሥና የመጡ ዓይነት ሰው አልነበሩም። በዘመናችን አነጋገር ፎጋሪ (ምስጥ ዓይነት) ሰው ነበሩ። ጃንሆይ የኢትዮጵያ ህዝብ በእውቀትም ሆነ ያለ እውቀት የእግዚአብሔር ስም ሲነሳ አንገቱ የሚደፋ፣ መሬት ላይ ለጥ ብሎ የሚሰግድ ቅንና “እግዚአብሔርን በመፍራት” የሚታወቀው ሕዝብ መሆኑን አውቀው “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሥ ነገሥት ዘኢትዮጵያ”ሚል አጉል ጽድቅ ነበር በላዩ ላይ የተከመሩበትና ለአርባ ዓመታ ያክል የጨፈሩበት።

ጃንሆይ ማለት ተሳላሚ መስለው የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት የዘረፉ፤ ያሸሹ፤ በቤተ ክርስቲያን ስም ደንበኛ ዘራፊ የነበሩ አውራ ቂስ ነበሩ። ርዕሴ አይደለም እንጅ ጃንሆይና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተ ክርስቶያን ግኑኝነት በተመለከተ ብዙ ማለት ይቻላል። በሁለቱም መካከል የነበረ ግኑኝነትም ብዙሐኑ ዜጋ እንደሚያውቀው ሳይሆን እውነቱ የተገላቢጦሽ ነው።

በጃንሆይ ዘውዳዊ አገዛዝ የአገዛዝ ሥርዓት የትግራይ ሕዝብ ምን ዓይነት መልክና ገጽታ ነበረው ያልን እንደሆነ፥ ጃንሆይ በዘመነ ንግሥናቸው ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በርሃብ አለንጋ ሲገረፍና እንደ ቅጠል ሲረግፍ ውሾቹን የሽንጥ ስጋ ይቀልብ የነበረ፤ ቀይ ባህር ለአሜሪካ መንግሥት አሳልፎ በመስጠትም በምትኩ ከአሜሪካ በተገኘ/በተቀበሉት መሳሪያ በዘመኑ አጠራር “ትግራይ ትግርኚ” ተብሎ ይታወቅ የነበረ ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ አከባቢ (ኤርትራን ጨምሮ) “እንቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው” እያለ ጭካኔ በተሞላበት አመራር ሲያደቁ፣ ሲያደሙ፣ ሲወጉ፣ ሲደመሱና ይጨፈጭፉም እንደነበር ነው በታሪክ የሚታወቀው።

በወታደራዊ የደርግ ዘመነ መንግሥትም እንደዚሁ፥

  • የትግራይ ደም ያለበት በኩራዝ እየተፈለገና እየታደነ ሲገደልና ሲፈጅ የነበረ ሕዝብ ነው።
  • በደርግ ዘመነ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ ይቅር ወደ ሥልጣን ሊመጣ አንድ ትውልድ ያጣ ሕዝብ ነው።
  • ይህ ሕዝብ በራሱ ቋንቋ የመናገርና የመጻፍ መብቱ ተነፍጎ በሰው አገር ቋንቋ እንዲጽፍና እንዲናገር የተገደደ ሕዝብ ነበር። 
  • የትግራይ ሕዝብ የራሱ ባህልና ወግ በመለማመድና በማዳበር ፈንታ የገዚዎቹ ባህል ይላበስ ዘንድ የተገደደ ሕዝብ ነበር። 
  • የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የመቆም መብት ያልነበረው በገዛ አገሩ ባይተዋር የነበረ ሕዝብ ነው። 
  • የትግራይ ሕዝብ ትናንት በኦራልና በካማዝ ሬሳውን ሲጎተት የኖረ ሕዝብ ነው።
  • ዛሬም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ ታሪክ (የህወሐት ታሪክ) የተራ ሽፍቶች ታሪክ እየተደረገ የሚነፋው ፕሮፖጋንዳ ሌላ ምንም ሳይሆን የደርግ ቅሪቶች በትግራይ ሕዝብ ላይ ያላቸው መራራና ሥር የሰደደ ጥላቻ ምልክት ነው። 

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ “ኢትዮጵያዊነት ማለት እኩልነት ነው!” ብንል ቀልድ ነው የሚሆነው። አይመስሎትም? ለመሆኑ ኢትዮጵያ ለትግራይ ህዝብ ምኑ ናት? “ሊበልዋት የፈለጉ አሞራ ዝግራ (ጅግራ) ይሏታል” አለ ያገሬ ሰው። “ኢትዮጵያ” ማንን ነው የምትወክለው? “ኢትዮጵያ” ስንል ምን ማለት ነው? “ኢትዮጵያ” የት ነው ያለችው? የትግራይ ህዝብ “ኢትዮጵያዊነት” በሚል የማታለያ ማዕቀፍ ለዘመናት የመብቱ ተጠቃሚ ሆኖ አያውቅም፣ አልነበረም፣ አይደለምም። 

ይህን የምለው በኢትዮጵያ ፖለቲካ የትግራይ ህዝብ እንደ አጀንዳ ሲነሳ ስለሚገርመኝ እንጅ ሌላ የተለየ ለትግራይ ሕዝብ ያደላ አጀንዳ ኖሮኝ አይደለም። ሀገራዊ ጉዳዮች በተመለከተ የዜግነት ግዴታየ ከመወጣትና በሕዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተማመንና እንዲወርድ፣ ፍጹም የሆነ ሕብረትና ውህደት እንዲመጣ፣ እንዲሰፍንና እንዲነግስ ከመትጋት ያለፈ አድሎዊ የፖለቲካ አጀንዳ ያለኝ ሰው አይደለሁም። ታድያ ይህንም የማደርገው በመሸቃቀጥ ሳይሆን እውነት እውነቱን በመናገር ነው።

እውነቱ ምንድ ነው? ለሚለው ጥያቄ፥ ምናልባት ትናንት ሰው በላውን የደርግ መንግስት በዘፈን አጅቦ በንጽሐን የትግራይ ተወላጆች ሬሳ ላይ ቆሞ ከበሮ ሲደልቅ፣ ሲፎክር፣ ሲሸልልና ሲዘል የነበረ ደንቆሮ ላይገባው ይችላል። ይገባውም ዘንድ የሚጠብቀው ሰው የለም። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ማንም ይሁን ማን አንድ ነገር ያውቅ ዘንድ ይጠበቅበታል። ይኸውም፥ ሕዝብን የመስደብ፣ የማንቋሸሽ፣ የማንኳሰስና የማጣጣል መብት ያለው ግለሰብም ሆነ ድርጅት ጨርሶ ሊኖር እንደማይችልና የራሱ ባህል፣ የራሱ ታሪክ፣ የራሱ ስልጣኔ፣ የራሱ አስተሳሰብና የራሱ ሥርዓት ባለው ሕዝብ ላይ በሚከፈት አፍ፡ በተከፍተ አፍ የሚገባ ሆድ ውስጥ ገብቶ የሚፈነዳ ነገር ይኖራል።

ጸረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አቋም የሚራምዱ ቀና ብለው የሚሄዱበት፣ የሚሞካሹበትና የሚሸለሙበት ሰንካላ ፖለቲካ ተይዞ ነው ደግሞ ፖለቲካ! ፖለቲካ! እየተባለ ክብር ያለው ሕዝብ የሚሰደብና የሚዋረደው? ነፈሰ ገዳይ ሁላ። የሰው አገር ሰው ገድለህ እኮ ነው አሜሪካ መጥተህ ባልዋልክበትና ባላለፈብህ የሞያ ዘርፎች “አክቲቪስት”፣ “ጋዜጠኛ”፣ “አርበኛ”፣ በረኛ … የሚለውን መጠሪያ ለጥፈህና ራስህን በራስህ አጥምቀህ በሰው አገር ተዘልለህ እየኖርክ ያለኸው።

ከእንግዲህ ወዲህ … ! (አምስተኛና የመጨረሻ ክፍል)

ይቀጥላል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 20, 2013

Advertisements