ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንጅ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም! 

ካለፈው የቀጠለ (ክፍል ሦስት)salsaywoyane

የጽሑፉ ዓላማ፥

ጽሑፉ በይዘቱ አብዛኞቻችን አፍ አውጥተን እንድንናገረው የማንፈልገው ርዕሰ ጉዳይ የሚዳስስ ሲሆን ዓላማው፥

አንደኛ፡ የምድራችን መሰረታዊ ችግር መጠቆም፤

ሁለተኛ፡ ከነ ልዩነቶቻችን ሁሉን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ አንድነት መፍጠር እንደሚቻል ለማበረታታት፤

ሦስተኛ፡ ኢሳትና በመሳሰሉ አንዳንድ የጎሳ ዜማ አቀንቃኝ ድረ ገጾች ከምን ጊዜም በላይ አንድን ሕዝብ ያነጠጠረ የከፈቱት የጦርነትና የጥላቻ ዘመቻ ከወዲሁ ይታሰብበት ዘንድ ለማሳሰብ ተጻፈ።

ጥብቅ ማሳሰቢያ፥ 

 • ጽሑፉ በማንነት ዙሪያ የሚያጠነጥንና የሀገራችን የፖለቲካ ችግር የሚጠቁም እንጅ ብሔር ተኮር አጀንዳ የለውም። እንዲህ ያለ እንቅስቃሴም አያበረታታም። የጽሑፉ ዓላማ ከሚለው ሥር ግልጽ በሆነ ቋንቋ ከሰፈረው ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ዓላማ እንደሌለው በድጋሜ ለማሳወቅ እወዳለሁ።
 • ካርታው በተመለከተ ጥያቄ ካሎት ካርታው እስካልሰራሁት ድረስ አልጠይቅበትም።
 • የጽሑፉ ርዕስ ስያሜ፥ የሀገራች ሥር የሰደደ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና በአሁን ሰዓት ትልቁም ትንሽም በማዋረድ ያለውን ጎሳ ማዕከል ያደረገ ፖለቲካ የሚያመላክት እንጅ ርዕሱ የጸሐፊው ግላዊ ድምዳሜ አይደለም።

ሐተታ፥

የኦሮምያ ክልል ተወላጆች በማንነቱ ኦሮሞ ለሆነ ሰው ያላቸውን አስተሳሰብና አመለካከት ከሌላ ብሔር ለሆነ ወገን ማለትም ለአማራ፣ ለትግራይ፣ ለደቡብ ያላቸውን አስተሳሰብና አመለካከት ሲነጻጸር አንድ አይደለም። አማራ ወገኔ የሚለውን  ከአማራ ነገድ  የሆነውን ሰው በሚያይበት መነጽር የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ  … ተወላጆችን እኩል አያይም። የትግራይ ተወላጆችም እንዲሁ የራሴ የሚለውን የትግራይ ሰው በሚያይበት መነጽር የአማራ ክልል ወይም የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ  … እኩል አያይም።

 • በግልጽም በስውርም እያፋጀን ያለው የማንነት (የብሔርተኝነት) ጥያቄ ነው። [የብሔር ጥያቄ ማንሳት በራሱ ኃጢአት ነው እያልኩ አይደለም። ለጥያቄው የሚሰጠው መልስ ላይ ነው የእኔ ትኩረት]
 • አንድ ማንነት ቢኖረን ኖሮ አንዱ አንዱን ለመግደል ባላሴረና ባልተሳ ነበር።
 • ታሪካችን የመገዳደል ታሪክ ነው። ከዚህ ታሪክ ጀርባ ያለው ታሪክ ደግሞ  የማንነት ጉዳይ ነው። ዛሬም ቢሆን አቅም ታጥቶ ነው እንጅ ሰዎች ተኝተው ስላደሩ አይደለም።
 • ኢትዮጵያውያን የአንድ ማንነት ባለቤቶች ብንሆን ኖሮ እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ባልገባን ነበር። ጥያቄአችን በዲሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በሰብዓዊ መብት ወዘተ ሸፋፍነን አሳመርነው እንጅ ጥያቄአችን የማንነት ጥያቄ። ባይሆን ኖሮ ችግሮቻችን ለመፍታትና ለመደማመጥ ባልተሳነን ይህን ያህልም ባልተቸገርንና ነበር።
 • የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ አማራጭ መንገድ ታጥቶ አይደለም። ታድያ ጥያቄው “ማን ይሁን የበላይ?” ነው። ለነገሩማ ማንስ የበታች መሆን ይወዳል ብለው ነው። እንግዲያውስ መሬት ላይ ያለው ሐቅ ይህ ነው።

ኢትዮጵያዊነት በፓስፖርት የሚለካ ከሆነ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ ቅሬታ ያላቸው አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ጨምሮ በፓስፖርት ደረጃ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። በማንነት ደረጃ ግን ቀደም ሲል እንደተገለጸው ነው። ማንነት በደፈናፍ እንዲህና እንዲያ ነው ተብሎ የሚታለፍ አልያም በመፎክርና በጭሆት የሚገለጽ ሳይሆን ማንነት የሚታይ፣ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ፣ ወጥነት ያለው፣ የሚገለጽ፣ አንዱ ከሌላው ተለይቶ የሚታወቀው ልዩ መታወቂያ ነው።

ማንነት “ሰው ሰራሽ” አይደለም። ማንነት “ተፈጥሮአዊ” ነው። አንዱን ብሔር ከሌላኛው ብሔር የሚልዩ ነጥቦች (ለምሳሌ፡ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ አስተሳሰብ ወዘተ) እንዲሁ የሰው ማንነት መገለጫ ናቸው። ኢትዮጵያውያን የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ባህል፣ የጋራ ታሪክና አስተሳሰብ እስከሌለን ድረስ ደግሞ የጋራ ማንነት ሊኖረን አይችልም። የችግሮቻችን ምንጭም ይህ ነው።

ጎበዝ! ፍጥጥ ያለ እውነታ በመካድ ወይንም በማዳፈን የሚመጣ ለውጥ የለም። በምድሪቱ ፈውስ ሆነ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ መቀበል ያለብንን እውነታ በመቀበል እንጅ ከእውነታው በመሸሽ አይደለም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የራሳቸው መገለጫ ማንነት ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድምር መሆንዋን በምርጫ ሳይሆን ይህን ሐቅ የመቀበል ግዴታ እንዳለን በማመን ሐቁን በሐቅነቱ ልንቀበል ይገባናል። ከዚህ ሐቅ በሸሸን ቁጥር ግን በስህተት ላይ ስህተት እየሰራን እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል።

* * * * *

“ኢትዮጵያዊነት” ምንድ ነው?

ኢትዮጵያዊነት ክብር! ኢትዮጵያዊነት ኩራት! ኢትዮጵያዊነት ፍቅር! ኢትዮጵያዊነት …! ወዘተ አይደለም የእኔ ጥያቄ። ጥያቄው በኢትዮጵያ ታሪክ የት ቦታ ነው ብሔር ብሔረሰቦች በኢትዮያዊነታቸው ተጠቃሚ የሆኑት? ምድሪቱ “ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ከያዘች አንስቶ በማን ዘመን ነው ብሔር ብሔረሶች ተጠቃሚዎች የሆኑ? ጥቅማ ጥቅሙ ቀርቶባቸው ህልውናቸውስ በውል ይታወቅ ነበር ወይ? “ነት” የሚለውን አነጋገር መደለያ ቋንቋ ከመሆኑ አልፎ ያስገኘለት ጥቅም ምንድ ነው? እንደ ኢትዮጵያዊ ከሌላው ትልቁ ኢትዮጵያዊ ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያዊነት የሚያስገኘው ጥቅማ ጥቅም እኩል ተካፋይና ተቋዳሽ ነበር ወይ? ነው ጥያቄው። መልሱ አልነበረም ነው። ስለዚህ “ኢትዮጵያዊነት” ምንድ ነው? ኢትዮጵያዊስ ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢና ምክንያታዊ የሆነ ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል። እንግዲያውስ ግልጽነት ሆነ ለችግሮቻችን መፍትሔ ከዚህ ነው የሚጀምረው።

“ኢትዮጵያዊ” ማን ነው?

ትግራዋይ – ትግራዋይነቱን ትቶ፣ አማራ – አማራነቱን ትቶ፣ ኦሮሞ – ኦሮሞነቱን ትቶ፣ ሀረሬ፣ አፋር፣ ደቡብ … ሌሎችም እንደዚሁ የየራሱ ልዩ ማንነት (መታወቂያ) ትቶ “ኢትዮጵያዊ” ተብሎ ይጠራና ይታወቅ ዘንድ የተፈለገበት ምክንያት ምንድ ነው? ኢትዮጵያዊነት እርስ በርስ መጨራረስ ከሆነ “ኢትዮጵያዊ” መባል የሚያስገኘው ልዩ ጥቅም ምንድ ነው? ቻይናዊ? ኢትዮጵያዊ ተብሎ ባለ መጠራቱ ምን ቀረበት? ሁከትና ጦርነት።

ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት እያልኩ አይደለም። አላልኩም። አላልኩም። ስለ ኢትዮጵያ አሉታዊ አመለካከት እያንጸባረቅኩም አይደለም። ኢትዮጵያ ለእኔም አገሬ ናት። የእኔ ጥያቄ፥

 • ኢትዮጵያውነት እኩልነት ካልሆነ፤ 
 • ኢትዮጵያዊነት ፍትሐዊነት ካልሆነ፤
 • ኢትዮጵያዊነት እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ “ትልቁም” “ትንሹም” የምድሪቱ በረከት እኩል ተካፋይ የማያደርግ ካልሆነ፤ [ምን ጥግ ጥጉን ያስኬደናል፡ በታሪክ የምናውቃት ኢትዮጵያ ለአንዱ እናት ለእንድ ደግሞ የእንጀራ እናት ናት።]
 • ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦች የማንነት ጥያቄ የማይመልስ ከሆነ፤
 • ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦች የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ነጻነት ዋስትና የማያረጋግጥ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትኖር የተፈለገበት/የሚፈለግበት ምክንያት ምንድ ነው?
 • ኢትዮጵያዊነት አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ማለት ከሆነ ኢትዮጵያ የምትባል አገር በመኖርዋ/በህልውናዋ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ነው?ኢትዮጵያዊነት በቀጥታም በተዘዋዋሪም አንድን ሕዝብ እየነጠልቅ ማጥቃት ማለት ከሆነ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ከሚለው ጩኸትና ሽለላ ጀርባ ያለው አንጀንዳ ምንድ ነው? ይህ የምለው ከመሬት ተነስቼ አይደለም። ሳትወለድ የተጨናገፈች ሀገር መሪ የሆኑት የሲዖል ፈላስፋ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ኢትዮጵያን አስመልክተው የሰነዘሩት ቃል ምስክሬ ነው። ራሱን ከፈጣሪ ማስተካከል የሚቃጣው የመብት ሕጋዊ ትርጉም የማያውቅ “የሰብዓዊ” መብት ተሟጋች፣ ሥመ “ጋዜጠኛ”፣ “አክቲቪስት” ወዘተ ሀገር ስትገሸለጥና ሕዝብ በቁሙ ሲሸለት ምን አሉ? አገሬ ለሚላት ኢትዮጵያ ምን አደረገላት? ሕዝቤ ለሚለው ሕዝብስ? ባዶ። በኢትዮጵያዊነቱ ለድርድር የማይቀርብ ሕዝብ ለመዝለፍና ለማዋረድ ግን ተኝተው አላደሩም። [በነገራችን ላይ እነዚህ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋች”፣ “ጋዜጠኛ”፣ “አክቲቪስት” ወዘተ የሚሉ ተቀጽላዎች አንድ ሰው በዳይስፖራ የጥላቻና ዝሩው ፖለቲካ ሲጠመቅ በገጸ በረከት/በቸርነት ያለ ወረፋ የሚሰጡ “የክርስትና” ስሞች ናቸው።]

ሌላ “የማይገባኝ” ነገር፡ አንዱ ሌላውን “የለም! ተነጥለህና ተገንጥለህማ የራስህን መንግሥት ማቆም አትችልም።” ሲል የሚሞግትበት ምክንያት ምንድ ነው? መገነጣጠሉ፣ መለያየቱና መነጣጠሉ ሁላችን የማይበጅ ጎጂ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው (እንዳልሆነማ አውቃለሁ) ወይስ ሌላ ምክንያት አለው? ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸውን አጥተውና ተረግጠው በምትገነባ አገር ተጠቃሚ የሚሆን ማን ነው? ይህም በግልጽ መቀመጥ አለበት። ይህ ትውልድ የራሱ የሆነ ነገር አሳልፎ የማይሰጥ የሌላውንም የማይፈልግ ትውልድ ነው። እንዴት ነው ነገሩ? እስከ መቼ ነው ትውልድ በባንዴራ ሽፋን ማንነቱ ያጣ ዘንድ የሚገደደው። “አባቴ” መግዛት ተችሎ ይሆናል እኔና “ልጄ” ግን በመቃብራችን ላይ መቆም ይቻል እንደሆነ ብቻ የማውቀው።

በተረፈ ጸሐፊው፥ ከነ ልዩነቶቻችን እንዴት አንድነት መፍጠርና አስተማማኝ፣ ዘለቀታዊ ሰላም ያላት፣ ዜጎች በማንነታቸው አንገታቸው ቀና አድርገው የሚሄዱባት፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩል ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያላት፣ የበለጸገች አንዲት አገር (ኢትዮጵያ) መገንባት እንደምንችል ብንመካከርና ብንፈላለግ ነው የሚሻለው ይላሉ እርስዎስ?

ክፍል አንድና ክፍል ሁለት ለማንበብ፥

“ኢትዮጵያዊነት” ጸረ ትግራይና የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ መቆም ነው!

ይቀጥላል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

United States of America

Oct 18, 2013

Advertisements