“ኢትዮጵያዊነት” ጸረ ትግራይና የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ መቆም ነው!

Viva salsaywoyane

እኔ ራሴን እስከማውቀው ድረስ፡ እግዚአብሔር በህይወቴ ያስተማረኝ ቁምነገር ቢኖር ትልቁም ትንሹም፣ ሊቁም መሃይሙም፣ ያለውም የሌለውም፣ “መልከ መልካሙም” “ፉንጓውም”፣ “ነጩም” “ጥቁሩም” የሰው ዘር በመላ ያለ አድልዎ በእኩል ዓይን አይና ከልብ በሆነ ፍቅርም እወድና አከብረው ዘንድ፤ እውነትን በፍቅር መናገርና ለክብሩም (ለእግዚአብሔር) ዝቅ ማለትና መገዛትን ነው። ከፍቅር በቀር ዕዳ የለኝም። ጎበዝ! ዓይን ያወጡ ችግሮቻችን አፍ አውጥተን ካልተናገርናቸው ለችግሮቻችን መፍትሔ አይገኝበትም።

የጽሑፉ ዓላማ፥

ሰው ፈርተን እስከመቼ? “ይህን ብል እንዲህ አባላለሁ” ማለት እስከመቼ? መቼ ነው እውነት እውነቱን ተነጋግረን ተመራርቀን የምንሸኛኘው? የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ቀደም ሲል በተከታታይ የቀረቡ ሦስት ጽሑፎች ተከታይ ክፍል ሲሆን ኢትዮጵያዊነት በዳያስፖራ ዓለም ምን ዓይነት አፍራሽ መልክና ገጽታ እንዳለው የሚያስቃኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ጸሐፊው ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋና እየከረፋ በመሄድ ላይ የሚገኘው የሀገራችን አስቀያሚ ፖለቲካ በማስቆም ረገድ አንባቢ የበኩሉን ድርሻ ያበረክት ዘንድ ጥሬን አቀርባለሁ።

ሐተታ፥

በአሜሪካ የከፍተኛ ተቋም ትምህርት ቆይታዬ በዋናነት ከትምህርት ጓዶኞቼ በምናደርገው አጫጭርና ረጃጅም ጉዞዎች (road trip)፣ በዕረፍት ጊዜዬ በግሌ የማደርጋቸው ጉብኝቶች፣ አልፎ አልፎም በስብሰባ ምክንያት (ትምህርት ቤቱ በሚያዘጋጃቸው) በአጠቃላይ ሃያ አምስት የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች ለማሰስ ችያለሁ። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም የሚያረካ ነው ባይባልም በጥቂቱም ቢሆን በየ ማኅበራዊ ሚድያዎችና መካነ ድሮች ከምሰማውና ከማየው ባሻገር የእኛ ሰው በአሜሪካ ምን እንደሚመስል በአካል ለማየት ዕድል ፈጥሮልኛል።

በጉብኝቴ አንዳንድ አስደሳች ነገሮች ለማየት እንደቻልኩ ሁሉ ሰው በተለወጠ አገር አሜሪካ እየኖረ እንዴት ነው …? የሚያስብል ብዙ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ልምምዶችም ለማስተዋል ችያለሁ። ከዚህ በፊትም በተለያዩ አጋጣሚዎች በጽሑፎቼ በኩል እንደጠቀስኩት የእኛ ሰው የልቡ ትርታው ለማዳመጥ ከተፈለገ ቤተ ክርስትያን በቂ ቤተ ሙከራ ናት።

በአሜሪካ ስለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ በፊት ብዙ ስላልኩኝ አሁን እግዚአብሔር ምህረቱን ይዘዝላችሁ ከማለት አልፌ የምለው አይኖረኝም። ቢሆንም በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ የኢትዮጵያውያን አብያተ ክርስቲያናት እግር ጥሎት ብቅ ያሉ እንደሆነ ሰዉ የሚባላው የምግብ በየ ዓይነቱ ብቻ ሳይሆን የነገር በየ ዓይነቱም እንዳለ ሲያዩ ይቅር ሕብረት ሊፈጥሩ ራስዎን በራስዎ ጠልፈው ሳይጥሉ ለመሸሽ ነው የሚቾኩሉ።

የዚህ ሁሉ አሳፋሪ የአሜሪካ አብያተ ክርስቶያናት ዋና በሽታም ያልተለወጠ “ማንነታችንና” ፈውስ የሚያስፈገው የሻገተ “አእምሮአችን” ውጤት ነው። መላዕክቱ፣ ቅዱሳኑና ታቦቱ ሳይቀር በጎሳ፣ በብሔርና በነገድ የተደራጁ ናቸው። ምን አለፋዎት! ታቦቶቹ በብሔር ስማቸው ነው የሚጠሩ። ታቦቶቹ በትክክለኛ ስማቸው የጠሩ እንደሆነ የከተማ ነዋሪዎች “አባው፡ ለከተማችን እንግዳ ነህ እንዴ?” ብሎ ነው በማኅበረሰቡ የነገሰውና ቀንድ ያወጣ የልዩነት በሽታ ‘ኮርስ’ የሚጀምርሎት። ብቻ አሁንም እግዚአብሔር ይቅር ይበለን።

ሌላው በሀገርኛ ስመ አጠራር “የብሶት አደባባይ” በመባል ይታወቃል። ይህ ማለት የእኛ ሰው በአሜሪካ ሻይ ቡና እያለ ቁጭ ብሎ … (“የብሶት አደባባይ” ከሚለው ስያሜ ራሱ መረዳት ይቻላል) የሚያወጋበት በአሜሪካ ግዙፉ የቡና ኩባንያ ‘ስታር ባክስ’ (Starbucks) ማለት ነው። ‘ስታር ባክስ’ አከባቢ የእኛ ሰው (ኢትዮጵያዊ ማለቴ ነው) አገኘሁ ተብሎ ዘው ብለው አይቀላቀሉም። ማንነትዎ ሳይጣራ … ። ብቻ ይገባዎታል ብዬ አምናለሁ።

ወደ ፖለቲካው ልመለስ። ፖለቲካ የአንድ የማኅበረሰብ ነጸብራቅ ለመሆኑ አያከራክረንም። በፖለቲካ መስተዋት የሚታየው ሕዝብም ራሱ ሕዝቡ ነው።  ፖለቲካ መስተዋት ነውና። ስለሆነም የእኛ ሰው በአሜሪካ የተጸናወተው የክፍፍል፣ የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ ዋና ተዋናዮችም “እኛው ራሳችን” እንጅ ሌላ አካል ሊሆን አይችልም። በእርግጥ ይህ በእኛ ማሕበረሰብ መካከል የሚስተዋለውና የሚታየው አሳፋሪና አስቀያሚ ድርጊት የዳያስፖራ ማኅበረሰብ በደፈናው እንደማይወክል አሳምሬ አውቃለሁ።

የተደራጀው በዋናነት አገር ቤት ያለውን ሕዝብ እርስ በርስ ደም ለማቃባት ብቻ ሳይሆን ከአገሩ ሩቅ ሰፈር ከትሞ የሚኖረውን ማኅበረሰብ ሰላም ለማደፈረስ፣ ዕረፍት ለመንሳት፣ ለማወክ፣ ለመከፋፈልና ለመለያየት ጭምር እንደሆነ ለአፍታ አልጠራጠርም። ይህ ተቋም ኢሳት ይባላል። ኢሳት ማቋቋም ያስፈለገበት ዋና ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱን በማጥበብ ወደ አንድነትና ወደ ሕብረት ለማምጣት ሳይሆን ከነተረቱ “የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንደሚባለው የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩነቶቹን በማስፋት እርስ በርሱ እንዲተላለቅና ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲገባ በማድረግ ሊገኝ የሚችለው ትርፍ ያሰሉ የሀገርና የትውልድ ጠላቶች የተቋቋመ ነው። የኢሳት ግብ፣ ተልዕኮና ዓላማም እሳት ማያያዝ፣ ማንደድና ማቀጣጠል ለመሆኑ ሥራዎቹን በጥሞና መከታተል ይሻል።

የዳያስፖራ ፖለቲካ በኢሳት ልክ ነው ወይም ዳያስፖራ በኢሳት ነው የሚለካው እያልኩ አይደለም። በዳያስፖራ ብዙ ሰላም ወዳድ፣ አንደነት ፈላጊ ንጹሕ ማኅበረሰብ እንዳለ በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅሰው አላልፈም። በአሁን ሰዓት የኢሳት የጦርነት ፕሮፖጋንዳ፣ ጥላቻ የተሞላበት የግብር ይውጣ ሥራ በመጸየፍና በኢሳት አሳፋሪ ውሸት የተሰላቸ በጣቢያው ላይ ፊቱ እያዞረ ያለው የዳያስፖራ ማኅበረሰብም ቁጥር ቀላል አይደለም። በከፍተኛ ሁኔታ በተመልካች እጦት ድርቅ ለመመታቱና የሞት ጣር ውስጥ እንደሚገኝም ኢትዮጵያን ሪቪው የተባለ ድረ ገጽ በያዝነው ወር መጀመሪያዎቹ ቀናት አከባቢ ዋቢ አድርጎ ይፋ ያደረገውን ሪፖርት ማየት በቂ ነው።

ዳያስፖራ በተነሳ ቁጥር ግን “እውነት የጫማ ክርዋን እስክታስር ድረስ ውሸት ዓለምን ታዳርሳለች” እንደሚባለው ጎልቶ የሚታይና የሚታወቀው እነዚህ በጃንሆይና በደርግ ዘመነ መንግሥት ዜጎች ያለ ምሕረትና ያለ ርህራሄ ስጨፈጭፉ፣ ሲያርዱና ሲገድሉ የነበሩ ወታደሮች፤ የፕሮፖጋንዳና የቅስቀሳ ካድሬዎች ነበር፤ በአጠቃላይ ከፍትሕ ያመለጡና ዛሬ “ጋዜጠኛ”፣ “አክቲቪስት”፣ “የሰብዓዊ መብትና” የመሳሰሉ ማስክ አጥልቀው የሚክለፈለፉና የሚወራጩ ደም የለመዱ ቅሪላዎች የሚመራ የጥላቻና የልዩነት ፖለቲካ አከፋፋዮች ነው። “ኢትዮጵያዊነት” የሚለካና የሚወሰነውም በእነዚህ ነፈዞች ስብስብ ነው።

ይህ የነፍሰ ገዳዮችና የጎጠኞች (ሰውን “ዘረኛ” እያሉ ሲያቃልሉና የጥላሸት ሲቀቡም አያፍሩም) ስብስብ በሰፊው በተቆጣጠረው በውጭ የሚገኙ ሚድያዎችና ድረ ገጾች “ኢትዮጵያዊ” ያለው ኢትዮያዊ ነው፤ የሻረው ደግሞ የተሻረ ነው። “የዳይስፖራ” ፖለቲካ እውነተኛ ገጽታና ማንነት በአጭር ቋንቋ ላስቀምጠውና ኢትዮጵያዊነት በዳስፖራው ዓለም ምን ዓይነት ትርጓሜና ይዘት እንዳለው ነጥብ በነጥብ በማስቀመጥ ጽሑፌን ልቋጭ።

የዳያስፖራ ፖለቲካ “ወያኔ” ለማጥፋት ተሰባስቦ ለራሱ የጠፋ፤ ያረጀ፣ ጊዜው ያለፈበት፣ ጥርስ አልባ “አንበሳ” ነው! የሚል አገላለጽ ሲያንስበት ነው።

  • አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ “ኢትዮጵያዊነት” ጸረ ትግራይና ትግርኛ ተናጋሪ ሕዝብ መቆም ነው። 
  • “ኢትዮጵያዊ” እየተባለ የሚጠራና የሚታወቀው ግለሰብ ሆነ ድርጅት ጸረ ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ የተሰለፈ ኃይል ነው።
  • አንድ ሰው በዳያስፖራው ዓለም “ኢትዮጵያዊ” ተብሎ ለመታወቅም ሆነ ለመጠራት የትግራይ ህዝብ እንደ ሕዝብ በጠላትነት መፈረጅ ይጠበቅበታል። 
  • በዳያስፖራው ዓለም “ኢትዮጵያዊ” ተብሎ ለመጠራት ሆነ እውቅና ለማግኘት የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት ያደረገው ትግልና የከፈለው የህይወት መስዋዕትነት ማብጠልጠልና ዋጋ ማሳጣት ይጠበቅበታል። 
  • ኢትዮጵያዊ ለመባል የኢትዮጵያ ፖለቲካ “በትግራይ ገዢ መደብ” የበላይነት የሚመራ ነው ብሎ ማመንና መቀበል ይጠበቅበታል።
  • አንዳንድ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘት አጉል ተግባር ላይ የተሰማሩ ተመጻዳቂዎች፣  የማንነት ቀውስ የሚታይባቸው መሃል ሰፋሪዎች፣ ራሳቸውን ለመግለጽ የሞት ያክል የሚከብዳቸው አስጎብዳጆችና አሳባቂዎች የትግራይ ተወላጆችም ቀኑ እስኪደርስ ድረስ ከአንገት በላይ “ኢትዮጵያዊ” ተብለው የመጠራት ዕድል አላቸው።

ነገሩ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ፥ ኢትዮጵያ ለትግራይ ሕዝብ ምኑ ናት?፡ በሚል ርዕስ በሚቀጥለው ጽሑፌ በሰፊው እንዳስሰዋለን። 

ኢትዮጵያ ለትግራይ ሕዝብ ምኑ ናት?

ይቀጥላል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 19, 2013

Advertisements